9. 1. እሳትን በእሳት

9. 1. እሳትን በእሳት

 

ሳይንስ እንደሚነግረን አንድ ቦታ ሕዋ (Vacuum) ካልሆነ በስተቀር የግድ በአየር የተሞላ ነው፡፡ ባዶ መስሎ የሚታየን ዕቃ ውስጥም እንኳ ቢሆን አየር አለ፡፡ ለምሳሌ፡- አንድ ብርጭቆ ወስደን ውሃ ብንሞላው፣ ውኃው አስቀድሞ በዚያ ብርጭቆ ውስጥ የነበረውን አየር ካስወገደ በኋላ ነው የአየሩን ቦታ ተክቶ የሚገባው፡፡ መልሰን ውኃውን ብናፈሰው ብርጭቆው ባዶውን አይቀርም፤ ተመልሶ በአየር ይሞላል፡፡ ምናልባት አየሩን ማየት ስለማንችል ባዶ መስሎ ይሰማን ይሆናል፡፡ ሌላ ምሳሌ እንውሰድ፣ እስከ አፉ ድረስ በውኃ በተሞላ ብርጭቆ ውስጥ ጠጠሮች ብንጨምርበት የጠጠሩን ይዞታ (Volume) ያህል ውኃው ወደ ውጪ ይፈሳል፡፡ ብርጭቆው ሙሉ ለሙሉ በጠጠሮች ቢሞላ፣ የዚያን ያህል ውኃው ይፈስና ቦታውን ለጠጠሮቹ ይለቃል፡፡ እንደገና ጠጠሮቹን አውጥተን ብንጥላቸውም ብርጭቆው ባዶውን አይቀርም፤ በአየር ይሞላል፡፡ ከዚህ የምንረዳው በግዙፉ ዓለም ውስጥ የቦታዎች መተካካት ሕግ ('Law of displacement) እንዳለ ነው፡፡ ይህም የተፈጥሮ ሕግ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ያልኩበት ምክንያት የሳይንስ ክፍል ለመስጠት ሳይሆን፣ ይህ የቦታዎች መተካካት ሕግም በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ የሚንጸባረቅ እውነታ መሆኑን ለመጠቆም ያህል ነው፡፡ በዚህ አቅጣጫ መጽሐፍ ቅዱሳችንን እና በመንፈሳዊ ሕይወት አመራር የታወቁትን የቤተ ክርስቲያን ታላላቅ ሰዎችን ጽሑፎች ስናነብ፣ ይህ የተጠቀሰው ሕግ መንፈሳዊ ሕይወትን በድል በመምራቱ በኩል የተዋጣለት ስልት መሆኑን ያስገነዝቡናል፡፡

 

እግዚአብሔር ለሕዝቡ የገባላቸውን አዲስ ቃል ኪዳን ሲገልጽ እንዲህ ብሎ ነበር፡- "... አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ፤ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ፡፡ መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፤ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ፡፡" (ሕዝ. 36፡26-27)

 

እዚህ ላይ ጌታ እግዚአብሔር በግልጽ እንደተናገረው፣ የማይታዘዘውን ትዕቢተኛ ልብ ከሕዝቡ ማስወገድ ብቻ ሳይሆን በእርሱ ቦታ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስን እንደሚተካላቸው ቃል ይገባል፡፡ ምክንያቱም ክፉውን ማስወገድ የድል ግማሽ መንገድ እንጂ ሙሉ ድል አይደለምና! እንደ ድንጋይ የደረቀውን የሕዝቡን ልብ አውጥቶ ቢተውው፣ በጎ ለማድረግ ኃይል ገና ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህም በደረቁ ልብ ምትክ ታዛዥ የሆነና እንደ ሥጋ የለሰለሰ አዲስ ልብ በአሮጌው ፈንታ ሊሰጣቸው ቃል ገባ፡፡ እውነተኛ ድልና ነፃነትም ይህ ነው፡፡ ከዓለማዊና ሥጋዊ እሳቶች መራቁ ብቻም ድል አይደለም፤ የነርሱ ተቃራኒ የሆነው መለኮታዊው እሳት የነርሱን ቦታ መቆጣጠር አለበት፡፡ አለዚያ የባሰ ከበፊቱ በበለጠ ሁኔታ ወደቀድሞዎቹ ጣዖታት መመለስ አይቀሬ ነው፡፡ ለመሆኑስ በግል ጥረት ብቻ፣ ያለ መለኮታዊው እሳት ድጋፍ ከፍጥረታውያን እሳቶች እንዴት ተደርጎ ነው መራቅ የሚቻለው? ይህ የማይታሰብ ነው! ምክንያቱም ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና "ድል የምትነሣው በመንፈሴ እንጂ በአንተ ኃይልና ብርታት አይደለም" (ዘካ. 4፡6)፡፡ ደረቁና ትዕቢተኛው ልብ ተወግዶ በአዲስ ልብ ከተተካ በኋላና፣ አዲስ የአምላክ መንፈስ ሁለንተናን ከተቆጣጠረ በኋላ ነው የአምላክን ትእዛዝ ማክበር የሚቻለው፡፡

