ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ለግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የላኩት መልእክት

Coptic"ዛሬ ከመቼዉም ጌዜ ይልቅ በደም ሰማእትነት ተዋህደናል። ይህም ወደ ሰላም እና ወደ ዕርቅ ለምናደርገው የጋራ ጉዞ የበለጠ ኃይል ይሰጠናል፣ ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ አንድ ሆነን የተዋሃድን ባንሆንም ከሚያለያየን ነገር በላይ አንድ የሚያደርገን ነገር ይበልጣል።" ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ለኮፕቲክ/ለግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በላኩት መልእክት በአሁኑ ሰአት ክርስቲያኖች ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ለአንድነት ልዩ ትኩረት መስጠት አለባቸው በማለት ክርስቲያኖች ስለአንድነታቸው ማሰብ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ር.ሊ.ጳ. ግንቦት 10 ቀን ለአሌክሳንደርያው ሊቀጳጳስ አቡነ ቴዎድሮስ ዳግማዊ በላኩት ደብዳቤ " ዛሬ ከመቼዉም ጌዜ ይልቅ በደም መሥዋዕትነት ተዋህደናል። ይህም ወደ ሰላም እና ወደ ዕርቅ ለምናደርገው የጋራ ጉዞ የበለጠ ኃይል ይሰጠናል" በማለት ተናግረዋል።

ር.ሊ.ጳ. ይህንን መልእክት የላኩበት ዕለት ከአሌክሳንደርያው ሊቀጳጳስ ጋር የተገናኙበትን ሁለተኛ ዓመት አስመልክቶ ሲሆን ዕለቱ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና በኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ኣብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ወንድማዊ ፍቅር በሁለቱም በኩል የተዘከረበት መልካም አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ በመልእክታቸው " በዚህ ልዩ አጋጣሚ እግዚኣብሄርን እያመሰገንሁ በአንዲት ጥምቀት አንድ በመሆናችን በወንድማዊ ፍቅር ረጅም ርቀት በአንድነት ያደረግነዉን ጉዞ ላስታውሳችሁ እወዳለሁ። ምንም እንኳን ሙሉ
በሙሉ አንድ ሆነን የተዋሃድን ባንሆንም ከሚያለያየን ነገር በላይ አንድ የሚያደርገን ነገር ይበልጣል። ስለዚህ በፍቅር እና በጥበብ በማደግ ወደ አንድነት የምናደርገዉን የጋራ ጉዞ ኣጠናክረን እንድንቀጥል አደራ ለማለት እወዳለው" በማለት ለክርስቲያኖች አንድነት ያላቸዉን ተስፋ ኣና ቁርጠኝነት አሳይተዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ር.ሊ.ጳ. በሊቢያ ስለክርስትና እምነታቸው በግፍ የተገደሉትን ክርስቲያኖች ዘወትር በጸሎታቸው እንደሚዘክሯቸው እና ለዛሬይቱ ቤተክርስቲያን የሓዋርያትን የእምነት ምስክርነት ሕያው ያደረጉ የዘመናችን ሰማዕታት መሆናቸዉን አያይዘው ገልጸዋል።

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ በክርስቲያኖች አንድነት ዙርያ የሚደረጉ ወይይቶችን በጥልቅ መንፈሳዊ ቅናት እንደሚደግፉ በመግለጽ የአሌክሳንደርያው ሊቀጳጳስም ይህንኑ የተቀደሰ ተግባር እንደሚደግፉት እና ተገቢዉን የአንድነት ፍሬ ያፈራ ዘንድ የበኩላቸዉን አስተዋጾ እንደሚያደርጉ ያላቸዉን ተስፋ ገልጸውላቸዋል። በተለይም በካቶሊካዉያን እና
በኦርቶዶክሳዊያን ክርስቲያኖች መካከል የሚፈጸመዉን ቅልቅል ጋብቻ በተመለከተ ዘርፈ ብዙ ሃዋርያዊ ስራ መሰራት እንዳለበት ያላቸዉን እምነት እና ጽኑ ፍላጎት ለጳጳሱ አቅርበዉላቸዋል። ባለፈው የፈረንዾቹ ዓመት በክርስቲያናዊ ቤተሰብ ዙርያ በሮም ቫቲካን በተደረገው ሲኖዶስ ላይ ኦርቶዶክሳዊያን ወንድሞቻችን መሳተፋቸው የሚታወስ ነው።

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ ለአሌክሳንደርያው ሊቀጳጳስ የአንድነት ዐምድ እና ምሶሶ በሆነው በጌታችን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ሰላምታቸዉን በማቅረብ መልእክታቸዉን አጠናቅቀዋል።

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።