እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ፍጹም ኃያልና ፍጹም ውብ፣ ደጋፊ የማይሻ ጽኑዕ

"ከቅዱስ አውጉስጢኖስ ኑዛዜዎች"

ምዕራፍ አንድ

Agustine confessions"ጌታ ሆይ! አንተ ታላቅ ነህ፡፡ ከፍ ከፍም በል፡፡ ኃይልህ ታላቅ ነው፡፡ ጥበብህም አይሰፈርም፡፡" ሰውም አንተን ማመስገንን ይሻል- ከፍጥረትህ አንዱ ነውና ፡፡ አንተ ትዕቢትንና መታጀርን እንደምትጠላ ምስክር ይሆን ዘንድ የኃጢአተኝነቱን ምልከት የሆነውን ሟችነቱን ተሸክሞ ይዞራል፡፡ ግና አሁንም ይህ የፍጥረትህ አንዲት ቅንጣት የሆነው ሰው ሊያመሰግንህ ይወድዳል፡፡ አንተን አመስግኖ ይደሰት ዘንድ አንተ ራስህ ቀስቅሰኸዋልና፡፡ አንተ ለአንተነትህ ፈጥረኸናልና ልባችን በአንተ እስኪያርፍ ድረስ ዕረፍት አልባ ሆኖ ይኖራል፡፡

ጌታ ሆይ! አንተን ከመለመንና አንተን ከማመሥገን የትኛውን ማስቀደም እንዳለብኝ ማወቅና መረዳቱን ስጠኝ፡፡ አንተን ከማወቅና አንተን ከመጥራት የትኛውን እንደማስቀድምም እንዳውቅ አድርገኝ፡፡ ነገር ግን አንተን ሳያውቅ ማን ሊለምንህ ይችላል? አንተን የሚያውቅ አንተን ከአንተነትህ ውጪ መለመን ይቻለዋልን? ምናልባትም መለመን ያለብን አንተን እንድናውቅህ እንድታደርገን ነው፡፡ ነገር ግን የማያምኑበትን እንዴት ሊጠሩት ይቻላቸዋል ያለሰባኪስ እንዴት ያምናሉ? እርሱን የሚፈልጉት ያከብሩታል፡፡ "የሚፈልጉት ያገኙታልና፡፡" አግኝተውም ያመሰግኑታል፡፡ ጌታ ሆይ! እፈልግሃለሁ፤ እጠራህማለሁ፡፡ በሰባኪህ አገልግሎትና በልጅህ ሰው መሆን በሰጠኸኝ እምነት እጠራሃለሁ፡፡

ምዕራፍ ሁለት

አምላኬና ጌታዬ የሆነውን አምላኬን እንዴት ልጥራው? ስጠራው ወደውስጤ እንዲመጣ እጠራዋለሁ፡፡ ግን አምላኬ ሊገባበት የሚችል ቦታ በእኔነቴ ውስጥ አለን? ሰማይንና ምድርን የሠራ አምላክ እንዴት ወደእኔነቴ ውስጥ ሊመጣ ይቻላል፡፡ ጌታሆይ! አንተን ሊይዝ የሚችል ነገር በእኔ ዘንድ አለን? አንተ ያበጃጀሃቸው ና እኔንም በእነርሱ ውስጥ የሠራኸኝ ሰማይናምድርስ ቢሆኑ አንተን መያዝ ይቻላቸዋልን? እርግጥ ነው ህልው የሆነው ነገር ሁሉ ህልውናውን ያገኘው ባንተ ነውና ህልው የሆነው ሁሉ አንተን የሚቀበልበት ጥቂት ዐቅም አያጣም፡፡ ታዲያ ህልውናዬ በእኔ በምትኖር በአንተ ከሆነና ያለአንተ ህልው መሆን ካልቻልሁ እንዴት ወደ እኔ እንድትመጣ መጠየቅ እችላለሁ? ምክንያቱም ያለሁት በሲዖል አይደለም፤ እርግጥ ነው "ወደ ጥልቁም ብወርድ አንተ በዚያ አለህ" ተብሎ እንደተጻፈ አንተ በዚያም አለህ፡፡ ስለዚህም ሁሉ ካንተ በሆነ፣ ሁሉ ባንተ በሆነና ሁሉን በምትይዝ በአንተ ውስጥ ባልሆን ኖሮ ምንም ዓይነት ህልውና አይኖረኝም ነበር፡፡ በቃ አልኖርም ነበር፡፡ አዎን ጌታ ሆይ! አዎን! በአንተ ውስጥ እየኖርሁ አንተን ወዴት እጠራሃለሁ? ከወዴትስ ወደእኔ ትመጣለህ? "በሰማይና በምድር የመላሁ ነኝ፡፡" ያለው አምላኬ ወደእኔ ይመጣ ዘንድ ከሰማይና ከምድር ውጪ ወዴት መሄድ ይቻለኛል?

