ዘአስተምሕሮ 2ኛ

ዘላለማዊነትን በዘመናዊነት መለወጥ!

ዮሐ.5:16-27 ቆላ.1:12-29 1ጴጥ.1:13-20 ሐዋ.19:21-40

Ab Weldየዛሬው ወንጌል ክርስቶስ ከአይሁዳውያን ጋር ያደረገውን ንግግር በመተረክ ስለ እግዚአብሔር ቀጣይ ምሕረት እንድናስተነትን ይጋብዘናል። ኢየሱስ ሠላሳ ስምንት ዓመት ሙሉ የታመመን አንድ ሰው በዓይናቸው ፊት ከፈወሰ በኋላ አይሁዳውያን ኢየሱስን ያሳድዱት ጀመር። ኢየሱስ ግን "አባቴ ሁልጊዜ ይሠራል፤ እኔም እሠራለሁ" ሲል መለሰላቸው (5:17)። ይህንን የኢየሱስ መልስ በሰሙ ጊዜ አይሁዳውያን ኢየሱስን ይገድሉ ዘንድ ይበልጥ ተነሣሡ። ምክንያቱም ይላል ወንጌል ሰንበትን በመሻሩ ብቻ ሳይሆን "እግዚአብሔር አባቴ ነው" በማለቱ ነበር።

ሰው ለምን በእግዚአብሔር መልካም ሥራ አይደሰትም ብለን ብንጠይቅ ብዙ ምላሽ ይኖር ይሆናል፤ ግን ሰው የራሱ ሥራ ክፉ በሆነና እግዚአብሔርን እንደሚያሳዝን ባወቀ መጠን ሆኖም ግን ወደ ቀና መንገድ መዞር መምረጥን ካልፈለገ እግዚአብሔር ለሌሎች ሰዎች በሚያደርግላቸው መልካም ነገር ሁሉ ያዝናል። የሌሎቹ መልካምነት የርሱን ጎዶሎነት ያስታውሰዋልና መልካም ነገሮችን በይፋ መቃወም ይጀምራል። አባት፣ አባባ ብለን እንጠራው ዘንድ የተሰጠንን ጸጋ በመርሳት እግዚአብሔርን አባት ያለማድረግ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም አባት መሆኑን እንቃወማለን። አይሁዳውያን ከነበራቸው የሃይማኖታቸው ግንዛቤ ባሻገር የመመጻደቅ ድርጊቶቻቸው የእግዚአብሔርን ሥራ እንዳያዩ ጋርዷቸው ነበር።

የኛን ውስጣዊ የእግዚአብሔር ስዕል በመጠኑ እንይ። ክርስቶስ "አባታችን ሆይ!" ብላችሁ ጸልዩ ብሎ ሲያዘንና "የሰማይ አባታችሁ" ብሎ ሲያስተምረን "እግዚአብሔር አባቴ ነው" የሚለውን እወጃ ለኛም ሰጥቶናል። ክርስቶስ ከአባቱ ጋር ያለው ብቸኛ የልጅነት ደረጃን ባይሆንም የጸጋ ልጅነት ተሰጥቶናል፤ ታዲያ አፋችንን ሞልተን "እግዚአብሔር አባቴ ነው" ማለት እንችል ይሆን?

ይህን ማለት መቻል በሌላ አባባል እኔ የእግዚአብሔር ነኝ የሚል መልእክት ማስተላለፍ ማለት ነው። ዛሬ ዛሬ እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ማለት በማኅበረሰባችን ውስጥ ብዙ ቅጽል ነገሮችን የሚያሰጥ ስለሆነ የዘመናዊነት ክፍል መሆን እፈልጋለሁ ብሎ የሚያስብ ሰው የእግዚአብሔርን አባትነት በይፋ ሕይወቱ ማወጅ ብዙም አይዋጥለትም። ይህ አካሄድ ግን ድምዳሜው ላይ ሲደርስ መዘዙ ዘላለማዊንትን በዘመናዊነት መቀየር ይሆናል። ይህ በሕይወቴ ይታያል ወይ በማለት እናስተንትን።

እግዚአብሔር አባቴ ነው ማለት ትልቅ ምስጢር ውስጥ ራስን ማስገባት ማለት ነው። ክርስቶስ ወንድሜ፣ ቅድስት ድንግል ማርያም እናቴ፣ መላእክቶች ጠባቂዬ፣ ቅዱሳኖች አማላጆቼ ማለት ነው። የእሱን አባትነት ተቀብሎ ሌሎቹን ማስወገድ ያስቸግራል፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቤተሰብ ስፋት እኛ ከምንገምተው በላይ እርስ በርስ የተሳሰሩና ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚለው እጅና እግር አንዱ ለአንዱ እንደሚረዳ እንዲሁ የተጠማመረ ኅብረት ያለው ነው። እስቲ ይህን ምስጢር እናስበው፤ ደካማነታችን ዓይናችንን ጋርዶን ራሳችንን ብቻ በሚያሳየን ሰዓት የእንደዚህ ዓይነት ትልቅ ቤተሰብ አባል መሆናችን ትልቅ ጸጋ መሆኑን እናስታውስ። ተፈጥረን በዚች ፕላኔት ተውጠን እንድንቀር አይደለም የእግዚአብሔር ፈቃድ። የዚች ዓለም ውስንነት መልእክት ሁልጊዜ ከዚህም በላይ ሕይወት አለ የሚል ነው። የእርሱ ልጅ መሆናችን ገድበው ከያዙን ነገሮች ላቅ ያለ ዓላማና ውሳኔ እንዲኖረን ይጋብዘናል።

ጠንካራ የሚመስለው ሰው ሲወድቅ፣ ሀብታሙ ሀብቱን ትቶ ከምድር ሲሰናበት፤ ነገሮች ሁሉ ቁርጥራጭ ሆነው ሲታዩን ማንነታችንን ወደ ሕያው ከፍታ የሚያነሳው ብቸኛ እውነት የእግዚአብሔር ልጅ መሆናቸን ነው። ይህ ባይሆን በርግጥ ምድር ከመልስ ይልቅ ጥያቄን የምታበዛ መቆያ ቦታ ብቻ ሆና ተስፋ ባሳጣችን ነበር። ነገር ግን ይህች ዓለም እናተርፍባት ዘንድ ተሰጥታናለች፤ ከርሷ የበለጠውን እናገኝ ዘንድ ወደርሷ መጥተናል እንጂ እርሷን አግኝንተን ከርስዋ የበለጠውን እንድናጣ አይደለም። ክርስቶስ "ሰው ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ቢሆንና ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል" (ማቴ.16:26) እንዳለው ነው። "እግዚአብሔር አባቴ ነው" ማለት የዚችን ምድር ነገር ለቀቅ ለቀቅ ማድረግ ማለት ነው። ቅዱስ አውጎስጢኖስ ዕድሜያችን ዘላለማዊነትን እናገኝበት ዘንድ ተሰጥቶናል እንጂ ምድራዊውን ኑሮ ብቻ እንኖር ዘንድ አይደለም፤ ለምድራዊ ኑሮ ብቻ የተፈጠርን ከሆንንማ ይህች ዕድሜያችን በጣም አጭር ናት ይላል።

ውሏችንን ስንጀምር "እግዚአብሔር አባቴ ነው" ብለን እንውጣ፣ ስንውልም ሆነ ውሏችንን ስንደመድም "እግዚአብሔር አባቴ ነው" ብለን እናስብ። ምናልባትም ይህን በምናነብበት ሰዓት ራሱ አቋርጠን "እግዚአብሔር አባቴ ነው" እንበል......። ማን ያውቃል ይህን ማለት የሚከብደን ሁኔታ ውስጥ ልንሆን እንችላለን፤ እግዚአብሔር ግን ከሁኔታዎች በላይ ነውና አባትነቱ አይቀየርም። ስለዚህ ውስጣችን ቢዝል፣ ተስፋ ማድረግ ቢሳነን፣ ከኃጢአታችን ጋር ያለን ቁርኝት የበረታብን ቢመስለን፣ የኑሯችን ደባል ራሱ ብቸኝነት ሆኖ በሚሰማን ሰዓት.....ሁሉ ኢየሱስ ሊያጠምዱት በሚያሳድዱት ፊት የሰጠው መልስ በአንደበታችን ይሁን:- "እግዚአብሔር አባቴ ነው"።

ኢየሱስ ለአይሁዳውያን ሲመልስላቸው "አባቴ ሁልጊዜ ይሠራል" አላቸው። ይሄኮ ለሰው ሁሉ መልካም ብስራት መሆን የሚገባው ነገር ነው። ከመደሰት ይልቅ ሁሌ ይሠራል ስላላቸው ያሳድዱት ጀመር። እግዚአብሔር የማይሠራበት ጊዜ ቢኖር ምን ይውጠን ነበር። ኢየሱስን አይሁዳውያን ሰንበት ነውና ምንም አትሥራ ሲሉት፤ እሱ ግን "ሁልጊዜ" መሥራት እንዳለበት ያውቃልና እንደ አምላክነቱ ለሰው ልጅ በጎን ከማድረግ ምንም እንደማይገታው አስረዳቸው።

አንዳንዴ የሰው ልጅ እግዚአብሔር እንዳይሠራ የሚፈልግበት ጊዜ ሊኖር ይችላል ብለን ካሰብን ክፉን ስናደርግ ወይም ማድረግ ስንፈልግ ብቻ ሊሆን ይችላል፤ ግን እሱ ሁሌም ይሠራል። ክፋትን ስናደርግም ቢሆን እሱ ይሠራል፦ የእሱ ሥራ ምሕረት ነው። በምንፈልገውም በማንፈልገውም ጊዜና ቦታ፣ የዕድሜ ደረጃና የአናኗር ዘይቤያችን ሁሉ እሱ ሁልጊዜ ይሠራል፣ ሁልጊዜ ይቅር ይላል። ቤኔዲክቶስ 16ኛው "እግዚአብሔር ሲገባበት በረሃው ለምለም ይሆናል" እንዳሉት የደረቀና የጠወለገ መንፈሳዊነታችንን እሱ እንዲያለመልምልንና የእርሱ ልጅ የመሆናችንን ክብር ዳግም እንጎናጸፍ ዘንድ ከርሱ ሰፊ ቤተሰብ ጋር የቃሉና የማዕዱ ተካፋይ እንሁን፤ ሁልጊዜ የሚሠራ አባት ሊሆነን ስለፈቀደም የተመሰገነ ይሁን።