እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ክፍል 6 - የአውጎስጢኖስ እናት ሞኒካ መሞት

የአውጎስጢኖስ እናት ሞኒካ መሞት

አውጎስጢኖስ የክርስትናን እምነት ከተቀበለ በኋላ የአስተማሪነት ሥራውን ትቶ ወደ አፍሪካ ለመመለስ ከቤተሰቡ ጋር ተነሣ። ኦስቲያ በተባለ ወደብ ሆኖም መርከቦችን ለመጠበቅ ውሎ ማደር ግድ ሆነባቸው። በዚህ ጊዜ ሞኒካ እናቱ በጠና ታማ ሞት አፋፍ ላይ ደረሰች። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች በአገሯ መቀበር እንዳለባት ሲጠይቋት “የትም ይሁን የት ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም፤ በሙታን ትንሣኤ ጊዜ ጌታ ለፍርድ ሲመጣ እኔ የምነሣበትን ሥፍራ እርሱ ይስተዋል ብሎ ማሰብ አይቻልም” ብላ መለሰችላቸው።

ቅድስት ሞኒካ በኦስቲያ ወደብ

አውጎስጢኖስ የቅድስት እናቱን የምድራዊ ጉዞ መጨረሻ ምዕራፎች እንዴት እንዳሳለፈች ሲመሰክር ሰፋ አድርጎ እንዲህ ገልጾታል፦

“ከዚህ ዓለም የምትለይበት (ሞኒካ) ጊዜ ሲደርስ አንተ ያወቅኸው እኛ ግን ያላወቅነው ቀን፤ አንተ ባዘጋጀኸው ምሥጢራዊ እቅድ በመሬት ላይ ካደረግነው ርጅምና አድካሚ ጉዞ ለባህር ጉዟችን ዕረፍት እይደረግን እኔና እርሷ ወደ አትክልት ቦታ አቅጣጫ ወዳለው መስኮት ተደግፈን ቆመን ነበር። እዚያ ሁለታችን ብቻ በጥልቅ ደስታ ተነጋገርን። ከኋላችን የተውናቸውን ነገሮች በመርሳት ከፊታችን ያለውን ነገር ተወያየን። እውነት የሆንህ ጌት አንተ ባለህበት ዓይን ያላየው፣ ጆሮ ያልሰማውና ወደ ሰው ልብ ውስጥም ያልገባው የቅዱሳን ዘለዓለማዊ ሕይወት ምን እንደሚመስል ማለትም ምን ሊመስል እንድሚችል ተጨዋወትን። ነገር ግን የልባችን አፍ ከፍተኛውን የምንጭህን ውሃ ካንተ ጋር ያለውን የሕይወት ምንጭ ተጠማ።
…ጌታ ሆይ! ስለነዚህ ነገሮች በተነጋገርንበት ቀን ዓለምና በውስጧ ያለው ደስታ ሁሉ ከምንነጋገረው ጋር ሲነጻጸር በጣም ርካሽ እንደነበር አንተ ታውቃለህ። እናቴም “ልጄ ሆይ! በበኩሌ እዚህ ዓለም ውስጥ ከዚህ በላይ ምንም ደስታ አላገኝም፤ ከዚህ ዓለም ምንም ነገር ከአሁን በኋላ ስለማልጠብቅ እዚህ ምን እንደምሠራ ወይም ለምን እዚህ እንዳለሁ አላውቅም። በዚህ ሕይወት ለትንሽ ጊዜ መቆየት ፈልጌ የነበረበት ምክንያት አንተ ክርስቲያን ሆነህ ለማየት ነበር። ይህንንም እግዚአብሔር ፈቅዶ አንተ የዓለምን ደስታ ንቀህ የእርሱ አገልጋይ ለመሆን መብቃትህን አይቻለሁ። ታዲያ ምን እሠራለሁ?” አለችኝ።
ምን ዓይነት መልስ እንደሰጠኋት በግልጽ ትዝ አይለኝም። ከዚህ በኋላ አምስት ቀን በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ኃይለኛ ትኩሳት ያዛት። በዚህም በሽታዋ አንድ ቀን ለጥቂት ደቂቃዎች ራሷን ሳተች። ወደርሷ ሮጠን ደረስን፤ ነገር ግን ወዲያው ነፍሷን አወቀች። እኔና ወንድሜ አጠገቧ ቆመን በማየቷ በመደነቅ “የት ነኝ?” ብላ ጠየቀች። ከዚያም በኀዘን ሰምጠን ምንም ሳንናገር በመቆማችን ትኩር ብላ አይታን “እናታችሁን የምትቀብሩት እዚህ ነው” አለች። እኔ ምንም ሳልናገር ላለማልቀስ እታገል ነበር፤ ወንድሜ ግን በትውልድ አገሯ ብትቀበር እንደሚደሰት ተናገረ። ነገር ግን እናቴ በዚህ ጊዜ በጭንቀት ተመለከተችው፤ ንግግሩ የምድራዊ ነገሮች ቃና ስለነበረው በዓይኗ ልትገታው ሞከረች። ከዚያም እኔን ተመለከተችና “እንዴት እንደሚናገር ተመልከት” አለች። በኋላም ለሁለታችንም “ይህን አካል በየትም አኑሩት፤ ስለሱ አትጨነቁ!...ነገር ግን በያላችሁበት ቦታ በጌታ መንበረ ታቦት እንድታስቡኝ እለምናችኋለሁ” አለችን። በምታውቀውና በምትችለው መንገድ ይህን ምኞቷን ከተናገረች በኋላ በሽታዋ ስለበረታባት ጸጥ አለች።”

አውጎስጢኖስ በገለጸልን በዚህ አኳኃን ሞኒካ በ56 ዓመቷ በ 387 ዓ.ም. ኦስቲያ በሚባል ቦታ ጣልያን ውስጥ አረፈች።

ሞኒካ የመንግሥተ ሰማይ ወራሽ መሆኗ የማያጠራጥር ቢሆንም ሞት የሚፈጥረው ጊዜያዊ አካላዊ መለያየት ኀዘንን ያስከትላልና በተለይም የአውጎስጢኖስ ልጅ ወጣቱ አድዮዳቱስ ስለ አያቱ ሞት አምርሮ ሲያለቅስ ያዩት የአባቱ ጓደኞች “ምሕረተ ወፍትሐ አኀሊ ለከ፤ እዜምር ወእሌቡ ፍኖተ ንጹሐ…” (መዝ.50) ማለትም አቤቱ ምሕረትንና ፍርድን እቀኝልሃለሁ፤ ንጹሕ መንገድንም አስታውሳለሁ የሚል መዝሙር በበገና ታጅበው መዘመር ጀመሩ፤ አውጎስጢኖስ በበኩሉ በር ዘግቶ በአንድ ክፍል ቤት ውስጥ ያለቅስ ነበር መሪር ኀዘኑን “መላ ዕድሜዋን ላለቀሰችልኝ እናቴ ትንሽ ባለቅስላት እንደ ኃጢአት የሚቆጥርብኝ ይኖር ይሆን?...” በማለት በልቅሶ ይገልጽ ነበር። እናቱንም ከመንገድ ዳር ከቀበረ በኋላ ወደ ሰሜን አፍሪካ ተጓዘ። ከዚህ በኋላ ሁለት ጊዜ ሮማን ከመጎብኘቱ በስተቀር የተቀመጠው በትውልድ አገሩ በሰሜን አፍሪካ ነው። አባቱ ካወረሰው ንብረት ለኑሮው የሚሆነውን ብቻ አስቀርቶ ሌላውን ሁሉ በመሸጥ ለድኾች አከፋፈለው። ከዚያ በኋላ ከወዳጆቹ ጋር ሦስት ዓአት ያገኙትን በአንድነት በማድረግ በኅብረት መኖር ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ከዓለማዊ ሐሳብ ተለይቶ በጸሎትና በመጻሕፍት ምርምር ተጠምዶ ክርስቲያናዊ ሕይወቱ እይበረታ በሄደ መጠን በሰቂለ ኅሊና የአምላክ ጸጋን ማሰላሰልና የተቀደሰ ሕይወትን መኖር ቀጠለ።

በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ምእመናን ሀብትን በሚመለከት ረገድ መስገብገብን ትተው እርስ በርስ በፍቅር እንዲተሳሰሩ መክሯቸዋል፤ አስተምሯቸዋልም። አውጎስጢኖስ ራሱ በንጽሕና ለመኖር ወሰነ፤ ብዙ ገዳማትንም ተከለ። በታጋስቴና በሂፖ አካባቢ ያቋቋማቸው ገዳማት ለአያሌ ዘመናት በሰሜን አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ያገለገሉ ካህናትና ዲያቆናት እየተማሩ የሚወጡበት፤ የክህነት ጥሪም የሚያብብበት ሆኖ ቀጥሎ ነበር።

የቅድስት ሞኒካ አስክሬን አሁን የሚገኝበት በልጇ ስም የተሰየመው ደብር - ሮማ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት