እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ክፍል 5 - የአውጎስጢኖስ ይበልጥ ወደ ክርስትና ማዘንበል

የአውጎስጢኖስ ይበልጥ ወደ ክርስትና ማዘንበል

አውጎስጢኖስ የክርስትናን እምነት ለመቀብል በተቃረበብት ጊዜም ኔኦፕላቶኒዝም በተባለ አንድ የፍልስፍና ዓይነት ተማረከ። ሆኖም እውነትን ያስጨብጠኛል ብሎ የተከተለው ይህ ፍልስፍና ባስያዘው ፈለግ የሰው ልጅ በራሱ ኃይልና ችሎታ ብቻ ለነፍሱ ዕረፍትን ማግኘት እንደማይችል፤ እንዲሁም ሌላ ረዳት ኃይል የግድ እንደሚያስፈልገው ስለተረዳ ስለቅዱሳት መጻሕፍት አጥብቆ ለማሰብ እነርሱንም ለመመርመር ፈለገ። የእግዚአብሔርም ቃል እንደ ሰናፍጭ ዘር በልቡ ውስጥ ተስፋፋ። የቅዱስ መጽሐፍ ብርሃን ሙሉ በሙሉ በራለት፤ በተለይም በጳውሎስ መልእክታት ስለ ክርስቶስ አዳኝነትና ቤዛነት የተሰጠው ዘላለማዊ ትምህርት በቂ ማስረጃ ሊሰጠው ቻለ። ከዚህም ጋር በጠቅላላ የኃጢአት ክፋት በተለይም የራሱ ኃጢአት ጥልቀትና ክብደት ምን ያህል እንደሆነ በመረዳት ደኅንነት የሚያስፈልገው መሆኑን ተገንዝቦ በገዛ ራሱ ጥረት ወደዚሁ ግንዛቤ ቢደርስም ክርስትናን ሙሉ በሙሉ እንዳይቀበል መሰናክል የሆኑት አንዳንድ የሐሳብ ችግሮችና ሰብአዊ ድክመቶች ወደ ኋላ ይጎትቱት ነበር።

በአንድ ወቅት ፖንቲያኑስ የተባለ ክርስቲያን መኮንን አውጎስጢኖስን ከወዳጁ አሊፒዩስ ጋር አብሮ አገኛቸውና መወያየት ጀመሩ፤ በሚወያዩበት ጊዜም ፖንቲያኑስ በግብጽ ከሚገኙ ጓደኞቹ መካከል ሁለቱ መመነናቸውን ስለገለጸላቸው ሁኔታው የአውጎስጢኖስን ልብ በብርቱ ነካው፤ አውጎስጢኖስ በመላ ሕይወቱ ድክመቱንና ውድቀቱን ለማሸነፍ ባደረገው ጥረት የመንፈስ ጽናትና ብርታት የጎደለው መሆንን ተረዳ ተገነዘበም።

ቅ.አምብሮዝዮስ አውጎስጢኖስን እንዳጠመቀው

ከዚህ ሁሉ ሁከት፣ ችግርና ፈተና በኋላ አውጎስጢኖስ በመላ ዕድሜው በብርቱ ድካም የመንፈስ ዕረፍትና እፎይታን ማግኘትና ወደተመኘው የላቀ ዓላማ መድረስም ቻለ። ጋርዶት የነበረው የጥርጣሬ ጭጋግና ጨለማ ተወገደለት። የኃጢአቱን ይቅርታ ማግኘቱም ተሰማው፤ ተገነዘበም። ዓለማዊ ሐሳቦችና የተሳሳቱ ልማዶች ይፈነጩበት በነበረ ልቡ ውስጥ ሰላም፣ ደስታና እፎይታ ሰፈነ። ሰማይና ምድር ብሩህ ሆኖ ታየው፤ ሁሉን ነገር ጨርሶ በመተው ክርስቶስን ብቻ ማገለገል ፈለገ፣ ቁርጥ ውሳኔም አደረገ። ይህንንም ጥዑም ዜና ለእናቱ ሊያበሥራት ወደርሷ ሄደ። እናቱ ሞኒካ የረጅም ጊዜ ጸሎቷና ምኞቷ ስለተፈጸመላት አምላክን አመሰገነች። ይህ ሁኔታ በተፈጸመበት ጊዜ የአውጎስጢኖስ ዕድሜ 33 ዓመት ነበር፤ ይህም እ.ኤ.አ. በ386 ዓ.ም. ነው።

አውጎስጢኖስ እግዚአብሔርን በክርስትና እምነት የማግኘት ሂደቱን ጣዕም በሞላው ሁኔታ ሲገልጽ፦

“ታላቅ ነህ፤ ታላቅነትህ የማይለወጥ ዝንተዓለም ያው ሆኖ ሳለ እኔ ዘግይቼ ነው ያፈቀርኩህ። በርግጥ በውስጤ ነበርህ፤ እኔ ግን አንተን ፍለጋ ውጭ ውጩን ስባዝን ከቆየሁ በኋላ ዘግይቼ ወደድኩህ፤ አንተ በኔ ውስጥ እኔም ከውጭ ነበርኩና…አንተ ከኔ ጋር ነበርክ። እኔ ግን ካንተ ጋር አልነበርኩም። አንተ ወደኔ ጮኸህ ጠራኸኝ፤ ድንቁርናዬንም ከፈትህ። ጮራህዎችህን ልከህ አበራህልኝ፤ ዕውርነቴንም አባረርህ። ጣፋጭ መዓዛህን በኔ ላይ ተነፈስህ፤ እኔም ይህን ትንፋሽ ስቤያለሁ” ይላል።

በዚያን ጊዜ በነበረው ልማድ መሠረት ንኡሰ ክርስቲያኖች (ለመጠመቅ የታጩ) ሲዘጋጁ ይቆዩና በትንሣኤ ሰሞን ጥምቀትን በመቀበል ከኃጢአት ሞት ተነሥተው ክርስቶስን መስለው የሚታዩበት ወቅት ነው። በዚሁ ጊዜ ደግሞ በ387 ዓ.ም. በጌታችን ትንሣኤ በዓል ዕለት አውጎስጢኖስ ከልጁ አድዮዳቱስና ከአሊፕዩስ ወዳጁ ጋር በሚላኖው ጳጳስ በቅዱስ አምብሮዝዮስ አጥማቂነት ከመንፈስ ቅዱስ ዳግም ተወለደ።

እግዚአብሔር ፈቃዱን ለመፈጸም ሰውን እንደ መሣሪያ ስለሚያደርግ አውጎስጢኖስን በዝነኛው ቅዱስ አምብሮዝዮስ አማካይነት ለመልሰው ወደደ። ቅዱስ አምብሮዝዮስ በ340 ዓ.ም. የዛኔ ጎል ይባል በነበረው በዛሬው ፈረንሳይ አገር የተወለደ ሲሆን አውጎስጢኖስ በቤተ ክርስቲያን እቅፍ ውስጥ በገባበት ወቅት እሱ የሚላኖ ጳጳስ ሆኖ አሥራ አንድ ዓመት አገልግሎ ነበር። ቅ. አምብሮዝዮስ ከካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አበው መምህራን አንዱ ነው። የእርሱ ስመ ጥሩነትና ስብከተ ወንጌል አውጎስጢኖስ ሕይወት ላይ ታልቅ ግምትና ተጽዕኖ አለው።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት