እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ጾም እንዴት ናት?

ጾም እንዴት ናት?

ከሣህለ ሚካኤል

ዛሬ የማካፍላችሁን ትምህርት ያገኘሁት "ማር ይስሐቅ" ከተሰኘው ባለፈው ጊዜ ስለ ንስሐ፣ ፍቅርና ፈሪሃ እግዚአብሔር ከተማርንበት መጽሐፍ ነው፡፡ ጊዜው የጾም ወቅት ስለሆነ በእኛ በምሥራቃውያን ክርስቲያኖች ዘንድ ደግሞ የጾም ትውፊት እጅግ ይከበራል፡፡ ይህም ጥሩ ልምምድ ነው፡፡ ነገር ግን ጾምን የምንጾመው አባቶቻችን ሥርዓቱን ስለሠሩት ብቻ የምንፈጽመው ግዴታ አድርገን መሆን የለበትም፡፡ አንዳንዶቻችን "ጾም ሳይገባ እንብላ! እንጠጣ!" ብለን የምናካሒደው የቀበላ ሰሞን የግጦሽ ዘመቻ፣ አንዳንዶቻችን ደግሞ ጾም ላለመጾም የምናካሒደው የምክንያት ድርደራና የቅድስተ ቤተክርስቲያንን ትእዛዝ ያለመፈጸም ሽሽት ጾምን ጥቅሟን እንደማናውቅ ይመሰክርብናል፡፡ አንዳንዶቻችን ደግሞ አንደበቶቻችንን ለመቆጣጠር አንዳችም ጥረት ሳናደርግ፣ በምላሳችን የሰዎች ቁስል ላይ ጥዝጣዜን እየጨመርን፣ ፍርድ እያጓደልን፣ ሠራተኞቻችንን እየበደልን፣ ጉቦ እየበላን፣ ሚዛን እያጭበረበርን፣ "በርበሬ ነው፡፡" ብለን ሸክላ እያቀረብን፣ "ቅቤ ነው፡፡" ብለን ሙዝ እየሸጥን፣ በንግድ ስም በአልጠግብ ባይነት ከሚገባን በላይ ትርፍን በመፈለግ ድኃውን እየመዘበርንና እያስጨነቅን ለተወሰኑ ሰዐታት ከምግብ በመከልከላችን ብቻ ጾምን በጥሩ ሁኔታ እየጾምን እንደሆነ እናስባለን፡፡ ባጠቃላይ ስናየው ይህ ሁሉ የሚያመለክተው ወደ አንድ አቅጣጫ ነው- የጾምን ምንነትና ጥቅም አለማወቃችንን፡፡

ስለሆነም ጥቅሙን ዐውቀን ስለምን እንደሆነ እንድንረዳ ስለጾም ምንነት ከአበው ትምህርቶች ጥቂት ፍርፋሪ ብንቀማምስ ለነፍሳችን ጥሩ ስንቅ ይሆነናል፡፡ እርግጥ ነው "ማር ይስሐቅ" የተጻፈው በዐቢይነት የመነኮሳትን ሕይወት ለመምራትና ለማረቅ ነው፤ ይህ በራሱ ግን ያልመነኮሱና የማይመነኩሱ ሰዎች ሊያገኙበት የሚችሉትና ሊያገኙትም የሚገባቸው ትምህርት የለም አያሰኝም፡፡ በተለይም ደግሞ ክርስትና ራስን የመግዛት ሕይወት ስለሆነ ከመነኮሳት ኑሮ በርግጥ ብዙ የምንማረው ይኖረናል፡፡ ልንማርም ይገባናል፡፡ መጽሐፍ "ተሰአሎ ለአቡከ፤ ወይነግረከ፡፡" (ዘዳግ. 32፣7) (አባትህን ጠይቅ ይነግርህማል፡፡) ይል የለምን?

እነሆ! የአንድ ሺህ ስድስት መቶ ዓመቱ አረጋዊ መጽሐፍ ማር ይስሐቅ አንቀጽ 4 ምዕራፍ 6 ላይ እንዲህ ይላል ፡-

ጥያቄ፡- በክርስትና ሕይወት ተጋድሎ ለመጀመር የሚፈልግ ሰው ሥራውን በምን ይጀምራል?

መልስ፡- ይህማ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ ሰው በሥጋው በኩል የምትዋጋውን የኃጢኣትን ጦር ድል ለመንሣት፣ ፍትወትንም ከእርሱ ለማራቅ በሚያደርገው ተጋድሎ በቅድሚያ የምትመጣው የመታገያ መንገድ በጾም ሥጋን ማድከም ናት፡፡ ዕንቅልፍን ቀንሶ በሌሊት ለጸሎት መትጋትም እንዲሁ ጾምን የምታግዝ መሣሪያ ናት፡፡ በዘመኑ ሁሉ እነዚህን የሚጠብቅ ሰው ንጽሕናን ገንዘቡ ማድረጉ አይቀርም፡፡ ጥጋብ የክፉ ሥራ መጀመሪያ እንደሆነች ሁሉ የዕንቅልፍ ብዛትም ሥጋዊ ፍላጎትን ያበረታዋል፡፡ ስለዚህም ከዕንቅልፍ ቀንሶ ጸሎት ማድረግና ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ደግሞ በምግባር በትሩፋት ለማደግ ጥሩ መሠረት ይሆናሉ፡፡

ጾም የምግባር የትሩፋትን ሥራ ሁሉ ለመሥራት ታነቃቃለች፡፡ እርሷ እንደ ትጉኅ ገበሬ ራሳቸውን ለክርስቶስ ጠምደው ለሚኖሩ አክሊላቸው ናት፡፡ ዳግመኛም በክርስትና ሕይወት ለሚደረግ ተጋድሎ መጀመሪያ፣ ስለኃጢኣታችንና ስለወገኖቻችን ልናወርደው የሚገባንን እንባ የምናገኝባት፣ የጸሎት ምንጭ፣ የድንግልናና የንጽሕና ጌጣቸው፣ የንጽሕና መገለጫ፣ የወንጌል ሥራ መጀመሪያ፣ አርምሞን የምታስተምር ናት፡፡

ጤነኛ ዓይኖችን ዘወትር ብርሃን ማግኘት እንደሚስማማቸው ሁሉ ትክክለኛ ጾምም ጸሎትን ማዘውተር ይስማማታል፡፡ ሰው ጾም በጀመረ ጊዜ ኅሊናው በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ይጀምራል፡፡ ከዕንቅልፉ ቀንሶም ይጸልያል፡፡ ሰው አብዝቶ አፉን በጾም ከምግብ የከለከለውን ያህል በዚያው መጠን በትሕትና ሁኖ እያለቀሰ መጸለይን ገንዘቡ ያደርጋል፡፡ ጸሎታትም ከልቡናው ይታሰባሉ፡፡ ልቡ ጸሎታትን በማሰላሰል ይጠመዳል፡፡ በፊቱ ላይም ትዕግስት ትነበባለች፡፡ ስለኃጢኣቱ ያዝናል፡፡ ክፉ ሐሳቦችም ይርቁለታል፡፡ ከንቱ ንግግርም ትሸሸዋለች፡፡

ጾም የበጎ ምግባራት ግምጃ ቤት ስለሆነች ሰይጣን ከበጎ ምግባራት እንድንርቅ ሊያደርገን ሲሻ በቅድሚያ የሚያደርገው እርሷን እንድንንቅና እንድናቃልል መጋበዝ ነው- ምክንያቱም የጾምን ምንነቷን ዐውቆ ጥቅሟን ተረድቶ የሚጾማት ሰው የበጎ ነገሮች መከማቻ በሆነች ቤት ውስጥ ይኖራልና ከሥጋ፣ ከዓለምም ሆነ ከሰይጣን ለሚመጡለት የክፉ ፈቃድ ጥሪዎች አይገዛም፡፡ በዚህም የተነሣ ጾምን የሚያቃልል ሰው በፈቃዱ በጎውን ነገር ሁሉ ከራሱ አራቀ፡፡ አዳምን "ከእርሷ እንዳትበላ!" ብሎ በማዘዝ እርሷ እኛን ለክፉ ፈቃድ ከመገዛት እንድትጠብቀን እኛም እርሷን በመታዘዝ እንድንጠብቃት ከጥንት ጀምሮ ከፈጣሬ ዓለማት ተሰጥታናለችና፡፡

የሁላችን አባት አዳም እርሷን ባለመጠበቁ በሰይጣን ድል ተነሣ፡፡ እርሱ በመብላቱ ስለተሸነፈም ቅዱሳን ነቢያት ሁሉ ከሥጋ፣ ከዓለምና ከሰይጣን ክፉ ፈቃዳት ጋር በመጣላት ሕጉን ለመጠበቅ ያደረጉትን መጋደል በጾም ጀምረው ፍጹም ወደሆነው ፈሪሃ እግዚአብሔር ደረሱ፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን በዚህ ዓለም በተገለጠ ጊዜም ሥራውን በጾም ጀመረ፡፡ እርሱን ለመምሰል የፈቀዱ ቅዱሳንም ሁሉ ጾምን የገድላቸው መጀመሪያ አደረጓት፡፡ እርሷ ከልዑል እግዚአብሔር የተሰጠች ጋሻ ናትና ጾምን የሚንቅና የሚያቃልል ሰው ተግሣፅ ይገባዋል፡፡

ትእዛዝን የሰጠ፣ ሕግን የሠራ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከጾመ ሕግን ለመጠበቅ ከሚፈቅዱ ሰዎች መካከል ጾምን የማይወድዳት ማን ነው? በዘመነ ብሉይ ጌታ ስላልጾማት የሰው ልጆች ጾም በሰይጣን ላይ ፍጹማዊ የበላይነትን አልተቀዳጀችም ነበር፡፡ በዘመነ ሐዲስ ግን ክብር ይግባውና ለአዳም ካሣ ሊሆነው የመጣለት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳም ያልተጠቀመባትን ይህችን ሰማያዊ የጦር ዕቃ ጾምን አንሥቶ ሰይጣንን ተበቅሎልናል፡፡ በዚህም እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዲስ ኪዳን ገዳማዊ ሥርዓትን ለመጀመር በኵር ሆነ፡፡ ሰይጣንንና ክፉ ፈቃዳትን ለመዋጋትና ድል ለማድረግም በኵር ሆነልን፡፡ እነሆም በሰይጣን ተሸንፎ ወድቆ፣ ተጥሎ ለነበረ እኛነታችን የማሸነፍን አክሊል አቀዳጀ፡፡

ስለዚህም ዛሬ ሰይጣን ከሰው ልጆች መካከል አንዱን እንኳ ለጾም ሲጠመድ ሲመለከተው እጅግ ይፈራል- ጌታ እንዴት ድል እንደነሣው ያስታውሰዋልና፡፡ ከሊቀ ካህናታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በተሰጠችን በጾም የሰይጣንና የመሣሪያዎቹ የክፉ ፈቃዳት ኃይላቸው ይደክማል፡፡ አቤት! ጌታ እንዴት ያለ ድንቅ ምክር ሰጠን! ከአጋንንት ጋር ለመዋጋት ለልቡና ጽንዓትን የሚሰጥ እንደዚህ የጦር ዕቃ (እንደ ጾም) የሚበረታ ሌላ የጦር ዕቃስ ወዴት ይገኛል? የሰው ልጅ ክብር ይግባውና ክርስቶን ለማገልገል በመራብ ሥጋው በጾም በደከመ መጠን የዚያኑ ያህል አጋንንትን ጸንቶ ይዋጋል፡፡ ድል ያደርጉኛል ብሎም አይፈራም- የሚዋጋው ድል ከተነሣ ጠላት ጋር ነውና፡፡

ጾምን ፈጽመህ ውደደው!

ጾምን የናቀና ያቃለለ ሰው ሌላውን ትሩፋት ከመሥራት ቸል ይላል፤ ይደክማል፡፡ በስንፍና ምልክትነቷም ኃጢኣትን ወደሰውነቱ መርታ ታደርሳታለች፡፡ ኃጢኣትም ነፍሱን በመውጊያዋ ታቆሳስላታለች- የጦር ዕቃ ሳይይዝ ወደ ጦርሜዳ ሔዷልና፡፡ ዳግመኛም፣ ፈተና በሚመጣበት ጊዜ የሚጸናበትን፣ ከፈተና ጦር የሚጠበቅበትን ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተሰጠችንን ጋሻ ጾምን አልያዘምና ከሚነሣበት ፈተና የተነሣ የጀመረውን ክርስቶስን የመምሰል ገድል አቋርጦ ይሸሻል፡፡

አንተ ግን ሰማዕታትን ምሰላቸው፡፡ እነርሱ የምስክርነት አክሊል የሚቀበሉበትን (ማለትም ስለክርስቶስ ሲሉ የሚገደሉበትን) ቀን ካወቁ በዚያች ሰማዕትነትን በሚቀበሉባት ቀን አንዳች ምግብ ሳይቀምሱ ሰማዕትነታቸውን በጾም ይቀበሏት፣ ይጠባበቋት ነበር ይባላል፡፡ ከጾሙ ጋርም ጸሎትን አብዝተው ያደርሱ፤ ወደ ሠርግ እንደሚሔድ ሰውም በምሥጋና፣ በደስታና በሐሴት ወደ ሰማዕትነታቸው ይጓዙ ነበር፡፡ ክርስቲያን በመሆን "እናንተ የአባቴ ቡሩካን በወደ እኔ ኑ!" የሚለውን ቃል ለመስማት የታጨን እኛም እንግዲህ ይህንን የሕይወት ቃል ለመስማት ንቁዎች ሁነን ልንኖር፣ ለጠላቶቻችን ለአጋንንትም መንገድ በሕይታችን ላይ መንገድ እንዳንሰጥ ልንጠነቀቅ፣ ከአካል ክፍሎቻችን አንዱም ቢሆን ክፉ ሥራ የሚያስብበትን ምልክት እንዳንሰጠው ልንጠበቅ ይገባናል፡፡

"ንዑ ኀቤየ ቡሩካኑ ለአቡየ!" የሚለውን የሚያረጋጋ ድምጹን ለመስማት የበቃን፣ የነቃን፣ የተጋን ያደርገን ዘንድ ልዑል እግዚአብሔርን በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እንለምነዋለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት