Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ከቅዱስ ዮሴፍ ምን እንማራለን? 2013 ዓ.ም.

st Joseph annual

ከቅዱስ ዮሴፍ ምን እንማራለን?

መግቢያ

ከቅዱስ ዮሴፍ ምን እንማራለን? በሚል ርዕስ ለዚህ የቅዱስ ዮሴፍ ቁምስና ዓመታዊ የቅዱስ ዮሴፍ ክብረ-በዓል ቅድመ-ዝግጅት የዘጠኝ ቀናት ጸሎትና አስተንትኖ መርሃ-ግብር ዝግጅት ላይ የተረዳሁትን፣ የገባኝን፣ ያስተነተንኩትንና በከፊል የኖርኩበትን እንዳጋራ ዕድሉ በክቡር ቆሞስ አባ ሙላት ስለተሰጠኝ ከልቤ አመሰግናለሁ፡፡ በተሰጠኝ ጊዜ፣ የማጋራችሁን እናንተም አስተንትናችሁ ትንሽ ጥቅም ታገኙበታላችሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህችን ጊዜ፣ ሰላምና ጤናውን ሰጥቶ በዚህ እንድንሰባሰብ ላደረገን ቸሩ አምላካችን ክብርና ምስጋና ይድረሰው፡፡ የቅዱስ ዮሴፍ ያላሰለሰ አማላጅነትም ከኛ ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡

ከቅዱስ ዮሴፍ ምን እንማራለን? ወደሚለው ከመድረሳችን በፊት አንዳንድ ቀዳሚ ነገሮችን መዳሰሱ ይጠቅማል ብዬ አሰብኩ፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ዮሴፍ ማን ነው፣ ምን ዓይነት ሰው ነው፣ ቤተክርስቲያን ስለቅዱስ ዮሴፍ ምን ስትል ቆየች፣ የቅዱስ ዮሴፍ ዓመት መከበር ለምን አስፈለገ? በሚሉት ላይ አንዳንድ ሀሳቦችን አነሳለሁ፡፡ በመጨረሻም ከቅዱስ ዮሴፍ ምን እንማራለን? የሚለውን ማጠቃለያ በማየት እናጠቃልላለን፡፡  

1.ቅዱስ ዮሴፍ ማን ነው

ቅዱስ ዮሴፍ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እጮኛ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል በማቴ.1፡18-20፣24 “እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ ሳለች… እጮኛዋ ዮሴፍ…እጮኛውን ወደ ቤቱ ወሰዳት …” እያለ የዮሴፍን ማንነት ይነግረናል፡፡

ቤተክርስቲያንም ቅዱስ ዮሴፍን “የአዳኙ አሳዳጊና ጠባቂ” “Guardian of the Redeemer” ብላ ትገልጸዋለች፡፡

2. ቅዱስ ዮሴፍ ምን ዓይነት ሰው ነው

የቅዱስ ዮሴፍን ባህርያዊ ምንነት ለመረዳት መጽሐፍ ቅዱስ “ደግ” ሰው፣ “ጻድቅ” ሰው በማለት ይገልጸዋል፡፡ “እጮኛዋ ዮሴፍ ደግ ሰው ስለነበር ማርያምን በሰው ፊት ሊጋልጣት አልፈለገም፤ ስለዚህ በስውር ሊተዋት አሰበ፡፡”(ማቴ.1፡19) እርሱ ይህን ሲያስብ የጌታ መልአክ ደግሞ በህልም ይገለጥለትና እንዲህ ይለዋል፡፡ “የዳዊት ዘር ዮሴፍ ሆይ! እጮኛህ ማርያም የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ስለሆነ እርስዋን ወደ ቤትህ ለመውሰድ አትፍራ፡” (ማቴ.1፡20)፡፡

እዚህ ላይ ልብ እንበል! የእግዚአብሔር መልአክ ሁልጊዜ ደግ ወደሆኑ ሰዎች ቀርቦ ማድረግ ባለባቸው ነገር ያበረታታቸዋል ወይም ማድረግ በሌለባቸው ነገር ላይ ያግዳቸዋል፡፡ መልአኩ ዮሴፍን አበረታታው፡፡ በዘፍጥረት መጽሐፍም ተቀራራቢ ድርጊት በአብርሃም ላይ እናያለን፡፡ አብርሃም ልጁን ይስሃቅን ለመሰዋት ሰይፉን ሲያነሳ የእግዚአብሔር መልአክ ጠርቶት “ልጁን አትንካ፣ ምንም ዓይነት ጉዳት አታድርስበት አንድ ልጅህን እንኳ ለእኔ ለመስጠት ስለ አልተቆጠብክ እነሆ፣ እኔን እግዚብሔርን የምትፈራ መሆንህን ተረድቻለሁ፡፡” (ዘፍ.22፡12)

ስለ ደግ ሰው ስንቀጥል፡ ደግና ቅን ሰው ቀጥተኛና የማያወላውል፣ ግብረገባዊ ባህርይ ያለው ነው፡፡ ታዛዥና በእግዚአብሔርም ዓይን ፍጹም የሆነ ነው፡፡ ምሳሌ 20፡7 ላይ “ጻድቅ ሰው በቅንነት ይኖራል፡” ይላል፡፡ በብሉይ ኪዳንም ኖህ ደግ ሰው እንደነበር ይነገራል፡ በዘፍ.6፡9 “ኖህ በዘመኑ ምንም በደል የማይሠራና የእግዚአብሔርን መንገድ የሚከተል ደግ ሰው ነበር፡፡” ይላል፡፡

የቅዱስ ዮሴፍም ደግነትና ጻድቅነት በዚሁ መልክ ይታያል፡፡

3. ቤተክርስቲያን ስለ ቅዱስ ዮሴፍ ምን አለች

በ13ኛው ክፍለ ዘመን (1181-1226) የኖረው የአሲዚው ቅዱስ ፍራንሲስኮስ ቅዱስ ዮሴፍን የአባቶችና የሠራተኞች ጠባቂና ባልደረባ፣ በሞት ጣር ላሉት ረዳት ይለዋል፡፡

ቅዱስ ፍራንሲስኮስ በቅዱስ ዮሴፍ ለጋስነት፣ ትህትና፣ ጽናት፣ ቁርጠኝነትና ጥንካሬ ይመሰጥ ነበር፡፡

በሰብአዊነቱ ቅዱስ ዮሴፍ ድንግል ማርያምን የቀረባት በፍጹም ንጽህና ነበር፡፡ በዚህም ንጽህና ምክንያት ሕፃኑ ኢየሱስን በደስተኛነት ነበር ያሳደገው፣ የተንከባከበው፣ የጠበቀውም፡፡ እውነተኛ ፍቅርን በመስጠት፡፡ እስቲ እናስብ፡ የዘመናችን አባቶች (እናቶችም ጭምር) በብዙ የኑሮና የሥራ ጉዳዮች ተወጣጥረው ለልጆቻቸው እውነተኛ ፍቅር የማጋራት ጊዜ ሲያጥራቸው፣ ልጆቻቸው ፍቅራቸውን ሲሹ፣ ወላጆች ግን ስማርት ሞባይል በማቀበል ባንድ በኩል ጊዜያዊ ፋታ ያገኙ ቢመስላቸውም በመዘዙ ልጆቻቸውን የቁሳዊ ፍቅር ሰለባ እያደረጓቸው መሆናቸውን ስንቶች ልብ ብለውት ይሆን? ሕፃናት ባልበሰለ አእምሮአቸው በቁሳዊ ፍቅር ተመንዝረው ከሰብአዊ ፍቅር ሲታገቱ የምናስተውልባቸው አጋጣሚዎች እየተበራከቱ ይገኛሉ፡፡

በ16ኛው ክፍለ ዘመን (1550ዎቹ) የኖረችው የአቪላዋ ቅድስት ቴሬዛ ለቅዱስ ዮሴፍ ልዩ ፍቅርና ክብር ነበራት፡፡ ከመሠረተቻቸው 17 የካርሜላይት መነኮሳያት ገዳማት 12ቱን በቅዱስ ዮሴፍ ጥበቃ ሥር አድርጋ ገዳማቱ በተለያዩ የቅዱስ ዮሴፍ ምስሎች እንዲያሸበርቁ አድርጋለች፡፡

ከሁሉ በላይ ደግሞ ር.ሊ.ጳጳሳት ቅዱስ ዳግማዊ ዮሐንስ ጳውሎስ በ1989 (እ.ኤ.አ) ባስተላለፉት REDEMPTORIS CUSTOS  በተሰኘው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው የቅዱስ ዮሴፍ በእምነት የፀና ለአምላክ መታዘዝ፣ ቤተሰብ፡ “የፍቅር ማበልፀጊያ ጥብቅ ሥፍራና ሕይወት የሚጠነሰስበት ሥፍራ” መሆኑን በበቂ ያሳየ ሰው ነው ይሉታል፡፡ ሲቀጥሉም፡ ቅዱስ ዮሴፍ ራሱን አሳልፎ በመስጠት ፍቅር፤ የትዳር አብሮነትን እውነታና አባትነትን በተግባር ያሳየ ነው፡፡ ከቤተሰብ ውጭ የሥራን ክቡርነት በማሳየት፣ ሥራ ከደህንነት ምስጥር ጋር የተያያዘ መሆኑን ያሳየ ነው፡፡ እርሱ የተግባርንና የማሰላሰልን ሕይወት (የሲታውያን መርህ “work and prayer, Latin: ora et labora” እንደሆነ) አጣምሮ በመኖር ለኛ ሞዴላችን ነው ይላሉ፡፡ 

4. የቅዱስ ዮሴፍ ዓመት ለምን አስፈለገ

ር.ሊ.ጳጳሳት ፍራንሲስ የቅዱስ ዮሴፍ ዓመት (ከኅዳር 27 ቀን 2013 እስከ ኅዳር 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ባለው ጊዜ) ያወጁት በሁለት ምክንያቶች እንደሆነ ይታመናል፡፡

