እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ቅዱሳን አበው ስለ እመቤታችን


emebete.ስለ እመቤታችን ንጽሕና አባቶች ብዙ ብለዋል፡፡ እንዲያው በደፈናው እመቤታችን ለብዙዎቹ አባቶች የድርሰታቸው መጀመሪያ፣ የቅኔዎቻቸው ምንጭ ነበረች ማለት ይቻላል፡፡ ጥቂት ላካፍላችሁ፡-

ከሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ውዳሴ ማርያም ልጀምር አባቶቻችን እንደሚነግሩን ይህ አባት የእመቤታችን ፍቅር ቢጠናበት “ምነው ምስጋናዋ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ምድር አሸዋ በዝቶልኝ እንደምግብ ተመግቤው” እያለ ይመኝ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ለቅዱሳኑ የወደዱትን ያደርጋልና እመቤታችን ተገልጣለት፣ ውዳሴዋም በዝቶለት “አኃዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ፡፡” (ጌታ ሆይ የጸጋህን ሞገድ ያዝልኝ) እስኪል ድረስ ረክቷል፡፡ (ውዳሴ ማርያም አንድምታን ይመልከቱ)

ከሰባቱ ቀን ውዳሴዎቿ መካከል ሁለቱን አንቀጽ ከማክሠኞና ከዐርብ እንጥቀስ፡-

“አክሊለ ምክሕነ፣ ወቀዳሚተ መድኃኒትነ፣ ወመሠረተ ንጽሕነ ኮነ በማርያም ድንግል እንተ ወለደት ለነ መድኅነ፡፡”        (የማክሠኞ ውዳሴ ማርያም)

ትርጉም፡- “የመመኪያችን ዘውድ፣ የደኅንነታችንም መጀመሪያ፣ የንጽሕናችንም መሠረት መድኃኒታችንን በወለደችልን      በድንግል ማርያም ሆነልን፡፡”

ማርያም ንጽሕት ድንግል ወላዲተ አምላክ፣ ማእምንት ሰአሊተ ምሕረት ለውሉደ ሰብእ ሰአሊ ለነ ኀበ ክርስቶስ ወልድኪ ይሥረይ ኃጢአተነ፡፡(የዐርብ ውዳሴ ማርያም)

ትርጉም፡-

“ንጽሕት ድንግል የሆንሽ፣ አምላክን የወለድሽ፣ ለሰው ልጆችም የታመንሽ ምሕረትን አሰጪ ማርያም፣ ልጅሽ ክርስቶስ ኃጢኣታችንን ይሠርይልን ዘንድ ለምኚልን፡፡”

ግብጻዊው አባ ሕርያቆስ ደግሞ በቅዳሴ ማርያም እንዲህ ይላል፡-

“ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዐብየኪ፣ እስመ ወለድኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን፡፡”

ትርጉም፡-

“ማርያም ሆይ እውነተኛ የጽድቅ መብልንና እውነተኛ የሕይወት መጠጥን ወልደሽልናልና እንወድሻለን ከፍከፍም እናደርግሻለን፡፡”

 

ኢትዮጵያዊው የማኅሌተ ጽጌ ደራሲም የነቢዩ ኢሳይያስን “እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደሰዶም በሆንን ገሞራንም በመሰልን ነበር፡፡” (ኢሳይያስ 3፡ 9) የሚል ትንቢት መሠረት አድርጎ የሚከተለውን ይላል፡-

“ከመ ሰዶም እምኮነ ወከመ ገሞራ እምመሰልነ

እግዚአብሔር ኪያኪ ለእመ ኢያትረፈ ለነ፡፡” 

ትርጉሙም “እግዚአብሔር አንቺን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን ገሞራንም በመሰልን ነበር፡፡” ማለት ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ለእመቤታችን ያለንን ፍቅር የታዘቡ የውጭ ሀገር ሰዎች “ኢትዮጵያዊ ሰውነቱ ቢቆረጥ ከደሙ ጋር አብሮ ማርያም የሚል ስም ይገኛል፡፡” ብለዋል ይባላል፡፡ መቼም በእውነት ይበሉትም አይበሉት የእመቤታችን ከኢትዮጵያውያን ሕይወት ጋር መቆራኘት ግን ማንም የማያብለው ሐቅ ነው፡፡ ነፍሰ ጡር ልጅ ልትወልድ ስታምጥ “ማርያም! ማርያም!”፣ ስትወልድ “እንኳን ማርያም ማረችሽ፡፡” “ማርያም ጭንሽን ታሙቀው፡፡” “ማርያም በሽልም ታውጣሽ፡፡” ትባላለች፡፡ በአራስነት ወራቷም “የማርያም አራስ” ተብላ ድንግል ማርያም በአደራ ትሰጣለች፡፡ ሕጻናት ለብቻቸው ሲስቁ “ማርያም እያጫወተቻቸው ነው፡፡” ይባላል፡፡ ሕጻናቱም አድገው ሲጫወቱ ማምለጫ ፍለጋ “የማርያም መንገድ ስጠኝ/ ስጪኝ፡፡” ይባባላሉ፡፡ አንድን ሰው አንዳች ነገር እንዲያደርግልን ሽተን ስንለምንም “እንደው ለእኔ እንደ ቆምህልኝ ማርያም ትቁምልህ” ብለን ስሟን ጠርተን እንማጸነዋለን፡፡ ሰማዩን ቀና ብለን ለኖኅ የተሰጠውን ውብ የቃል ኪዳን ምልክት ቀስተ ደመና ስናይም “የማርያም መቀነት”፣ ፈረስ የምትመስል በራሪ ፍጥረትንም “የማርያም ፈረስ” እንላለን፤ ወዘተ.፡፡

እዚህ ላይ አያቴ ትዝ አለችኝ (ነፍሷን ይማርልኝ)፡፡ እውነቱን ለመናገር ከመጠመቋና ክርስቲያን መሆኗን ከማወቋ በስተቀር ስለክርስትና የምታውቀው ነገር የለም ማለት ይቀላል፡፡ ነገር ግን የእመቤታችን ድንግል ማርያም ማኅበር ነበራት፡፡ ሌላ መዝሙር አታውቅም፡፡ ነገር ግን “ስሟ ስንቅ ነው የእመቤቴ፤ ስሟ ስንቅ ነው የእመቤቴ፡፡” እያለች ስታወድሳት አስታውሳለሁ፡፡ ማርያም ማለት ለእርሷ የእምነቷ መሠረት ነበረች፡፡

አንዳንዴ ሳስበው በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ እንደማርያም ትልቅ ስፍራ ያለው ምንም ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ማርያምን ከቤት እስከ ቢሮ፣ ከትምህርት ቤት መታወቂያ ውስጥ እስከ ታክሲ ጋቢና ድረስ ታገኟታላችሁ፡፡ እኔ እንዳስተዋልሁት ስሟን፣ እናትነቷን የማይሰብክ የኢትዮጵያ ጥግ ብዙ አይደለም፡፡ በቤተክርስቲያኗን ትውፊት ስንመለከትም እንደድንግል ማርያም ብዙ መልክእ የተደረሰለት[i]፣ በርካታ መጽሐፍ የተጻፈለት[ii]፣ ቁጥሩ የበዛ በዓል[iii] የሚከበርለት አንድም ጻድቅ ወይም ቅዱስ አይገኝም፡፡ የዚህ ሁሉ ምክንያቱ ግን ሌላ አይደለም፡- ከላይ እንደጠቀስነው እውነተኛ የጽድቅ መብልንና እውነተኛ የሕይወት መጠጥን የወለደችልን ኃጢኣታችን ከክርስቶስ እንዳያርቀን የምትተጋ፣ እውነተኛ የክርስቲያኖች ረዳት፣ ርኅርኅተ ኅሊና መሆኗ ነው እንጂ፡፡

ብጹዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንዳሉትና እኔም ተስፋ እንደማደርገው የክርስቲያኖችን አንድነት ለማምጣት (በተለይ በኦርቶዶክስና በካቶሊክ መካከል) ነገረ ማርያም (Mariology) ትልቅ አስተዋጽዖ ማድረግ ይችላል፡፡ ቅዱስነታቸው ሲናገሩ ከዐራቱ የቤተክርስቲያንን አንድነት ለማምጣት ከሚመረመሩ ነገሮች መካከል አንዱ ነገረ ማርያም ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከተመለከትን ደግሞ በኦርቶዶክስና በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያን በሚገኙ ምእመናን መካከል ለእመቤታችን ባላቸው ፍቅር አንዳችም ልዩነት አንመለከትም- የፍቅራቸው መገለጫዎች እንደው ላይ ላዩን (superficially) ይለያይ ካልሆነ በስተቀር፡፡

ይሁን እንጂ ብዙው ሕዝብ በአብያተ ክርስቲያኑ መካከል የአስተምህሮ (ዶክትሪን) ልዩነት እንደሌለ አያውቅምና አንዳንዴ እንደ ጠላት ሲተያይ ማየቱ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ሌላው ቀርቶ አንዱ ሐዘን ሲደርስበት ሌላኛው ፈጥኖ ቀርቦ ሲያጽናናው እንኳ አይታይም፡፡ አንዳችን የሌላኛችንን ሐሳብ ባለመረዳት የተነሣና በሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት በመለያየት ለአንድ ሺህ ስድስት መቶ ዓመታት ያህል የጎዳነውን የክርስቶስን ቅዱስና ገር ልብ በማርያም አማላጅነት መንጋውን ወደአንድ እረኛ በመሰብሰብ ለመካስ በፍቅር መጣር፣ በእንባ መጸለይ አለብን፡፡ ክርስቶስ “ከመ ይኵኑ አሐደ ብነ ከማነ” (ዮሐ17፡ 21) ብሎ የጸለየለትን መንጋ ለገዛ ፈቃዳችን በማድላትና አፍቃሪ ልብ በማጣት ከፋፍለነው ሁላችን ኃጢአትን ሠርተናልና “We have all sinned.”፡፡ ሁላችንም በድለናልና ማንም ማንም ላይ ጣቱን ሊጠቁም አይበቃም[iv]፡፡ ይልቁንስ ዛሬ ፍቅርን እንፈልግ፡፡ ክርስቶስ ፊት በምንቀርብ ጊዜ የምንጠየቀው የማይጠቅሙ የሜታፊዚክስ ጭቅጭቆቻችንን ሳይሆን ወንድማችንን ምን ያህል መውደዳችንን ነውና፡፡[v] ዳግመኛም ክርስቶስ “የሰው ልጅ ዳግመኛ በመጣ ጊዜ በምድር ላይ እምነት ያገኝ ይሆንን?” እንጂ “እውቀት ያገኝ ይሆንን?” አላለም (ሉቃ 18፡ 8)፡፡

እርግጥ ነው አንዳንድ ሰዎች ክርስቲያኖችን የለያየው ራስን የመውደድና የኩራት አጥር አንድቀን እንደ በርሊን ግንብ ተንዶ ይፈርሳል ማለት የማይመስል ነገር ሆኖ ሊታያቸው ይችላል፡፡ ሆኖም አባቶቻችን “እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል፡፡” እንዲሉ የዚህ የመለያየት ግንብ መፍረስ ከድንግል በድንግልና መውለድና ከአምላክ ሰው መሆን በምንም አይበልጥምና ይፍጠንም ይዘግይ አንድ ቀን አይቀርም፡፡ ደግሞስ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ እጆቹን ለችንካር ዘርግቶ እግዚአብሔርና ሰውን፣ ሰውና መላእክትን፣ ሕዝብና አሕዛብን አላስታረቀምን? ዳግመኛም “በዘሯና በዘርህ መካከል ጠላትነትን አኖራለሁ፡፡ እርሱ ራስ ራስህን ይቀጠቅጣል፤” ተብሎ የመለያየት አባት ዲያብሎስ አልተረገመምን? የድንግል ማርያም ልጅስ በመስቀሉ የቀደመ የኃጢአት ግድግዳችንን አላፈረሰልንምን? ታዲያ ይህኛውን ለወንጌል መስፋት እንቅፋት አድርገን በትዕቢታችን የገነባነው የመለያየት ኃጢኣታችንን ግድግዳ እንዴት አይንድልንም? “እመን እንጂ አትፍራ!”

       ሰላም ለመዛርዕኪ ዘተረሰያ ኃይለ

 ከመ ይጹራ ነበልባለ

ማርያም ድንግል እንተ ኃጣእኪ መምሰለ

ኃጢኣትየ ለገብርኪ እመ ፈድፈደ ተለዐለ

ከመ ጥቅም ዘባቢሎን ረስዪ ንሑለ፡፡ (መልክአ ማርያም)

ቅድስት ማርያም የአምላክ እናት ለእኛ ለኃጢአተኞች አሁንም በሞታችንም ጊዜ ለምኝልን፡፡          

ከሣህለ ሚካኤል

[i] መልክአ ማርያም፣ መልክአ ኪዳነ ምሕረት፣ መልክአ ሥዕል፣ መልክአ ውዳሴ፣ ተፈሥሒ ማርያም ዘዘወትር፣ ተፈሥሒ ማርያም ዘሰሙነ ፋሲካ፣ ስብሐተ ፍቁር ዘእግዝእትነ፣ መዝሙረ ድንግል ወዘተ.

 

[ii] ድርሳነ ማርያም፣ ነገረ ማርያም፣ ተአምረ ማርያም፣ ራእየ ማርያም፣ ውዳሴ ማርያም፣ ቅዳሴ ማርያም፣ ቅዳሴ መዓዛ ወዘተ.

 

[iii]  ለምሳሌ ተአምረ ማርያም ላይ ድንግል ማርያም በዓመት ውስጥ 33 በዓላት እንዳሏት ይገልጣል፡፡ 

[iv]The Second Vatican council does not ignore the fact that "people on both sides were to blame" for causing the divisions among Christians." (UR no. 3)Pope John Paul II for his part writes: "The Catholic Church acknowledges and confesses the weaknesses of her members, conscious that their sins are so many betrayals of and obstacles to the accomplishment of the Savior's plan." (UUS no. 3)  http://www.columbia.edu/cu/augustine/a/unity.html and http://www.vatican.va/holyfather/john_ paulii/encyclicals/documents/hf_jp-ii_enc_25051995_ut-unum-sint_en.html

[v] What good does it do to speak learnedly about the Trinity if, lacking humility, you displease the Trinity? Indeed it is not learning that makes a man holy and just, but a virtuous life makes him pleasing to God. I would rather feel contrition than know how to define it. (Thomas a Kempis: Imitating Christ)

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት