ንስሐ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔርና ፍቅር - ማር ይስሐቅ

ንስሐ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔርና ፍቅር

በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ዘንድ በትውፊት እጅግ ላቅ ያለ ቦታ ከሚሰጣቸው መጻሕፍት መካከል “ማር ይስሐቅ”“አረጋዊ መንፈሳዊ”ና “ፊልክስዩስ” በመባል የሚታወቁ ሦስት መጻሕፍት አሉ፡፡ የጥቅል ስማቸው “መጻሕፍተ መነኮሳት” ይባላል፡፡ በዋናነት የመነኮሳትን ሕይወት የሚመለከቱ መጻሕፍት ሲሆኑ ብዙጊዜ ለየብቻቸው አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሦስቱም አንድ ላይ በአንድ መድበል ተጠርዘው እንደ አንድ መጽሐፍ ይገኛሉ፡፡ ስለ“አረጋዊ መንፈሳዊ”ና ስለ “ፊልክስዩስ” መወያየቱ ለሌላ ጊዜ ይቆየንና ለዛሬ “ማር ይስሐቅ” ስለሚባለው የ1600 ዓመት የዕድሜ ባዕለ ጸጋ መጽሐፍ ጥቂት እንነጋገር፤ ጥቂትም ከሀብቱ እንካፈል፡፡

ይህ መጽሐፍ ደራሲው “ማር ይስሐቅ” የሚባል የቂሳርያ ሰው እንደሆነ ይነገራል፡፡ ቂሳርያም የተወለደባት ሳትሆን ከአጎቱ ከቅዱስ ኤፍሬም[i] ዘንድ ሆኖ በአካልና በመንፈስ ያደገባት፣ የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር የተማረባትና በክህነት ለእግዚአብሔር የተለየባት ቦታ ናት፡፡ ይሁን እንጂ ወላጆቹ ለክህነት የሚያበቃውን ትምህርት ከተማረ በኋላ ሌላ የዕለት እንጀራውን የሚያሸንፍበት ዓለማዊ ትምህርት እንዲማርላቸው ስለፈለጉ ወደተወለደባት ወደ ሶርያ ይመለስ ዘንድ አጎቱን ቅዱስ ኤፍሬምን ጠየቁት፡፡ በጥያቄያቸው መሠረትም ወደ ወላጆቹ ሀገር ወደ ሶርያ ጉዞ ይጀምራል፡፡ በዚህ ጊዜ የተፈጠረውን ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እንዲህ ሲሉ ይተርኩታል[ii]፡-

ሲሔድ ሳለ ኅሊና ሥጋዊትና ኅሊና መንፈሳዊት ሰውነቱን ሜዳ አድርገው ይራወጡበት ጀመረ፡፡ ኅሊና ሥጋዊት “የካህን ሞያ ተምሬ የሰዎች የበላይ እንደሆንሁ የጨዋ[iii] ሞያ ተምሬ የበላይ እሆናለሁ፡፡ ወይም በሕግ ጸንቼ፣ ሥጋውን ደሙን ተቀብዬ፣ ገንዘቤን መጽውቼ እኖራለሁ፡፡” አለችው፡፡ ኅሊና መንፈሳዊት ደግሞ “ዓለም እንደ ጥላ ያልፋል፤ እንዳበባ ይረግፋል፡፡” ብላ ተሟገተች፡፡ እርሱም ለኅሊና መንፈሳዊ አጋዥ ሆኖ “ቆይ! እዚህ ደርሼ ልምጣ፡፡” ብሎ ዱር ለዱር ሄዶ ከአባ እብሎይ ገዳም ገብቶ መነኮሰ፡፡ በዚያም ለ25 ዓመታት በረድእነት ሲያገለግል ኖሮ አባ እብሎይ ከዚህ ዓለም ድካም በሚያርፍበት ጊዜ “እርሱን ባየሁበት ዓይኔ ማንንም አላይም ብሎ አራዊት ከበዙበት፣ ልላሜ ዕፅ፣ የውኃ ምንጭ ከሌሉበት ቦታ ሔዶ ብሕትውና ያዘ፡፡ በዚያ ብሕትውናው እያለም ይህ መጽሐፍ ተገልጾለት በጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ጻፈው፡፡[iv]

መጽሐፉ በዐቢይ ጉዳይነት የመነኮሳትን ሥራዎችና ፈተናዎቻቸውን ያስተዋውቃል፡፡ ከፈተና መውጫና ማምለጫ መንገዶችንም ይጠቁማል፡፡ ነገር ግን በውስጡ ያሉ በርካታ ትምህርቶች ላልመነኮሱም ሆነ ለማይመነኩሱ ሰዎች እጅግ የሚጠቅሙ ናቸው፡፡ አንዳንዴ ያስጸልያል፤ አንዳንዴ ይገሥጻል፤ አንዳንዴ ደግሞ ያጽናናል፤ አንዳንዴም በአስተንትኖ ያፈላስፋል፡፡  ነገር ግን በቀላልና ትውልዱ ሊገባው በሚችል ቋንቋ በማቅረብ ረገድ ብዙ ሥራ ይቀራል፡፡[v] ለማንኛውም ዛሬ ከዚህ መጽሐፍ ስለ ንስሐ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔርና ፍቅር የተማርሁትን በዘመናችን አማርኛ ላካፍላችሁ (አንቀጽ26፣ ምዕራፍ 1)[vi] ቅድስት ቤተክርስቲያን ስለ ፍቅር ያላትን እይታ ለመገንዘብ በትንሹም ቢሆን የሚረዳ ይመስለኛል፡-

ንስሐ ለተጠመቅን ሰዎች ከጥምቀታችን ቀጥሎ የተሰጠችን ታላቅ ሀብታችን ናት፡፡ በእርሷም ምክንያት የእግዚአብሔርን ቸርነት የምናገኝባት ለሚሹዋት ሰዎች ሁሉ የተከፈተች የይቅርታ በር ናት፡፡ በእርሷ በርነትም ከፈጣሪ ወደሚገኝ ቸርነት እንቀርባለን፡፡ ከእርሷ ከራቅን ግን ይቅርታን ማግኘት አንችልም- አምላካዊው መጽሐፍ እንደሚነግረን “ሁላችን በድለናልና”[vii]፡፡ በእርሷ በኩል ግን ያለአንዳች ዋጋ በነጻ በይቅርታው እንነጻለን፡፡

 

ንስሐ ምንጯ ምንድነው?

ንስሐ እግዚአብሔርን ከመፍራትና ከሃይማኖት የተነሣ በልቡና ውስጥ የምትወለድ ጸጋ ናት፡፡ ማለትም እግዚአብሔር ፈጣሪያችን፣ መጋቢያችን፣ አባታችን እንደሆነ አምነን ትእዛዛቱን ልንጠብቅ እንደሚገባን በመቀበል “አድርጉ!” የተባልነውን ትእዛዝ ሳናደርግ፣ “አታድርጉ!” የተባልነውን ሕግ ደግሞ ሳናከብር በመቅረታችን ልዑል እግዚአብሔር በአባትነቱ እንደሚያዝንብን፣ በአምላክነቱም እንደሚፈርድብን ማሰብ ስንጀምር ስለ ክፉ ሥራ መጸጸት የሆነችው ንስሐ በእኛ ውስጥ ትወለዳለች፡፡ ክፉ ሥራችንን ከአባታችን ከእግዚአብሔር ፍቅር አንጻር ዓይተን የምናወርደውን የጸጸት እንባ ጠጥታም ትፋፋለች፡፡ የአባታችንን የእግዚአብሔርን ምክንያትየለሽ የማይደበዝዝ ፍቅር አስታውሳም ከወደቅንበት አፈፍ ብለን በመነሣት ክርስትና በተባለው መንገድ በመገሥገሥ ወደአባታችን ቤት እንድንመለስ ትቀሰቅሰናለች፡፡[viii]

