ክፍል 1 - አንተ ፈጠረኸዋልና ባንተ ዘንድ ካልሆነ በቀር ልባችን በሌላ አያርፍም

አንተ ፈጠረኸዋልና ባንተ ዘንድ ካልሆነ በቀር ልባችን በሌላ አያርፍም

"አንተና ስላንተ ፈጥረኸናልና፤ በአንተ ውስጥ እስኪያርፍ ድረስ ልባችን ሰላም የለውም"። እነዚህ ቃላት "ኑዛዜ" በሚል ርእስ ስለ ገዛ ራሱ ሕይወት በግልጽ የተረከበትና የእምነቱን፣ ፍልስፍናዊና ነገረ መለኮታዊ አስተሳሰቡን፣ ባጭሩ መላ ማንነቱን ለመግለጽ ከጻፈው በጣም ዝነኛ መጽሐፉ የተቀነጨቡ ናቸው። አውረልዮስ አውጎስጢኖስ በተለመደው አጠራሩ ደግሞ አውጎስጢኖስ እ.ኤ.አ.በ354 ዓ.ም. ታጋስተ የዛሬይቷ ቱኒዚያ ውስጥ ተወለደ። አባቱ ፓትሪስዩስ በተጋስተ ከተማ የምክር ቤት አባል ሲሆን በሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ ግን ክርስቲያን ቢሆንም ለብዙ ዓመታት ወደ አረመኔነት ያዘነበለ ነበር። እናቱ ሞኒካ ስትባል፤ ሕይወቷ በፈሪኃ እግዚአብሔር የተሞላ፣ ትዕግሥተኛና አመለ ወርቅ የምትባል ዓይነት ሴት ከመሆኗም በላይ ቤተሰቧን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመሳብ ሌት ተቀን በጸሎት በብርቱ ትደክም የነበረች ጠንካራ ክርስቲያን ናት። የሃይማኖት ብርታት አላቸው ተብለው በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ ካላቸውና እውነተኛ እናትነትና ክርስቲያንነት ምን መሆኑን ሊያሳዩ ከቻሉ ብፁዓት አንስት መካከል አንዷ ናት።

{gallery}news3{/gallery}
ቅዱስ አውጎስጢኖስና ቅድስት ሞኒካ- ስዕሉን ይጫኑት 

ሞኒካ ልጆችዋን ከሕፃንነታቸው ጀምራ የክርስትና ትምህርትን እያስተማረች፣ በተግባርም እያሳየች የክርስትና መንፈስ እንዲሰርጽባቸው ደክማለች። በዝህ ጥረቷም የመጨረሻ ወንድ ልጅዋና ሴት ልጅዋ እንደተመኘችው ታንጸው ሲያድጉ፤ አጎስጢኖስ ግን ወለም ዘለም በማለት ይህ ዕድል አመለጠው። ትምህርት ቤት ከገባ በኋላ ደግሞ እስከነጭራሹ ፈጽሞ ከእናቱ ቁጥጥርና ፈቃድ ወጣ። ቀጥሎም ትምህርቱን ትቶ የትም መዋል ሥራዬ ብሎ ተያያዘው። ካደገ በኋላ ግን የታላላቅ ደራሲያን ጽሑፎችን ማንበብና መመራመር ጀመረ። በዚህ መስክ ያለውን ዝንባሌ በማሳየት አእምሮው እየሰላና አስተያየቱ እየሰፋ ሄደ። በሃሳብ አገላለጽ፣ በጣዕመ ልሳን፣ በአንደበተ ርቱዕነትና በንግግር ችሎታው ከጓደኞቹ የላቀ ሆኖ ተገኘ። አባቱ የልጁን ዝንባሌና ጉጉት በማየት "ምናልባት የንግግር ችሎታ ያለው ወይም ደግግሞ የሕግ ጠበቃ ሊሆን ይችላልና እስቲ ይማር" ብሎ በአሥራ ስድስት ዓመቱ በዝነናው በካርቴጅ ከተማ ከፍተኛ ትምህርት ቤት እንዲገባ አደረገ።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን አባቱ በመሞቱ አጎስጢኖስ ረጂ አጣ፤ ሆኖም እግዚአብሔር ጥሎ አይጥልምና ሮማንያኑስ የተባለ ሀብታም ዘመዱ በታጋስተ ይኖር ስለነበር አጎስጢኖስንና እናቱን መርዳት በመጀመሩ አጋር የለህ ሆኖ አልቀረም። ይህ በጎ አድራጊ ሰው ለአጎስጢኖስ የቀኝ እጁ እንደነበር የሚያስረዳው አጎስጢኖስ ከብዙ ዓመታት በኋላ የጻፈው የመጀመሪያ መጽሐፉን ለሮማንያኑስ አምኀ ማበርከቱ ነው። በካርቴጅ በነበረበት ወቅት የሚያስደንቅ ብስለትንና የትምህርት ችሎታን አሳየ።

ታሪኩን የሚናገሩ ሰዎች እንደሚሉት ገና ተማሪስ ሳለ የንግግር ችሎታና ጣዕመ ልሳን ያለው ብልህና ንቁ ሰው መሆኑን አስመሰከረ። በአንድ በኩል በዚህ ዓለም እውቀትና ተፈጥሯዊ ችሎታው ወደ ላይ ሲመጥቅ በሌላ በኩል ግን በመጥፎዎቹ ጓደኞቹና በደካማነቱ ምክንያት ወደ ታች ወደ ኃጢአት ጥልቅ አዘቅት ቁልቁል እንደወረደ ይነገራል። የዚህ ገሀድ ምልክቱ ገና የአሥራ ስምንት ዓመት ወጣት ሳለ ያለ ቃል ኪዳን አንዲት ሴት አግብቶ ከርስዋ ጋር አሥራ ሦስት ዓመት መኖሩ ነው። በጊዜው በነበረው የአረማዊ ዓለም አስተሳሰብ ያለ ቃል ኪዳን መውለድና አብሮ መኖር እንደነውር ሆኖ ይገመት ያልነበረ ቢሆንም አጎስጢኖስ ለፈጸመው ተግባር ኋላ ራሱ ተመልሶ በዓይነ ክርስትና በተመመለከተው ጊዜ በእውነት እጅግ ከባድ ኃጢአት መሆኑ ተረዳው።