መግነጢሳዊው ቅዱስ (ቅ. በርናርዶስ)

ቅዱስ በርናርዶስወጣት በርናርዶስ ተሸሊን በ22 ዓመት ዕድሜው ማለት በ1112 ዓ.ም. ወደ ገዳመ ሲቶ ገባ፣ ከሦስት ዓመት በኋላም አበምኔት ተሾሞ አዲስ ገዳም እንዲመሠርት ወደ ክለርቮ ተላከ፡ ወጣቱ በርናርዶስ የንግግር፣ የስብከት እንዲሁም የመምራት የተለየ ስጦታና ችሎታ የነበረው ብዙዎችን ይማርክና ይስብ የነበር መግነጢሳዊ ስብእናን የተላበሰ ነበር፡፡ ከመንፈሳዊ ሕይወት ምስክርነቱ የተነሣም ብዙዎች እሱን መከተል ጀመሩ፡፡ በነበረው የተለየ ስጦታና ችሎታ፣ እንዲሁም በንግግሩ ጣፋጭነት ‹‹ከአፉ የማር ወለላ የሚያፈስ፣ የሚያወጣ ሊቅ ወይም ዶክተር›› ተባለ፡፡ በዚህ ላይም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘማሪ ፈረሰኛ ተብሎ ይጠራል፡፡ ምክንያቱም በጣም ከፍ ያለ የእመቤታችን ፍቅርና ክብር ስለነበረው ነው፡፡

አበምኔት በርናርዶስ "የ12ኛው ክፍለ ዘመን ሰው" ተብሎም ይጠራል፣ ይህ የተባለበትም ምክንያት በዚያን ጊዜ ሁሉም የሰው ልጆች፣ ከጳጳሳት እስከ ተራ ምእመን፣ ከነገሥታት እስከ ተራ ገበሬ ሁሉም ለምክር፣ ምሪትና መፍትሔ ለማገኘት ወደ እርሱ ይሮጡ፣ ይጠሩትም ነበር፡፡

የክለርቮው አበምኔት በርናርዶስ የአርእስተ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሊቃነ ጳጳሳት፣ የጳጳሳት፣ የአበምኔቶች፣ የካህናት፣ የመነኩሴዎች የደናግሎች፣ የነገሥታት፣ የመሳፍንት፣ የባለስልጣኖች እና የተራ ሕዝብ መካሪ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያትም ዕርቅንና ሰላምን ለማስፈነው መላ ኤውሮጳን ዞሮአል፡፡ በመንበረ ሮሜ ተነሥቶ የነበረው በጣም ከባድ ችግር ማለትም የመንበር ድርርቦሽ እንዲወገድ አድርጓል፡፡ በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ኤውጀንዩስ 3ኛ (መጀመሪያው ሲታዊ ር.ሊ.ጳጳሳት) ትእዛዝም ቅድስት ሃገርን ነጻ የሚያወጡ ሁለተኛ የመስቀላውያን ወታደሮች ቡድን አዘጋጅቶ ልኳል፡፡ መናፍቃንን ተቃውሞአል፣ ብዙ ተአምራትም አድርጓል፡፡


የአበው ምሥክርነት

(ቅ. ሮበርቶስ በላርሜን1542-1621) የተባለ ኢየሱሳዊ ሊቅ ስለ ቅ. በርናርዶስ ሲጽፍ ‹‹በርናርዶስ እውነተኛ ሐዋርያ ነበር፤ ብዙ ተአምራቶችንም ፈጽሞአል፣ ከምናውቃቸውና ታሪካቸው ከተጻፈላቸው ቅዱሳን የተአምራቶች ብዛት በተመለከተ ከሱ የሚወዳደርና ከሱ የሚበልጥ ማንም የለም›› ይላል

(ቅ. ቶማስ ዘአኩኖ 1225-1274) የተባለ የታወቀ ሊቅም ስለ ቅ. በርናርዶስ ሲናገር ‹‹እግዚአብሔር የመረጠው የሃይማኖት መስተዋትና አብነት፣ የቤ/ክ ምሰሶ፣ የተመረጠ የአምላክ ሠራተኛ፣ እንደ ጣፋጭ ወይን ጠጅ ማር በሚያፈሰው አፉ ዓለምን አጥግቦአል፣ ዓለምን አስክሮአል›› ይላል፡፡

(ማርቲን ሉተርም) ስለ ቅ. በርናርዶስ ሲናገር ‹‹ሁሉንም የቤ/ክ ሊቃውንት ይበልጣቸዋል፣ ከሁሉም መነኩሴዎች በላይ አድርጌ አየዋለሁኝ፣ አባት ተብሎ መጠራት የሚገባውና ሥራውም በጥንቃቄ መጠናት ያለበት እሱ ብቻ ነው›› እስከ ማለት ደርሷል፡፡ ስለ ቅዱስ በርናርዶስ የጻፉና የተናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሦስት ሰዎቨዋ ለማስረጃ ያህል የተጠቀሱ ናቸው፡፡


የሲታዊ ሕይወት

የሲታዊ ሕይወት ዓይነተኛ መንፈሳዊነት በነፃነትና በመንፈስ ቅዱስ ደስታ የሚቀበሉት ተጋድሎ በማድረግ ቀላልና ተራ የሆነ አኗኗር በመከተል፣ በክርስቶስ ትስብእት የተገለጠውን መለኮታዊ ፍቅር በማስተንተን ነው፡፡ በሲታዊ መንፈሳዊነት በጣም ጎልቶ የሚታየው ወይም ጎልቶ መታየት የሚገባው የቅዱስ ቁርባንና የቅዱስ ልብ ኢየሱስ መንፈሳዊነት ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ ለክርስቲያናዊ ፍጽምና መሠረታዊ ነገር ፍቅር ነው፡፡ ይኸውም አባቱንና የዳም ልጆችን እስከ መጨረሻ የወደደውን የክርስቶስን አርአያ በመከተል ተግባራዊ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህንን መለኮታዊ ፍቅር የሚመግብና ሕይወት የሚሰጥ ደግሞ ምልእተ ጸጋ የሆነችው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልዩ ፍቅርና መንፈሳዊነት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም የቤተክርስቲያን እናት ከመሆንዋም በላይ የማኅበራችን ባልደረባና ጠባቂ ሆና ትከበራለች፡፡ የዚህ ከፍተኛ የማርያም አክብሮትና ፍቅር ሕያው ምስክር የሆነ፣ ከዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ መንፈሳዊ ተግባር አለ፡፡ ይኸውም በሁሉም የሲታውያን ገዳማት የቀኑ ሙሉ የጸሎትና ሥራ ተግባር ፍጻሜ ማለትም በጸሎት ዘንዋም መጨረሻ ላይ ‹‹ሰላም ለኪ ኦንግስት›› የሚለው ወደ እመቤታችን በዜማ የሚደረግ ጸሎት ነው፡፡ ስለእመቤታችን ብዙ የጻፈና የሰበከው የማርያም መዘምር ተብሎ የሚጠራው ቅ. በርናርዶስ አባታችን የሲታዊ ሕይወትን መልክ እንዲህ በማለት ያብራራዋል፡-

‹‹ሕይወታችን የፍጹም ትሕትና፣ የነጻ ድሃነት፣ የተአዝዞና በመንፈስ ቅዱስ የሰላም ሕይወት ነው፡፡ ሕይወታችን ለአለቃ፣ ለአበምኔት፣ ለሕግና ለሥርዐት የመታዘዝ (ራስን ዝቅ የማድረግ) ሕይወት ነው፡፡ ሕይወታችን የጽሞና (የዝምታ)፣ የጾም፣ የንቃት፣ የጸሎት፣ የእጅ ስራ ከሁለም በላይ ግን የበለጠችውን የፍቅር ጎዳና የመከተል፣ ከቀን ወደ ቀን በፍቅር የመበልጸግና እስከ መጨረሻ በርሷ ጸንቶ የመኖር ሕይወት ነው›› (ከቅ.በርናርዶስ መልእክቶች ቁ.142)፡፡

ቅ.በርናርዶስ ከተናገራቸው ውስጥ

የቅዱስ በርናርዶስ ጥንካሬ ከትህትናው የመጣ ነው፤ በዚህም በራሱ ደካማነት ከመመካት ይልቅ ትምክህቱን ሁሉ በመለኮታዊው አዳኝ እና በቅድሰት እናቱ ላይ አደገ፡፡ (ቶማስ ሜርተን)

‹‹ቅዱስ በርናርዶስ ስለ እመቤታችን የፃፈውን ነገር ከማጥናታችን በፊት ስለ እርሷ በአጥጋቢ ሁኔታ መናገርም ሆነ መጻፍ አይቻልም›› (ቶማስ ሜርተን)


የክርስቶስ ፍቅር የግዴታ ወደ እናቱ ፍቅር ይጠቁመናል፡፡ እርሱን ስናከብር እርሷንም እንዲሁ እናከብራታለን፡፡ ስለዚህ የኢየሱስ እና የማርያም ፍቅር ሊነጣጠሉ አይችሉም ሁለቱም አንድ ናቸው፡፡ እርሷን ሳናፈቅር እርሱን ማፍቀር አንችልም፤ እርሷን የምናፈቅርበት ብቸኛው ምክኒያት የበለጠ እርሱን ለማፍቀር ነው፡፡


ጸሎት ወደ ቅዱስ በርናርዶስ

ቅዱስ አባት ሆይ!

መላ ልጆችህን ወደ ፍጹም ፍቅር የምትጠራና

የተወሰኑትን ደግሞ በቅርብ የልጅህን ፈለግ

ይከተሉ ዘንድ የምትጋብዝ፤

በቅዱስ በርናርዶስ አማላጅነት በሙላት

ያንተ እንዲሆኑ የመረጥካቸውን ለዓለምና ለቤተ ክርስቲያን

ያንተን መንግሥት ይገልፁ ዘንድ ኃይልን ስጣቸው፡፡ አሜን፡፡


ብርሃነ ሲቶ - ግጥም

ቤቱ ደካክሟል ሰው የለበትም

በር የሚያንኳኳ እንግዳ አልመጣም

በውስጥ የቀረው ተስፋ አይሰጥም

ለስንት ዘመን ለዓለም ያበራ

‹‹ሰው›› በጠፋበት በወና ሥፍራ

ሊለይ ደርሷል ጸሎት ከሥራ፡፡

የምታፅናናን አንዲት ቃል ጠፍታ

ከኛ ርቃ የተስፋ ጠብታ

የሲቶ ብርሃን ወጣ ወደ ማታ፡፡

የደብሩ ደውል እንዲህ ይጮሃል

የበርናርዶስ እጅ በሩን ይመታል

ይከፈትለት ያድሰን ገብቶ

ቅዱስ በርናርዶስ ብርሃነ ሲቶ፡፡