ቀስቅሳንም አትቀርም፡፡ በዚህ ከሰው ልጆች ኃጢኣት የተነሣ ሽታው እጅግ በሚከረፋ የትዕቢት ማዕበል በምትናጥ ዓለም ውስጥ ለሚካሄደው የክርስትና ጉዟችንም በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት የተሰበረ ልቡናና ትሑት መንፈስ እንዲኖረን በማድረግ  መርከብ ትሆነናለች፡፡ ቀዛፊዎቿም በየጊዜው ፈሪሃ እግዚአብሔርን የሚያስተምሩ መምህራነ ቤተክርስቲያን ናቸው፡፡ የእነርሱን ትእዛዝ መከተልና በምንም ምክንያት ቢሆን ከመርከቧ አለመውረድ ጉዞውን ለማጠናቀቅ ዋስትና ነው፡፡ በመርከብ ያልተጫነ ሰው የውቅያኖስን ማዕበል መሻገርና ከወደብ መድረስ እንደማይቻለው ሁሉ የንስሐ ሕይወት የሌለውና በንስሐ ያገኘውን ጸጋ በተነሳሒ ትሕትና የማይጠብቅ ክርስቲያንም ከወደቡ ሳይደርስ በማዕበሉ ተውጦ ይቀራል- ጉዞው ትዕግስት የሚጠይቅ ረጅም ነውና፡፡ እዚህ ላይ ሰዎች እንደመሆናችን መጠን የጉዞውን ርዝማኔና የማዕበሉን እንግልት ተሰቅቀን የሚከተለውን የመሰሉ ጥያቄዎች በአእምሯችን መመላለሳቸው አይቀርም፡፡ “ወደኋላችን በመመለስ ጉዞውን ብንተወውስ ምን ይቀርብናል?”

ወደቡ

በፈሪሃ እግዚአብሔር በምትቀዘፈው ንስሐ የተባለችው መርከብ ላይ መጓዛችን ከአንድ ወደብ ለመድረስ ነው፡፡ ይኸውም ወደብ ፍቅር ይባላል፡፡ የክርስትና ሕይወትን ውጣ ውረድ በንስሐ መርከብ ላይ በትዕግስት ተጉዘን እስከ መጨረሻይቱ ኅቅታ ስንጸና የዮሐንስ ራእይ ላይ “የሕይወት አክሊል” ተብሎ ከተገለጸውና ሌላው ስሙ ፍቅር ከሚሰኘው ወደብ እንደርሳለን፡፡ የሚገርመው ነገር ይህ ወደብ በጉዟችን ሁሉ አብሮን ይጓዝ የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ስሙም የተጓዦች አፍቃሪና ምሳሌ ተጓዥም፣ የደካሞች ምርኩዝና አጋዥ፣ የመንገደኞች አቅጣጫ መሪ ብሩሕ ኮከብ፣  የመርከቧም መድረሻ ወደብ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ይባላል፡፡ በጉዟችን ሁሉ በጥበቃውና በረድኤቱ አንድም በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ አብሮን ነበረ፡፡ እንግዲህ ከመነሻው ጀምሮ የያዝነው የጉዟችን ዓላማ ይህንን ወደብ ፊት ለፊት ለማግኘት ነው- ምክንያቱም እዚህ ወደብ ላይ የዓይኖቻችን ቅርፊቶች በቅድስናው ሰይፍ ይገፈፉልንና እርሱን ፍቅር የተባለውን ወደብ እናየዋለንና፡፡ የማይለወጥ እርሱ እኛን ወደፍጹም መንፈሳዊነት ይለውጠናል፡፡ የፍጥረት ዓይን ልታየው የማትችል እርሱን እናየው ዘንድ የማየትን አክሊል ያቀዳጀናል፡፡ ይህ የማየት አክሊልም ራሱ ፍቅሩ ነው፡፡ እዚህ ተአምረኛ ወደብ ስንደርስ ሁሉ በእርሱ አንድ ይሆናል፡፡ ሀገሩ ስሙ ፍቅር ነው፤ የቦታው ንጉሥም ራሱ ፍቅር ነው፤ እኛ ነዋሪዎቹ የምንመገበውም እርሱኑ ፍቅርን ነው፤ ልብሳችንም እርሱው ራሱ ፍቅር ይሆናል፡፡ ዓይኖቻችንም ራሱ ውበት በሆነው በፍቅር እይታ ይነደፋሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሀገር ጎብኝቶ ሲመለስ ያየውን ውበት ለመግለጽ የሰው ቋንቋ ቢያጥርበት “ዓይን ያላየው፣ ጆሮ ያልሰማው፣ በሰው ልቡናም ያልታሰበ”[ix] በማለት ከሰው አእምሮ በላይ የሆነ “እጹብ! እጹብ!” ብቻ ብለው የሚያደንቁት መሆኑን መሰከረ፡፡

