የዘጠኝ ቀን ዝግጅት (ቅዱስ ዮሴፍ) ቀን 5

St Joseph Novena 2013 5

5ኛ ቀን ጸሎተ ተሰዓት (ኖቬና) ዘቅዱስ ዮሴፍ  

ቅዱስ ዮሴፍ ፡ የቤተክርስቲያን ባልደረባ፣ ጠባቂ!

ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ አንተ የቅድስት ቤተሰብ አባወራ፣ ተንከባካቢ፣ ደጋፊ እና ራስ ነበርክ፡፡ ስለዚህ   ቅድስት ቤተሰብ ላይ ለተመሠረተችው አንዲት፣ ቅድስት፣ ኹላዊትና የሐዋርያት ጉባኤ ለሆነችው ቤተክርስቲያን ልዑል እግዚአብሔር ባልደረባ፣ ጠባቂ አደረገህ፡፡

ቤተክርስቲያን በምድር ላይ ያለች የእግዚአብሔር ቤተሰብ መሆኗን እናምናለን፡፡ የምትተዳደረውም በክርስቶስ አካል ላይ ሥልጣን ባለው ክህነታዊ ሥርዓት ሲሆን በባህርይው ከቅዱስ ቁርባን ምሥጢር ጋር የተሳሰረና የኢየሱስም ሕይወት በቤተክርስቲያን በእውነት ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርግ ኃላፊነት ነው፡፡ በዚሁም ምክንያት ክህነት የክርስቶስ አካል በሆነችው ቤተክርስቲያን ላይ ሥልጣንና ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡ ይህም ሥልጣን ነፍሳትን የማስተማር፣ ከእግዚአብሔር ጋር የማስታረቅ፣ የመባረክና ለነእርሱም የመጸለይ ነው፡፡

ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ ከአዳኛችን ጋር ባለህ የጠበቀ ቁርኝት ምክንያት አንተ ከክህነት ምሥጢር ጋር ልዩ ትስስር አለህ፡፡ ሕይወትህና የፈጸምካቸው ግዴታዎችህ ክህነታዊ አገልግሎቶች ነበሩ፡፡ ካህን በመሥዋዕት ቅዳሴ ሥርዓት አዳኛችንን ኢየሱስን መካከላችን እንደሚያመጣ ሁሉ አንተም በተወሰነ መልኩ ጌታችንን ወደ ምድር መምጣት መንገድ ነበርክ፡፡ ለተራበ ሕዝበ እግዚአብሔር ስንዴ ያዘጋጀው የቀድሞ የግብጽ ባርነት ዘመን ዮሴፍ የአንተ ጥላ ነበር፡፡ የአንተ ሚና ግን እጅግ ያላቀ ነው፡፡ የቀድሞ ዮሴፍ ለሕዝቡ ምድራዊ ምግብን ሰጣቸው፤ አንተ ደግሞ ከፍ ያለውን ሰማያዊ ምግብ የሆነውና በቅዱስ ቁርባን ውስጥ ሆኖ ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚሰጠውን ተንከባክበህ ለቤተክርስቲያን ሰጠህ፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የቤተክርስቲያን ባልደረባ፣ ጠባቂ ያደረገህ ምክንያት የቅድስት ቤተሰብ አባትና ራስ በመሆንህና ለሚሥጥረ ሥጋዌ መዘጋጀትም የአንተ ሚና ታላቅ ስለነበረህ ነው፡፡ ትውልድህ ከነቢዩ ንጉሥ ዳዊት ቤት ስለሆነ የመሢሁ መምጣት አብሳሪዎች ቀደምት አበው ጋር በመተሳሰርህ በምድር ላይ ዙፋኑን የምትወክለውን ቤተክርስቲያን ባልደረባ፣ ጠባቂ ሆንክ፡፡ እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም እጮኛነትሀና የኢየሱስ ሕጋዊ አባትነትህ ከወልደ እግዚአብሔር ጋር በቀጥታ ትዛመዳለህ፡፡ ጥሪህ በልዩ ሁኔታ ከኢየሱስ ጥሪ ጋር ይገናኛል፡፡ ሥራህ ሁሉ እርሱን ይመለከታልና፡፡  አንተ በናዘሬት የመሠረትከውና የመራኸው ቤተሰብ የብሉይ ኪዳን መዝጊያ፣ የአዲስ ኪዳን መክፈቻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከነቢያት የላቀ ሚና ተጫውተሃል፡፡

ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ አንተ የቤተክርስቲያን ባልደረባ፣ ጠባቂና አገልጋይ ስለሆንክ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡

የቤተክርስቲያን ብቁ አባል እንድንሆን መዳንም እንድችል ጸጋ አሰጠን፡፡ ካህናትን፣ ገዳማውያንን፣ ገዳማውያትን፣ ምዕመናንና ንዑሰ ክርስቲያንን በእግዚአብሔር ፍቅርና በታማኝነት አገልግሎት ከእለት ወደ እለት እንዲያደጉ እርዳቸው፡፡ ቤተክርስቲያንን በየጊዜው ከሚነሳው ክፉ ነገርና ከጠላት ጥቃት ጠብቃት ፡፡ አሜን፡፡

የቤተክርስቲያን ባልደረባና ጠባቂ ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ - ለምንልን፡፡

(በየዕለቱ የሚደገም)

ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ እኔ ደካማው ልጅህ ሰላም እልሃለሁ፡፡ አንተ የሚወዱህንና የሚያክብሩህን ትከላከላለህ፤ ታማልዳቸዋልህ፡፡ በአንተ ላይ ልዩ የሆነ መታመን እንዳለኝና ከአዳኜ ኢየሱስና ከቅድስት እናቱ በመቀጠል የደኅንነት ተስፋዬ አንተ ነህ፡፡ ምክንያቱም አንተ የእግዚአብሔር ወዳጆችን ለመርዳት ከቶ አታመነታም፡፡ ስለዚህም በትህትና ስምህን እጥራለሁ፡፡ ከምወዳቸው እና የቅድስት ቤተስብ አፍቃሪ ከሆኑት ጋር አማላጅነትህን በመተማመን ወደ አንተ እንቀርባለን፡፡ ለአዳኛችን ኢየሱስና ለወላዲተ አምላክ ባለህ ፍቅር በዚህች አለም እስካለንና በሞታችን ጊዜ እንዳትለየን እንለምንሃለን፡፡

የእመቤታችን ቅድስት ደንግል ማርያም እጮኛ ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ ንጹሕ፣ ትሑት፣ በቸርነት የተሞላ አዕምሮና ፍጹም ለእግዚአብሔር ፈቃድ የመገዛት ጸጋ አሰጠኝ፡፡ አንተ በኢየሱስና በድንግል ማርያም እጅ እንደትክ እኔም ተመሳሳይ ዕድል ያጋጥመኝ ዘንድ መሪ፣ አርአያ እና አባት ሁንኝ፡፡

አፍቃሪና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ተከታይ ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ ለመንፈሳዊና ለየእለቱ በጎነት በተለይ ደግሞ መልካም ሞት አገኝ ዘንድ በዚህች ሰዓት በልቤ ውስጥ ያለውን አሳብ አስፈላጊ የሆኑትን ጸጋዎች ከኢየሱስ መለኮታዊ ልብ ታሰጠኝ ዘንድ አማላጅነትህን እማጸንህለሁ፡፡

/እዚህ ላይ በልብ ያለውን አሳብ መጥቀስ/

ሥጋ የለብሰው ቃል ጠባቂ ስለእኔ የምታቀርበው ጸሎት በእግዚአበሔር ፊት እንደሚሰማ እተማመናለሁ፡ አሜን፡፡

የቅድስት ድንግል ማርያም እጮኛ፣ አፍቃሪና ጠባቂ ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ ጥበቃህናን እርዳታህን የፈለገ፣ መጽናናትን ሳያገኘ የቀረ ማንም የለም፡፡ በቅዱስነትህ በመተማመን እነሆ ወደ ፊትህ እቀርባለሁ፡፡ የመድኃኒታችን ምድራዊ አባት ሆይ ልመናዬን በቸርነት ተቀበለኝ እንጂ ችላ አትበለኝ፡፡ አሜን፡፡

የቅዱስ ዮሴፍ መዝሙር

ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ ጠብቀን

ወደ ገነትም አድርሰን፡፡

በሰማይ በላይኛው

አንድ ጌታ የሌለው

አንተ ብታሳድገው

ታዘዝን ላንተው፡፡