ቅ. አቡነ ቡሩክ- እግዚአብሔር ለአንድ ተግባርና ሥራ ይጠራናል

ግቢያ

St_Benedict_

እግዚአብሔር ዓለምን ጥንት ከነበረው ትርምስ ነፃ እያወጣ ወደ ሕይወት ሲጠራ፤ ቅዱስ ቡሩክም ልክ እራሳቸውን ስተው ከተኙበት ጭልጥ ካለ እንቅልፍ ድንገት እንደባነኑ ያህል በእግዚአብሔር ጥሪ ነቅተው የሰው ልጅን የሥራ ጥሪ ባዘጋጁት ደንብ ውስጥ ገልጸዋል፡፡ ይህን የመሰለው የቅዱስ ቡሩክ ገለፃ በራሳቸው ሕይወት ውስጥ የተሞከረውን የዳግም ልደት ልባዊ ፍቅርና ትልቅ የትኩረት አቅጣጫ አካቷል፡፡

የሰው ልጅ አንዴ ከነቃ የጥሪውን ይዘት ለመቀበል ዝግጁ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ለአንድ ተግባርና ሥራ ይጠራናል፤ ጌታ የራሱን ሠራተኛ በእነዚህ ቃላት ይጠራዋል፡፡ “ሕይወትን የሚሻና ጥሩ ቀናትን ለማየት የሚወድ ሰው ማነው?” ይህንን ጥሪ የምታዳምጥ ሰው “እነሆ እኔ ነኝ!” ብለህ ከመለስክ እግዚአብሔር የሥራ ኮንትራቱን ያደራጃል፡፡ እንዲህም ይልሃል፡፡ “ምላስህን ከእኩይ ነገር ጠብቅ ከንፈሮችህም ክፋ ነገር እንዳይናገሩ ተጠንጠቅ፣ ከክፋ ሥራ በመራቅ ጥሩ ሥራ ሥራ፤ ሰላምን ፈልግ ከተከላትም”

ይህንን ተግባር በሚገባ ከተወጣን፤ “ዓይኖቼ እናንተ ላይ ጆሮዎቼም ለጸሎታችሁ ክፍት ይሆናል፤ እናም እኔን ከመጥራታችሁ በፊት እንዲህ እላለሁ “እዩ እኔ እዚህ ነኝ” ውድ ወንድሞቼ ጌታ

እኛን ከጋበዘበት ከዚህ ድምጽ የበለጠ የሚጣፍጥ ነገር ምን አለ ተመልከቱ፤ ርህራሄ በተሞላበት ደግነቱ ጌታ የሕይወትን መንገድ አሳይቶናል፡፡ ፍሬያማነቱም የአንድ ሰው ለክርስቶስ ሙሉ በሙሉ መገዛት ሲሆን፤ እሱ ከሚሻው ባሻገር ማለትም ፈቃዱን ከመተግበርና በትዕዛዛቱ ከመታመን ሌላ ምንም ነገር የማይፈለግበት ነው፡፡

አንባቢ ሆይ እዚህ ውስጥ የምታገኘውን በሙሉ ውሰድ፤ በርግጥ ረሃብህን ታስታግስበታለህ፡፡ አንድ ብዙ ትኩረት ያልተሠጠው ነገር ግን ሕይወትን በሚቀይር ነገር፡፡ ይህም ስለ አቡነ ቡሩክ ነው፡፡ በርግጥ ይዘቱ ስለ ገዳም ቢሆንም እንኳን “ጸሎት እና ሥራን” የምናስማማበትን ደንብ የምንረዳበት ነው፡፡

“መቅደሱ እንደመጠሪያው ይሁን ስሙን ይጠብቅ። ሌላ ምንም ተጨማሪ ሥራ አይሠራበት፤ እግዚአብሔርን የተመለከተ ሥራ ማለትም ጸሎት ከተጠናቀቀ ሁሉም በፍጽም ፀጥታ ይውጡ ለጌታ ጥልቅ አክብሮት ያሳዩ፡፡ ማንም ለብቻው ሆኖ መጸለይ ከፈለገ  ከፍ ባለ ድምፅ ሳይሆን በትሕትና እንባ በተሞሉ ዓይኖችና በተመሰጠ ልብ ይጸልይ” ቅ.አቡነ ቡሩክ ("መቅደስ" የኛም ሰውነት መሆኑን ልብ ይሏል){jathumbnail off}

ቅዱስ አቡነ ቡሩክ

ታላቋ ሮም ታላቅ ሆና መቆየት አልተቻላትም፣ አደባባዮቿ የውድቀትን ነፋስ ማስተጋባት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ሕዝቦች ለጥበብ ከመትጋት ይልቅ መሳርያዎቻቸውን ወዲያ ጥለው የማያልቅ ዘፈን አዝማሪዎች ሆነዋል፡፡ በዚህ ወቅት በኡምበርያ ከተማ ኖርቺያ ከምትባል አንዲት ታናሽ መንደር አንድ ህፃን ከሮማውያን ቤተሰ ተወለደ፡፡ ይህ ህፃን በ17 ዓመት ዕድሜው የዕውቀት ረገቡን ለማስታገስ ወደ ሮም ዩኒቨርስቲ አመራ፤ ህይወት እንደታለመችው አልሆነችም፤ ዩኒቨርስቲው የዕውቀት ዛብ ከማብቀል ይልቅ የሞት ዕፀ በለስ ያፈራ ነበርና አቡኑ ህይወታቸውን በዚህ ውስጥ ጥለው ማጥፋትነ አልመረጡም፤ ይልቁንስ በጊዜው ለርሳቸው ነፍስ ብቻ በታየው አምላካዊ ብርሃንና መለኮታዊ ጥሪ መሪነት ወደ በረሃ ሄዱ፡፡

“ጌታ በታናሽ  መንደር እንደተወለደ አቡነ ቡሩክም ከተረሳች ከተማ ተወለዱ፤ ሁለቱን የሚያመሳስላቸው ነገር ያ ነው፤ ሁለቱም ዓለምን ከውድቀት ወደ ብርሃን አምጥተዋልና”

ከሮም በስተምስራቅ በሚገኘውና “ሱቢያኮ” በተባለው በረሃ በአንዲት ዋሻ ውስጥ በቀን ቁራሽ ዳቦ በመብላት ለ20 ዓመታታ በዚየ ኖረዋል፡፡ አቡኑ ምንም ያልተነራቸው ሲሆን የሚቀምሷትን ቁራሽ እንኳን የምታመጣላቸው አንዱት ቁራ ነበረች፡፡ ጊዜው እየረዘመ በመጣ ቁጥር በዚያች ዋሻ ውስጥ የሰው ዘር እንዳለ ታወቀ፤ የኢየሱስን ልደት ለማየት እረኞች እንደ ተመረጡ ሁሉ እኚህንም ቅዱስ ለማወቅ የቻሉት እረኞች ነበሩ፡፡ በዚህ ጊዜ በአቡነ ቡሩክ ሕይወት እጅግ የተማረኩ እረኞች በሕይወት ምሪታቸው አለቃቸው እንዲሆኑ ለመኗቸው፤ ይህን መሰል ጥያቄ ለኢየሱስም በመንጌል ውስጥ እንደቀረበለት እናነባለን፡፡ ሆኖም ግን አቡነ ቡሩክ ጥያቄውን ሳይቀበሉት ቀሩ፡፡ የኋላ ኋላ የሰዎቹን ፍላጐት እውነተኛነት ከመረመሩና ከተረዱ በኋላ ጥያቄያቸውን በመቀበል ወደ 12 የሚጠጉ ማኅበራትን አቋቋሙ፡፡

“ገዳም ቅዱስ መንፈስ ክርስቶስን በዚህ ዓለም ውስጥ የሚያስተዋውቅበት ልክ አንደ መነሻ ነጥብ የሚታይ ቅዱስ ሥፍራ ነው”

ለመነኮሳት ሕይወት ቀላል አልነበረችም፤ እንደ መሪያቸው መኖር ታላቅ መስቀል ሆኖ ፈተናቸው ከስንዴው ዛላ መካከል እንክርዳድ እንደነበረው ይሁዳ በዚያም ነበሩና አቡኑን ለመግደልና ለነርሱ የሚሆን የኑሮ ህግ ለመፍጠር በመስማማት እጅግ አደገኛ የሆነ መርዝ በወይን ቀላቅለው አቀረቡላቸው፡፡ ጌታ ኢየሱስ በወንጌል በስሜ የሚጐዳ መርዝ እንኳን ብትጠጡ አንዳች አትሆኑም እንዳለ አቡኑ በፅዋው ላይ የመስቀል ምልክት እንዳደረጉ ፅዋው ተሰባበረ፤ መርዝ የተቀላቀለውም ወይን ተደፋ፡፡ እግዚአብሔር የሆነው ነገር ስለገለጠላቸው የምንኩስና ሀሁ የቆጠሩበትን የሱብያኮን ዋሻ ጥለው ወደ “ሞንቴ ካሲኖ” ሄደው ተቀመጡ፡፡ በዚህም ለታላቁ ገዳም ምስረታ ከመጣላቸውም በላይ “ወርቃማውን ህግ” ፅፈዋል፡፡

“እግዚአብሔር በዚህ ውስጥ ለአዲስ ሕይወት መጀመር የዘር ፍሬ አኖረ እርሱም አቡነ ቡሩክ ነበሩ”

የአቡነ ቡሩክ ደንብ ለርሳቸው ገዳም መነኮሳን ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙርያ ላሉ መነኮሳን እንዲሁም መልካም ክርስቲያናዊ ሕይወት ለመኖር “ለወሰኑ” ሰዎች ጭምር የተፃፈ ነው፡፡ አቡነ ቡሩክ ብህትውናን ከውጫዊነት ይልቅ ውስጣዊነት ላይ የተመሠረተ ይሆን ዘንድ አድርገዋል፡፡ ይህ ማለት ከስጋ ይልቅ ነፃ የነፍስ ፈቃድ ላይ የሚያተኩር እንዲሆን አድርገውታል ማለት ነው፡፡ የዚህ ደንብ ተቀዳሚ ዓላማ  በቀላል የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ የጋለ የጸሎትና የሥራ ባህል በመጨመር የመነኮሳትን ልብ ማንፃት ነው፡፡ በዚህ አይነት አቡነ ቡሩክ ጥልቅ እና ጠንካራ ካቶሊካዊ መንፈስን ከመለኮታዊ ጸጋ አንፃር ተቀብለዋል፡፡ የተጐሳቆለው የጋራ የተዓዝዞ እና የራስን ዝቅ ማድረግ የሕይወት ሕግ የእያንዳንዱን መነኩሴ ዓይን የእግዚአብሔርን ብርሃን ያይ ዘንድ ለመክፍትና በዚህም ደስተኛ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡

የአቡነ ቡሩክ ደንብ የሰፈረው ሥነ-ሥርዓት ከወታደር ቤት ሥነ-ሥርዓት ይልቅ እንኳን የተለየ ሲሆን ሥነ-ሥርዓቱ በተአዝዞ በማድረግ ፍፃሜውን ወንጌልን በሙላት ይኖር ዘንድ ለወሠነው ክርስቲያናዊ ማኀበረሰብ የተዘጋጀ ነው፡፡

  • በአቡነ ቡሩክ ደንብ ላይ የተገለጸው ቤተሰባዊ ኑሮ በእርሳቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠረ ነው፤ ታዋቂው “በአንድ ቦታ ላይ የመርጋት ህግ” መነኩሴው ገዳሙ በወሠነለት ሥፍራ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ እንዲኖር ያደርገዋል፡፡ ከአበምኔቱ ፈቃድ ውጪ ማንም መነኩሴ በፈለገው ቦታ ሊኖር አይችልም፡፡ ይህም ለምንኩስና ሕይወት ዐብይ መሰረት የጣለ ነው፡፡
  • በአቡነ ቡሩክ ደንብ መሠረት ገዳም አንድ ቤተሰብ በመሆኑ አለቃው የሁሉም አባት ነው፤ ከክርስቶስ አባታዊ ሚና ቀጥሎ የገዳም አበምኔት የአባትነትን ቦታ ይዞ ይቀመጣል፤ የገዳሙ አለቃ በርግጥ ሌላኛው ክርስቶስ ነው፡፡
  • ሕጉ ሰብአዊ እውነታን የያዘ ነው፤ ለምሳሌ አበምኔቱ በመንፈሳቸው ደከም ያሉትን መነኮሳት በተለየ መልክ ይደግፋቸዋል፤ በመንፈስ ጠንካሮቹ የበላይነት ስሜት እንዳይገዛቸው ይቆጣጠራል፡፡ አበምኔቱ ተጠራጣሪ እንዳይሆን ይመክራል፤ ምክንያቱም ተጠራጣሪ ከሆነ መቼም ቢሆን ሰላማዊ አይሆንም፡፡
  • በርካታ የታሪክ ምሁራን ይህ ደንብ በመነኮሳንና በማኀበረሰቡ ኑሮ ላይ ያሳደረውን አዎንታዊ ተፅዕኖ ለአያሌ ጊዜ እያጣቀሱ ፅፈዋል፡፡ ደንቡ እጅግ በርካታ በሆኑ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡

ገዳም ራሱን ከጸጥታ ሥፍራ መነሻ ያደረገውንና በእምነት የኖረው ገዳማዊ ሕይወት ለራሱ ውበትና ፍጹም ስምረት ለተጋፈጡት ሰዎች ሁሉ እንዴት በዚህ ድንቅና ተአምራዊ ሥራ እንዳነሳሳቸው እንቆቅልሽ ነው፡፡

“ገዳም በምርጫ የተመረጡ ሰዎች መሰብሰቢያ መዕከል ሳይሆን ጌታ ተጐጅዎችን ጐንበስ ብሎ ለመርዳት በፍቅር የተከሰተበት ሥፍራ ነው”

ገዳም የተፈጠረው እራሱን በቻለ ልባዊ እውነት እንጂ በፕሮጀክት ግንዛቤ አይደለም፡፡ ይህም ተስፋ እራሱን የመሰረተው ሁሉም ነገር በእግዚአብሔር ዕቅድ መታደስና መዳን እንደሚቻል እግርጠኛነት ላይ በመመስረት ነው፡፡ ገዳማት ራሳቸውን የቻሉ ዓለማት እንጂ መጠለያ አይደሉም፡፡

“የገዳም ህልውና የክርስቲያንነት ልዩ ውበት እያሳየ እንዲሁም ለክርስቶስ በዓለም ውስጥ መገኘት ማስረጃና ምልክት በመሆን የሚቀጥል የክርስቲያንማኀበረሰብ ልብ ነው”

በእርግጥ ይህ እግዚአብሔር ወደ ዓለም ለመግባት የተጠቀመበት ዘዴ ነው፡፡ አጀማመሩም አፈር ውስጥ ያለ የዘር ፍሬን ይመስላል፤ በጣም ትንሽና ጠቃሚነቱ ከሰው ግንዛቤ ውጪ የሆነ፤ አብዛኛውን የማይታይ ትንሽ የዘር ፍሬ በዚህ መንገድ ሥልጣኑ የኛ እንዳልሆነ በግልጽ ያሳያል፡፡ እናም ከኛ ጥልቅ ዕውቀት ወይም ኃይል ሣይሆን ለዓለም ሁሉ የሚሆን መልካም ነገር ከኛ ኢምንትነትና ባዶነት ውስጥ ማፍለቅ ወይም ማውጣት የሚችለው የእርሱ ኃይል ብቻ ነው፡፡ በእኛ ፈቃደኝነት በኩል እግዚአብሔር ተዓምር ይሠራል፡፡ በዚህም መሠረት በስፋት ግልፅ በሆኑት ቀናነትና ብልህነት አማካይነት የእርሱን አዲስነት ለመገንዘብ ወይም ለመረዳት ትልቁ አዋቂነት በህይወት ውስጥ ልጅ መሆን ነው፡፡

“ፍጹም በሆነ ድህነት በቋጥኞች መካከል በሚገኘው ዋሻ ውስጥ ሁሉም ነገር መጀመሩ እንቆቅልሽ ነው ያሰኛል፡፡ እናም በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይህን ራስን ለክርስቶስ ትቶ የመኖርን ሕይወት እየፈጸመ አቡነ ቡሩክ ምናልባት ሳያውቀው አዲሱን የስልጣኔ ዘር ፍሬ ዘርቷል” ር.ሊ.ጳጳስ ቤኔዲክቶስ 16ኛ

መላው የገዳም እንቅስቃሴ ለሌሎች ሰዎች ትልቅ ሚና የልግስና አገልግሎት ይሠጣል፡፡ ፍቅር ከሆነው እግዚአብሔር ጋር “ፊት ለፊት” ባለው ግንኙነት ሁሉም መነኮሳን እግዚአብሔርን ከማገልገል ባሻገር ሕይወቱን ሙሉ ለሰዎች አገልግሎት የማዋል አስፈላጊነት እንደ የውዴታ ግዴታ አድርጐ ይቆጥረዋል፡፡ እናም የሰው ልጅ ሙሉ ስብዕናውን የሚቀበለው ከገዳሙ አባትና ከጌታ ነው፡፡

ጸሎትና ሥራ

ከእግዚአብሔር ሥራ የሚቀድም ምንም ነገር የለም ይህም ለጸሎት ነው፡፡ ምክንያቱም ክርስቶስንም ወንድሞችንም ለማፍቀር ዕውቀት የሚያስጨብጥ ዋና መሳሪያ ጸሎት ነው፡፡ ድርጊቱ ሕይወትን በመስጠት ጭምር በእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ውስጥ እንድንሳተፍ ያደርጋል፡፡ እኛም በአንድነት እንድንቀሳቀስ ከማስቻሉም በላይ ሁሉንም ነገር ከእግዚአብሔር እጆች እንድንቀበል ያስተምረናል፡፡

“የተቀደሰው የእግዚአብሔር ቤት የሚከፈትበት ሰዓት መዳረሱን የሚያሳውቀው ደወል እንደተሰማ ለመቅረት ምንም ምክንያት አይኖርምና ሁሉም ሰው የሚሠራውን ማንኛውንም ነገር በመተው በተቻለ ፍጥነት ይገስግስ”

ሥራ ማለት ለአንድ ሰው ፍላጐት የቁሳቁስ ምላሽ እንዲሰጥ የተደረገ ጥረት ብቻ ሳይሆን እንዲያውም ከሁሉም በላይ በሥራ ውስጥ ክርስቶስን መስሎ መገኘትም ነው፤ በዚህ ምክንያት ስራው ከእግዚአብሔር ጋር በሚደረገው ግንኙነት መካከል ድንገት የተከሰተ አጋጣሚ ነው፡፡ ሰውነት ሥራ ሲሠራ መንፈስም የሃሳብ መበታተን ሳያጋጥመው ለሥራው ትኩረት በመስጠት ነው፤ ሲሰራም ለምን ምክንያት እንደሚሠራ ያስባል በዚህ ልዩ ዕሳቤም በእግዚአብሔር እጆች ውስጥ ይበልጥ ትሁቶች በእርሱም መኖር በፊቱ ለማኞች እንሆናለን፡፡

“ጸሎት እና ሥራ ሁለት የተለያዩ ዕሳቤዎች አይደሉም፤ ምክንያቱም እየጸለይን እንሠራለን፤ እየሠራንም እንጸልያለንና”

በዚህ ዓይነት ሥራ እውነተኛ /ሐቀኛ/ ጸሎት ነው፡፡ እናም ሥራ ካልሆነና ሥራንም ካልገለፀ ምንም ጸሎት ህልውና አያገኝም፡፡ እኛም ልባችንን በሠፊው ከፍተን ክርስቶስን ይበልጡን እንድንረዳ ካላደረግን ሙሉ በሙሉ ንቁ የሆነ ወይም ሐቀኛና እውነተኛ ሥራ አለ ማለት ነው ሊባል አይቻልም፡፡ ሥለዚህ በርግጥ ሥራ ጸሎት ነው፡፡ ልክ እንደ ጸሎት ያህል በትክክለኛ ትርጉም የመጨረሻና ሥሜት ሰጪ የሥራ ዓይነት ነው፡፡

“ኦ! አምላክ ድርጊቶቻችንን ባርክልን በእርዳታህም አጅባቸው የእኛም ሁሉ ነገር፤ ጸሎት እና ሥራ በአንተ ተጀምረው ባንተ ሞገስነት ይሞላ ዘንድ አሜን፡፡”

እናም ለክርስቶስ “ሳይሠራ” ከተተወው ከዚህ የመስዋዕትነት ሥራ እንቆቅልሽ ነው ባሰኘ መልኩ ለዘመናት የአውሮፖን ኢኮኖሚ ያዳበሩት የሥራዎች አስደሳችነትና ፍሬያማነት በገዳማዊ ሕይወት ውስጥ በድንገት ፈለቁ ወይም መነጩ፡፡ የሁሉም ሰው ተግባር እምነታዊ ሥራውን ማሳየት አለበትእናም በልዩ ሁኔታ ለእግዚአብሔር ክብርና ሞገስ ከተሠራ ማንኛውም ሥራ ክቡር ነው፡፡

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።