ይህ እይታ ከጣዕሙ ጣፋጭነት የተነሣ ዘማውያንን ለንጽሕና አብቅቷል[x]፡፡ በትንሣኤ ሙታን የማያምኑ ሰዱቃውያንን በትንሣኤው ሕያዋን እንዲሆኑ አስችሏል[xi]፡፡ ወይንን አብዝተው የሚወድዱትን በጾም የሚተጉ አገልጋዮች አድርጓል፡፡ ኃጢኣተኞችን የዓመጻ መንገድን አስረስቷል፡፡ ድሆችንም በመንግሥተ ሰማያት ተስፋ የከበሩ ባዕለ ጸጎች ወደመሆን ቀይሯል፡፡ ድውያን በእርሱ ተፈውሰዋል፡፡ ድኩማን በእርሱ በርትተዋል፡፡ አላዋቂዎችም በእርሱ የጠቢብነትን ካባ ተጎናጽፈዋል፡፡

ስለሆነም የማዕበሉን እንግልት ተሰቅቀን ወደኋላ ብንመለስ የምናጣው ይህንን ጥዑም ምግብ ሳንመበው እንቀራለን፤ ይህንን የሚያምር መጎናጸፊያ ሳንለብሰው ያመልጠናል፤ ይህንን ልዩ ውበት ለማየት አንችልም፤ በዚህ ልዩ ፍቅርም ሳንነካ ባለመነካታችንም ሳንቀየር እንቀራለን፡፡[xii]

ትሩፋት በመሥራት የደከሙ፣ በገድል ተቀጥቅጠው የኖሩ፣ ጥርጥር በሌለባት ሃይማኖት የጸኑ ጻድቃን የሚያዩት፣ የሚወርሱት ይህንን ሀገር ነው፡፡ ወደእርሱ መድረሻዋ መንገድም “እርስበርሳችሁ ተፋቀሩ፡፡”[xiii] የምትለው የብቸኛው መንገድ የኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅር ትእዛዝ ናት፡፡ ፍቅርን ገንዘብ ካደረግናት ወደእግዚአብሔር እንቀርባለን፡፡ የክብር ባለቤት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ወደሚያወርሳት መንግሥተ ሰማይም እንደርሳለንም፡፡

ስለሆነም ለፍጹም ፍቅሩ የነቃን ያደርገን ዘንድ እንዲሁም እርሱን በመፍራት በፍቅሩ ለምትወረስ ለመንግሥተ ሰማያት የበቃን ያደርገን ዘንድ በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እንለምነው፡፡ ከእርሱ ጋር ክብር ጽንዕ ያለው ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ከሣህለ ሚካኤል


[i] ቅዱስ ኤፍሬም በኢትዮጵያውያን ትውፊት “ውዳሴ ማርያም” ብለን የምንጠራውን የእመቤታችን ውዳሴ የደረሰው የአራተኛው ክፍለ ዘመን ቅዱስ

[ii] አማርኛውን ተለምዷዊ ለማድረግ እንደዘመናችን አማርኛ አለዛዝቤዋለሁ፡፡

[iii] መሠረታዊ ትርጉሙ ካህን ያልሆነ ግን በማኅበረሰቡ ውስጥ ፍርድና አስተዳደር የተማረ የተከበረ ሰው ማለት ነው፡፡

[iv]መቅድም፡፡” በውስተ ሦስቱ መጻሕፍተ መነኮሳት፡፡ አዲስ አበባ፣ ተስፋ ገብረሥላሴ፣ 1988፡፡

[v] በተለይ አእምሮው ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እየገነነ በመጣው ባዶ ኤሮሳዊ ስብከትና የንግድ ማስታወቂያዎች ፕሮፓጋንዳ የተመላና ከዚህም የተነሣ ምንኩስናንና እስከ ጋብቻ ድረስም ንጽሕናን እጅግ የሚሰቀቀውን ትውልድ በንጽሕና የመኖርን ጥቅምና የምታስገኘውን ታላቅ ጸጋ ለማስተማር ገዳማትን የሥራ ቦታዎች ለማድረግ የሚተጋውን ያህል ገዳማቱን በዕውቀት ማዕከልነት በማበልጸግ እንዲህ ያሉ የሚያንጹ መጻሕፍትን ለትውልዱ በሚገባ ቋንቋ ተርጉሞ ማቅረብ ግድ ይላል፡፡ ለእንዲህ ዓይነቱ ሥራም እያንዳንዱ መነኮስ ታላቅ ኃላፊነት ከትከሻው ላይ እንዳለ ሊሰማው ይገባል፡፡ እንደናትናኤል “ናና እይ!” የሚል ጥሪ ለትውልዱ መቅረብ አለበት- “ወበዘርኢነ ሰማዕተ ንከውን” (“ያየነውን እንመሰክራለን፡፡”) ተብሎ በዮሐንስ ወንጌላዊ እንደተጻፈ፡፡ በኤልያስ መንፈስ የሚሔድና ኤልሳዕን ለእግዚአብሔር አገልጋይነት የሚመለምል፣ የሚያሠለጥን፣ የሚያበቃ አባት ያስፈልጋል፡፡ ልክ እንደቅዱስ ዮሐንስ ቦስኮና እንደኢትዮጵያዊው አባ ኢየሱስ ሞዓ ችግረኞችን ብቻ ሳይሆን ችግኞችንም የሚወድድና የሚፈልግ፣ ፈልጎም በዕውቀትና በመንፈሳዊነት ኮትኩቶ የሚያሳድግ አባት ዛሬ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ ክርስትና ዛሬ በምዕራቡ ዓለም ውስጥ እየደረሰበት ያለውን ዓይነት መዳቀቅ ነገ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳያጋጥመው ዛሬ እረኞች በእጅጉ መትጋት ያስፈልጋቸዋል፡፡ አለበለዚያ አንድ ፈላስፋ “ከታሪክ የምንማረው ከታሪክ አለመማራችንን ነው፡፡” ያለው ነገር የሚገጥመን ይመስለኛል፡፡

[vi]ማር ይስሐቅ፡፡” በውስተ ሦስቱ መጻሕፍተ መነኮሳት፡፡ አዲስ አበባ፣ ተስፋ ገብረሥላሴ፣ 1988 (ገጽ. 214-218)፡፡

[vii] መዝ. 13

[viii] እዚህ ላይ ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ Dues Caritas Est (በላቲን “እግዚአብሔር ፍቅር ነው፡፡” ማለት ነው፡፡) በተሰኘው ውብ ጽሑፋቸው “በሐዲስ ኪዳን ፍቅር ትእዛዝ ሳይሆን እኛን በማፍቀር የተነሣ ሰው የሆነልን አምላክ ለሰጠን ፍቅር የምንሰጠው ምላሽ ነው፡፡” ያሉትን ማስታወስ ይቻላል፡፡

[ix] 1ኛ ቆሮ. 2፡9

[x] ጌታ በቀራጩ በስምዖን ቤት ተቀምጦ ሳለ እግሩን በእንባዋ ያራሰችው፣ በጸጉሯም ያበሰችውና ራሱን ሽቱ የቀባችው ባለሽቱዋ ማርያም

[xi] ቅዱስ ቶማስ

[xii] እግረ መንገዳችንን ይህን መዝሙር እናስብ፡-

 

መንገዴን እንዳልስት

ጌታዬ ሆይ!

በትዕግስት ልጠብቅ

አባቴ ሆይ!

ለሥጋዬ ምቾት

ጌታዬ ሆይ!

ጉዞዬን እንዳልተው ጠብቀኝ፤

ከጉያህ እንዳልወጣ ደጋግፈህ ያዘኝ፡፡ 

 

እውነተኛ ጽድቅን የምጠማ ልሁን ዘወትር በፊትህ፤

ትንሹን ፈተና ወድቄ እንዳላሳዝንህ፡፡

ውድቀቴን ለሚሻ ጠላቴም አትስጠኝ፤

በድል አክሊልህን እንድቀበል እርዳኝ፤

በድል አክሊልህን ለመቀበል አብቃኝ፡፡

[xiii] ዮሐ. 13፡34