ቅድስት ዮሴፋዊት ባኪታ /1869-1947/

ቅድስት ዮሴፋዊት ባኪታ /1869-1947/

Bakhita

Bakhita Kwashe-big

"ዓለም ገና ክርስቶስን አታውቅምና ሥጋዬን ሁሉ በጣጥሼ እስከ ምድር ዳርቻ በመዝራት ጌታ ኢየሱስን በሕይወቴ እሰብካለሁ" ቅድስት ባኪታ

የዚህች አስገራሚ ሱዳናዊት ወጣት የሕይወት ጉዞ፣ በ191ዐ አንዲት መነኩሲት ከተረከችላት ታሪኳ የተገኘ ነው፡፡ በልጅነት ዕድሜዋ በባሪያ ንግድ ምክንያት በእጅና በእግር ብረት ታስራ ከመንደሯ ተወሰደች፣ ከብዙ ስቃይ በኋላ በጣሊያን የካኖሲያን መነኮሳት አባል በመሆን ለ5ዐ ዓመታት በምንኩስና ኖረች፡፡ ስሟ ማን እንደነበር የማታስታውሰው ይህቺ ቅድስት ፍቅር ከሞላበት ትልቅ ቤተሰብ እንደተወሰደች ትናገራለች፣ /በባሪያ ንግድ ገና በሕፃንነቷ በመወሰዷ እና በማታውቃቸው ሥፍራዎች በተለያየ ጊዜ በቤት ሠራተኛነት ማገልገሏ ለዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል/ የዚህች ቅድስት የትውልድ ስፍራ በምዕራብ ሱዳን የምትገኘው ዳርፉር ግዛት ውስጥ ከሚኖረው የደጁ ጐሣ ነው፡፡ በባርያ ንግዱ ወቅት ከስለትና ከጠመንጃ አፈሙዝ በመትረፏ ከአፋኞች አንዱ እንዳው በመላ "ባኪታ" ሲል ስም አወጣላት፣ ትርጉሙም "እድለኛዋ" እንደማለት ነው፡፡ ባኪታ ለአንድ ቱርካዊ የጦር አዛዥ ተሸጠች፣ በዚህ ቤት ውስጥ እጅግ ዘግናኝ የሆነ ድርጊት ተፈጸመባት፡፡ ገላዋን በስለት በመብጣት አንድ መቶ አርባ ጊዜ ነቀሷት፡፡ ቁስሉ ውስጥም ጨው ጨመሩበት፤ ከሶስት ዓመታት በኋላ የጦር አዛዡ ወደ ቱርክ በመመለሱ ባኪታ አለቃ ካሊስቶ ሌኛኒ ለተባሉ አንድ ኢጣሊያናዊ ሰው ተሸጠች፡፡ ከዚህ ቤተሰብ ውስጥ በነፃነት መኖር ቻለች፣ አሳዳሪዎቿ ደግ ሰዎች ነበሩና ስቃይ ከርሷ ራቀ፡፡ በ1889 ዓ.ም በኢጣሊያ እያለች ባኪታ ከክርስትና ሃይማኖት ጋር ተዋወቀች "ኢሉማናቶ ቼኪኒ" የተበለ ፖለቲከኛና ጸሐፊ የጌታን ሥቅለት ያዘለ መስቀል ከሰጣት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ኢየሱስ ነገራት፡፡

ባኪታ በጥር 9 ቀን 189ዐ ዓ.ም ጥምቀት ፣ ቁርባንና ምስጢረ ሜሮን በአንድ ላይ ተቀበለች፡፡ ከሶስት ዓመታት በኋላ ስዓሊ /ፖስትላንት/ ሆና የካኖሲያን እህቶች ገዳም ተመክሮ ቤት ገባች፡፡ በዚህ መልክ "ባሪያ" የነበረችው አፍሪካዊት የሱዳን ተወላጅ በኢጣሊያ ነፃ ሆና የምንኩስና ሕይወት መኖር ጀመረች፡፡ ጥቁርነቷ በሁሉ ዘንድ ዝቅ ተደርጋ እንድትታይ ምክንያት እንደሆነ ባወቀች ጊዜ "አዎ እኔ ጥቁር ነኝ ምስኪን ጥቁር ሴት" በማለት በተደጋጋሚ ትናገር ነበር፡፡ በኢጣሊያ ሃገር ጥቁር ሆኖ መገኘት ብዙም ባልተለመደበት ወቅት ባኪታ ባላት ቅንነትና ተንከባካቢነት የአገሬው ሰው "ትንሿ ጥቁር እናታችን" እያለ ይጠራት ነበር፣ ከዚህም በላይ በአካባቢው ማኀበረሰብ እንደ ቅዱስት ትታይ ነበር፡፡ ሕይወቷ አስገራሚ ክርስቶስን የማወቅ ጉዞ በመሆኑ ለብዙዎች አስተማሪ ነበር፤ ብዙ እህት መነኮሳንን ያጽናና ነበር፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እርሷ በገዳሙ ውስጥ በመኖሯ ብቻ ገዳሙ ከቦንብ ድብደባ የድናል ብለው መነኮሳን ያምኑ ነበር፡፡ ቅድስት ባኪታ የካቲቲ 8 ቀን 1974 ዓ.ም በሳንባ ምች በሽታ ሕይወቷ አለፈ፡፡ በግንቦት 17 ቀን 1992 በብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ብፅዕናዋ ታወጀ፣ ቅድስቲቱ ስትጠቀምባቸው የነበሩት እቃዎች በሙሉ በ1993 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ ብፁዕ ዮሐንስ ዳግማዊ እጅ በሱዳን ካርቱም በተደረገ ቅዳሴ ላይ ለሊቀ ጳጳሱ ተሰጠ፡፡ ቅድስናዋ በ2ዐዐዐ ኢዮቤልዩ ታወጀ፡፡ ቅድስት ባኪታ የተጨቆኑ ሴቶችና ሕፃናት እንዲሁም ስለ ክርስቶስ መከራን በመቀበል ላይ ለሚገኙ ሁሉ ጠባቂ ቅድስት ተደርጋ ትከበራለች፡፡