ምዕራፍ ሦስት

ሰማይና ምድርን ትመላለህና እነርሱ ሊይዙህ ይችሉ ይሆን? ወይስ ሊይዙህ ስለማይቻላቸው ሞልተህ ትፈስ ይሆን? ሰማይና ምድርን መልተህ ተትረፍርፈህ ስትፈስስ ወዴት ትፈስ ይሆን? ወይስ ሁሉን የምትይዝ አንተ በርግጥ በምልዐትህ ሁሉን ትይዛለህና በምንም ልትያዝ አትችልም? በምልዐትህ የምትገኝባቸው ሸክላዎች አንተን አይዙህም- ቢሰበሩም እንኳ አንተ አትፈስምና፡፡ በእኛ ላይ ስትፈስም አንተ የምትወርድ አይደለህም- እኛ ወደላይ ከፍከፍ እንላለን እንጂ፡፡ አንተ የምትበተን አይደለህም- እኛን ትሰበስበናለህ እንጂ፡፡

ግን ነገሮችን ስትመላ በአንተነትህ ሙሉ ትመላቸዋለህን? ወይስ ሁሉም ነገሮች ተሰብስበው ሊይዙህ አይችሉምና አንዱ ነገር አንዱን የአንተነትህን ክፍል ይይዝ ይሆን? ሌሎቹስ ነገሮች ያንኑ ክፍል በዚያው ሰዐት ይይዙ ይሆን? ነጠላ ነገሮች በነጠላነታቸው አንድነትህን ይይዛሉን? ታላላቅ ነገሮች የበለጠ አንተነትህን ታናናሽ ነገሮች ደግሞ በአነስተኛ መልኩ አንተነትህን ይይዙ ይሆን? ወይስ አንተ በሁሉ ምሉዕ የሆንህና ነገር ግን ምንም በምልዐት ሊይዝህ የሚችል የሌለ ነህ?

ምዕራፍ አራት

እንግዲህ አምላኬ ምንድነው? "ከአምላካችን በቀር አምላክ ማነው? ከጌታችን በቀርስ ጌታ ማነው?" ተብሎ የተነገረለት ጌታዬ ምንድነው?

የሚተካከለው የሌለ ልዑል፣ የሚመስለው የሌለ ሥሉጥ፣ ሁሉን ማድረግ የሚችል፣ ምሕረቱ ተነግሮ የማያልቅ መሐሪ፣ በፍርዱም እንከን የሌለበት ጻድቅ፣ ኅሊና የማይደርስበት ረቂቅ፣ በሁሉ የሚገኝ፣ ፍጹም ኃያልና ፍጹም ውብ፣ ደጋፊ የማይሻ ጽኑዕ፣ ሁሉን የሚለውጥ እርሱ ግን ፈጽሞ የማይለወጥ፣ የማይታደስ፣ የማያረጅ ነገር ግን ሁሉን የሚያድስ ትዕቢተኞችን ሳያውቁት የሚያስረጃቸው፣ ሁሌም የሚሠራ፣ ሁልጊዜም በዕረፍቱ ፍጹም፣ ሁሉን የሚሰበስብ ግን አንዳችም የማያስፈልገው፤ ሁሉን የሚመግብ፣ ሁሉን የሚይዝና ሁሉን የሚጠብቅ፤ ፈጣሪ፣ መጋቢ፣ ተንከባካቢ፡፡ ሁሉ ገንዘቡ የሆነ ፈላጊ፡፡

ሣህለ ሚካኤል

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት