የተጠራነው ለቅድስና ሕይወት ነው

የተጠራነው ለቅድስና ሕይወት ነው

የእግዚአብሔር ዓላማ በሰው ልጆች ሕይወት ላይ እስኪፈጸም ድረስ በነገሮችና በሁኔታዎች በመረጣቸው ሰዎችና ቅዱሳን፣ በተፈጥሮና በአካባቢ በትልቁም በትንሹም በቅድስና ሕይወትን እንድናውቅና እንድንኖር ዘወትር በመለኮታዊ ኃይሉ እንድንመለከት ይፈልጋል፡፡ እውነቱን አውቀን ከእውነታው ተስማምተን በተከለልን ቅዱስ ቃል ተመርተን የእርሱ ብቻ ሊያደርገን ካሰበልን የሕይወት መንገድ ተዘናግተን እንዳንጠፋ ሊረዳን ሌት ተቀን ይተጋል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ እንደምናየው ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያምን ከሴቶች መካከል ሲመርጣት በእግዚብሔር  የተለየች፣ ለዓላማው ጽኑ ልብ ያላት፣ በሁኔታዎች የማትለዋወጥ፣ ችግሮችንና ፈተናዎችን ያለ ምንም ማወላወል የምትጋፈጥ ቅን አገልጋይቷን በተግባር ማስመስከር የቻለች ብፅእት ሆና ስላገኛት የሁላችን እናት እንድትሆን ፈቀደ፡፡ “ከጌታ የተነገረላት ያመነች ብፅእት ናት” ሉቃስ 1፡45 በድንግልናዋ የአምላክ ማደሪያ እንድትሆን እግዚአብሔር ሲመርጣት ለራሷ ሀሳብና ፍቃድ ፍኞትና ሰብአዊ ፍላጐቶቿ ልትጠቀምበት አልሞከረችም፡፡ እንዲያውም በሙሉ ፍቃዱ እርሱ እንዲገለገልባት “እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” ሉቃስ 1፡38 አለች፡፡ ለእግዚአብሔር ባላት የተለየ ጽናት በልጇ የመስቀል ጉዞ ወቅት ለእናትነት ልቧ ሳትሸነፍ በትእግስት የእግዚብሔርን ሀሳብ በመፈጸም የስቃዩ ተካፋይ ሆናለች፡፡

በዘመናችን እንደማርያም ሁሉ በምድር ሕይወት የእግዚያብሔርን ፈቃድ በመፈጸም ለቤተክርስቲያን ታላቅ ተስፋ ለአገልጋዮች ምእመናን ወጣትና ህፃናት በጎ ምሳሌ የሆኑ በርካታ ቅዱሳንን ማግኘት ችለናል። ከነዚህም መካከል ሚያዝያ 23 ቀን 2003 ዓ.ም ብጹዕ የተባሉት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እግዚአብሔር በወደደው ምርጫ ሕይወታቸውን ለእርሱ በመስጠት ለዓለም ሕዝብ የቅድስና ሥራ ማሳያ ሆነዋል ዘር ጎሳና ጾታ፣ ሀይማኖት ሳይለዩ ለሰው ልጆች መብት መከበር የቆሙና አያሌ መልካም ስራዎችን የሰሩ አባት ናቸው። ብጹእነታቸው የተቀበሉትን ጸጋ በመጠቀምና የክርስቶስን ምድራዊ ህይወት ምሳሌ በማድረግ አለምን ባስገረመ መልኩ የይቅርታን ምንነት ለሁላችን ያሳዩ ስለሰላም ቆመው እውነትን የሰበኩ መንፈሳዊ ህይወትን ተላብሰው እና ኖረው የብዙዎችን ነፍስ ወደ አምላክ የመለሱ ታላቅ የእግዚአብሄር አገልጋይ ናቸው። "ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና።" ማቴ 5.5

ቅድስት ቤተክርስቲያን ለዘመናት ልጆችዋን  በማስተማር ለተቀደሰ ህይወት እንዲበቁ ታደርጋለች እኛም የቅድስና ሕይወት ለመኖር እንድንበቃ በማይታበይ ፍቅሩ ወደዘላለማዊ ህይወት እንድንጓዝ በነጻነት ለፈቀደልን አምላክ ሕይወታችንን አሳልፈን መስጠት ይኖርብናል፡፡ እንደተጠራንበት መጠን እግዚአብሄር በጸጋ ዝግጁዎች ያደርገናል፡፡ እኛም በፈቃዳችን ምላሽ በመስጠት ለቅድስና ህይወት እንድንበቃ በመንፈስ ጠንካራነት የድል አክሊል ተሸላሚዎች እንድንሆን እውነተኛ ወደሆነው ክርስቲያናዊ ህይወት በመመለስ የመንግስቱ ተጋሪዎች ልንሆን ይገባናል፡፡

ምንጭ፡- ፍቅርና ሰላም ግንቦት ፳፻፫ ዓ.ም.