እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

19. በመሠዊያው ላይ ያለው እሳት ሳይጠፋ ሌሊትና ቀን ዘወትር ሲነድ ይኑር (ዘሌዋ. 6፡12)፡፡

19. በመሠዊያው ላይ ያለው እሳት ሳይጠፋ ሌሊትና ቀን ዘወትር ሲነድ ይኑር (ዘሌዋ. 6፡12)፡፡

sacred flameእግዚአብሔር ሙሴን ስለሚቃጠል መሥዋዕት ያዘዘው ይህ ትእዛዝ እኛንም በተለየ መንገድ ይመለከተናል፡፡ በዚሁ ንባብ ውስጥ በተለይ ከቁ.8-13 ላይ ይህ ትእዛዝ ሦስት ጊዜ ሲደጋገም ይታያል፤ ቁ.9፣ 12፣ 13፡፡ ይህም የትእዛዙን ጥብቅነት ያሳያል፡፡ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ለሚቃጠል መሥዋዕት ይቀርቡ የነበሩት እንስሳት እንደነበሩ እናነባለን፡፡ "በዚህ ዓይነት የሚቀርቡት መባና መሥዋዕት የአቅራቢውን ሰው ኅሊና ፍጹም ሊያደርጉት አይችሉም" (ዕብ. 9፡9) የተባለለትን የብሉይ ኪዳን የመሥዋዕት አቀራረብ በሚመለከት፥ ጌታ በተደጋጋሚ የእሳቱን ያለማቋረጥ መንደድ በጽናት ከተናገረ፥ በዘለዓለማዊ ጌታ ኢየሱስ ንፁሕ ደም የታጠብነውን ሕዝቡን መሥዋዕት በሚመለከትስ ከዚህ ባነሰ መልኩ ይናገረን ይሆን? የበለጠ በጽናት ይናገረናል እንጂ ወደኋላ የሚመለስ ቀዝቃዛ ትእዛዝን አይሰጠንም፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመንም እንኳ ቢሆን፥ መሥዋዕቶች ይቀርቡ የነበሩት እጅግ በተቀደሰ ስፍራ (በቅድስተ-ቅዱሳን) ውስጥ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ክቡር ስፍራም ቢሆን፥ በሰው የተሠራ ነበር ይህ ስፍራ፡፡ ዛሬ ግን ያ ቅዱስ ስፍራ፥ ያ ቤተ መቅደስ፥ ያ የአምላክ ታቦትና ማደሪያ በሰው የታነጸ ድንኳን ወይም ግንብ ሳይሆን፥ በአምላክ እጆች የታነጸና፣ በጌታ ኢየሱስ ደም ተረጭቶ፣ በዘለዓለማዊው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ የተቀባ፣ የሰው ልብ ወይም ሰው ራሱ ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን ቅድስተ ቅዱሳን እኛ ነን፡፡

"የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሆናችሁንና የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ መኖሩን ታውቁ የለምን? ... የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነው፤ ይህም ቤተ መቅደስ እናንተ ናችሁ" (1ቆሮ. 3፡ 16-17) እንዲሁም "ሰውነታችሁ፥ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁትና በውስጣችሁም የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ መሆኑን ታውቁ የለምን?" (1ቆሮ. 6፡19)

በዚያ ወደ ፍጽምና ሊያደርስ አይችልም የተባለለት የመሥዋዕት አቀራረብ እንኳ እሳቱ ያለማቋረጥ እንዲነድ ካስፈለገ፥ በእኛ መሥዋዕትስ ላይ ምን ያህል እጥፍ ድርብ ያ እሳት መንደድ ያስፈልገው ይሆን? ከዚህ በፊት እንዳልነው የኛ መሥዋዕት የሚቃጠል ሳይሆን የምስጋናና የአምልኮ መሥዋዕት ነው፡፡ በፍቅር ያልነደደ፣ በናፍቆት ያልተቀሰቀሰ፣ ምስጋናና አምልኮ፥ ኃይል የለሽና አሰልቺ ነው፡፡ ከአምልኮነቱ ይልቅ፣ ደረቅ ትእዛዝና ሥርዓትን ለመፈጸም ብቻ የሚደረግ ልማዳዊ ተግባርነቱ ያዘነብላል፡፡ የአምላክ ፍቅር በልባቸው ያልነደደባቸው ሰዎች "ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል" (2ጢሞ. 3፡4-5)፡፡ እውነተኞች የጌታ አምላኪዎች መሆንን ከፈለግን፥ የጌታን እሳት ሳያቋርጥ ሌትና ቀን በልባችን እንዲነድ እናድርግ፡፡ ይህ እንዲሆን ከፈለግንም እሳቱ የሚነድበትን መንገድ ማመቻቸት ይጠበቅብናል፡፡ ዘሌዋ. 6፡12 ላይ እንደተገለጸው "በመሠዊያው ላይ ያለው እሳት ሳይጠፋ ሌሊትና ቀን ዘወትር ሲነድ ይኑር፤ ካህኑም ማለዳ ማለዳ የማገዶ እንጨት ይጨምርበት"፡፡ ካህኑ የማገዶ እንጨት ማለዳ ማለዳ ካልጨመረበት ይጠፋል፤ እኛም ከልባችን የአምላክ ፍቅር እንዳይጠፋ ከፈለግን በየጊዜው ለእርሱ የሚስማማ ማገዶ መጨመር ይኖርብናል፡፡ ይህ ማገዶም ጸሎትና የጌታ ቃል ጥናት (ንባብ) ነው፡፡ ጸሎታችን ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ የሚያገናኘን፥ እንድንወያይም የሚያስችለን ልዩ መንገዳችን ነው፡፡ እግዚአብሔር አብን "አባ፤ አባት" ብለን መጥራት መቻል ይኖርብናል፡፡ ጌታ ኢየሱስንም "ጌታዬ" ብለን በአውነት መጥራት መቻል አለብን፡፡ ይህ ግን ያለ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ ሊሆን አይችልም፡፡ እግዚአብሔር አብን "አባ አባት" ብለን መጥራት የምንችለው መንፈስ ቅዱስን የተቀበልን ከሆንን ብቻ ነው፡፡ "በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና፡፡ አባ አባት ብለን የምንጮህበትን የልጅነትን መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደ ገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል፡፡" (ሮሜ. 8፡14-16)

"ልጆችም ስለሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮህ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ፡፡ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ" (ገላ. 4፡6-7)፡፡ ስለዚህ ከአብ ጋር ለመገናኘት መጀመሪያ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ልዩ ግንኙነት ሊኖረን ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም መለኮታዊ እሳት መሆኑን አስቀድመን አይተናል፡፡ ማገዶአችንም ለመንፈስ ቅዱስ ያለንን መንፈሳዊ መሰጠት (devotion) በየዕለቱ ማነሳሳት ነው፡፡ ይህን ችላ ስንል፥ ከአብና ከወልድ ጋር ያለንም ግንኙነት እንዲሁ ቀዝቅዞ ይቀራል፤ ሊጠፋም ይችላል፡፡

ጌታ ኢየሱስን "ጌታ" "ጌታዬ" "ጌታችን" ብሎ መጥራት የቃላት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የዕለታዊ ሕይወታችንን እንቅስቃሴ ሁሉ የሚመራ ውሳኔም ነው፡፡ በመጨረሻም የዘለዓለማዊ ሕይወት ድርሻችንን የሚወስን ከፍተኛ ጉዳይ ነው፡፡ የኢየሱስን ጌትነትም ለማወጅ የሚያስችለን መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ያለርሱ አይቻልም፡፡

"ስለዚህ ማንም በእግዚአብሔር መንፈስ ሲናገር፡- ‹ኢየሱስ የተረገመ ነው› የሚል እንደሌለ፥ በመንፈስ ቅዱስም ካልሆነ በቀር፡- ‹ኢየሱስ ጌታ ነው!› ሊል አንድ እንክ እንዳይችል አስታውቃችኋለሁ፡፡" (1ቆሮ. 12፡3) ‹ኢየሱስ ጌታ ነው!› ብለን ለሌሎች ከማወጃችን በፊት ‹ኢየሱስ የኔ ጌታ ነው!› የሚል ግላዊ ውሳኔ በራሳችን ላይ ማስተላለፍ ይኖርብናል፡፡ የኢየሱስን ጌታነት በግላዊ ሕይወታችን ውስጥም ይሁን፥ በማኅበራዊ ኑሯችን ላይ እንድንለማመደው የሚያስችለን መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ‹ኢየሱስ ጌታ ነው!› የሚለውን አባባል፥ መንፈስ ቅዱስ፥ ከልማዳዊ ቃል ወደሚኖር ሐቅ ይለውጠዋል፡፡ በሌላ አነጋገር፥ ይህን የእምነት ቃል፥ ሕይወት ይዘራበታል፡፡ ያለ መንፈስ ቅዱስ፥ ቅዱስ እርዳታ፥ በልጅነት መንፈስ ወደ አብ መቅረብም ሆነ፥ በታዛዥነት መንፈስ ወደ ጌታ ኢየሱስ መቅረብ አይቻልም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋርና በእኛ ውስጥ ሲኖር ግን፣ ከአብና ከወልድ ጋር የሚኖረን ግንኙነት ትክክለኛና የሰመረ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለንን ግንኙነት በየዕለቱ ያለማቋረጥ ማሳደግ ይኖርብናል ማለት ነው፡፡ ይህን የፍቅር እሳት ዘወትር በልባችን መሠዊያ ላይ ማቀጣጠል ያስፈልገናል፡፡

በመሠዊያችን ላይ መንደድ ያለበት ማገዶአችን ጸሎትና የጌታ ቃል ጥናት እንደሆነ እላይ ገልጬ ነበር፡፡ ስለ ጸሎት በጥቂቱ አይተናል፡፡ የቃሉ ጥናትን በተመለከተም፥ አሁንም ቢሆን፥ ያለ መንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ቃሉን በሚገባ መረዳት እንደማንችል የጌታ ቃል ያረጋግጥልናል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ያላቸው ይህን ያስረዳናል፡፡ "የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም፡፡ ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፡፡" (ዮሐ. 16፡12-13) (በተጨማሪ ዮሐ. 14፡26) በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ከተደገፈ ጸሎት ጋር የጌታን ቃል ስናነብ፥ ስለ እግዚአብሔር ያለን እውቀት ከማደጉም በላይ፣ በእምነት የበሰሉና የጠነከሩ ሰዎች እንሆናለን፡፡ እሳታችን እንዳይጠፋ በየዕለቱ መትጋቱ እንግዲህ ሊዘነጋ የማይገባው ጉዳይ ነው፡፡ ጌታም እሳታችን የነደደ ችቧችንም ዘወትር የሚበራ ይሆን ዘንድ ይሻል፡፡ ከዚህ ጋር አያይዘን ልንመለከታቸው የምንችላቸው ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም አሉ፡፡ እነርሱም፡- ዘጸ. 27፡20-21 እና ማቴ. 25፡1-13 ናቸው፡፡ በመጀመሪያው ንባብ ላይ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ታቦት ፊት፥ ዘወትር ሳይጠፋ መንደድ ስላለበት መብራት እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውን መመሪያ እናገኛለን፡፡ አሮንና ልጆቹ ይህ መብራት እንዳይጠፋ በየጊዜው ጥሩ የወይራ ዘይት በመቅረዙ ላይ መጨመር ነበረባቸው፡፡ በሁለተኛው ንባብ ላይም የዓሥሩን ልጃገረዶች ታሪክ እናነባለን፡፡ አምስቱ ልባሞች አምስቱ ደግሞ ሰነፎች ነበሩ፡፡ ልባሞቹ በቂ ዘይትና መጠባበቂያም ይዘው ነበር፤ አምስቱ ሰነፎች ግን መጠባበቂያ አልያዙም ነበር፡፡

እኛም በልባችን ውስጥ በሚኖረው ጌታ መንፈስ ቅዱስ ፊት ዘወትር የሚበራ የእምነት እና የፍቅር መብራት ሊኖረን ይገባል፡፡ መብራታችን እንዳይጠፋ አስተማማኝ ምንጫችን እርሱ ስለሆነ ሙሉ በሙሉ ተስፋችንን በእርሱ ላይ ማኖር ይገባናል፡፡ የጌታ ኢየሱስን ምጽአትም ስለማናውቅ እንደነዛ አምስት ልባም ልጃገረዶች መቅረዛችንን እና ማድጋችንን ከመንፈስ ቅዱስ በሆነው ዘይት ሞልተን መጠባበቅ ይገባናል፡፡ በዚህ ዓይነት መንገድ ነቅተን የጠበቅነው እንደሆነ ብቻ ነው ሽልማታችንን፥ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ አባባል አክሊላችንን መቀበል የምንችለው፡፡

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት