“ከሚከፋፍለን ይልቅ አንድ የሚያደርገን የላቀ ነው!” ር.ሊ.ጳ ፍራንቼስኮስ (የክርስቲያኖች ኅብረት)

Patriarch Pope“ከሚከፋፍለን ይልቅ አንድ የሚያደርገን የላቀ ነው!” ር.ሊ.ጳ ፍራንቼስኮስ በቫቲካን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓትሪያሪክ ዘኢትዮጵያን በተገናኙበት ወቅት በአጽኖዖት የተናገሩት ነው።
ብፁዕ ፓትሪያርኩ ካለፈው ዓርብ ጀምሮ በቫቲካን የተገኙ ሲሆን፡ በቫቲካን ውስጥ በ“ኮሌጆ ኢቶፒኮ” የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ተማሪ ካህናት በመኖሪያቸው አቀባበል እንዳደረጉላቸውና ተይዞ በነበረው መርኀ ግብር መሠረት በካቶሊካዊት ቤ/ያን የክርስቲያኖች ኅብረት እንቅስቃሴን ከሚያጠናክረው ምክር ቤት ጋር ስብሰባ ማካሄዳቸው ታውቋል። በቆይታቸውም በቫቲካን የሚገኘውን የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መቃብር እንደጎበኙና በኡርባኒያኑም ኮሌጅ ቤተ ጸሎት ፓትሪያርኩና በሮም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በጋራ ሥርዓተ አምልኮ ተካፍለዋል።
ር.ሊ.ጳ ፍራንቼስኮስ ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት “ሁሉ ነገራቸው አንድ ነው ማለት ይቻላል” ምክንያቱም አንዲት እምነት፡ አንዲት ጥምቀትና አንድ አዳኝ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንጋራለንና በማለት ለፓትሪያርክ ማቲያስ ቀዳማዊ ንግግር አድርገዋል።
ር.ሊ.ጳ ፍራንቼስኮስ ሲቀጥሉም “እኛ በክርስቶስ ወንድማማቾችና እህታማቾች ነን፤ ብዙ ጊዜ እንደተስተዋለውም ከሚከፋፍለን ይልቅ አንድ የሚያደርገን የላቀ ነው” በማለት የሚሰማቸውን ቅርበት ገልጸዋል። በማያያዝም በተለያዩ መንገዶች የተለያዩ ክርስቲያኖችን በጋራ የሚቀበሏቸው ስቃዮች እንዴት ወደ በለጠ መቀራረብ እንዳመጧቸው በመናገር “በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሰማዕታት ደም አዲስ ክርስቲያኖች ይግኙ ዘንድ ዘር በመሆን እንዳገለገለ ሁሉ ዛሬም የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት አባላት ሰማዕትነት የክርስቲያኖች አንድነት ዘር ሆኗል” ብለዋል።
ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ይህንኑ የክርስቲያኖች መስዋዕትነት ለአንድነት አሁንም የሚያበረክተውን ጥቅም በማመልከት “የሰማዕታቱ አንድነት እኛ ወደ ላቀ የአንድነት ጎዳና እንድንጓዝ ይጠራናል” ሲሉ ሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ሰማዕታት እንዳሏቸው አስታውሰዋል።
በመቀጠልም ቤተ ክርስቲያን ሕዝባቸውን በሚያስተዳድሩ መንግሥታት ውስጥ ያላትን ሚና ሲገልጹ ር.ሊ.ጳ ፍራንቼስኮስ “የዓለምን ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ሥልጣን የያዙትን ሰዎች አብሮ በሰላም ተቻችሎና ተከባብሮ በእርቅ በይቅርታና በመተባበር መኖርን ያስፋፉ ዘንድ መማጠናችንን አሁንም ቢሆን ማቋረጥ የለብንም” ሲሉ አሳስበዋል። አያይዘውም በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ያለው የተሻለ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሴቶችንም ያካተተውን ጥረት አመስግነው፡ “መንፈስ ቅዱስ ሆይ! ወደ ስምምነትና ሰላም በምናደርገው ጉዞ ላይ ብርሃንህን ስጠን ምራን!” የሚል ጸሎት በማሳረግ ደምድመዋል
ምንጭ- www.zenit.org

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።