እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

23.2 - ንስሐ ግባ

፪. ንስሐ ግባ

Holy Spirit n Confession"ንስሐ ግቡ... የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡" (የሐዋ.ሥራ 2፡38) በበዓለ-ኀምሣ ዕለት፥ ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ እንደተሞሉ፥ ጴጥሮስ ግልጽ እና ቀጥተኛ የሆነ ጠንከር ያለም ስብከት በማድረጉ የብዙ ሰዎች ልብ ተነካ፡፡ ስለዚህም በሰሙት ቃል መሠረት ለመኖር ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ለማወቅ ጥያቄን አቀረቡ፡፡ የጴጥሮስ መልስ አሁንም ቀጥተኛ ነበር፥ "ንስሐ ግቡ"፡፡ ንስሐ መግባት ማለት፥ ሕይወትን መቀየር ማለት ነው፤ ከሰፊው መንገድ ወጥቶ ወደ ጠባቡና ትክክለኛው መንገድ መግባት ማለት ነው፤ የልብና የአእምሮ ለውጥ ማካሄድ ማለት ነው፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ አገላለጽ ከተጠቀምን፥ ንስሐ ማለት፡- ፊተኛ ኑሮን በማሰብ፣ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰውነት አስወግዶ፥ በአእምሮ መንፈስ መታደስ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰውነት መልበስ ማለት ነው፡፡ (ኤፌ 4፡22-24 ተመልከት)፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳለው፥ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ለመቀበል መጠመቅና ንስሐ መግባት አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ "ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ" (የሐዋ.ሥራ 2፡38) ጴጥሮስ ይህን የተናገራቸው ሰዎች አስቀድመው ያልተጠመቁ (ክርስቲያኖች ያልሆኑ) አይሁዳውያን እንደነበሩ መዘንጋት የለብንም፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደ ክርስትና ለመግባት የግድ መጠመቅ ነበረባቸው፤ የቀድሞ ኃጢአታቸውንም መናዘዝ ነበረባቸው፡፡ እዚህ ላይ ጥምቀትና ንስሐ አብረው ይሄዳሉ፤ ምክንያቱም ተጠማቂዎቹ አዋቂዎች (ትልልቅ ሰዎች ወይም ለአቅመ አዳም የደረሱ ሰዎች) ስለነበሩ፥ ወይም ቢያንስ ቢያንስ ክፉና ደጉን ለይተው ማወቅ ይችሉ በነበሩበት የዕድሜ ክልል ውስጥ ስለነበሩ ነው፡፡ አስቀድመው ለተጠመቁ ክርስቲያኖች ግን የሚፈለግባቸው ንስሐ መግባት ብቻ ነው፤ ምክንያቱም ጥምቀት የማይደገምና በሕይወት ዘመናችን ሁሉ አንድ ጊዜ ብቻ ልንቀበለው የሚገባን ምስጢር ስለሆነ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን በተጠቀሰው ጥቅስ ላይ አንዳንድ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን የሚሰነዝሩ ሰዎች ስላሉ፥ ቢያንስ ሁለት ዓበይት ነጥቦችን ግልጽ አድርጎ ማቅረቡ ተገቢ ነው፡፡

የመጀመሪያው ነጥብ፥ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ለመቀበል መጠመቅ ያለባቸው ከዚያ በፊት ያልተጠመቁ አረማውያን እንጂ ክርስቲያኖች ይህን እንዲያደርጉ አልታዘዙም፡፡ እላይ እንደተገለጸው፥ ጴጥሮስ ይህን የተናገረው ለአይሁዳውያን እንጂ ለክርስቲያኖች አልነበረም፡፡ ስለዚህ ከኛ የሚጠበቅብን (ክርስቲያኖች ለሆንን) ሕይወታችንን በንስሐ መለወጥ ብቻ ነው፡፡ አረማውያን ግን ከአዳም የወረሱትን ኃጢአትም (Original Sin) ይሁን የገዛ ራሳቸውን ኃጢአት በጥምቀት ሊያስወግዱ ይችላሉ፡፡ የጴጥሮስ ንግግርም ጥምቀት ኃጢአትን የማስተሰረይ ኃይል እንዳለው ያመለክታል፡፡

ሁለተኛው ነጥብ፡- "በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ" (የሐዋ.ሥራ. 2፡38) የሚለውን የጴጥሮስን ንግግር በተሳሳተ መንገድ የሚተረጉሙትም አሉ፡፡ እንደነርሱ አባባል ጥምቀት የሚከናወነው የኢየሱስን ስም በመጥራት ብቻ ነው፡፡ ይህ ግን እጅግ የተሳሳተ አተረጓጎምና አስተሳሰብም ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ራሱ ስለ ጥምቀት ሲያስተምርና ይህንን ምስጢርም ሲመሰርት ያለው "እንግዲህ ወደ ዓለም ሕዝብ ሁሉ ሂዱ፤ በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው የእኔ ደቀ መዛሙርት አድርጉአቸው" ነው፡፡ (ማቴ 28፡19)

በሐዋርያት ሥራ ላይ "በኢየሱስ ስም መጠመቅ" የሚለው አባባል የተጠቀሰው "ከዮሐንስ ጥምቀት" ለይቶ ለማሳየት ነው እንጂ፥ የኢየሱስ ስም ብቻ የጥምቀት ፎርሙላ ነው ለማለት አይደለም፡፡ ጳውሎስ የኤፌሶን ሰዎች መንፈስ ቅዱስን መቀበል አለመቀበላቸውን ለማወቅ በጠየቃቸው ጊዜ የሰጡት መልስና የእርሱ ማብራሪያ ይህን ግልጽ ያደርገዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስን እንዳልተቀበሉ እንዲያውም ስለ መንፈስ ቅዱስ ሕላዌም እንደማያውቁ በነገሩት ጊዜ "ታዲያ ምን አይነት ጥምቀት ነው የተጠመቃችሁት?" አላቸው፡፡ እነርሱም በዮሐንስ ጥምቀት እንደተጠመቁ ነገሩት፡- (ኤፌ 19፡1-7 ተመልከት) ከንግግሩ ግልጽ የሚሆኑልን ነጥቦች አሉ፡፡ እነርሱም፡- በክርስቲያናዊ ጥምቀት መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጥ፥ በዮሐንስ ጥምቀት ግን ይህ እንደማይሆን እና ሁለቱ ጥምቀቶች የተለያዩ እንደሆኑ ነው፡፡

"በኢየሱስ ስም ተጠመቁ" የሚለውን አገላለጽ ከቅድስት ሥላሴ ሦስቱ አካላት ስም ማለትም ከአብ "ወልድ እና" መንፈስ ቅዱስ ስም ነጥለን "የኢየሱስ ስም ብቻ" በሚል ትርጉም የምንወስደው ከሆነ፥ "የዮሐንስ ጥምቀት" የሚለውንም አባባል እነኛ ሰዎች ሲጠመቁ በነርሱ ላይ የተጠራው "የዮሐንስ ስም" ነበር ማለታችንም ነው፡፡ ይህ ግን ስህተት ነው፡፡ ልክ በዮሐንስ ጥምቀት ላይ የዮሐንስ ስም ይጠራ እንዳልነበረው ሁሉ፥ በክርስቲያናዊ ጥምቀት ላይም የኢየሱስ ስም ብቻ አይጠራም፡፡ የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ስም ነው የሚጠራው፡፡ "የዮሐንስ ጥምቀት" የሚለው አገላለጽ ዮሐንስ ያካሂደው የነበረውን ጥምቀት ሲመለክት፥ "በኢየሱስ ስም መጠመቅ" የሚለው አገላለጽም በጌታ በኢየሱስ የተጀመረውን ጥምቀት ያመለክታል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን የዮሐንስ ስምም ይሁን የኢየሱስ ስም የጥምቀት ፎርሙላዎች ነበሩ ማለት አይደለም፡፡ የሁለቱ ስሞች የሚያመለክቱት በሁለቱም ይሰጡ የነበሩትን የተለያዩትን ሁለቱን ዓይነት ጥምቀቶች ለይቶ ለማሳየት ብቻ ነው እንጂ ሌላ ትርጉም የላቸውም፡፡

የኤፌሶን ሰዎች ክርስቲያኖች ስላልነበሩና ከዚያ በፊት ስለ ጌታ ኢየሱስ ጥምቀትም ይሁን ስለመንፈስ ቅዱስ እውቀት ስላልነበራቸው ሁሉንም "ሀ" ብሎ መጀመር ነበረባቸው፤ ስለዚህም በአብ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ ነበረባቸው፡፡ እንደተጠመቁ ወዲያውኑ ጳውሎስ እጁን ጭኖ ጸለየላቸው፡፡ በጥምቀታቸው መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፥ በጳውሎስ እጅ መጫንም የመንፈስ ቅዱስ ሙላትና ስጦታዎቹን ተቀበሉ፡፡

እኛ ግን የክርስትናን ጉዞ "ሀ" ብለን ጀምረናል - በጥምቀታችን፡፡ ዳግም መጠመቅ አያሻንም፡፡ ንስሐ ግን ያለጥርጥር መግባት ያስፈልገናል፡፡ መለኮታዊው እንግዳችንን በቆሸሸ ልብ ውስጥ ልናስተናግደው አንችልም፤ ልባችን መጥራት አለበት፤ የሚያጠራውም ንስሐ ነው፡፡ ንስሐ መንፈስ ቅዱስንና ስጦታዎቹን ለመቀበል ሁለተኛው ቅድመ ሁነታችን ነው፡፡

ከአባ ኤፍሬም ዓንዶም

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት