ክፍል 4 - ከሰሜን አፍሪካ ወደ አውሮጳ

ከሰሜን አፍሪካ ወደ አውሮጳ

አውጎስጢኖስ በውጫዊ አኗኗሩ የማኒ ተከታይ ቢመስልም በልቡ ከማንኛውም እምነት ፈጽሞ ራቀ። ኅሊናውም እረፍትን አጣ፤ ስምንት ዓመት ያህል በካርቴጅ ውስጥ የሙግት ጥበብንና ክርክርን (ሬቶሪክ) ሲማር ቆየ። ከዚህ በኋላ እውነትን ለማግኘት ያደረገው የአእምሮ ጥረትና የኅሊና ጉዞ አልበቃ ብሎት እውነት እንደ ወርቅና ጨርቅ ተጠቅልሎ አንድ የሆነ ቦታ የምትገኝ ይመስል ሊፈልጋት ወደ ሮማ ለመሄድ ወሰነ።

ከፊቷ ሊለይ የማትሻ እናቱ ርቆ እንዳይሄድባት የተቻላትን ሁሉ ጥረት አደረገች፤ ግን እርሱ በሐሳቡ ስለጸና አብራው ለመሄድ ወሰነች። እርሱ ደግሞ አሮጊት እናቱን ይዞ ሊጓዝ ስላልፈለገ እንደነገ ሊሄድ ማታውን “ወደ ሩቅ አገር የሚሄድ ጓደኛዬን ልሸኝ ነው” በማለት በቅዱስ ቆጵሪያኖስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትቷት ሄደ።

እርስዋ ልጅዋ ከአሰበው ጉዞ እንዲቀር በብርቱ ጸለየች፤ በማግስቱ የጉዞው መነሻ ወደሆነው ወደብ ስትሄድ እርሱ አስቀድሞ ሄዶ ቆያት። ያገደደን ምክር አይመልሰውም እንደተባለው ሆነ። ሞኒካ በልጅዋ መንፈሳዊ ሁኔታ በብርቱ ተጭንቃ እንቅልፍ በማጣት ሁልጊዜ ታዝን ስለነበር ወደ ሮማ ከመሄድ በፊት ወደ አንድ አቡን ዘንድ ሄዳ ያላትን ጭንቀትና ኀዘን ገለጸችላቸው። እሳቸውም “ልጅሽ መንፈሳዊ ምክር የማይሰማና የማይቀበል ደረቅ ስለሆነ ምንም ለማድረግ አልችልም” ብለው ተስፋ የሚያስቆርጥ መልስ ሰጧት። እርሷ ግን ልጇ ወደ ክርስትና መንገድ እንዲመለስ እንዲያግዟት ደጋግማ ስላስቸገረቻቸው ጳጳሱ “ይህን ያህል እንባ የፈሰሰለት ልጅ ጠፍቶ አይጠፋም” በሚል ተስፋ በተሞላበት ቃል አጽናንተው ላኳት።

አውጎስጢኖስ በዘመኑ ከነበረው ከመላው የሮማ ግዛት ሁለተኛ ደረጃ ወደ ነበራት ወደ ሚላኖ ከተማ የአንደበተ ርቱእነት (ሬቶሪክ) ለመማር ሄደ። ይህ አካሄዱ ምንም እንኳ ወደተመኘው የሕይወት ግብ እንዲደርስ የሚረዳው ቢሆንም አሁንም በሚላኖ ከተማ ውስጥ ብዙ የአእምሮና የኅሊና ውጣ ውረደ መንገላታትም አጋጠመው።

ኑሮውን በሚላኖ ከተማ ውስጥ ከመሠረተ በኋላ የስመ ጥሩው አቡን የቅዱስ አምብሮዝዮስ ቃለ ስብከት ወደሚደመጥበት ቤተ ክርስቲያን ሄደ። አውጎስጢኖስ በአምብሮዝዮስ የንግግር ችሎታና መንፈሳዊ ግርማ እጅግ በጣም ስለተደነቀና የአምብሮዝዮስ ጠቅላላ ሐሳብ ስለማረከው እየተመላለሰ ስብከቱን ማዳመጥና መከታተል ጀመረ። እጅግ በበዛ ማዕበል የተንገላታች ነፍሱም የወንጌል ብርሃን ጭላንጭል ማየት ጀመረች።

አውጎስጢኖስ “ኮንፌሽን” (ኑዛዜ) በተሰኘው መጽሐፉ የራሱን ሆኔታ ሲገልጽ፦

“ፈልጌ ያላገኘሁዋትን እውነት ሊገልጽልኝ ነው በሚል ሐሳብ ሳይሆን፤ ግርማ ሞገሱ፣ ሃሳቡና ውቃቢው ደስ አለኝ፤ ለሕዝብ ይሰጠው የነበረውን ትምህርትም ስከታተለው የነበረው ይጠቅመኛል በማለት ሳይሆን የንግግሩ ችሎታና የቃሉ ጣዕም ኣንደሚወራለት እውነት መሆኑን ወይም ያለመሆኑን ለማረጋገጥ ነው እንጂ ይገልጻቸው የነበሩ ኃይለ ቃላትና ንግግሮች ጆሮዬ ላይ ሲደርሱ እግረ መንገዴን በአእምሮዬ ባመዛዝነውም ምስጢሩና ሐሳቡ ይጠቅመኝ ይሆናል የሚል ኅሊና አልነበረኝም። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜማ አምብሮዝዮስ ይገልጸው የነበረውን ሐሳብ እስከ መንቀፍ ደርሼ ነበር። በንግግሩ ጥራት፣ በቃላቱ አሰካክና አገላለጽ ብወደውና ባደንቀውም ዓላማዬ ምን ተናገረ? ምንስ ማለት ነው? ማለት ሳይሆን አባባሉን ለመስማትና ለመታዘብ ነበር። ነገር ግን የማልፈልገውና ይህን ያህል እመኘው ያልነበረ ቢሆንም እንኳ ይጥመኝና በጆሮዬም ያለማቋረጥ እየተንቆረቆረ ደስ ያሰኘኝ ከነበረው ንግግሩ ሳይታውቀኝ አንዳንድ ቁም ነገር ያዘለ ፍሬ ሐሳቡን መረዳት ጀመርሁ። እንዲያውም እያደር ፍሬ ነገሩን ወደ ጎን በመተው የንግግሩን ጣዕም ብች ማጣጣም አልቻልህ አለኝ። በቀጣይነት አነጋገሩን ለመስማት በተመኘሁ መጠን ቁም ነገሩንም ለማስተንተንና ለመረዳት የበለጥ ጉጉት አደረብኝ። ያ ስመ ጥሩ የወንጌል ሰባኪ ያሰማው የነበረው ፍሬ ሐሳብም ቁምነገሩና እውነቱ ጥቂት በጥቂት በልቤ ውስጥ ተመቻችቶ ሥር መስደድ ጀመረ።” ይላል።

የሚላኖ ጳጳስ አምብሮዝዮስ ያዘወትረው የነበረ ስብከተ ወንጌልና ያንፀባርቀው የነበረው ዘላለማዊ እውነት በቀጥታ በአውጎስ{jcomments on}ጢኖስ ላይ ቢያርፍም እንኳ ጠቅላላ ምስጢሩና ሐሳቡ የማይገባና ደስ የማይሰኝ ሆኖ ታየው። በዚህ ምክንያት አሁንም ወደ ቅዱስ መጽሐፍ መመለስና ቅዱሳት መጻሕፍትን እንደገና መመርመር ጀመረ። በርሱ ጊዜና ከርሱ በፊት የነበሩ ሊቃውንት የጻፏቸውን የጥበብና የእውቀት መጻሕፍት ስልና ብሩኅ በሆነ አእምሮውና በሰፊ አመለካከቱ ቶሎ ሲገነዘባቸው የቅዱሳት መጻሕፍትን ምስጢርና ትርጉም ግን በቀላሉ ሊረዳና ሊገነዘብ ስላልቻለ በወቅቱ ክርስትናን አልተቀበለም። ነገር ግን እንደዚህ ሆኜ እስከመቼ ድረስ እቀጥላለሁ? በማለት የልብ እረፍትና የመንፈስ ርካት የሚገኝበትን ተጨባጭ ነገር አገኛለሁ በሚል ሐሳብ ትምህርተ ክርቶስን ከሚማሩ ሰዎች ጋር መማር ጀመረ።

በዚህ ጊዜ እናቱ ሞኒካ ልጇን ለማግኘት ከሰሜን አፍሪካ ወደ ሚላኖ መጣች። አውጎስጢኖስም ትምህርተ ክርስቶስ ለመማር ያደረገው ቁርጥ ሐሳብ ደስ አሰኛት። ሆኖም ይህ ይበቃል ሳትል ልጅዋ ክርስትናን ከልብ እንዲቀበልና ቀጥሎም ንጹሕና የታረመ ኑሮን እንዲመሠርት ከፍ ያለ ጥረት አደረገች። በዚህ መሠረት በሕግና በቃል ኪዳን እንዲኖርም ለእርሱ እንድቶን ያሰብቻትን ልጃገረድ አጨችለት፤ ይሁን እንጂ የእጮኛይቱ ዕድሜ ለቃል ኪዳን የሚያበቃ ስላልነበር ወዲያውኑ ጋብቻ ለመፈጸም አልተቻለም ነበርና ጋብቻው ከሁለት ዓመት በኋላ እንዲሆን ተወሰነ። በዚህ ጊዜም ያለ ቃልኪዳን 13 ዓመታት ያህል አብራው የነበረችው ሴት ወደ አፍሪካ እንድትመለስ ተደረገ።

አውጎስጢኖስ የአእምሮና የመንፈስ እረፍት በማጣቱ አሊፒዩስ የተባለ ጓደኛውን “አረ ለመሆኑ ምን ይመስልሃል? ያልተማሩ ተራ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ባላቸው ኃይል ሁሉ ጥረት ሲያደርጉ እኛ ተምረና ተመራምረናል ባዮች በሥጋና ደም ተውጥን የምቀርበት ምክንያት ምንድነው…? በማለት ጠየቀው። አሊፒዩስ ግን ምንም አልመለሰም፤ በዚያን ጊዜ አውጎስጢኖስ ራቅ ብሎ ወደ አንድ በለስ ተክል ሥር ሄዶ በሉ ተደፍቶ “አምላኬ ፈጣሪዬ ሆይ! እስከ መቼ ነው የምትተወኝ? ብሎ ጸለየ። ይህን ጸሎት ካደረገ በኋላ አጠገቡካለ አንድ ቤት ውስጥ “አንሣውና አንብበው፤ አንሣውና አንብበው!” የሚል የአንድ ሕፃን ድምጽ ሰማ፤ ወዲያው ብድግ ብሎ ወደ አሊፒዩስ ሄዶ በዚያ የነበረን የጳውሎስ መልእክት መጽሐፍን ገልበጥ ቢያደርገው “በቀን ብርሃን እንደሚኖሩ ሰዎች በተገቢው አኳኋን እንመላለስ፤ ዘፈንንና ስካርን፣ ዝሙትንና መዳራትን፣ ጭቅጭቅንና ምቀኝነትን እናስወግድ። ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት እንጂ የሥጋችሁን ፍላጎት ለማርካት አታስቡ።” (ሮሜ 13:13-14) የሚሉት ሐረጎች አነበበ። ካነበበውም በኋላ በውስጡ የተሰማውን ለውጥ ለአሊፒዩስ ወዳጁ ገለጸለት፤ አሊፒዩስም ደግሞ ይህን የጳውሎስን መልእክት አነበበና እርሱም ወዲያውኑ ክርስቶስን ለመከተል ወሰነ።