 

ጌታ ኢየሱስም የቦታዎች መወራረስን ሕግ ሲጠቀምበት እናያለን፡፡ ሸክማቸው የከበደባቸው ተከታዮቹ ወደ እርሱ እንዲመጡ ይጋብዝና፣ በከባዱ ሸክማቸው ፈንታ ቀላልና ልዝብ የሆነውን የእርሱን ቀንበር እንዲሸከሙ ይጠይቃቸዋል፡፡ "እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ፡፡ ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና፡፡" (ማቴ. 11፡28-30) ጌታ እንደሚያስተምረን የመንፈሳዊ ዕረፍት ሕግ፣ ከባድ ሸክምን ወደ እርሱ በማምጣት ብቻ ሳይሆን በእርሱ ፈንታ የጌታን ቀንበር በመሸከም የሚከናወን የተሟላ ጉዞ ነው፡፡ የከበደብንን ሸክም ሁሉ ወደ ጌታ ማምጣት ትክክልና ተገቢ ነው፡፡ ሆኖም በሸክም የደቀቀና የጎበጠው ትከሻ ነፃ ወጣሁ ብሎ የሚዝናናበት ጊዜ ሊኖረው አይተልም አይገባምም፡፡ ከበፊቱ ችግር ከተላቀቀ በኋላ፣ ወዲያውኑ የተለየ ሸክምን መሸከም ያስፈልገዋል፡፡ የተሟላ ነፃነትንና ዕረፍትን የሚያገኘውም በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ አዲሱ የጌታ ቀንበር ግን ጨቋኝ ሳይሆን ነፃ አውጪና ዕረፍት ሰጪ ነው፡፡

በማቴ. 12፡43-45 እና ሉቃ. 11፡24-26 ላይ የምናነበው የርኩስ መንፈስ ወደ ሰው ተመልሶ የመግባት ሁኔታም የሚያሳስበን የቦታዎች መተካካት ሕግን ነው፡፡ በነዚህ ተመሳሳይ መጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አማካይነት ጌታ ኢየሱስ እንደሚያስተምረን፣ አስቀድሞ በርኩስ መንፈስ ተይዛ የነበረች ነፍስ፣ ርኩስ መንፈስ ከተወገደላት በኋላም ቢሆን ሙሉ ሰላም የላትም፡፡ ርኩሱ መንፈስ ሌላ ማረፊያ ቦታ ሲያጣ፣ ሰባት እጥፍ ተጠንክሮ ወደ ቀድሞ ማደሪያው ሊመለስ ይፈልጋል፡፡ የቀድሞ ቦታው ነድቶና ጸድቆ ቢቆይም ቅሉ ባዶ ከመሆኑ የተነሣ ለበለጠ ስቃይ ይዳረጋል፡፡ ርኩሱ መንፈስ "በዚያን ጊዜም፡- ‹ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ› ይላል፤ ቢመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል፡፡" (ማቴ. 12፡44) "ባዶ ሆኖ፣ ተጠርጎ እና አጊጦ" ቁልፍ ቃላት ናቸው፡፡ የዚያች ነፍስ ኋለኛና የከፋ ዕጣም ባዶ ሆኖ የመቆየቷ ውጤት ነው፡፡ በርግጥ ከእስራቷ ተፈትታ ነፃ ወጥታለች፤ ነፃ በመውጣቷ የተነሣም አጊጣና አምራ ትገኛለች፤ ቢሆንም ቅሉ ባዶ ናት፡፡

አንድ እንግዳን ለመቀበል እንደተዘጋጀ ያማረ ቤት ተጋጊጣለች፤ ስለዚህም ቀድሞ የመጣ እንግዳ እርሷን መውሰዱ አይቀርም፡፡ ያች ነፍስ እንዳማረባት እስከዘለቄታው ልትቀጥል ካሻች፣ ነፃ እንደወጣች ወዲያውኑ በፊት ይገዛት የነበረው ርኩስ መንፈስ ተቃራኒ የሆነውን ቅዱስ የእግዚአብሔር መንፈስ ተቀብላ ማስተናገድና በእርሱም ሙሉ ለሙሉ መሞላት ያስፈልጋታል፡፡ በዚያ ባማረና ባጌጠ ስፍራ ላይ መንፈስ ቅዱስ ሙሉ ጌትነቱን ሲረከብ፣ የበፊቱ አስጨናቂዋ ሰባት እጥፍ ሳይሆን ሰባ ጊዜ ሰባት እጥፍም ተጠናክሮ፣ አጋንንትን ሁሉ ከአጥናፍ ከተራራ አሰባስቦም ቢመጣ ሊደፍራትና ተመልሶ ሊሰፍርባት አይችልም፡፡ ምክንያቱም አሁን ባዶ አይደለችም፡፡ ርኩሱ መንፈስ ለአንዴና ለዘለቄታዊ ከዚያች ነፍስ ተጠራርጎ በመውጣቱ የተነሣ፣ ምንም እንኳ በተደጋጋሚ ወደ እርሷ ተመልሶ ለመግባት ቢሻና ቢሞክርም ሊሳካለት አይችልም፡፡ በውጭ ሊዞር፣ ሊሽከረከር፣ ሊፈትንና ሊያስፈራራ ይሞክር ይሆናል፤ በዚያች ነፍስ ውስጥ የሚኖረው ግን መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ስለዚህም ነው በጥምቀታችን ጊዜ ከርኩስ መንፈስ ግዛት ነፃ እንደወጣን ወዲያውኑ መንፈስ ቅዱስን እንድንቀበል ጸሎት የሚደረግልንና በመንፈስ ቅዱስም የምንሞላው፡፡ ያኔ፣ ርኩሱ መንፈስ ከእኛ እንዲወገድ ተገስጾ ከተባረረ በኋላ፣ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ጸሎት ባይደረግልን ኖሮ፣ ነፍሳችን ነጽታና አጊጣ በተገኘች ነበር፤ ግን ባዶዋን በቀረች ነበር፡፡ ስለዚህም ያ ወደረኛ ሰባት እጥፍ አጋንንትን ጠርቶ ተመልሶ በኛ ላይ ባደረ ነበር፡፡ እኛም ከበፊቱ የኋለኛው በከፋብን ነበር፡፡ እግዚአብሔር ይመስገንና በዚህ ሁኔታ ላይ አልተተውንም፤ ከጨለማው ግዛት ነፃ መውጣት ብቻ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስንም ተቀብለናል፡፡

እግዚአብሔር ሙሉ ድልን እንጂ ግማሽ ድልን አላጎናጸፈንም፤ የጳውሎስ አባባል ይህንን የሚገልጽና ደስ የሚያሰኝም ነው፡፡ እግዚአብሔር አብ በእኛ ውስጥ ያከናወነውን ታላቅ ሥራ ሲገልጽ ይህን አለ፡- "እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፣ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘነበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን" (ቆላ. 1፡ 13-14) እግዚአብሔር ከዲያብሎስ ግዛት ነፃ አወጣን፤ ቀጥሎም ወደ ተወደደው ልጁ ወደ ጌታ ኢየሱስ መንግሥትም እንድንገባ አደረገን፤ ስሙ ይባረክ! እኛም በዚህ ስልት የፍጥረታዊ እሳት ኃይላትን ከእኛ እያራቅን፣ በመለኮታዊው እሳት መቀጣጠል ይገባናል፡፡ የተሟላና አስተማማኝ የሆነ ድል ማግኘት የምንችለውም በዚህ መንገድ ነው፡፡

