18.2 - አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ (ይሁዳ 23)

18.2 - አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ (ይሁዳ 23)

Guardian Angelእውነተኛ መልእክተኛ፥ የሚያደርሰውን መልእክት በሚገባ የሚያውቅና በትክክልም ማስተላለፍ የሚችለው ሰው ነው፡፡ ከአጥፊው እሳት ሌሎችን እንዲያወጣ የሚላከው አገልጋይም ስለአጥፊው እሳት ምንነት የሚያውቅ ብቻ ሳይሆን ለደኅንነት የሆነውን እሳትም የተላበሰ መሆን ይገባዋል፡፡ ያ አስቀድሞ በጌታ ቸርነት ከእሳት (ከአጥፊው) የተነጠቀውና የዳነው አገልጋይ፥ የመለኮታዊውን እሳት አጥሪነት፥ ቀዳሽነትና ባራኪነት በግሉ ከቀመሰና ካየ በኋላ፥ ባለበት አርፎ ሊቀመጥ አይችልም፡፡ ወዲያውኑ ያን የደኅንነት እሳት ይዞ በጥፋት ወዳሉት ወገኖቹ ይገሰግሳል፡፡ ይህ ባሕርያዊ ጉዳይ ሲሆን፥ በዚህ ብቻ ግን አያበቃም፡፡ አምላካዊ ትእዛዝም ነው፡፡ "አንዳንዶችንም (ከአጥፊው) እሳት ነጥቀህ አድን" የሚል የአደራ ቃልም በጌታ ቃል ውስጥ ሰፍሮለታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የጌታን ብርሃን እንዳዩ ወዲያውኑ የእርሱ አገልጋዮች በመሆን የሮጡለትን የብዙ ሰዎች ታሪክ ይዟል፡፡

ሳምራዊቷ ሴት የሕይወትን ውኃ ከጌታ እንደተቀበለች ወዲያውኑ ወደ አገሯ ሕዝብ ሄዳ እንደመሰከረች (ዮሐ. 4) ይነግረናል፡፡ ሁለቱ ዕውሮችም በጌታ ከተፈወሱ በኋላ ወዲያውኑ በየቦታው ስለእርሱ ማውራት (መመስከር) ጀመሩ (ማቴ. 9፡27-31)፡፡ በጌርጌሴኖን አገር በባሕር ዳርቻ ላይ፥ ጌታ ያገኘውን፥ በርኩስ መንፈስ የተያዘ አንድ ሰው በሚያስገርም ሁኔታ ከፈወሰው በኋላ "ወደ ቤትህ በቤተ ሰዎችህ ዘንድ ሄደህ ጌታ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገልህ እንዴትስ እንደ ማረህ አውራላቸው አለው፡፡" (ማር. 5፡19) ይህ ሰው እንዲመሰክር ነበር የታዘዘው፣ እርሱም ይህን ፈፀመ፡፡ "ሄዶም ኢየሱስ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት ዐሥር ከተማ በሚባል አገር ይሰብክ ጀመር፥ ሁሉም ተደነቁ፡፡" (ቁ.20) ከጥቂት ሰዓታት በፊት በዲያብሎስ እስራት ለዘመናት ታስሮ የነበረው ሰው፥ ከእሳት እንደተነጠቀ፥ ወዲያውኑ የክርስቶስ ሰባኪ ሲሆን ይታያል፡፡ ከጨለማ ወደሚያስደንቅ ብርሃን የመጡና የምሥራቹ ቃል አብሳሪዎች የሆኑትን ሰዎች ታሪክ ብንዘረዝር አንዘልቀውም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ከእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች አንዱ ነበር፡፡

"አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ" የሚለውን የአደራ ቃል ከምስክርነት ጋር አያይዘን መመልከታችን ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በእርግጥ አዳኙ ራሱ ጌታ ኢየሱስ ነው፡፡ እኛ የፈለገውንም ብናደርግ አዳኞች ልንሆን አንችልም፡፡ ግን በደኅንነት ሥራ ላይ ትልቅ ድርሻ አለን፡፡ አዎ ወደ እውነተኛው አዳኝ በጥፋት ላይ የሚገኙትን ሰዎች ማምጣትና መምራት እንችላለን፡፡ ከሁሉ የበለጠው ነፍሳትን ወደ ጌታ የማምጫው (ሰዎችን የማጥመጃው) መንገድም ምስክርነታችን ነው፡፡ የቃልና የሕይወት ምስክርነት! ስለ እኛና ስለ ምስክርነታችንም ይህ ተጽፏል፡- "እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደንቅ ብርሃኑ የጠራችሁት የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ" (1ጴጥ. 2፡9)፡፡

በጨለማ ቆይተን ወደ ብርሃን መምጣታችን፥ በሁለቱ መካከል ያለውን ታላቅ ልዩነት ገና በጨለማ ላሉት በሚገባ እንድናስረዳ ያስችለናል፡፡ በምስክርነታችን ምክንያት ወደ ጌታ የሚመለስ አንድ ሰው እንኳ ብናገኝ ዋጋችን ብዙ ነው፡፡ ቃሉ እንደሚለው "ኃጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን፥ የኃጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ" (ያዕ. 5፡20)

የኃጢአተኛውን ነፍስ ከሞት እንዳዳኑ ሰዎች እና የፍቅር ሰዎች እንደሆኑ ይቆጠርልናል፡፡ የኃጢአትን ብዛት የሚሸፍን ፍቅር ነው፡፡ እኛም ፍቅርን በሥጋችን ተሸከምን ወይም ፍቅር በኛ ላይ ሥጋ ለበሰ ማለት ነው፡፡ ግሩም ድንቅ ዋጋ! ልክ እኛ ከእሳት እንደተነጠቅነው ሁሉ፥ በተራችን እኛም ሌሎችን ከእሳት ነጥቀን አውጥተን ወደ ጌታ ማምጣት ይጠበቅብናል፡፡ ይህን እንድናደርግም "የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል" (2ቆሮ. 5፡14)፡፡ በጥፋት ላይ ያሉትን ወገኖች ከሚገኙበት የጥፋት እሳት ውስጥ ነጥቆ ማውጣት ፋታ የማይሰጥ እጅግ አጣዳፊ ግዴት ነው፡፡ አንድ ሰው በእሳት በተያያዘ ቤት ውስጥ በስቃይ ላይ እያለ እርሱን ከማደን የበለጠ ሌላ አስቸኳይ ጉዳይ ሊኖር አይችልም፡፡ ከዚህ አስቸኳይ ጥሪ ለማምለጥ የሚያስችል ምክንያት ሊቀርብ አይችልም፡፡ ቢቀርብ ግን ያ ምክንያት ደርዳሪ አንድም ጨካኝ፥ ወይም "እኔ ከሞት ሰርዶ አይብቀል" ባይ ራስ ወዳድ መሆን አለበት፡፡ የዚህ ዓይነቱ ሰዎች ከመሆንስ ያድነን! 

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።