22.3 - የመንፈስ ቅዱስና የእሳት ጥምቀት የሚባለው ነገር ምንድነው?

(ካለፈው የቀጠለ - ክፍል ሦስት)

menfes kidus 2በሐዋ.ሥራ ምዕ. 10 እና ምዕ. 11፡1-18 ላይ የተዘገበው የአሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት ታሪክ ደግሞ ለየት ያለ ገጽታን ያሳየናል፡፡ በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች ያልተጠመቁና ከአይሁዳውያን ወገንም ያልነበሩ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ እየሰበከላቸው ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፡፡ "ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ፡፡" (የሐዋ.ሥራ. 10፡44) ነገሩ ከጴጥሮስ ጋር የነበሩትን አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በእጅጉ አስገርሟቸው ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር ጴጥሮስ እነኛን ሰዎች እንዲጠመቁ ያዘዛቸው፡፡ "በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፡- ‹እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው?› አለ፡፡

በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው፡፡" (የሐዋ. ሥራ 10፡47-48) በዚህ ታሪክ ላይ የምናገኘው ቅደም ተከተል፥ አስቀድመን ካየናቸው የተለየ ነው፡፡ መጀመሪያ "በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ" ቀጥሎም "የውኃ ጥምቀት" (ሳክራሜንታል ባፕቲዝም) ሲከናወኑ እናያለን፡፡ ይህም የሚያሳየን አንድ ዓቢይ እውነታን ነው፡፡ ይኸውም "የውኃ ጥምቀት" (ምስጢረ ጥምቀት) "በመንፈስ ቅዱስና በእሳት መጠመቅ" ከሚባለው ክስተት በላይና እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስም ቢሆን "ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል" (ማር. 16፡16) ነው ያለው እንጂ "የመንፈስ ቅዱስና እሳት ጥምቀትን ያልተለማመደ አይድንም" አላለም፡፡ ስለዚህ ለመዳን የመጀመሪያው አስፈላጊ ነገር ምስጢረ ጥምቀት (የውኃ ጥምቀት) ነው እንጂ፥ እርሱን እንዲያጠናክር የሚሰጠው ቀጣዩ የመንፈስ ቅዱስ ርደት አይደለም፡፡ እንደዚህ ባይሆን ኖሮ በእነኛ አሕዛብ ላይ መንፈስ ቅዱስ እንደወረደ፥ ጴጥሮስ ሳያጠምቃቸው በተዋቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ያለጥምቀት ደኅንነት ስለሌለ፥ ምንም እንኳ እፁብ ድንቅ የሆነ ስጦታንም ቢቀበሉ (የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ)፥ ለመዳናቸው ማረጋገጫ ሊሆናቸው በሚችለው በምስጢረ ጥምቀት በኩል የግድ እንዲያልፉ ጴጥሮስ አዘዛቸው፡፡ "በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው" (ቁ.48) እዚህ ላይ ምስጢረ-ጥምቀት ትእዛዝ እንጂ ምክር ወይም አስተያየት አይደለም፡፡ ጴጥሮስም ይህን ትእዛዝ ከኪሱ አውጥቶ የሰጠው ሳይሆን፥ ከጌታ ኢየሱስ የተቀበለውን ትእዛዝ ነው ያስተላለፈው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ እንዳለው፥ "ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም" (ዮሐ. 3፡5) "ከውኃና ከመንፈስ መወለድ" ማለትም መጠመቅ ማለት ነው፡፡ በዚህም የውኃ ጥምቀትን ታላቅነት ጌታ በግልጽ ያሳያል፡፡ የውኃ ጥምቀት (sacramental baptism) ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የመግቢያ የመጀመሪያው በር ወይም ማለፊያ እንደሆነም ከቃላቱ እንገነዘባለን፡፡ በአጭሩ፥ ምስጢረ ጥምቀት "የመንፈስ ቅዱስና የእሳት ጥምቀት" ከሚባለው ልምምድ በላይ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል፡፡ ምክንያቱም፥ የውኃ ጥምቀት ከሰባቱ የቤተ ክርስቲያን ምስጢራት መካከል አንዱና የመጀመሪያውም ሲሆን ሌላኛው ግን ከጌታ የሚሰጥ ልዩ ጸጋ እንጂ ምስጢር አይደለም፡፡ በጥምቀት ወደ ጌታ ማኅበር የገባውን አማኝ የበለጠ በማበርታት ለአገልግሎት የሚያስታጥቅ መለኮታዊ ስጦታ ነው፡፡ በእርግጥ እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው፤ ቢሆንም ከምስጢረ ጥምቀት ጋር ግን ልናወዳድረው አንችልም፡፡

ከሰባቱ የቤተ ክርስቲያን ምስጢራት መካከል ሦስቱ ፈፅሞ የማይደገሙ ናቸው፡፡ አንዴ ከተሰጡ ለዘለዓለም የማይጠፉ ማኅተምን በአማኙ ነፍስ ላይ ያደርጋሉ፡፡ እነርሱም፡- ምስጢረ-ጥምቀት፣ ሜሮንና፣ ክህነት ናቸው፡፡ በነኚህ ምስጢራት አማካይነት በተቀባዩ ነፍስ ላይ የሚወርደውን መንፈስ ቅዱስን የፈለገውንም ዓይነት ሁኔታ ቢፈጠር ሊያጠፋውና ሊያባርረው አይችልም፡፡ ለምሳሌ በምስጢረ ጥምቀት አማካይነት መንፈስ ቅዱስን የተቀበለ ክርስቲያን፥ ከተጠመቀበት ቀን አንስቶ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ የፈለገውን ያህል ክፉ ሰው ቢሆን፥ ጌታውን ቢክድ፥ ከኃጢአት ሁሉ የከፋውን ኃጢአት ቢያደርግ፥ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ሊሰርዝ የሚችል ነገር ሊከሰት አይችልም፡፡ ያ ሰው ኃጢአተኛ ቢሆን፣ ከዳተኛ ቢሆን፣ የረከሰ ቢሆን፥ ኃጢአተኛ የእግዚአብሔር ልጅ፣ ከዳተኛ የእግዚአብሔር ልጅ ወዘተ ሆኖ ይኖራል፥ እንጂ የልጅነት መንፈሱን ሊነጥቅበት የሚችል ምንም ኃይል አይኖርም፡፡ ጽድቁና ኩነኔው እንደ እግዚአብሔር ልጅነቱ መጠን ነው የሚለካው እንጂ፥ ከጥምቀት በኋላ ጻድቁ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ፣ ኃጢአተኛው ግን የሰይጣን ልጅ የሚሆንበት ምንም መንገድ የለም፡፡ ግን ጻድቁ የእግዚአብሔር ልጅ አባቱን ስላከበረ ይከብራል፡፡ ኃጢአተኛውና ከዳተኛው የእግዚአብሔር ልጅም አባቱን ስላላከበረ ይቀጣል፡፡ ይህ የምስጢረ ጥምቀት ታላቁ ውጤት ነው፡፡ ምክንያቱም "እግዚአብሔር በጸጋው ስጦታና በመጥራቱ አይጸጸትም" (ሮሜ. 11፡29)፡፡ ልጄ ሆይ ብሎ ልጁን በጠራበት አፉ መልሶ ከእንግዲህ ወዲህ ልጄ አይደለህም የሚል አባት አይደለም፡፡

ምስጢረ ጥምቀት ለአንዴና ለዘለዓለም የሚሰጥ ሲሆን የመንፈስ ቅዱስ መውረድ ግን በተደጋጋሚ ሊሰጥ የሚችል ጸጋ ነው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ገና በማሕፀን ሳለች አንስቶ ጸጋ የሞላት፣ መንፈስ ቅዱስ በርሷ ላይ የነበረ ነበረች፥ ኢየሱስን ስትጸንስ መንፈስ ቅዱስ እንደ አዲስ በሷ ላይ ሲወርድ እናያለን፡፡ ከሐዋርያት ጋርም የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ስትቀበል እናያታለን፡፡ ሐዋርያትም ለአገልግሎት ሲላኩ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ነበር፡፡ "ኢየሱስም... አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው፡፡ ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፡፡" (የሐ. 20፡ 21-22) ከጥቂት ጊዜ በኋላም በበዓለ-ሃምሣ ዕለት እንደ አዲስ የመንፈስ ቅዱስን ሙላት ሲቀበሉ እናያለን፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎችም ይህን ስጦታ እንደተቀበሉ የሐዋ.ሥራ በሰፊው ይተርክልናል፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት በተለያዩ ሁኔታዎች ሊከሰት እንደሚችል ከዚህ እንገነዘባለን፡፡ የውኃ ጥምቀት ግን አንድ ጊዜ ብቻ ነው የሚሰጠው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳመለከተው "አንዲት ጥምቀት" (ኤፌ. 4፡5) ብቻ ናት ያለችው፡፡ ነገር ግን በዚህ መሠረት ላይ ተገንብተን፥ በተደጋጋሚ የመንፈስ ቅዱስን ሙላት ልንቀበል እንችላለን፡፡ አስፈላጊ ነገርም ነው፡፡

በኣባ ኤፍሬም ዓንዶም 

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።