የሕፃኑ ኢየሱስ ቅድስት ተሬዛ

የሕፃኑ ኢየሱስ ቅድስት ተሬዛ

St Therese of the Child Jesus WEBየሕፃኑ ኢየሱስ ቅድስት ተሬዛ እ.ኤ.አ. በ1873 ዓ.ም. አሌንኮ ፈረንሳይ ውስጥ ተወለደች፡፡ ገና በወጣትነቷ ወደ ቀርሜሎሳውያት ገዳም ገብታ ትሕትናን፣ ወንጌላዊ የዋህነትንና በአምላክ ጽኑ እምነትን ተማረች፡፡ በቃላቷና በምሳሌዋ ወደ ማኅበሩ የሚገቡትን አስተማረች፡፡ ይህች ቅድስት ሴት ሕይወቷን ለነፍሶች ደኅንነትና ለእምነት መሰራጨት በጥልቅ ፍቅር ስታቀርብ ኖራ መስከረም 20 ቀን 1897 ዓ.ም. በ24 ዓመት እድሜዋ አረፈች፡፡

ከቅድስት ትሬዛ የሕፃኑ ኢየሱስ የግል ሕይወት ታሪክ የተወሰደ ንባብ

“በቤተ-ክርስቲያን ጥልቅ ልብ ውስጥ ፍቅር ስለመሆን”

መልስ አገኛለሁ ብዬ በማሰብ የቅዱስ ጳውሎስን መልእክቶች ለማማከር በወሰንኩበት ወቅት ባልረኩ ከፍ ያሉ የሰማእትነት ምኞቶች ጥያቄ እቸገር ነበር፤ ለጸሎቴም እንቅፋት ሆኖብኝ ነበር፡፡ በዚያም ወቅት የማረኩኝ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ከተላከው አንደኛ መልእክት አሥራ ሁለተኛውና አሥራ ሦስተኛው ምዕራፎች ናቸው፡፡

አሥራ ሁለተኛው ምዕራፍ ሁላችንም ሐዋርያት፣ ነቢያት፣ ወይም የሃይማኖት ምሁራን ልንሆን እንደማንችል አስረዳኝ፣ ቤተ-ክርስቲያን በሙያቸው በተለያዩ አባላት የተገነባች ናት፤ ዓይን የተለየ ተግባር አለው፤ እጅም እንደዚሁ፡፡ ይህ ግልጽና ብቁ መልስ ነበር፤ ነገር ግን ምኞቴን አላረካልኝም፤ ልቤንም አላሳረፈልኝም፡፡ እስከ ምዕራፉ መጨረሻ ሳነብ “የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ፣ ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ” የሚለውን የመጽናኛ ቃል አገኘሁ፡፡ ይህ የጸጋ ስጦታ ምንድነው? ሐዋርያው ማብራሪያውን ሲቀጥል ፍጹሞች የሰማይ ስጦታዎች እንኳን ያለ ፍቅር ምንም ጥቅም እንደሌላቸው ይነግረናል፡፡

ፍቅር ከሁሉም የበለጠው መንገድ ነው፤ በቀጥታ ወደ እግዚአብሔር ይመራልና፡፡ አሁን ሰላም አግኝቻለሁ፤ ቅዱስ ጳውሎስ ስለተለያዩት የረቂቅ አካል አባላት የተናገረውን ሳነብ ራሴን በማናቸውም ውስጥ ላውቅ አልቻልኩም፤ ወይም ራሴን በሁሉም ውስጥ ላውቅ ችዬ ነበር፡፡ ነገር ግን ፍቅር የተልእኮዬ ምሰሶ ነው፡፡

ቤተ-ክርስቲያን በተለያዩ አባላት የተገነባች አካል ከሆነች ከሁሉ የበለጠው ስጦታ ሊጐድላት አይችልም፤ በፍቅር የሚቃጠል ልብ ሊኖራት ይገባል፡፡ ሌሎቹ የቤተ-ክርስቲያን አባላት እንዲሠሩ ያስቻላቸው እውነተኛ አነሳሽ ኃይል ይህ ፍቅር እንደነበረም ተረድቻለሁ፡፡ ይህ ፍቅር እንቅስቃሴውን ካቋረጠ ሐዋርያት ወንጌልን መስበክ እንዳለባቸው ይዘነጋሉ፤ ሰማእታትም ደማችንን አናፈስም ይላሉ፡፡ በርግጥ ፍቅር ሌሎቹን ሁሉ የሚያጠቃልል ተልእኮ ነው፤ ጊዜንና ቦታን የያዘ የራሱ ዓለም አለው፤ ዘለዓለማዊም ነው፡፡

በደስታ ራሴን ረስቼ “ኢየሱስ የኔ ፍቅር፣ ተልእኮዬን ተረድቻለሁ፤ እሱም ፍቅር ነው” ብዬ ጮህኩኝ፡፡ በቤተ-ክርስቲያን ውስጥ የኔ ቦታ የትኛው እንደሆነ፤ እግዚአብሔር ለኔ ያዘጋጀልኝን ምቹ ቦታ አግኝቸዋለሁ፡፡ በእናት ቤተ-ክርስቲያን ጥልቅ ልብ ውስጥ ከፍቅር ሌላ ምንም መሆን አልፈልግም፡፡ ይህም በአንድ ጊዜ ሁሉም ዓይነት ነገር መሆን ነው፤ ከዚህ ሌላ ያለምኩት ሕልም አልነበረምና!

ከአበው መንፈሳዊ ፍርፋሪ የተወሰደ።

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።