15.2 - የእሳት ቅጥር (አምላካዊ ጥበቃ)

15.2 - የእሳት ቅጥር (አምላካዊ ጥበቃ)


ማግኔት የራሱ የሆነ ማግኔቲክ ፊልድ (magnetic field) አለው፡፡ ኤሌክትሪክም እንዲሁ የራሱ electrical field አለው፡፡ በእግዚአብሔር አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ስም በመጠመቁ ምክንያት የቅድስት ሥላሴ ታቦት የሆነ ማንኛውም አማኝም በዙሪያው የመለኮታዊው እሳት ቅጥር እንዳለው አምናለሁ፡፡ በተለይም ከትልቅ ኃጢአት ሁሉ ነጽቶ፣ የጌታን ቅዱስ ሥጋና ደም አዘውትሮ የሚመገብ ትጉ ክርስቲያን፣ በውስጡ ከያዘው መለኮታዊ ኃይል የተነሣ ዙሪያው ሁሉ አንድ ዓይነት መልስን ይሰጠዋል፡፡ ወይ ይስማማዋል ወይ ደግሞ ይቃወመዋል፡፡ ምክንያቱም በዙሪያው የመንፈስ ቅዱስ ወላፈን ስለሚንበለበል ነው፡፡ የሥጋ ዓይን ይህን አያየውም፡፡ ውስጣዊውና መንፈሳዊው ዓይን ግን በደንብ ያየዋል፡፡ የቅድስት እናታችን ድንግል ማርያም ሕይወት ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው፡፡

ሉቃ. 1፡39-56 ማርያም ኤልሣቤጥን ስትጎበኝ ያጋጠማትን ነገር ሁሉ ይነግረናል፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚደንቀኝ ነገር ቢኖር በቁ.41-42 ላይ የተዘረዘረው ነው፡፡ ማርያም ወደ ዘካርያስና ኤልሣቤጥ ቤት ገባች፤ ኤልሣቤጥንም ሰላም አለቻት፡፡ የርሷ በዚያ ቤት ውስጥ መገኘትና ሰላምታ ማቅረብ ብቻ፣ ያንን ቤት የመጀመሪያው የመንፈስ ቅዱስ ሙላት የተከናወነበት ቤት ሲያደርገው እናያለን፡፡ "ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት" (ቁ.41)፡፡ "ገና በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል" ተብሎ በገብርኤል ትንቢት የተነገረለት ዮሐንስም ያኔ ነበር በመንፈስ ቅዱስ የተሞላው (ሉቃ. 1፡15፣ 41፣ 44)፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ማርያም ስብከት አልሰበከች፣ እጇን ጭናም ኤልሣቤጥ በመንፈስ ቅዱስ እንድትሞላ አልጸለየች፣ ሰላምታ ብቻ አቀረበች፡፡ ውጤቱ ግን አስደናቂ ነበር፡፡ በማርያም ሰላምታ ብቻ ይህ ተአምር እንዴት ተፈፀመ? ምስጢሩ ምን ይሆን? ብዙ ብዙ ሊባል ይቻላል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ግን የማያሻማ ጥርት ያለ መልስ ይሰጠናል፡፡ "መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣ የልዑልም ኃይል (መንፈስ ቅዱስ) ይጸልልሻል፣ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፡፡" (ሉቃ. 1፡35) ማርያም በማኅፀኗ ኢየሱስን (ወልድን) እንደተሸከመችው ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ውስጧንና ውጯን ሁሉ ሞልቶ ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ እንደ ጥላ አጥልሏት ነበር፡፡ ዙሪያዋ በሙሉ በእርሱ ኃይል ተከቦ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ሁለንተናዋ ውስጧና ዙሪያዋ በሙሉ በመለኮታዊ እሳት ተሞልቶና ተከቦ ነበር፡፡ ታዲያ ወደዚህ መለኮታዊ እሳት አጥር ውስጥ የገባ ሳይዳሰስ ይቀር ይመስላችኋል? ምስጢሩ ይህ ነበር! ማርያም በመለኮታዊ እሳት ቅጥር ውስጥ ሆና ወደ ኤልሳቤጥ ቤት ገባችና ሰላምታዋን አቀረበች፡፡ ኤልሳቤጥና በማኅፀኗ ያለው ሕፃን (ዮሐንስ) በዚህ እሳት ተነኩ፤ ስለዚህም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፡፡ "የልዑል ኃይል ይጸልልሻል" የሚለው የተስፋ ቃል ማርያም ሙሉ ለሙሉ በመንፈስ ቅዱስ ጥበቃ ሥር እንደነበረች ያሳያል፡፡

አንድ ክርስቲያንም በውስጡ ከሚኖረው ጌታ መንፈስ ቅዱስ ሕላዌ የተነሣ፣ ዙሪያው በመለኮታዊ እሳት የተጠበቀ ነው፡፡ ግን አምኖ ሊኖርበት ይገባዋል፡፡ ከብዙ ቅዱሳን የሕይወት ልምድና፣ አሁንም በዘመናችን ከሚገኙ ሐቀኛ የጸሎት ሰዎች ልምዶች እንደምንረዳው፣ እነርሱ ባሉበት ቦታ የሰይጣን እስረኞች ሲገኙ፣ ያልተለመደ ረብሻን ይፈጥሩባቸዋል፡፡ "ለምን?" ቢባል፥ ብርሃን ከጨለማ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከጣዖት ምንም ኅብረት ሊኖረው ስለማይችል ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እንደሚታየውና እንደሚሰማው፥ የመንፈስ ቅዱስ ሕላዌ ባጥለቀለቀው አነስተኛም ይሁን ትልቅ የጸሎት ጉባኤ ላይ ፥ ሰይጣናት "ተቃጠልን" እያሉ ሲጮኹና ከዚያ አካባቢ ለመራቅ እንዲፈቀድላቸው ሲጠይቁ ይደመጣሉ፡፡ አዎ፥ ድሮስ በመለኮታዊው እሳት ቅጥር ውስጥ ገብተው ሊመቻቸው? የማይሆን ነገር ነው፡፡

ስለዚህ እያንዳንዱ ክርስቲያን እንደ ማርያም በሄደበት ሁሉ ገና ሰላምታውን ሲያቀርብ አካባቢው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይጎበኝ ዘንድ የሚፈልግ ከሆነ፣ መጀመሪያ ማንነቱን ይወቅ፤ ክብሩን ይጠብቅ (የጌታ ማደሪያ መሆን እጅግ ታላቅ ክብር ነውና)፡፡ ቀጥሎም በተሰጠው ታላቅ የጌታ ስም ይጠቀም፡፡ የጌታ ስም በሚጠራበት በዚያ የጌታ ኃይል ይሠራል፡፡ የመንፈስ ቅዱስ እሳትን ተላብሶ መጓዝ መለኮታዊ ጥበቃን ያረጋግጣል፡፡ በዚህ ብቻ ግን አያቆምም የበረከት ምንጭም ያደርጋል፡፡ ይህንንም በማርያም ሕይወት አይተነዋል፡፡