‘ዘመናችን’ ምን ዓይነት አባቶች ያስፈልጉታል?

‘ዘመናችን’ ምን ዓይነት አባቶች ያስፈልጉታል?

አባትነት 1ቀደም ባለው ወር ር.ሊ.ጳጳሳት ፍራንሲስ ያለንበትን ዓመት (ከኅዳር 27 ቀን 2013 - ኅዳር 26 ቀን 2014) “የቅዱስ ዮሴፍ ዓመት” ብለው ሲያዉጁ፡ “አባታዊ ልብ” በሚል ርዕስ ካስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክት ውስጥ የቅዱስ ዮሴፍን አባታዊ ልብ የሚገልጹትን ሰባት ባህርያት ማየታችን ይታወሳል፡፡ አሁንም ዓመቱን በሙሉ የቅዱስ ዮሴፍን አባታዊ ስብዕናና ድርጊቶች እያሰላሰልን እንደመጓዛችን መጠን፡ ር.ሊ.ጳጳሳት በዚሁ መልዕክታቸው ውስጥ “ዓለም አባቶች ያስፈልጓታል፡፡” ያሉት ዐረፍተ ነገር ትኩረቴን ሳበው፡፡ ለምን አሉ? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ፣ ተያያዥ ሀሳቦችን ማንሳቱ ይጠቅመን ይሆናል የሚል እምነት አደረብኝ፡፡  ይህንኑ ዐረፍተ ነገር ወደ ጥያቄ በመቀየር የርዕሴ መነሻ በማድረግ አብረን እናሰላስል ዘንድ ወደድሁ፡፡

በዓለማችን ላይ ከሚከሰቱ ሰብአዊ፣ ማኅበራዊ፣ እምነታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አብዛኞቹ የሚከሰቱት በአመዛኙ በአባት ተብየዎች መሆኑን ብዙ የማኅበራዊ ጉዳይ አጥኚዎች ያነሱታል፡፡ ቤተክርስቲያንም የቅዱስ ዮሴፍን ዓመት እንድናስብ፣ እንድናሰላስል ስትጠይቀን በቀላል አገላለጽና ድርጊት በቅዱስ ዮሴፍ ላይ ብቻ እንድናተኩር ሳይሆን፣ በዚሁ ትኩረት መነሻነት ሁሉም አባቶች (መንፈሳዊም ሆኑ ሥጋዊ አባቶች) የአባትነት ልካቸውን እንዲያሰላስሉ፣ እንዲፈትሹ፣ ወደ ውስጣቸው በማየት “የእኔ የአባትነት ተፈላጊነት እንዴት ይለካል? ምን በጎ ነገር እያደረግሁ ኖርኩ? ምንስ ይጠበቅብኛል?” የሚሉትን ጥያቄዎች እንድናስብ ያደርገናል፡፡

የአባትነት ተፈላጊነት ሲነሳ ብዙ ጥያቄዎች ሊነሱና ሊሰላሰሉ ይችላሉ፡፡ የቤተሰብ ጥንካሬም ሆነ ድክመት፣ ቅንነትም ሆነ ክፋት፣ ቅድስናም ሆነ ርኩሰት መሠረቱን የሚይዘው በአመዛኙ በአባት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ አባት የቤተሰብ ‘ራስ’ ሲሆን፣ እናት ደግሞ የቤተሰብ  ‘ልብ’ መሆኗ እሙን ነው፡፡ እዚህ ላይ የእናትን ትቼ በአባት ላይ ማተኮሬ የእናትን ድርሻ በማሳነስ ሳይሆን ጉዳዩ ከቅዱስ ዮሴፍ ዓመት ጋር ተያያዥ በመሆኑ ነው፡፡ የእናትን ድርሻ ከላይ በተገለጸው እውነታ አዘል አባባል ላይ ተመርኩዤ ሌላ ጊዜ ስለሚመለስበት ይህንን የምታነቡ እናቶች፣ እህቶችና ሴቶች በዚህ መልኩ ትረዱኛላችሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ በትዕግሥት ስለ ተረዳችሁኝም አመሰግናችኋለሁ፡፡

ዘመናችን ምን ዓይነት አባቶች ያስፈልጉታል? ብለን ስንጠይቅ፡ የመልስ ዕይታችን አድማሱ ሊሰፋ ይችላል፡፡ በመሆኑንም ጠበብ ባለ ዕይታ በሚከተሉት ላይ ብቻ ማጠንጠን ፈለግሁ፡፡ አንባቢን ላለማሰልቸት በሦስት ነገሮች ላይ ማተኮር የተሻለ ሆኖ አገኘሁ፡፡ አብረን እንዝለቅ፡፡ 1. በቅድሚያ ከአምላኩና ከእምነቱ ጋር ብርቱ ቁርኝት ያለው አባት፣ 2. ለቤተሰቡ ቀጣዩን ሥፍራ የሰጠ አባት፣ 3. በጎነትን ተላብሶ በደግነትና በሚዛን ተግባሩን የሚያከናውን አባት፡፡

1. በቅድሚያ ከአምላኩና ከእምነቱ ጋር ብርቱ ቁርኝት ያለው አባት

ከአምላኩና ከእምነቱ ጋር ብርቱ ቁርኝት ያለው ቅዱስ ዮሴፍ የአባትነት ድርሻውን በተገቢው መንገድ እንደ ተወጣ ቀደም ብለን አይተናል፡፡ ቅዱስ ዮሴፍ በብዙ ፈታኝ ነገሮች ውስጥ ሲያልፍ ምርኩዝ ሆኖ የረዳው ከአምላኩ ጋር ያለው ቁርኝትና ላመነበት ነገር ራሱን አሳልፎ መስጠቱ ነው፡፡ በዚህ ድርጊቱም ቅዱስ ዮሴፍ በቤተክርስቲያን አባቶች ዘንድ “የእምነት፣ የተስፋና የፍቅር ምሉዕነት ሞዴል” አስብሎታል፡፡ ይህም አባትነት የሕይወት ዘመን ጥሪ መሆኑን አውቆ እንደተቀበለ፣ እንደኖረበትና በአብነቱ እንዳስተላለፈ የቤተክርስቲያን ዕውቅና ምስክር ነው፡፡ ቅዱስ ዮሴፍ ሁሉም ወንዶች ባላቸው የአባትነት ተፈጥሮ፡ በሥጋቸው ብቻ ሳይሆን በተሰጣቸው ንፁህና ፍሬያማ ፍቅር፣ ልጆች የእግዚአብሔር ልጆች ሆነው እንዲያድጉና እንዲቀረፁ ለማድረግ ያላቸውን የአባትነት ጥሪ ያሳየ አባት ነው፡፡

ከአምላኩና ከእምነቱ ጋር ብርቱ ቁርኝት ያለው አባት፡ አባትነት የሕይወት ዘመን ጥሪ መሆኑን ማወቅ ብቻ ሳይሆን፡ በዚህ ጥሪ እየኖሩ ልጆችም በዚያ መንገድ እንዲጓዙ ለማብቃት በሙሉ አቅም መሰጠት መሆኑን ይገነዘባል፡፡ በዚህ መሰጠት ውስጥ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለመሸከምም ሆነ፣ ተሸክሞ ለማለፍ፣ በጎ ነገሮችን ወደ ልጆችም ለማሻገር በአምላክ ላይ ያለ እምነትና ባመኑት ላይ ፀንቶ መቆም አስፈላጊ ነው፡፡

በአምላኩ ላይ ጽኑ እምነት ያለው አባት ራሱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የተገነዘበ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑና የአባትነት ድርሻን በመያዙ ይህ ማንነቱ ወደ ልጆቹም ይሸጋገር ዘንድ አጥብቆ ይሠራል፣ ሆኖ ለመገኘትም ይጥራል፡፡ ለዚህ ማሳያ ይሆን ዘንድ የካሮል ወይትላ - የወደፊቱ ቅዱስ አባት - የልጅነት ታሪክ ባጭሩ መጥቀሱ ይመቻል፡፡

ካሮል ወይትላ - በኋላም ለ27 ዓመታት የቤተክርስቲያን “ቅዱስ አባት” የተባለው ር.ሊ.ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ - እናቱን ያጣው በዘጠኝ ዓመት ዕድሜው ነበር፡፡ ከዚያ መሪር ሐዘን በኋላ አብዛኛውን የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው ከአባቱ ጋር ነበር፡፡ ከአባቱ ጋር አንድ አልጋ ላይ በመተኛት አድጓል፡፡ በልጅነቱ ካሮል ማልዶ የመነሳት ልምድ ነበረው፡፡ ማልዶ በተነሳ ቁጥር አባቱ ቀድሞት ተነስቶ፣ በጉልበቶቹ ተንበርክኮ በጸሎት ተመስጦ ውስጥ ሲሰጥም ይመለከተው ነበር፡፡ ይህ የአባቱ ድርጊትና በጸሎት መመሰጥ በካሮል የልጅነት አእምሮ ውስጥ የማይረሳ ስሜትና ድርጊት ጥሎበት አልፏል፡፡ አባቱ ከአምላኩ ጋር ያለው ቁርኝት ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ ልጁ ተረድቷል፡፡

በዚህ ሁኔታ ያደገው ካሮል ወይትላ በጊዜው ቀጣዩ “ቅዱስ አባት” ር.ሊ.ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ተብሎ በመሰየም፡ የቅዱስ ጴጥሮስ ወራሽ፣ የቤተክርስቲያን አባት፣ የበቃ መንፈሳዊ እረኛና መሪ ሆኖ ኖሯል፡፡ በዓለም ካሉ ታላላቅና ግልፅ የአባትነት ነፀብራቆች ሆነው ካለፉት አንዱ ሆነው በዓለም ታሪክ ላይ ሰፍረዋል፡፡ እንደቤተክርስቲያን ሥርዓትም ለቅድስና ማዕረግ በቅተው ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ተብለዋል፡፡ አባቱ ከአምላኩ ጋር የነበረው ጥልቅ ቁርኝት ወደ ልጁም ተጋብቶበታል፡፡ “እምነትን ይይዟል፣ ጥበብን ይቀስሟል” የአባቶች አባባል ይህንን እውነት ያሳያል፡፡  

ከአምላኩና ከእምነቱ ጋር ብርቱ ቁርኝት ያለው አባት፡ ፈሪሃ-እግዚአብሔር ያለው ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም “እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ለራሱና ለቤተሰቡ ጽኑ መታመኛና ዋስትና አለው፡፡”(ምሳሌ.14፡26) በማለት ያጸናዋል፡፡ ፈሪሃ-እግዚአብሔር ያለውና እግዚአብሔርን የሚያከብር አባት በረከቱ ብዙ መሆኑን በዚህ መልዕክት ይረዳል፡፡ “ሚስትህ በቤትህ እንደ ፍሬያማ የወይን ተክል ትሆናለች፤ ልጆችህም በማዕድህ ዙሪያ እንደ ወይራ ለምለም ቅርንጫፎች ይሆናሉ፡፡ እግዚአብሔርን የሚያከብር እንደዚህ የተባረከ ይሆናል፡፡”(መዝ.128፡3) ተብሎም ይመሰከርለታል፡፡ በዚህ በብዙ ውጥንቅጥ በታጀበ ዓለምና ዘመን የሚፈለገው አባትነት በዚህ እምነት የተቃኘ ከሆነ በረከቱ ብዙ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም “አባት ለልጆቹ የሚራራላቸውን ያህል እግዚአብሔርም የሚፈሩትን ይራራላቸዋል፡፡”(መዝ.103፡13) ያለው ቃል ታማኝ ስለሆነ ጥሎ አይጥልምና፡፡

ከአምላኩና ከእምነቱ ጋር ብርቱ ቁርኝት ያለው አባት፡ ስለልጆቹና ቤተሰቡ በጸሎት ስለሚተጋ የቤተሰቡ ኅብረት አይናወጥም፡፡ ምክንያቱም የጸሎቱን ውጤት በፊቱ ያያል፡፡ በዚህም “እርሱ[እግዚአብሔር] የወላጆችን ልብ ወደ ልጆች፡ የልጆችንም ልብ ወደ ወላጆች ስለሚመልስ” (ንጽ.ሚልክ.4፡6) ቤተሰባዊ ጽናቱ ብርቱ ይሆናል፡፡ 

በነዚህ ማሳያዎች በመመርኮዝ በዚህ ዘመን አባት የመሆንን ሥፍራ የያዝን አባቶች ከአምላካችን ጋር ያለንን ቁርኝትና የእምነት ሕይወታችንን በማጠናከር ለቤተሰባችንና ለልጆቻችን የበረከት ምንጭ ሆነን የተሻለ ዓለም የማሳየት ድርሻችንን ለመወጣት ብንተጋ መልካም ነው፡፡ ተፈላጊ አባትነታችንም ሊያድግ ይችላል፡፡

2. ለቤተሰቡ ቀጣዩን ሥፍራ የሰጠ አባት

ቅዱስ ዮሴፍ ከአምላኩና ከእምነቱ ጋር ካለው ብርቱ ቁርኝት ቀጥሎ ያለውን ሥፍራ የሰጠው ለቤተሰቡ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ለቤተሰብ ሥፍራን መስጠት ስንል አባትነት “ለምን?” እና “እንዴት?” የሚሉትን ጥያቄዎች ከመመርመርና ከመመለስ ጋር ይያያዛል፡፡ አባትነት ጥሪ ነው እንዳልን ሁሉ፡ አባትነት መሰጠትም ነው፡፡ መሰጠት ከራስ ባሻገር ማሰብና መሆን ነው፡፡ ለምን ወደ ትዳር ሕይወት እገባለሁ? ከገባሁስ እንዴት እወጣዋለሁ? እንዴት ያለስ የአባትነት ሚና ይኖረኛል? የሚሉትን ጥያቄዎች በጥልቀት ማሰላሰልን ይጠይቃል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ስናሰላስል የምናገኛቸው ምላሾች በርካታ እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡ ሆኖም ግን በተወሰኑት ላይ እናተኩር፡፡ ተፈጥሮአዊ ማንነታችንና ባህርያችን በድክመቶች የተሞላ ቢሆንም ዕለት በዕለት እንደ አባት ከድክመቶቻችን ለመላቀቅ ማሰብና ማድረግ የሚገቡን ነገሮች ይኖራሉ፡፡

2.1 የተክሊል ዝግጅታችንን፣ የፈጸምነውን ተክሊልና የተክሊል በረከቶቻችንን ማሰብና ማጋራት

ከእምነት ጉዞአችን አንዱና ዋነኛው እንደአባትና እንደቤተሰብ ስንኖር ሊተኮር የሚገባው የእምነት አብሮነት ጉዞአችን ነው፡፡ ለተክሊል ዝግጅት ስናደርግ፣ ምስጢራትን በጥልቀት ለመረዳት ሞክረናል፡፡ ተክሊል ስንፈጽም በተረዳነው መጠን በአብሮነት ለመኖር፣ በችግርም ሆነ በደስታ በሁለንተናችን ለመሸካከም በአምላክና በምስክሮች ፊት ቃል ገብተናል፤ ቃልም ተሰጣጥተናል፡፡ የቃል ኪዳን ቀለበቶችም በተክሊል አሳሪው ካህን ተባርከውልን እርስበርስ ተለዋውጠናል፡፡ የገባነውንም ቃል ኪዳን በመውደቅና በመነሳት እየኖርንበት እንገኛለን፡፡ እነዚህን ሁሉ ትውስታዎችና እውነቶች ስናስብ ለልጆቻችንም እንደ አባት እየኖርን ስለምናስተላልፈው ነገር ልናስብና ለልጆቻችንም የኖርነውንና እየኖርን ያለውን የሕይወት እውነት ማሳየት   ይገባናል፡፡

ባሁኑ ዘመን ብዙ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን በልጆቻችን ዓይኖችና አእምሮ ውስጥ በጎ ነገርን የማሥረጻቸውን ያህል፣ እጅግ በርካታ፡ ያለ ጊዜያቸው አማላይና ፈታኝ የሆኑ “አጓጉል ምስለ-ድርጊቶችን” እየረጩ ባሉበት ዘመን የተክሊል ሕይወታችንን እውነት ለልጆቻችን የምናስገነዝብበት መንገድና ጊዜ ያስፈልገናል፡፡ ይህም የሚሆነው እንደ እያንዳንዳችን ቤተሰብ አባትነት የተጓዝንበትን መንገድና እየኖርን ያለንበትን መስመር ከልጆቻችን የዕድገትና የመረዳት አቅም ጋር አገናዝበን፡ እያዋዛን ማሳየትና ማጋራት አስፈላጊ ነው፡፡ ለልጆቹ የወደፊት የሕይወት ጥሪ መስመር ተገቢውንና ተጨባጩን አቅጣጫ የሚያሳይ አባት ይህን ለማድረግ በቤተሰብ የጋራ ጸሎት፣ አብሮ ወደቤተክርስቲያን በመሄድ፣ ምስጢረ-ቁርባንን አብሮ በመጋራት የተክሊልን ቅዱስነት፣ ክቡርነትና በረከቶቹንም ለልጆቹ የሚያጋራ አባት፣ በተክሊላቸው ዓመታዊ በዓል መታሰቢያ ላይ ተመርኩዘው ከልጆቻቸው ጋር እንደዕድሜያቸውና የመረዳት አቅማቸው የሚመጥን የሕይወት ጉዞ ምስክርነትና ዝግጅት መወያያ ርዕስ በጋራ መርጦ የሚያሳትፍ አባት ያስፈልጋል፡፡ በዚህም ላይ ተመርኩዞ የቤተሰብ የጸሎት ሕይወትን መመሪያው ያደረገ፤ ስለቤተሰቡ አካላዊ፣ አእምሮአዊ፣ ግብረ-ገባዊ፣ መንፈሳዊ ዕድገትና ከክፉ ነገር ጥበቃ አጥብቆ የሚጸልይ አባት ያስፈልጋል፡፡

ይህንን ለማድረግ የመጀመሪያው የቤተሰብ አመራር የሚመጣው ከአባት ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለወጣቱ ጢሞቴዎስ እንደተናገረው “የገዛ ራሱን ቤተሰብ በደንብ ማስተዳደር የሚችል፡ ልጆቹ በተገቢ በአክብሮት የሚታዘዙለት”(1ጢሞ.3፡4) አባት ሆኖ መገኘት ነው፡፡

ይህንን ስናስብ ውድ የዚህ ዓምድ አንባቢያን የየራሳችሁንም ተሞክሮ ብትፈትሹና ምስክርነታችሁን በዚሁ ዓምድ ብታጋሩ የቅዱስ ዮሴፍን ዓመት ስናከብር አከባበራችን ተግባራዊ፣ አኗኗራችን ትምህርታዊና ምክንያታዊ መሆኑን የመጋራት ዕድል ይኖረናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህንን ማድረግ በራሱ መሰጠት ነው፡፡

2.2 ለቤተሰብ አብሮነት ጊዜ መስጠት የሚችል አባት

ያለንበት ኑሮን የማሸነፍ ሩጫ በተለይም በከተማው አካባቢ ለምንኖር አባቶች ቀላል እንዳልሆነ ይስተዋላል፡፡ ሆኖም ግን ዘማሪው ዳዊት “እግዚአብሔር ሆይ [የአብሮነት]ተስፋችንን ባንተ ላይ ስላደረግን፡ ዘላለማዊው ፍቅርህ ከኛ ጋር ይሁን፡፡”(መዝ.33፡22) ያለውን እየደገምን፡ በምናደርገው ኑሮን የማሸነፍ ሩጫ ውስጥም  “እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ የቤት ሠሪዎች ድካም ከንቱ ነው፡፡”(መዝ.127፡1) የሚለውንም ቆም ብሎ ማሰላሰል ጊዜን ለማጋራት ሳይጠቅም አይቀርም፡፡ ለቤተሰባችን የአብሮነት ጊዜ መስጠቱ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ህጻናትን ለማጫወት የምንሰጠውን ጊዜ ያህል፡ ለአዳጊና እየጎለመሱ ላሉ ልጆቻችንም ልንሰጥ ይገባል፡፡ ልጆች በአስተሳሰብና በአመለካከት እየዳበሩ ሲሄዱ የወላጆች በቅርባቸው መሆን አስፈላጊነት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ አዳጊዎችና እየጎለመሱ ያሉ ልጆች ይህንን የወላጅን አብሮነት ሲነፈጉ ነው ወደ አቻ ፍለጋ የሚሄዱት፡፡ ይህ ሳይታወቅ የሚሠራ ስህተት ሌላ ችግር እንዳያመጣ የቤተሰቡ የቅርብ ጓደኛነት ልምድ ያለው አባት ያስፈልጋል፡፡

የቤተሰብ የአብሮነት ጊዜ የመደሰቻና የመዝናኛ ጊዜ ብቻ ሳይሆን የመማማሪያና የማስተማሪያ ጊዜም ነው፡፡ በቤተሰብ አብሮነት ጊዜ ብዙ የሕይወትና የእምነት ጥያቄዎች ሊነሱበት፣ የሕይወት ተሞክሮና ምስክርነት ሊሰጡበት ይችላሉ፡፡ ይህም ጊዜ በተለይም በልጆች ውስጥ ያሉ ዕንቆቅልሾች ምላሽ የሚያገኙበትና ቤተሰብን የማመንና የመተማመን የግልጽነት ድባብ የሚሰፋበት መንገድ ነው፡፡ የመጽሐፈ ምሳሌው አባባል “ልጅን እንዴት መኖር እንደሚገባው ብታስተምረው፣ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ከዚያ ፈቀቅ አይልም፡፡”(ምሳሌ.22፡6)  ያለው እውን መሆኑን የምንገነዘበውም ይህን ጊዜ አመቻችተን ስንኖርበት ነው፡፡ ይህም ልምድ የቤተሰብ ወርቃማ ጊዜ ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

በዚህ የቤተሰብ የአብሮነት ጊዜ የመደማመጥ ባህል ይዳብራል፣ የአባት ሞዴልነት ጎልቶ ይወጣል፣ ጊዜን በአግባቡና በጋራ የመጠቀም ልምድ ይጎለብታል፣ በጋራ ማቀድና መተግበር ይለመዳል፡፡ በዚህም ልምድና ድርጊት ለራስ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም የተሻለውን መስጠት ይሆናል፡፡ ምክንያቱ ዛሬ በዚህ የቤተሰብ ወርቃማ ጊዜ ውስጥ ያለፈና የጊዜ አጠቃቀም ልምድ ከቤተሰቡ ያጎለበተ ልጅ ነገ በተለያየ ኃላፊነት ላይ ሲሰማራ የዓለም ልጅ ስለሚሆን የተሻለውን ነገር ለዓለም የማበርከት ዕድሉ የሰፋ ይሆናል፡፡ የዓለም ብርሃንነት ወንጌል መልእክትም ይህንኑ አይደል የሚያጠናክረው “ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው የሰማይ አባታችሁን እንዲያመሰግኑት የእናንተም ብርሃን በሰው ፊት ይብራ፡፡”(ማቴ.5፡16) በማለት፡፡ ለቤተሰብ አብሮነት ጊዜ የሚሰጥ አባት አስፈላጊነት አድማሱ የሰፋ መሆኑን ከዚህ መገንዘብ ይቻላል፡፡ የዚህ ተቃራኒ ድርጊትና ከቤተሰብ የሚወጣው አፍራሽ ክስተት ዓለምን በችግርና በሥቃይ ጨለማ ውስጥ እየከተተ መሆኑንም ልብ ይሏል፡፡  

3. በጎነትን ተላብሶ በደግነትና በሚዛን ተግባሩን የሚያከናውን አባት

በዘመናችን ፈታኝና አስቸጋሪ ከሆኑ ነገሮች አንዱ በጎነትን ተላብሶ በደግነትና በሚዛን ማገልገል አለመቻል ነው፡፡ በጎነትን ተላብሶ በደግነትና በሚዛን ሥራውን በመሥራት ሌሎችን የሚያገለግል፣ ለቤተሰቡም ተገቢውን የመኖሪያ ምክንያት የሚያስገኝ አባት አስፈላጊ ነው፡፡ በሚያከናውነው ተግባርና አገልግሎት ሁሉ በደግነትና በሚዛን የሚያከናውን አባት የበረከቱ ምንጭ ማን መሆኑን የሚያውቅና የሰላም አድማሱም የሰፋ ነው፡፡ ሰላሙ ከቤቱ ይጀምርና በሁሉም ዘንድ ይዳረሳል፡፡ “የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ ኢየሱስ እንደምታደርጉት ዓይነት በትጋትና በደስታ አድርጉት፡፡ ጌታ ርስትን ዋጋ አድርጎ እንደሚሰጣችሁ ታውቃላችሁ፡፡”(ቆላስ.3፡23)  በደግነትና በሚዛን የሚከናወኑ ተግባራት ትጋትን ይጠይቃሉ፡፡ በውጤታቸውም ደስታን ያስከትላሉ፡፡ የደስታውም ዓይነት ከሥራ ቦታ ወደ ቤት፡ ከቤትም ወደ ሥራ ቦታ የሚስተጋባ ስለሚሆን ሚዛኑ የተጠበቀ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ይሆናል የርስት ዋጋ የተባለው፡፡ ርስት መባሉም ዘላቂነትን ያሳያል፡፡ ደግነትና ሚዛናዊነት ሌላው የመሰጠት ማሳያ ነው፡፡ በአባትነት ለቤተሰቡ የተሰጠ ሰው፣ በአገልግሎቱም ለተገልጋዮቹ ወይም ለተደራሾቹ እርካታ የተሰጠ ነው፡፡ በሁለንተናው የተሰጠ አባት ሁልጊዜ ከራሱ ጥምቅ ይልቅ የሌሎችን ጥቅም የሚያስቀድም ነው፡፡ “እያንዳንዱ [ሰው] የራሱን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሰው ጥቅም ያስብ፡፡” (ፊልጵ.2፡4) የሚለውን መልዕክት የራሱ ያደረገ ነው፡፡

በማጠቃለያም ውድ አንባቢ የቅዱስ ዮሴፍን ዓመት እንደ አባት ስናስብ፣ ስናስተነትን፣ የየራሳችንን ያለንበትንና የምንኖርበትን የአባትነት ልክና ተፈላጊነት በነዚህ ሦስት የዕይታ መነጽሮች በማየት የየራሳችንን ትክክለኛ ሥፍራና ድርሻ ለክተን እንያዝ፡፡ እኔ እንደአባት በአምላኬ ፊት፣ በቤተሰቤ ውስጥ፣ በአገልግሎት ድርሻዬ ያለኝ የተፈላጊነት መጠን ምን ይመስላል? እንዴትስ ይለካል? ብለን ራሳችንን እንመርምር፡፡ ር.ሊ.ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ በ1981 (እ.ኤ.አ.) ቤተሰብ በዘመናዊው ዓለም በሚል ርዕስ ለቤተሰቦች ባስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው “መላው የቤተሰብ አባላት፡ እያንዳንዱ እንደየተሰጥዖው ቀን በቀን የሰዎችን መልካም ተግባቦት የመገንባት ፀጋና ኃላፊነት አለው፡፡ በዚህም ድርጊት ቤተሰብ ‘የጥልቅ ስብዕና ትምህርት ቤት’ ይሆናል፡፡”(ቁ.21) ብለዋል፡፡ ቤተሰብ ‘የጥልቅ ስብዕና ትምህርት ቤት’ እንዲሆን ቀዳሚውን ድርሻ የሚይዘው የዘመኑ ተፈላጊ አባት ነው፡፡ በአባትነት ማዕቀፍ ውስጥ ላለን ሁሉ ቅዱስ ዮሴፍ በትሁት አብነቱ በኛም ውስጥ ተፈላጊ አባትነት ይጸና ዘንድ ያማልደን፡፡ አሜን፡፡ (አርጋው ፋንቱ)