 

ቅዱስ ጳውሎስም ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው የመጀመሪያ መልእክቱ ላይ አዲስ ሊጥና አሮጌ እርሾ የሚል ምሳሌን ይጠቀማል፡፡

 

"እንግዲህ የምትታበዩት በከንቱ ነው፤ ትንሽ እርሾ ሊጡን ሁሉ እንደሚያቦካው ታውቁ የለምን? አሁን እንደሆናችሁት ሁሉ እርሾ እንደሌለበት እንደ አዲስ ሊጥ እንድትሆኑ፣ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ፤ ምክንያቱም የፋሲካችን በግ የሆነው ክርስቶስ ስለ እኛ ተሠውቶአል፤ ስለዚህ ዓመፅና ክፋት በሞላበት በአሮጌ እርሾ ሳይሆን፣ እርሾ በሌለበት ቅንነትና እውነት በሞላበት ቂጣ በዓላችንን እናክብር፡፡ (1ቆሮ. 5፡6-8)

 

አሮጌው እርሾ የዓመፅ የክፋትና የግፍ ተምሳሌት ሲሆን፣ አዲሱ ሊጥ ግን ከአሮጌው እርሾ ነፃ የሆነና የቅንነትና የእውነት ምሳሌ ነው፡፡ ትንሽ እርሾ ብዙ ሊጥን ሊያቦካ እንደሚችለው ሁሉ፣ ትንሽ እሳትም ነፍስንና ሥጋን ወደ ገሃነም እስከመጣል ያደርሳል፡፡ የትንሽ እርሾና የትንሹ እሳት ኃይል ራሱን መሰወር ይችላል፡፡ የሚያስከትለው ውጤት ግን ጥቂት እንደማይሆን ቀስ በቀስ ይገለጻል፡፡ አሁን ባነበብነው ጥቅስ ውስጥ ጳውሎስ አሮጌውን እርሾ እንድናስወግድ ብቻ ሳይሆን አዲሱን ሊጥ እንድንሆንም ይመክረናል፡፡

ዓመፅና ክፋት በሞላበት አሮጌ ማንነት ሳይሆን እውነትና ቅንነትን በተሞላ አዲስና የተለወጠ ማንነት ፋሲካችንን (ከአሮጌው ሕይወት ወደ አዲሱ ሕይወት መሸጋገራችንን) እንድናከብር ይነግረናል፡፡ በሮሜ መልእክቱም ላይ፣ በሌላ አነጋገር ይህንኑ አሮጌውን አስወግዶ አዲሱን የመልበስ ሕግ ሲጠቀምበት እናያለን፡፡ "ስለዚህ የጨለማን ሥራ አውልቀን ጥለን የብርሃንን የጦር መሣሪያ እንልበስ፡፡ በቀን ብርሃን እንደሚኖሩ ሰዎች በተገቢው አኳኋን እንመላለስ፤ ዘፈንንና ስካርን፣ ዝሙትንና መዳራትን፣ ጭቅጭቅንና ምቀኝነትን እናስወግድ፡፡ ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት እንጂ የሥጋችሁን ፍላጎት ለማርካት አታስቡ፡፡" (ሮሜ. 13፡ 12-14)

 

በግልጽ እንደሚታየው ጳውሎስ የመንፈሳዊ ሕይወት የድል ጉዞን የሚያቀርበው በሁለትዮሽ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የመጀመሪያው፣ መጥፎውን፣ ክፉውን፣ ርኩሱንና የጥፋት መሣሪያ የሆነውን ነገር ሁሉ ማስወገድ ሲሆን፣ ቀጥሎ የሚመጣው ሁለተኛውና አስፈላጊው እንቅስቃሴም በዚያ በተወገደው የማይፈለግ ነገር ምትክ ጠቃሚና መልካም የሆነ እግዚአብሔር የሚያስከብር ተግባርም ይሁን ልማድን ማዳበር ነው፡፡

 

ይህ መንፈሳዊ ስልት በጳውሎስ መልእክቶች ውስጥ አሁንም አሁንም ሲጠቀስ ይታያል፡፡ አስቀድመን ባየናቸው የጳውሎስ መልእክቶች ውስጥ አሮጌው እርሾ በአዲሱ ሊጥ መተካት፣ የጨለማን ሥራ አውልቆ የብርሃንን ጦር መሣሪያ መልበስ፣ የሥጋን ፍላጎት ለማርካት ከማሰብ ነፃ ወጥቶ ክርስቶስ ኢየሱስን መልበስ የሁለንተናዊ እድገት መስመሮች እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በሌላ ቦታም አሁንም ጳውሎስ ይህንን ስልት በሌላ አገላለጽ ሲጠቀምበት "አሮጌውን ሰውነት አስወግዶ አዲሱን ሰውነት መልበስ" የሚል አባባል ይጠቀማል፡፡

 

"ስለዚህ አታልሎ ወደ ኃጢአት በሚመራ ምኞት የተበላሸውን፣ አስቀድሞ ትኖሩበት የነበረውን፣ አሮጌውን ሰውነት አስወግዱ፡፡ አእምሮአችሁም በመንፈስ ይታደስ፡፡ በእውነተኛ ጽድቅና ቅድስና እግዚአብሔርን ለመምሰል የተፈጠረውን አዲሱን ሰውነት ልበሱ፡፡" (ኤፌ. 4፡22-24፤ ቆላ. 3፡8-10) በአጭር አገላለጽ "አሮጌውን ሰውነት አስወግዱ፤ በመንፈስ ታደሱ፤ አዲሱን ሰውነት ልበሱ" አሮጌውን ሰውነት በሚል ጥረት ማስወገድ እንደማይቻል እውቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ የሚያሻን፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ስንታደስ ግን አሮጌውን ሰውነት ማስወገድ ብቻ ሳይሆን አዲሱን ሰውነትም መልበስ እንችላለን፡፡ ጳውሎስም አሮጌውን ሰውነት በማስወገድና አዲሱን ሰውነት በመልበስ መካከል በመንፈስ ቅዱስ መታደስ እንደሚያስፈልግ የጠቆመው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡

 

ከኤፌ 4 ሳንወጣ ከቁ. 25-32 ያሉትን የሐዋርያውን ምክሮች ስናነብ፣ በአሮጌው ፋንታ አዲሱን የመልበስ ሕግን በስፋት ተጠቅሶ እናያለን፡፡ "ውሸት አትናገሩ" ብሎ አያቆምም፤ "እርስ በእርሳችን እውነት እንናገር" የሚል ምክርንም ያስከትላል (ቁ.25)፡፡ ቀጥሎም "ይሰርቅ የነበረ ከእንግዲህ ወዲያ አይስረቅ፤ ይልቅስ ለችግረኞች የሚያካፍለው ገንዘብ እንዲኖረው በገዛ እጆቹ መልካም ነገርን ይሥራ" ይላል (ቁ.28)

 

ውሸት አለመናገር መልካም ነው፤ ነገር ግን ያች መዋሸት ለምዳ የነበረችው አንደበት እውነት መናገር እስካልጀመረች ድረስ ሙሉ ለውጥ አግኝታለች ለማለተ አያስደፍርም፡፡ አለመስረቅም እጅግ መልካም ነገር ነው፡፡ ነገር ግን የእጅ አመል የነበረው ሰው እጅ እግሩን አጣምሮ "ስርቆት አቁሜአለሁና ከአሁን በኋላ ችግር የለም" ሊል አይችልም፡፡ አስቀድመው ለስርቆት የዋሉ እጆቹን በመልካም ሥራ እንዲጠመዱ ካላደረገ፣ ነግ ተነገ-ወዲያ የሚበላው ሲያጣ ወደ ባሰ ስርቆት ሊሰማራ ይችላል፡፡ በእርግጥ የተለወጠ ከሆነ በስርቆቱ መቃብር ላይ የመልካም ሥራ ችግኝን መትከል ይኖርበታል፡፡

 

"ከቶ ከአፋችሁ ክፉ ቃል አይውጣ፤ ነገር ግን ለሚሰሙት ጸጋን የሚሰጥና ለማነጽ የሚጠቅም፣ ለሰዎችም አስፈላጊ የሆነውን ቃል ተናገሩ" (ቁ.29) በክፉ ቃላት ፈንታ አፋችን በጸጋ ቃል ካልተሞላ በስተቀር ክፉ ቃላት ከመናገር ተቆጥበናል የሚያሰኝ ደረጃ ላይ እንዳልደረሱን ግልጽ ነው፡፡ እዚህም ላይ በአሮጌው ፋንታ አዲሱን የመተካት ሕግ ይንጸባረቃል፡፡

 

ሰዎችን የሚጐዳ ነገር አለመናገር ብቻ ሳይሆን ከዚያ አልፈን ሰዎችን የሚጠቅም ቃልን መናገር መቻል አለብን፡፡ እቅዳችንም እዚያ ለመድረስ መሆን አለበት፡፡

 

"መራራነት፣ ንዴት፣ ቁጣ፣ ጩኸት፣ ስድብና ማናቸውም ዓይነት ክፋት ሁሉ ከእናንተ ወዲያ ይራቅ፡፡ ይልቅስ እርስ በርሳችሁ ደጎችና አዛኞች ሁኑ፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ፣ እናንተም እርስ በርሳችሁ ይቅር ተባባሉ" (ቁ. 31-32)

 

በዚህ ጥቅስ ውስጥ እንደሚታየው መጀመሪያ ሥጋዊ እሳቶችን ማስወገድ ወይም ማራቅ፣ ቀጥሎም በነርሱ ፈንታ የመለኮታዊው እሳት ገጽታዎች የሆኑትን መልካም ልምዶች ማዳበር አስፈላጊ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ሁለቱ እንቅስቃሴዎች የሚነጣጠሉ ነገሮች ሳይሆኑ ተከታትለው የሚመጡና ወደ አንድ ግብ የሚያደርሱ ምዕራፎች ናቸው፡፡ ሁለቱንም እንቅስቃሴዎች አስተባብሮ በአንድነት የሚያካሂዳቸው መንፈስ ቅዱስ እንኳ ቢሆንም፣ በኛ በኩል ግን መሻት እና ውሳኔ ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ በሮም መልእክቱ ላይ ጳውሎስ እንዳለው "አስቀድሞ የሰውነት ክፍሎቻችሁን የርኩስትና የዓመፅ አገልጋዮች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ ሁሉ፣ እንዲሁም አሁን የሰውነት ክፍሎቻችሁ እንዲቀደሱ የጽድቅ አገልጋዮች አድርጋችሁ አቅርቡ፡፡" (ሮሜ. 6፡19) መንፈሳዊ ነፃነት፣ ሽግግርና እድገትን ለማግኘት፣ የኛ ፍቃድ ምን ያህል ወሳኝነት እንዳለው ከጳውሎስ አባባል መረዳት እንችላለን፡፡

ፍጥረታዊ እሳቶች እንዲገዙን አስቀድመን እንደፈቀድንላቸው ሁሉ፣ የሕይወት ለውጥን ስንሻ፣ አስቀድመን ለእነዚህ እሳቶች የእምቢተኛነት ድምፅን ለጥቆም ለመለኮታዊው እሳት ታዛዥነትን ልንሰጥ እንጠየቃለን፡፡ ለፍጥረታዊው እሳት እምቢተኛነትን ሳንሰጥ፣ ለመለኮታዊው እሳት ታዛዥነትን ልናሳይ አንችልም፡፡ ለፍጥረታዊው እሳት እምቢተኛነትን በምንሰጥበት ወቅት፣ ለመለኮታዊው እሳት እጃችንን መስጠት ጀምረናል ማለት ነው፤ ነገር ግን ጀመርን እንጂ አልጨረስንም! ለመለኮታዊው እሳት እጅን የመስጠት ሂደት የአንድ አፍታ ትእይንት ብቻ ሳይሆን በቀጣይነት እስከ ፍጻሜ ድረስ በየቀኑ የሚደረግ ራስን የመካድ ጉዞ ነውና፡፡ ጌታ የሚለው፡- "ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ በየቀኑም መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ" ነው፡፡ (ሉቃ. 9፡23፤ ማቴ. 16፡24፤ ማር. 8፡34)፡፡

9. 2. እሳትን በእሳት በሚል ርእስ ይቀጥላል