1. ቅዱስ ዮሴፍ የቤተክርስቲያን ጠባቂ ተብሎ የተሰየመበት 150ኛ ዓመት መታሰቢያ ለማድረግ ነው፡፡

በ1870 እ.ኤ.አ የዛሬ 150 ዓመት አካባቢ ር.ሊ.ጳጳሳት ቅዱስ ፕዮስ 9ኛ ቅዱስ ዮሴፍ የኩላዊት ቤተክርስቲያን ጠባቂና ባልደረባ ብለው አወጁ፡፡ ይህንን ያደረጉበትም ምክንያት በዚያን ዘመን ባንድ በኩል የኢንዱስትሪ አብዮት የሚባለው ምርትን በማሽን የመሥራት፣ ብዙ የማምረትና ለረጅም ሰዓት የመሥራት ዝንባሌ በሰዎች ላይ ጫና መፍጠር የጀመረበት ወቅት ነበር፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ባንድ በኩል የሰው ልጅ ፈጣሪ በሰጠው ዕውቀት ተመርቶ ማምረቻ መሣሪያ ቢሠራም በሌላ መልኩ የዚሁ ዕውቀት ትዕቢት ያመጣው ጣጣ ሰው በዓለማዊ አስተሳሰብና አመለካከት እየተሳበ መሄድ መስፋፋት የጀመረበት ወቅት ስለነበር፡ እነዚህ ሁለት ነገሮች በአማኞች ሕይወት ላይ ጫና ፈጥረው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የቅዱስ ዮሴፍ የቤተክርስቲያን ጠባቂነትና ባልደረባነት በቤተክርስቲያን አባቶች ዘንድ በብርቱ የታመነበት ጉዳይ ሆነ፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ር.ሊ.ጳጳሳት ቅዱስ ፕዮስ 9ኛ በ1870(እ.ኤ.አ) የዛሬ 150 ዓመት አካባቢ ቅዱስ ዮሴፍ የኩላዊት ቤተክርስቲያን ጠባቂና ባልደረባ ብለው ያወጁት፡፡

2. በዚያን ጊዜ የተጀመረው ጫና የበዛበት ሕይወት ቀጠለ እንጂ አልተረጋጋም፡፡ በዘመናችንም የብዙ ምዕመናን ግላዊም ሆነ ቤተሰባዊ ሕይወት መዘበራረቅ የበዛበት፣ ያለንበት ዘመን በእጅጉ ስላሳሰባቸው ር.ሊ.ጳጳሳት ፍራንሲስ “እያንዳንዱ አማኝ ምዕመን የቅዱስ ዮሴፍን አብነት በመከተል፣ በየቀኑ ያለውን የእምነቱን ጉዞ በማጠናከር በያንዳንዱ ምዕመን ላይ ያለው የእግዚአብሔር ፈቃድ ምሉዕ ይሆን ዘንድ” በማሰብ ነው፡፡

5. ከቅዱስ ዮሴፍ ምን እንማራለን

ከላይ ባየናቸው ነጥቦች ላይ ተመርኩዘን በዋናነት ከቅዱስ ዮሴፍ ልንማር የሚገቡንን ነገሮች ር.ሊ.ጳጳሳት ፍራንሲስ ቀዳማዊ ዓመቱን በማወጅ ባስተላለፉት መልዕክት ውስጥ ያስቀመጧቸውን ሰባት ነጥቦች ማሰላሰል በቂ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ እስቲ እንያቸው፡፡

1. ተወዳጅ አባት

ቅዱስ ዮሴፍ የማርያም እጮኛና የኢየሱስ ጠባቂና ተንከባካቢ በመሆን ራሱን ለመለኮታዊ የማዳን ዕቅድ አገልግሎት አሳልፎ የሰጠ ሰው ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ (ር.ሊ.ጳጳሳት) የቅዱስ ዮሴፍን አባትነት ሲገልጹ፡ “ሕይወቱን ለምስጢረ ሥጋዌና የማዳን ዕቅዱ የመስዋዕትነት አገልግሎት አድርጎ ያቀረበ አባት ነው፡፡ ሕጋዊ ኃላፊነቱን ቅድስት ቤተሰብን በሥራውና በሕይወቱ በሙሉ ለመንከባከብ አሳልፎ የሰጠ ሰው ነው፡፡ ሰብአዊ የአባትነት ጥሪውን በቤተሰብ ፍቅር ውስጥ በማኖር ልቡንና መላ ብቃቱን መሲሁን ለማሳደግና ለጉልምስና ለማብቃት አውሎታል፡፡” ብለዋል፡፡ ይህንን አባባል ስናስተነትን ስንቶቻችን የአባትነት ድርሻችንን በመስዋዕትነትና በተወዳጅነት ተወጥተን ልጆቻችንንና ቤተሰባችንን አምላክ ለፈለገው አገልግሎት አብቅተናቸዋል? ለማብቃትስ ቆርጠን ወደ ትዳር ገብተንበታል ወይ? ይህንንም መርህና ባህርይ ይዘን ወደ ትዳር ለመግባት እየተዘጋጀን እንገኛለን? ብለን ራሳችንን እንድንፈትሽ ዕድል ይሰጠናል፡፡

2. ተንከባካቢና አፍቃሪ አባት

ቅዱስ ዮሴፍ ኢየሱስ በየቀኑ “በእግዚአብሔርና በሰው ፊት የተወደደ ሆኖ፡ በጥበብና በቁመት እያደገ መሄዱን” (ሉቃ.2፡52) ያስተውል ነበር፡፡ በዚህም ዮሴፍ ሕጻኑ ኢየሱስን እጆቹን በመያዝ መራመድን አስተምሮታል፣ በማልበስና በማጉረስም ተንከባክቦታል፡፡ ኢየሱስም በዮሴፍ ውስጥ የእግዚአብሔርን ተንከባካቢ ፍቅር፡ “አባት ለልጆቹ የሚራራላቸውን ያህል እግዚአብሔርም የሚፈሩትን ይራራላቸዋል፡፡”(መዝ.103፡13) የሚለውን ተገንዝቧል፡፡ በዚህ መልኩ በአባትና በልጅ መካከል ያለውን መለኮታዊ ዕቅድ ተንከባካቢ አባትም ሆነ አዳጊ ልጅ እያስተዋሉ ተጉዘዋል፡፡

ይህንን በማስተንተን ስንቶች አባቶች እንሆን የእግዚአብሔር ፈቃድ በኛ የአባትነት ድርሻና እግዚአብሔር በልጆቻችን ላይ ላለው ዕቅድ የጥሞና ጊዜ ሰጥተን እያሰላሰልን የምናሳድጋቸው? በተለይም ባሁኑ ዘመን ያለን አባቶች፡ እኛ ልጆቻችን እንዲሆኑ የምንፈልገው ላይ እናተኩራለን ወይስ በልጆቻችን ውስጥ የእግዚአብሔር ዕቅድ ይፈጸም ዘንድ በጥሞና ተንከባካቢነታችንንና አፍቃሪ አባትነታችንን በተረጋጋ መንፈስ እንወጣለን? እንደ ክርስቲያን ትዳር አሳቢ ወጣትስ ትዳርን ስናስብ ይህንን የቅዱስ ዮሴፍን አብነት እንዴት ለመተግበር እናስባለን?

በቅዱስ ዮሴፍ ፍርሃትና ስጋት ውስጥ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሥራውን ሠርቷል፡፡ ከቅዱስ ዮሴፍ የምንማረው፡ በእግዚአብሔር ከተማመንን በኛ ፍርሃት ውስጥ እርሱ ድንቅ ሥራውን እንደሚሠራና፡ በድክመታችንም ውስጥ የእርሱ ዕቅድ ብርታት ሆኖ እንደሚወጣ ነው፡፡   

3. ታዛዥ አባት

እግዚአብሔር ለማርያም እንዳደረገ ሁሉ፡ ለቅዱስ ዮሴፍም የማዳኑን ዕቅድ በሕልም ገለጠለት፡፡ ቅዱስ ዮሴፍ በማርያም ምስጢራዊ እርግዝና በእጅጉ ተረብሾ ነበር፡፡ ሆኖም በአደባባይ ሊያጋልጣትለጥቃት ሊዳርጋት አልፈለገም፡፡

ሆኖም የእግዘብሔር መልአክ በሕልም ታይቶት “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ! እጮኛህ ማርያም የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ስለ ሆነ እርስዋን ወደ ቤትህ ለመውሰድ አትፍራ፡፡ እርስዋ ወንድ ልጅ ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ስለሚያድን ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ፡፡”(ማቴ.20-21) በማለት አበረታታው፤ ምስጢሩንም ገለጠለት፡፡ ዮሴፍም በፍጥነት እንደተነገረው አደረገ፡፡ መታዘዙም ከፍርሃት አላቀቀው፣ ድፍረትም ሰጠው፣ ማርያምን ከማጋለጥ ታደጋት፡፡

የዮሴፍ ፈተና ይህ ብቻ አልነበረም፡፡ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ ግብፅ ይሰደድ ዘንድ መልአኩ ነገረው፤ ቀጥሎም የሕፃኑ ገዳዮች ሲሞቱም ወደ ሀገሩ ይመለስ ዘንድ የመልአኩን ቃል ተቀብሎ ተመለሰ፡፡ አሁንም የሄሮድስ ልጅ አርኬላዎስ ገዢ ስለነበር በገሊላ ግዛት በናዝሬት ኑሮውን አደረገ፡፡

በዚህ ሁሉ የፈተና ገጠመኝ ቅዱስ ዮሴፍ ፍፁም ታዛዥ በመሆን ታላቁ የደህንነት ምስጢር እውን የሚሆንበትን ጊዜ በመጠበቅ እውነተኛ የደህንነት ተልዕኮ ፈጻሚ አገልጋይነቱን አሳይቷል፡፡

እኛም አባቶችና አባት መሆን የምናስብ ወገኖች አባትነትን ስንሻ፣ በቤታችን ውስጥ የኛ ፍላጎት እንዲፈጸም ብቻ ነው የምናስበው? ወይስ በቤተሰባችን ውስጥ በኛ ታዛዥነት የእግዚአብሔር ዕቅድ ይፈጸም ዘንድ ዕድል እንሰጣለን?

4. ተቀባይ አባት

ዮሴፍ የመልአኩን ቃል ሰምቶ ማርያምን ያለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ ተቀበላት፡፡ በዚህ ሀሳብ ላይ ቅዱስነታቸው ባንድ ወቅት ባሰሙት ቃለ-እግዚአብሔር ስለ ቅዱስ ዮሴፍ ይህን ብለዋል፡፡ “የዮሴፍ ልብ ታላቅነት የሚታየው፡ በሕግ ከተማረው ይልቅ ራሱን ለበጎ አገልግሎት መስጠቱ ነው፡፡ ዛሬ በዘመናችን በዓለማችን ላይ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ በርካታ ሥነ-ልቡናዊ፣ ቃላዊና አካላዊ ጥቃቶች በሚስተዋሉበት፤ ቅዱስ ዮሴፍ ስብዕናን አክባሪ፡ ለሰው ስሜት ተቆርቋሪ ሆኖ ሲቀርብ እናገኘዋለን፡፡ ምንም እንኳን ትልቁን የእግዚዘብሔር ዕቅድ ምስል በቅጡ ባይረዳውም፣ የማርያምን መልካም ስም፣ ክብርዋንና ሕይወቷን ለመጠበቅ ሲወስን ይስተዋላል፡፡ እርሱ ለመቀበል የቸገረውን እግዚአብሔር ገልጦለት ረዳው፡፡” ብለዋል፡፡

የሌላውን ችግር ከመቀበል ይልቅ በሌላው ላይ በተለይም በሴቶች፣ በእናቶችና በእህቶች ላይ ችግር የማብዛት ስሜት በነገሰበት ዘመን የምንገኝ አባቶች ይህንን ችግርን የመቀበል መለኮታዊ ፈቃድ እንዴት ተቀብለን በሌሎች ላይ ችግር እንዳይበዛ እንጥራለን? በየቤቱ መቀበል ያቃተን ችግር ተደማምሮ ብዙ እናቶችን ከነልጆቻቸው ለጎዳና ሕይወት የዳረጋቸውን የምንቸገረኝ ድርጊት ስናስብ፣ ይህን ችግር ለመታደግ የኛ ድርሻ (በአቅማችን) ምን ይሆን?

ቅዱስነታቸው ይነግሩናል፡ “ዮሴፍ በግድየለሽነት ማርያምን አልተዋትም፡ ይልቅስ በድፍረትና በቁርጠኝነት ተቀበላት [እንደ ዘመናችን ክስተት ልጅ አቅፎ ጎዳና ከመዉጣት ታደጋት]፤ በየራሳችንም ሕይወት ገጠመኞቻችንን እንዳመጣጣቸው መቀበል የመንፈስ ቅዱስ የድፍረት ስጦታ ነው፡፡ ከነተቃርኖው፣ ከነፍርሃቱና ከነመከፋቱ ሕይወትን እንዳመጣጡ እንድንቀበል የሚያስፈልገንን ብርታት ሊሰጠን የሚችለው ጌታ ብቻ ነው፡፡ ይህም በኛ የመቀበል ዝግጁነት ይለካል፡፡”

ቅዱስነታቸው ሲቀጥሉ፡“ክርስቶስ ያስተማረን እምነት በቅዱስ ዮሴፍ የምናየው ነው፡፡ እርሱ ከችግር ለመሸሽ አቋራጭ መንገዶችን አልፈለገም፣ ይልቅስ እውነታውን በተከፈቱ ዓይኖቹ በማየትና በአእምሮው በመረዳት በግል ኃላፊነቱ ተጋፈጠው እንጂ፡፡”

ይህን ክፍል ሲያጠቃልሉም፡ “የቅዱስ ዮሴፍ አመለካከትና ባህርይ እኛንም ያበረታታናል፤ ሰዎችን ያለ ልዩነት እንደነበሩና ከነማንነታቸው እንድንቀበላቸውና እንድናስተናግዳቸው፣ ለደካሞች ልዩ ትኩረት እንድናደርግ፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ደካማውን ይመርጣልና፡(1ቆሮ.1፡27)፡፡ እርሱ ‘አባት ለሌላቸው ልጆች አባት ነው፤ ባሎቻቸው ለሞቱባቸውም ሴቶች ጠባቂ ነው፡’(መዝ.68፡5)፡፡” ይሉናል፡፡ ይህንንም ያደረገው ሁሉንም ነገር በአባትነት በመቀበል ነው፡፡ እኔስ? የቤተሰቤንና የልጆቼን ሁኔታ እንዳመጣጡ የመቀበልና የማስተናገድ ብቃት ያለኝ አባት ነኝን?    

5. ትጉህና ደፋር አባት

ስለኢየሱስ የሕፃንነት ትርክት ስናነብ ይላሉ ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው “ለምንድር ነው እግዚአብሔር ቀጥተኛውንና ግልፁን የማዳን መንገድ ያልመረጠው ብለን እንገረም ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን እግዚአብሔር በድርጊቶችና በሰዎች በኩል ሥራውን ይሠራል፡፡ ዮሴፍም የደህንነትን ታሪክ ጅምር ይመራ ዘንድ በእግዚአብሔር የተመረጠ ሰው ነው፡፡” እዚህ ላይ እኛም በአባትነታችን ለምን እንደተመረጥን ቆም ብለን ልናሰላስል ዕድል ተሰጥቶናል፡፡

እግዚአብሔር ሥራውን የሠራውም በዮሴፍ ትጋትና ድፍረት ውስጥ ነው፡፡ ማሳያውም በቤተልሔም ለማርያም መውለጃ ሥፍራ ሲያጡ፣ ዮሴፍ የከብቶቹን ግርግም በተቻለው አቅም፣ ትጋትና ድፍረት የእግዚአብሔር ልጅ መወለጃ ሥፍራነት ቀየረው (ሉቃ.2፡6-7)፡፡ የሄሮድስ ሕፃኑን የመግደል ዕቅድ ዕውን መሆኑን በህልሙ እንደተረዳ በድፍረት በሌሊት ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ ግብፅ ለመሰደድ አላመነታም(ማቴ.2፡13-14)፡፡

ቤተሰብ በብዙ ፈተናዎችና ችግሮች ተከብቦ በሚገኝበት ባሁኑ ዘመን እኔስ እንደ አባት በቤተሰቤ ላይ ያንዣበበውን ፈተናና ችግር ተጋፍጬ ለማሸነፍ ነው የምተጋው ወይስ ቤተሰቤን ጥዬ በራስ ወዳድነት ብቻዬን ለማምለጥ እፈተናለሁ? ወይስ ፈተናውን በሽሽት እወድቃለሁ? ብለን እንጠይቅ፡፡  

6. ሠራተኛ አባት

ወንጌላዊው ማቴዎስ በ13ኛ ምዕራፉ ለምንድር ነው “ይህ የአናጢው ልጅ አይደለምን?” (ቁ.55) በሚል ሌሆሳሳዊ ጥያቄ የዮሴፍን ሥራ ሊነግረን የፈለገው? ብለን ብንጠይቅ፣ ጥያቄውን ለማስነሳት ምክንያት ከሆነው ታሪክ ጀርባ ያለው ነገር ሊገለጥልን ይችላል፡፡ አናጢነት ሥራ ነው፡፡ ሙያም ነው፡፡ አናጢ ሠራተኛ ነው፡፡ ባለሙያም ነው፡፡ ዮሴፍም ሠራተኛ አባት፣ ለቤተሰቡ የድካሙና የላቡ ውጤት የሆነውን እንጀራ አምጪ እንደሆነ ያሳየናል፡፡ አዳጊው ኢየሱስም የሥራን ዋጋ፣ ክብርና የሚያስገኘውንም እርካታ፣ የሥራ ፍሬ የሆነውን እንጀራ መብላትንም የተማረው ከዮሴፍ እንደሆነ ያመላክተናል፡፡

ቅዱስ ዮሴፍ በሥራው የተከበረና የሥራንም ክቡርነት ያሳየን ሠራተኛ አባት መሆኑን በዚህ እንረዳለን፡፡ አባትነት ኃላፊነት እንደሆነና ሠራተኛም አባት ሥራውን በመሥራት ቤተሰቡን አስከብሮ እንደሚያኖር ያስገነዝበናል፡፡ አባት ለመሆን ባለሙያ ሠራተኛ መሆን እንደሚገባም ከዮሴፍ ሕይወት እንማራለን፡፡ ሠራተኛ ሳይኮን አባት መሆን አይቻልምና፡፡

ቅዱስነታቸውም በመልዕክታቸው ይህንኑ ያስረግጣሉ፡፡ “ሥራ በደህንነት ሥራ ውስጥ መሳተፊያ መንገድ ነው፣ የመንግሥቱን ወደኛ መምጫ ማፋጠኛ ዕድል ነው፡፡ ብቃታችንንና ክህሎታችንን ማሳደጊያ፣ ለማኅበረስብ አገልግሎት ማበርከቻና የወንድማማችነት ጥምረት መፍጠሪያ መንገድ ነው፡፡ ሥራ የራስን ፍላጎት ብቻ ማሟያ ሳይሆን የዚያ ማኅበረሰብ ትንሹ ህዋስ የሆነውን የቤተሰብንም ፍላጎት ማሟያ መንገድ ነው፡፡ ሥራ የሌለው ቤተሰብ ለተለያዩ ችግሮች፣ ውጥረቶች፣ ጭቅጭቆች ብሎም ለመበታተን አደጋ የተጋለጠ ነው፡፡ ሁሉም ሥራውን ሠርቶ የሚገባውን በማያገኝበት ሁኔታ እንዴት ስለ ሰብአዊ ክብር መናገር እንችላለን?”

ሠርቶ ቤተሰቡን የሚመግብና የሚያስከብር አባት፣ ሰርቆና አጭበርብሮ ቤተሰቡን በጊዜያዊነት ከሚያጠግብ አባት በእጅጉ ይለያል፡፡ ለዚህም ነው ቤተክርስቲያን ቅዱስ ዮሴፍን የሠራተኞች ባልደረባ የምትለው፡፡   

7. በግርዶሽ ጥላ ውስጥ የሚገኝ አባት

ጃን ዶብራዝንስኪ የተባለ የፖላንድ ሀገር ደራሲ በፃፈው The Shadow of the Father በሚለው ታዋቂ መጽሐፉ ውስጥ ዮሴፍ ከኢየሱስ ጋር ስላለው ቀረቤታ ሲገልጸው “ዮሴፍ የሰማያዊው አባት ምድራዊ ጥላ ነው፡” ይለዋል፡፡ በጥላነቱም ሕፃኑ ኢየሱስን ተንከባክቧል፣ ጠብቋል፣ እንደፈለገው እንዲሆንም አልለቀቀውም፡፡ ልክ በብሉይ ኪዳን ሙሴ ለእስራኤላውያን፡ “…አንድ ሰው ልጁን እንደሚንከባከብ በሄዳችሁበት መንገድ ሁሉ አምላካችሁ እግዚአብሔር በምድረበዳው እንደተንከባከባችሁ አይታችኋል፡፡”(ዘዳግ.1፡31) እንዳለው፡፡ እንደ አምላክ ዕቅድና ምርጫ ዮሴፍም በመላ ሕይወቱ ለኢየሱስ ሰብአዊ ዕድገት ይህንን አደረገ ይሉናል ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፡፡ ዮሴፍ ደስተኛ የሆነው የሕይወት መስዋዕትነት ስለከፈለ ብቻ ሳይሆን፣ ኢየሱስንና እናቱ ማርያምን ለመንከባከብ ራሱን አሳልፎ በመስጠቱም ነው፡፡

የዮሴፍ የአባትነት ድርሻ እንደ ተለመደው የስም አባትነት ብቻ ሳይሆን የተግባርና ኃላፊነትን ለቤተሰቡና ለልጆቹ የመወጣት አባትነት ትክክለኛ ማሳያ ነው፡፡ አባት፡ አባት ሆኖ አይወለድም (ሙሉ የአባትነት ባህርያት ይዞ አይወለድም)፤ ነገር ግን የአባትነት ባህርያትን መምረጥና መያዝ ይቻላል፡፡ ዮሴፍም ያደረገው ይህንኑ ነው፡፡ አባት ልጅ ስላስወለደ ብቻ አባት ሊሆን አይችልም፡፡ አባት ለመሆን ሙሉ የአባትነትን ባህርያት ሊላበስ ይገባል፡፡ ባሁኑ ዘመን ለምን ልጆች በየጎዳናው ይገኛሉ? ለምንስ ሥርዓተ-ቢስ ሆነው ሲያድጉ ይስተዋላሉ? ብለን ብንጠይቅ፣ ከበርካታ ምክንያቶች አንዱ፡ አለመታደል ሆኖ ከአባት ተብየዎች ተወለዱ እንጂ ኃላፊነት በሚሰማቸው አባቶች ባለማደጋቸው እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡

አባት መሆን ልጆችን ለሕይወት እውነታ ማዘጋጀትን ይጠይቃል፡፡ ይህም ልጆች ምንም ነገር እንዳያደርጉ፣ እንዳይሞክሩ፣ እንዳይጠይቁ አፍኖ በመያዝ ሳይሆን፤ በሚችሉት፣ በሚረዱትና በሚፈልጉት መንገድ ነገሮችን እንዲያደርጉ፣ እንዲመራመሩ፣ እንዲጠይቁና እንዲያዉቁ በመርዳት ነው፡፡ ይህም በጥበቃ ሥር ያለ ነፃነታቸውን በመጠቀም አዳዲስ ነገሮችን በአቅማቸውና በመረዳት ልካቸው እንዲገነዘቡና እንዲያውቁ ያግዛቸዋል፡፡

ዮሴፍ በተለምዶ “ፍጹም ንጹህ” የሚለውን ስያሜ የያዘው ንጽህናው በእውነተኛ ፍቅር ላይ ስለተመሠረተ ነው፡፡ እውነተኛ ፍቅር ፈተናዎቹን ሁሉ በመሸከም፣ እውነተኛ ፍቅር ማርያምንና ኢየሱስን በመንከባከብ፡፡ በዚህም እርሱ ራሱን የነገሮች ማዕከል አላደረገም፡፡ ነገር ግን ማርያምና ኢየሱስ የነገሮች ማዕከላት ይሆኑ ዘንድ በግርዶሽ ጥላ ውስጥ የሚገኝ አባት ሆኖ ተገኘ፡፡

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ላይ፡“እያንዳንዱ ልጅ ልዩ ምስጢር ያዥ ነው፤ ያ ምስጢር ወደ ብርሃን ወጥቶ ሊገለጥ የሚችለው የልጁን ነፃነት በሚያከብር አባት ነው፡፡ ይህንን የሚገነዘብ አባት እውነትም አባትም አሰልጣኝም ነው፡፡ ልጁም የራሱ ልጅ ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ልጅ መሆኑን የሚገነዘብ አባት፡፡ የርሱ የአባትነት ድርሻ ልጁን ለዚያ ደረጃ ይበቃ ዘንድ ማብቃት ነው፡፡ ዮሴፍም ያደረገው ይኸንኑ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

በዚህም ከቅዱስ ዮሴፍ የምንማረው እንዴት ተወዳጅ አባት፣ ተንከባካቢና አፍቃሪ አባት፣ ታዛዥ አባት፣ ተቀባይ አባት፣ ትጉህና ደፋር አባት፣ ሠራተኛ አባት፣ አንዳንድ ጊዜም በግርዶሽ ጥላ ውስጥ የሚገኝ አባት መሆን እንደሚቻል ነው፡፡

ማጠቃለያ

የቅዱስ ዮሴፍ ጥንካሬና ክብር ለዘመናችን በአባት ለሚመሩ ቤተሰቦችና የአባትነት ማዕረግ ለተሰጣቸው መንፈሳዊ አባቶች ትልቅ አብነት ነው፡፡

የዘመናችን ቤተሰቦች እንደ ቅዱስ ቤተሰብ የተጣጣመ የቤተሰብ ሥርዓት ይኖረን ዘንድ የቅዱስ ዮሴፍን አማላጅነት አጥብቀን ልንሻ ይገባል፡፡

በቤተሰብ ሕይወት የምስጢረ-ተክሊልና የምስጢረ-ምንኩስና ክብር ከመንፈሳዊ ጥቅሞቹ ባሻገር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው ማሳያ የሚሆነው የቅዱስ ዮሴፍን የሕይወትና የአባትነት አብነት በጥልቀት ስናስተነትንና ስንኖርበት ብቻ ነው፡፡

በመንፈሳዊ ጥቅሙ፡ ቅዱሰ ዮሴፍ በእምነቱ የፀና፣ ለአምላኩ ፈቃድ ራሱን የሰጠ፣ የተጠራበትን የአባትነት ጥሪ ከነተግዳሮቱ የተቀበለና የኖረበት አባት ነው፡፡ ይህም ድርጊቱ ለቅድስና አበቃው፡፡ እኔስ? እኛስ? በያለንበት የጥሪ ሕይወት (እንደ ሥጋዊ አባት፣ መንፈሳዊ አባት፣ ሥጋዊ እናት፣ መንፈሳዊ እናት ሆነን) መንፈሳዊ ጥቅምን ለራሳችንም ሆነ በተቀበልነው ጥሪ ዙሪያ ላሉ ወገኖች እያጋራን እንገኛለን ወይ? መልሱን በየራሳችን እንፈትሽ፡፡

በማኅበራዊ ጥቅሙ፡ ቅዱሰ ዮሴፍ በማኅበራዊ ጉዳዮች በሚዛናዊ ማንነቱ የሚታወቅና የተከበረ፣ ኃላፊነቱን በትጋትና በትኩረት የተወጣ፣  ለሌሎች መብቃትና መኖር የኖረ አባት ነው፡፡ እኔስ? እኛስ? በያለንበት ቤተሰባዊም ሆነ ገዳማዊ ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ያለኝ ማኅበራዊ ጠቀሜታ እንዴት ይታያል? የኔ በዚያ ቦታ መኖር ተፈላጊነቴን ያጎላዋል? ወይስ ያደበዝዘዋል? የኔ በዚያ መኖር ተፈላጊነት ከኔ በሚገኝ ቁሳዊ ጥቅም ላይ ያተኮረ ነው? ወይም በሁለንተናዊ ማንነቴ መኖር ላይ ያተኮረ ነው?

በኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ፡ ቅዱሰ ዮሴፍ የጉልበቱና የጥረቱ ፍሬ አናጢነት በሆነ ሥራው በሚያገኘው ገቢ የቤተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አስከብሮ ኖረ፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ ሕፃኑ ኢየሱስ “በጥበብና በቁመት እያደገ መሄዱን” ሲነግረን፡ ኢየሱስ ቤት ያፈራውን በአናጢነት ገቢው ዮሴፍ ያመጣውን፣ ማርያም ያበሰለችውን በልቶ እንዳደገ በውስጠ-ታዋቂነት ነግሮናል፡፡

የኑሮ ጫናና ውጣ ውረድ እያዋዠቀ ፈተና በሆነበት ዘመን፡ በራሱ ጥረትና ፈጠራ ባገኘው ፈጣሪውን እያመሰገነ በ “ይበቃኛል” መንፈስ፣ ለቤተሰቡ ምጣኔ-ሀብታዊ ማብቃቃት በርስበርስ መተማመንና ቤተሰባዊ መግባባት፣ ያለውን በጥበብና በማስተዋል በመጠቀም በሁሉም ዘንድ በተአማኒነት የሚኖር ቤተሰብ መሆንን ከቅዱሰ ዮሴፍ እንማር፡፡

ከምን ጊዜውም ይልቅ ንጽህናና አባትነት በተቃለለበት፣ የሠራተኛ ክብር ባነሰበት፣ እውነተኛ እምነት በደበዘዘበት፣ የቤተሰብ የአብሮነት ሕይወት በተናጠበት ዘመን የምንኖር ቤተሰቦች በተለይም አባቶች(፣ እምነት አለን የምንል ወገኖች ወደ ቅዱስ ዮሴፍ መቅረብ፣ አማላጅነቱንም አጥብቀን መሻት ይገባናል፡፡

የቅዱስ ዮሴፍን ዓመታዊ ክብረ-በዓልና የቅዱስ ዮሴፍን ዓመት ስናከብር በቅዱስ ዮሴፍ አብነት ለመለወጥ እንጽና፡፡ የቅዱሰ ዮሴፍ አማላጅነት ሁልጊዜ ከኛ ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡

ለቅዱስ ዮሴፍ ቁምስና ዓመታዊ በዓል ዝግጅት

ከዘጠኝ ቀናት ጸሎት መርሃ-ግብር ባንዱ ላይ የቀረበ አስተምህሮ

ዝግጅት፡ አርጋው ፋንቱ

 ሰኞ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም.

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት