እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የአሲዚው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ መዝሙረ ፍጥረታት

የአሲዚው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ መዝሙረ ፍጥረታት - ከሣህለ ሚካኤል

st francis birdsቀጥሎ የቀረበላችሁን መዝሙር የደረሰው አባት ለፍጥረታት በነበረው ልዩ ፍቅር የሚታወቀው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ይባላል፡፡ የተወለደው በአሥራ ሁለተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ሲሆን በአሥራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን በነበረው የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ ታላቅ ሚናን ከተጫወቱ ሰዎች አንዱ ነው፡፡

የዚህ የፍራንቸስኮስ ብሔረ ሙላዱ ጥንተ ነገዱ እንደምን ነው? ቢሉ እነሆ እጅግ በጣም በአጭሩ ይህን ይመስላል፡-

በ1182 ዓ.ም. (G.C.) (አንዳንዶች 1183ም ይላሉ) አሲዚ በምትባለው ዛሬ ጣልያን ውስጥ በምትገኘው ቦታ አንድ ፒየትሮ በርናርዶን የሚባል ሀብታም የጨርቅ ነጋዴ ወንድ ልጅ ተወለደለት፡፡ ይህ ልጅም ክርስትና ሲነሣ ጆቫኒ (ዮሐንስ) የሚል ስም ተሰጠው፡፡ አባቱ ግን ፍራንቸስኮስ ብሎ ሰየመው፤ የዚህም ምክንያቱ አባትየው ፈረንሳይን እጅግ አጥብቆ የመውደዱ ነገር እንደነበር ይነገራል፡፡

ቅዱስ ፍራንቸስኮስ የባዕለ ጸጋ ልጅ ሊያገኘው የሚችለው እንክብካቤና ምቾት ሁሉ ሳይጎድልበት ስላደገ ገንዘብ እንደውኃ መርጨት፣ መዝናናትንና መሽቀርቀርን ማዘውተር ተለይቶ የሚታወቅባቸው የወጣትነት ጠባዮቹ ነበሩ፡፡ ታሪኩን የጻፉልን አበው እንደሚናገሩት የወጣትነት ዘመኑን የመጀመሪያ ዓመታት ያየ ማንም ሰው "ፍራንቸስኮስ ቅዱስ ይሆናል፡፡" ብሎ አይጠብቅም፡፡ ይሁን እንጂ ያኔም ቢሆን ለድኾች እጅግ የምታዝን ርኅርኅት ልብ ባለቤት እንደነበረው ሳይጠቅሱ አያልፉም፡፡

እድሜው ለዐቅመ አዳም ከደረሰ በኋላ የፍራንቸስኮስ ልቡ ከአባቱ ሥራ ከንግድ ይልቅ በዚያ ዘመን "Knights" ተብለው ይጠሩ የነበሩት ዓይነት ወታደሮች (በእኛ ሀገር በዘመነ መሳፍንት የነበሩት ጦረኛ መሳፍንት ዓይነት) መሆንን ይመኝ ጀመር፡፡ ሆኖም "መንክር እግዚአብሔር በላዕለ ቅዱሳኒሁ" (እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው፡፡) እንዳለ መዝሙረ ዳዊት ይህንን ሕልሙን ለማሳካት ጓዙን አሰናድቶ፣ ዝግጅቱን አጠናቅቆ በጨረሰባት ሌሊት በሕልሙ አንድ አዳራሽ ታየው፡፡ በአዳራሹ ውስጥ የመስቀል ምልክት የተደረገባቸው በርካታ የጦር ዕቃዎች ተሰቅለዋል፡፡ አንድ ድምጽም "እነዚህ ለአንተና ለወታደሮችህ ናቸው፡፡" ሲለው ሰማ፡፡ እርሱም "አዎን! ታላቅ ልዑል እንደምሆን ዐውቃለሁ፡፡" አለ፡፡ ነገር ግን የሕልሙ ምሥጢር አልገባውም ነበርና ጉዞውን ጀመረ፡፡ ነገር ግን ያ ፈርጣማ ወጣት ስፖሌቶ የምትባል ቦታ ላይ ሲደርስ ታመመና ጉዞው ተገታ፡፡ በሕመም ላይ እያለም የውትድርና ጉዞውን ትቶ ወደ አሲሲ እንዲመለስ በሕልም ተነገረው፡፡ እርሱም "አሜን" ብሎ ወደ አሲሲ ተመለሰ፡፡ ይህ የሆነው በ1205 ዓ.ም. (G.C.) ነበረ፡፡

ከሕልሞቹ በኋላ ሐሳቡ ከሐሳባቸው አልከተል እያለ፣ ከመካከላቸው ተቀምጦ ልቡ ርቋቸው ሲመለከቱ የነበሩት የቀድሞ ጓደኞቹ የትዳር ሐሳብ የያዘው፣ የሥጋ ፍቅር ያናወዘው መስሏቸው ይቀልዱበት፣ ይቀጣጠቡበት ጀመር፡፡ እርሱ ግን በቅጥጥባቸው ከመበሳጨት ወይም ከማዘን ይልቅ "አዎን! አንዲት እጅግ ውብ የሆነች እመቤት ላገባ ነው፡፡" ሲል መለሰላቸው፡፡ እነርሱም "ግምታችን ትክክል ሆነ፤ ጥርጣሬያችን ያዘልን፡፡" ብለው ልባቸው አረፈላቸው- ቅኔው አልገባቸውም ነበረና፡፡ እርሱ ግን በልቡ ሊያገባት ያጫትን ያውቅ ነበር እርሷም በንጽሕና ኑሮው ላይ የትዳር አጋሩ ያደረጋት እመቤት ድኽነት ነበረች፡፡ የሀብታም ልጅ ድኻ ሲያገባ ጉድ! ጉድ! አጀብ! አጀብ! የሚለውን ዓለም ጭራሽ ዕፁብ! ዕፁብ! ሊያሰኘው የባዕለ ጸጋው የፒየትሮ በርናርዶ ልጅ ፍራንቸስኮስ ራሷን ድኽነትን አግብቷት አረፈው፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው የነበረውን ሀብት ሁሉ የመመጽወቱን ነገር፣ ስቁል ኢየሱስን የማፍቀሩን መጠን፣ ሕሙማንን የመንከባከቡን ተጋድሎ፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ፍቅር ሲል "እብድ" የመባሉንና በድንጋይ የመመታቱን ነገር፣ በገዛ አባቱ በጨለማ ቤት የመታሠሩን ስቃይ፣ ቤተ ክርስቲያንን ለማደስ ከሀብታም አባቱ ተወልዶ ሀብት እየረጨ በኖረባት ከተማ በለማኝነት መንከራተቱን፣ እንዳልዘረዝር ጊዜ ያጥርብኛል፡፡ በዝርዝር ማወቅ ማጥናት የሚፈልግ ካለ ተከታዮቹን ፍራንሲስካውያን አበውን ወይም ካፑቺናውያኑን ታናናሾቹን ወንድሞች ጠጋ ብሎ ይጠይቅ፡፡ ከፈቀደም ስለዚህ ቅዱስ የተጻፉትን መጻሕፍት ይመለካከት፡፡

ለዛሬ ይህ ቅዱስ አባት ለቤተ ክርስቲያን ካበረከታቸው ውብ ነገሮች አንዱ የሆነውን ይህን መዝሙር አብራችሁት እንድትዘምሩት ጋብዤያችኋለሁ፡፡

በነገራችን ላይ፣ በዚህ ሣምንት ብዙዎቻችንን በመጻሕፍታቸው ያስተማሩንን፣ የግብጽን ቤተክርስቲያን ለ40+ ዓመታት ያስተዳደሩትን፣ በኑሯቸው ፍቅርን በማስቀደም ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ እንዲሁም ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጋር ለቤተክርስቲያን አንድነት የደከሙትን፣ ጸሐፊው ዳንኤል ክብረት

"አራት ሰው ሞተ ደረሰና ጥሪ፤

ደራሲ፣ ሰባኪ፣ ጳጳስና መሪ፡፡"

በማለት ሙሾ ያሟሸላቸውን፣ በዚህ በሰሙነ ደብረ ዘይት ወደ አምላካቸው የሔዱትን፣ አባታችን ሺኖዳ ሣልሣይን ወደ አባታችንና ወደ አባታቸው፣ ወደ አምላካችንና ወደ አምላካቸው ሸኝተናል፡፡ በእውነት ታላቅ አባት አጥተናል፡፡ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ ጥልቅ ሐዘናቸውን እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፡-

የሁላችን አባት፣ በወንጌላዊው ማርቆስ መንበር የእስክንድርያ ፓትርያርክ የሆኑት ቅዱስነታቸው አቡነ ሺኖዳ ከእኛ ወደ እግዚአብሔር የመለየታቸውን ነገር ስሰማ እጅግ ጥልቅ ወንድማዊ ሐዘን እንደተሰማኝ ለግብጽ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ፣ ለካህናትና ለመላው ምእመናን ልገልጥ እወድዳለሁ፡፡...

ለክርስቲያን አንድነት የነበራቸው ትጋት፣ በተለይም ደግሞ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛን መጎብኘታቸውንና ግንቦት 2 ቀን 1965 ዓ.ም. በሮም ስለ ነገረ ሥጋዌ የጋራ የእምነት መግለጫ ማውጣታቸውን፣ እንዲሁም የካቲት 16 ቀን 1992 ዓ.ም. ከዳግማዊ ዮሐንስ ጳውሎስ ጋር አምላክ ሰው የሆነበትን ታላቁን ኢዩቤልዩ (The Great Jubilee of Incarnation) ለማክበር በካይሮ መገናኘታቸውን በታላቅ አክብሮት አስታውሳለሁ፡፡

የእኔ ልብ ሙሾ ማሟሸት ስላልቻለ በዚህ በቅዱስ ፍራንቸስኮስ መዝሙር ልሰናበታቸው ወደድሁ፡፡ አብራችሁኝ ተሰናበቷቸው፡፡

መዝሙረ ፍጥረታት

ልዑል፤ ኃያል፤ እጅግም መልካም የሆንህ ጌታ ሆይ!

ምሥጋና፣ ክብር፣ ልዕልናና ባርኮት ሁሉ ያንተ ነው፡፡

እነርሱም ልዑል የሆንህ ያንተ ብቻ ናቸው፡፡

ሞት ከሚረታቸው ከናፍር መካከል ስምህን ለመጥራት የሚበቃ አንድም የለም፡፡

ጌታ ሆይ! ስለ ፍጥረታትህ ሁሉ እመሠግንሃለን!

በተለይም ደግሞ በእርሱ ብርሃንን ሰጥተኸን ቀን እንዲሆነን ስላደረግህልን ወንድማችን ፀሐይ፤

እርሱም ውብ፣ በታላቅም ክብር አንጸባራቂ ነው፤

ልዑል የሆንህ አንተንም ይመስላል፡፡

በሰማያት ብሩኃን፣ ድንቅና መልካም ስላደረግሃቸው

ስለ እኅታችን ጨረቃና ስለከዋክብትም

እናመሰግንሃለን፡፡

ለስላሳም ሞገደኛም ስለሚሆኑት ስለወንድሞቻችን ነፋስና አየር

እንዲሁም ፍጥረትህን ስለምታስደስትባቸው ልዩ ልዩ የአየር ጠባያት ሁሉ

እናመሠግንሃለን፡፡

ንጹሕ፣ እጅግ ጠቃሚ፣ ትሑትና፣ እጅግ ብርቅ ስለ ሆነችው

ስለ እኅታችን ውኃም እናመሠግንሃለን፡፡

ጌታ ሆይ!

በእርሱ ሌሊቱን ስላበራህበት ስለ ቆንጆው፣ ተጫዋቹ፣ ቆራጡና ጠንካራው ወንድማችን ስለእሳትም

እናመሠግንሃለን፡፡

ጌታ ሆይ!

በፍሬዎቿ፣ በደማቅ አበቦቿ እና በቅጠሎቿ ስለምትመግበን እኅታችን

ስለ ምድርም እናመሠግንሃለን!

ጌታ ሆይ!

ይቅርታን ስለሚያደርጉ

እንዲሁም ስለፍቅርህ ሲሉ ሕመምንና ፈተናን ሁሉ ስለሚታገሱ ሰዎችም

እናመሠግንሃለን፡፡

ልዑል ከሆንህ ካንተ አክሊልን ይቀበላሉና በሰላም የሚጸኑ እነርሱ ብፁዓን ናቸው፡፡

ጌታ ሆይ!

ሕያው የሆነ ሁሉ ከእርሷ ሊያመልጥ ስለማይቻለው

ስለ እኅታችን ሞትም

እናመሠግንሃለን፡፡

በኃጢኣታቸው እያሉ ለሚሞቱ ወዮላቸው!

ፈቃድህን እየፈጸሙ እርሷ የምታገኛቸው እነዚያ ደግሞ ብፁዓን ናቸው፤

ሁለተኛው ሞት ሊጎዳቸው አይቻለውምና፡፡

ጌታ ሆይ!

እናወድስሃለን! እናመሠግንሃለን! እንባርክህማለን!

በትሕትናም እናገለግልሃለን፡፡

በአሐዱ ወልድከ እግዚእነ ኢየሱስ፡፡

አሜን፡፡

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት