23 - ለምን፣ ፈልግ፣ አንኳኳ

Knockበዚህ ጽሑፍ ውስጥ በቀጣይ ቁጥሮች በአጠቃላይ ስለ ጸሎት ምንነት ሳይሆን፥ በተለየ መንገድ የመንፈስ ቅዱስ እሳት በሕይወታችን ላይ ይነድ ዘንድ ማድረግ ስለሚገቡን ነገሮች ነው ልንመለከት የምንሻው፡፡ በዚህ ፍለጋችን ላይ እጅግ ሊጠቅሙን የሚችሉትም የሐዋርያት የሕይወት ተመክሮ እና የጌታ ኢየሱስ የተስፋ ቃላት ናቸው፡፡ ስለዚህ የተለየ ትኩረት ለአዲስ ኪዳን ገጾች በመስጠት፥ አንዳንድ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ቅድመ-ሁነቶችን ልናስቀምጥ እንሞክራለን፡፡

፩. ለምን፣ ፈልግ፣ አንኳኳ

"እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ነገር መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ የሚኖር አባታችሁማ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም!" (ሉቃ. 11፡13)። {jathumbnail off}

በሉቃስ 11፡1-13 ላይ ኢየሱስ ስለ ጸሎት ያስተማረውን ትምህርት እናነባለን፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ጌታ ራሱ እንደጸለየ፣ የእርሱን ፈለግ በመከተልም ደቀመዛሙርቱ ጸሎት እንዲያስተምራቸው መፈለጋቸውን እናነባለን (ሉቃስ ላይ አንድ ደቀ መዝሙር ይህን ጥያቄ እንዳቀረበ ስናነብ፥ በማቴዎስ አገላለጽ ደግሞ ራሱ ጌታ ያለ ጥያቄ ጸሎት ሲያስተምራቸው እናነባለን)፡፡ "በሰማይ የምትኖር አባታችን" የተሰኘውን ጸሎት ለደቀ መዛሙርቱ ካስተማረ በኋላ፥ ያለማቋረጥና ተስፋ ባለመቁረጥ የሚደረግ ጸሎት መልካም ውጤትን እንደሚያስገኝ ያስረዳቸዋል፡፡ እላይ የተጠቀሰው የጌታ ቃል፥ ይህን ትምህርት ሲያስተምር ለመደምደሚያነት የተጠቀመበት ትምህርት ነው፡፡ በዚሁ ትምህርቱ ላይ ጌታ ሦስት ነገሮችን እንደምሳሌ ያቀርባል "የሚለምን ሁሉ ይቀበላል፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ መዝጊያ ለሚያንኳክም ይከፈትለታል" (ሉቃ. 11፡10፤ ማቴ. 7፡8)፡፡ የሰማይ አባታችንን ስለማንኛውም ዓይነት መልካም ስጦታ ሁሉ ልንለምነው እንችላለን፤ እርሱም ይሰጠናል፡፡ ምክንያቱም ቃሉ እንደሚያረጋግጥልን፥ "መልካም ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው" (ያዕ. 1፡17)፡፡

የማቴዎስ ወንጌል ስለማንኛውም መልካም ነገር (ስጦታ) ሁሉ እግዚአብሔርን እንድንለምን ቀጥለንም የእርሱን መልካም ስጦታ እንድንቀበል ሲያስተምረን፥ ሉቃስ ግን የበለጠ ነገሩን ጠበብ አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ የምንቀበለው መልካም ነገር (ስጦታ)፥ ሌላ ነገር ሳይሆን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ራሱ እንደሆነ ያሳየናል፡፡ በደንብ ለማነጻጸር ማቴ. 7፡7-11ን እና ሉቃ. 11፡9-13ን ማንበቡ ይበቃል፡፡

ከመንፈስ ቅዱስ የበለጠ ሌላ ምን መልካም ነገርን ልንመኝ እንችላለን? ከእርሱ የበለጠ ሌላ ምን ስጦታንስ ከጌታ ልንለምን እንችላለን? በዚህ አቅጣጫ የምናደርገው ጸሎት ውጤታማ እንደሚሆን ከጌታ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል፡፡ በሱ በኩል ሁሉም የተፈፀመና የተዘጋጀ ነው፤ የሚቀረው የኛ ድርሻ ብቻ ነው፡፡ በኛ በኩል የምናደርጋቸው ሦስቱ ነገሮች እላይ የተጠቀሱት ናቸው፡፡

ከለመንን ይሰጠናል፡፡ መለመን ማለት ከልብ መጠየቅ፣ ደጅ መጥናትንም ያመለክታል፡፡ የምሥራቹ ቃል ይህን ያረጋግጥልናል፤ እግዚአብሔር አብ መንፈስ ቅዲስን እንዲሰጠን ከለመንነው ይሰጠናል፡፡ እንዲውም አብልጦ ይሰጠናል፡፡

ከፈለግን እናገኛለን፡፡ መፈለግ ማለት ምን ማለት ነው? በአማርኛችን መፈለግ ሁለት ትርጉሞችን ሊሰጠን ይችላል፡፡ አንደኛ፡- የጠፋብንን (የተሰወረብንን) ነገር ለማግኘት (ለማየት) ፍለጋ እናደርጋለን (እንፈልጋለን) ወይም የማናውቀውን ነገር ለማወቅ ፍለጋ እናካሂዳለን፡፡ ሁለተኛ፡- ልባዊ ፍላጎታችንን ወይም መሻታችንንም መፈለግ ብለን እንጠራዋለን፡፡ ከልብ መመኘታችንም (ምኞታችንም) መሻታችንና ፍላጎታችን ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስንም ለመቀበል ፍለጋ ማድረግ (መፈለግ) አለብን፡፡ በሁለቱም አቅጣጫዎች ልንፈልገው እንችላለን፡፡ በኃጢአታችንና በልበ ደንዳናነታችን ከሕይወታችን ውስጥ አውጥተን አጥፍተነው እንደሆነ፥ እንደገና እንድናገኘው እንፈልገው፤ እንሻው፡፡ ከሁሉም ነገር ይልቅ የልባችን ፍላጎትና መሻትም እርሱ ብቻ ከሆነ እንፈልገው፤ እንሻው፡፡ በእርግጥ እናገኘዋለን፡፡ ምክንያቱም የሚፈልግ (የሚሻ) እንደሚያገኝ ጌታ ራሱ አረጋግጦልናልና! ስናገኘውም ከፍለጋችን በላይ ሆኖ ይቆየናል፡፡

መዝጊያውን ካንኳኳን ይከፈትልናል፡፡ መዝጊያውን ማንኳኳት ማለትም ያለመሰልቸትና ተስፋ ባለመቁረጥ እስከመጨረሻው ድረስ ደጅ መጥናት ማለት ነው፡፡ የመኳንንትንና የባለሥልጣኖችን ቤትና ጽሕፈት ቤት በሮች ምን ያህል ጊዜ አንኳኩተን ይሆን? ምን ያህል ደጅ አስጠንተውን ይሆን? እግዚአብሔር ግን የልባችንን ትልቅ ምኞትና ተስፋችን እርሱ ብቻ እንደሆነ ማወቃችንን ሲመለከት ወዲያውኑ በሩን ይከፍትልናል፤ በበረከቱም ያጥለቀልቀናል፡፡ የምናንኳኳው በር ግን የብረት ወይም የእንጨት በር አይደለም፤ ሕያው ሆኖ ሕይወትን የሚሰጥ በርን ነው፡፡ ያ በር ሌላ ማንም ሳይሆን፥ ራሱ ጌታ ኢየሱስ ነው፡፡ እርሱ ራሱ ይህን አስተምሮናል፡፡ "እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የበጎች በር ነኝ፤... በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ይድናል፤ ይገባል ይወጣል መሠማሪያም ያገኛል" (ዮሐ. 10፡7፣ 9)፡፡

 እያንዳንዱ ልመናችንና፣ የልብ መሻታችን የጌታ ኢየሱስን ርኅሩኅ እና ለጋስ ልብ ያንኳኳል፤ ለጥቂት ጊዜ ታግሠን ከጠበቅነውም፥ ወደ ልቡ ጓዳ ያስገባናል፡፡ በዚህ ቅዱስ ልብ ውስጥ የሚቆየን እጅግ ታላቅ እሳት ነው፤ ይህ ቅዱስ ልብ አስደናቂው የእሳት ምድጃ ነው፡፡ በዚህ ምድጃ ላይ ለዘላለም የሚነደው ዘለዓለማዊ ፍቅሩ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም ፍቅር ነው፡፡ ወደ ጌታ ኢየሱስ ቅዱስ ልብ ውስጥ በጥልቀት በገባን ቁጥር የምናገኘው እርሱን ነው፡፡

ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስ እሳት እንደ አዲስ በኛ ላይ ነድዶ፥ እንዲያነደን፥ ተቀጣጥሎ እንዲያቀጣጥለን ከፈለግን፥ ጌታ እግዚአብሔር ይህን እንዲያደርግልን ጥርት ባሉ ቀጥተኛ ቃላት እንለምነው፤ ያደርግልናል፡፡ ያለኛ ፍቃድና ፍላጎት በግድ እኛን የሚጠቅመንንም ነገር እንኳ ቢሆን አያደርግምና፥ ፍላጎታችንንና መሻታችንን ግልጽ አድርገን እንንገረው፡፡ ከሁሉ በፊት የኛን ነፃነትና ፍቃድ ማክበር የሚወደው አምላክም ይህን ሲመለከት በደስታ ከጥበቃችን በላይ ፍላጎታችንን ያሟላልናል፡፡ ምናልባት መልሳችን ቶሎ ካልመጣ በሩን እያንኳኳን በተስፋ እንጠብቀው፤ ሳይዘገይ ከተፍ ይላል፡፡ መልሳችንም ከግምታችን በላይ ስለሚሆን በአድናቆት እናመሰግነዋለን፡፡ "እንግዲህ በእኛ እንደሚሠራው ኃይል መጠን ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ ለሚቻለው፥ ለእርሱ በቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ኢየሱስ፥ እስከ ትውልዶች ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን፡፡" (ኤፌ 3፡20-21)

ከአባ ኤፍሬም ዓንዶም

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።