8.2 ገሃነመ - እሳት

8.2 ገሃነመ - እሳት

ዮሐንስ በራዕዩ እንደተመለከተው፣ ቅድስቲቷ ከተማ አዲሲቷና ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ዘወትር በብርሃን የተሞላት ከመሆኗ የተነሣ ፀሐይም ይሁን ጨረቃ ወይም ሌላ መብራት አያስፈልጓትም፤ ምክንያቱም ጌታ እግዚአብሔር በክብሩ ስለሚያበራት ነው፡፡ "ለከተማይቱም የእግዚአሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለሆነ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያሩላት አያስፈልጓትም ነበር፡፡ አሕዛብም በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፣ የምድርም ነገሥታት ክብራቸውን ወደ እርስዋ ያመጣሉ፤ በዚያም ሌሊት ስለሌለ ደጆችዋ በቀን ከቶ አይዘጉም፡፡" (ራዕይ 21፡23-27) እንዲሁም፡- "ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይሆንም፣ ጌታ አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና፣ የመብራት ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ለዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ይነግሣሉ፡፡" (ራዕይ 22፡5) በመንግሥተ ሰማይ ውስጥ የጌታ ብርሃን ዘወትር ስላለ ሌላ ብርሃን አያስፈልግም፤ በገሃነመ እሳት ግን የእሳት ባሕር ሲነድ እና ሲያነድ ይኖራል ብርሃን ግን የለም፤ ዘላለም ድቅድቅ ጨለማ ነው፡፡ ምክንያቱም በዚያ የሚገኙ ነፍሳት የብርሃናትን አምላክ ለአንዴና ለዘለዓለም ከሕይወታቸው፣ ሊጠገን በማይቻል መንገድ ስላስወጡትና ለዘለዓለም ከእርሱ ተነጥለው ስለሚኖሩ (በትክክለኛ አገላለጽ ለዘለዓለም ስለሚሞቱ) ነው፡፡ ይሰውረን! የጨለማን ሥራ በመሥራት በጨለማ ውስጥ የተመላለሰና በዚያው የመሸበት ወደ ዘለዓለማዊ ጨለማ ይገባል፡፡ የብርሃንን ሥራ እየሠራ ብርሃንን ለብሶ በብርሃን የተመላለሰም ማምሻውን ወደ ዘለዓለማዊ ብርሃን ይሻገራል እንጂ አይጨልምበትም፡፡ ለዚህም አስቀድሞ ከእውነተኛው ብርሃን ብርሃንን መቀበል ይኖርበታል፤ ያ ብርሃንም ጌታ ኢየሱስ ነው፡፡ "በእርሱ ሕይወት ነበረች፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች፡፡ ብርሃንም በጨለማ ይበራል፣ ጨለማም አላሸነፈውም፡፡ ... ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር" የተባለለት ለእርሱ ነው (ዮሐ. 1፡4፣ 5፣ 9) እርሱ ራሱም ስለራሱ "እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም" ብሎ መስክሮ ነበር (ዮሐ. 8፡12)፡፡ ዳዊትም ይህን የብርሃን ምስጢር ከብዙ ዘመናት በፊት አውቆ ኖሮ "የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና፣ በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን" ብሎ ዘምሮ ነበር (መዝ. 36፡9) ይህም የኛ መዝሙርና ጸሎት ይሁን፤ የጨለማን ሥራ ሁሉ አውልቀንም ብርሃንን (ጌታን) እንልበስ፤ በብርሃንም (በጌታ) እንመላለስ፡፡ ያኔ ጨለማ እያስፈራንም ገሃነምም አያሰጋንም፡፡

 

በገሃነም ውስጥ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይኖራል (ማቴ. 13፡ 42፡ 50፤ 24፡51፤ ሉቃ. 13፡28)፡፡ እግዚአብሔርን የተቃረኑና ያልታዘዙት ዘለዓለማዊ ጥፋትና ቅጣት እዚያ ይቆያቸዋል (2ተሰ. 1፡9-10 ተመልከት)፡፡ በገሃነመ እሳት ውስጥ "ተቃዋሚዎችን ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት አለ" (ዕብ. 10፡27 ተመልከት)፡፡

 

የይሁዳ መልእክት ሰዶምና ገሞራ የዘለዓለማዊው እሳት ምሳሌዎች እንደሆኑ ይናገራል፡፡ "በዚሁ ዓይነት ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸው ያሉ ከተሞችም የዝሙት ኃጢአት ፈጸሙ፤ የተፈጥሮ ሥርዓትንም በመለወጥ በግብረሥጋ ተገናኙ፡፡ ስለዚህ እነርሱ በዘለዓለም እሳት ለሚቀጡት ምሳሌ ሆነዋል፡፡" (ይሁዳ 7)

 

በዮሐንስ ራዕይ ውስጥ የገሃነመ እሳት ምንነት በአስፈሪ መልኩ ተስሎ ይታያል፡፡ እንደ ባለ ራዕዩ አገላለጽ ገሃነም፣ የእሳትና ዲን ባሕር፣ የዘለዓለም ስቃይ ስፍራ፣ ሁለተኛ ሞት፣ የዲያብሎስ የአሳቹ አውሬና የሐሰተኛው ነቢይ መጣያና፣ የዓመፀኞች ሁሉ ዕጣ ክፍል ነው፡፡ በሚከተሉት ሦስት ጥቅሶች ውስጥ ይህ ገጽታ በግልጽ ተስሎ ይታያል፡፡

 

"... ነገር ግን እሳት ከሰማይ ወርዶ በማቃጠል ደመሰሳቸው፡፡ ያሳታቸው ዲያብሎስ፣ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት በዲን በሚቃጠል እሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ፤ ሌሊትና ቀን ለዘለዓለም ይሠቃያሉ፡፡" (ራዕይ 20፡9-10) "ሞትና ሲኦልም ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ፤ ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው፤ ስሙ በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘ ሁሉ ወደ እሳት ባሕር ተጣለ፡፡" (ራዕይ 20፡ 14-15)

 

"ነገር ግን ፈሪዎች፣ እምነተ ቢሶች፣ ርኩሶች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ አመንዝሮች፣ አስማተኞች፣ ጣዓት አምላኪዎች፣ ውሸታሞች ሁሉ ዕጣ ክፍላቸው በዲን በሚቃጠለው በእሳት ባሕር ውስጥ ይሆናል፤ ይህም ሁለተኛው ሞት ነው፡፡" (ራዕይ 21፡8)

 

እስከ አሁን የተመለከትናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የገሃነሙ እሳትን ምንነትና ሕላዌ ሊያሳዩን ይችላሉ፡፡ ሐሳባዊ እንጂ ተጨባጭ ላልሆነ፣ የአእምሮ ፈጠራ እንጂ ህልውና ለሌለው ነገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ያህል በስፋትና በጥንካሬ እንደማይናገር የታወቀ ነገር ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ምን ያህል ጊዜ ስለ ገሃነም ፍርድ ወይም ስለ ዘለዓለማዊ እሳት ቅጣት እንደተናገረ አዲስ ኪዳን ይመሰክራል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ላልሆነና ለማይሆን ነገር ጊዜውን እንደማያባክን ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶን እያለ እንኳ አረማመዳችን ኃላፊነት የጎደለው ሆኖ ይታያል፡፡ የአምላክን ሆነ የማንኛውንም መንፈሳዊና መልእልተ ባህሪያዊ ነገር ህልውና ስለሚክዱት ግዙፋውያን (ማቴሪያሊስቶች) ትተን፣ በክርስትና ስም ስለሚጠሩት አማኞች እንኳ ብንናገር፣ የገሃነመ እሳትን ህልውና የሚክዱ አያሌ ክርስቲያኖች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ የብዙዎቹ መከራከሪያ ነጥብ በአምላክ ፍቅርና ምሕረት ላይ የተመረኮዘ ይመስላል፡፡ ፍቅር የሆነው አምላክ ፍቅሩና ምሕረቱ ዘለዓለማዊና ወሰን የለሽ ከመሆኑ የተነሣ፣ ገሃነመ እሳትን የመሰለ የቅጣት ቦታ ሊያዘጋጅ ወይም ይህ ቦታ እንዲኖር ሊፈቅድ አይቻለውም የሚል ምክንያትንም ያቀርባሉ፡፡ እውነቱ ግን ገሃነመ እሳት ምንም ይምሰል ምን፣ የአምላክ ሠራና ፍጥረት ሳይሆን፣ የኃጢአትና የአልታዘዝ ባይነት ውጤት ነው፡፡ ይህን የስቃይ ቦታ የፈጠረ፣ የወደቁ መላእክትና የሰው ኃጢአት እንጂ አምላክስ የፈጠረው የሠራው ሁሉ መልካምና እጅግ ያማረ ነገር ብቻ ነው (ዘፍጥ. 1፡4፣ 10፣ 13፣ 18፣ 21፣ 25፣ 31 እይ)፡፡

 

የጌታን ጽድቅ ሥራ እያዩ ፍጡራንም እንኳ ሳይቀሩ "ሁሉን ነገር በመልካም አደረገ" ብለው ስለርሱ መስክረዋል (ማር. 7፡37) ስለዚህ ከእርሱ እጅ ክፉ ይወጣል ብሎ ሊያስብ የሚችል ማንም ሊኖር አይችልም፡፡ ይሁን እንጂ ጌታ የሰውን ነፃነት በፍፁም አይቀማም፡፡ ሰው በፍቃዱ የዘለዓለም ሕይወትን ወይም ሞትን መምረጥና በዚያ መሠረት መኖር ይችላል፡፡ ጌታም ያለኛ ፍቃድ በግድ ከገሃነም ደጆች መንጭቆ አያወጣንም፤ በፍቃዳችን እርዳታውን  ሽተን እጃችንን ከዘረጋንለት ግን ሳይዘገይ ሊረዳን ይመጣል፡፡ የመዳን ተስፋችንም በእርሱና ለእርሱ መኖራችን ነው፡፡ በእርግጥም እንደተባለው "እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም" (ሮሜ. 8፡1)፡፡ ያች "አሁን"ም እያንዳንዷ አሁን የምናሳልፋት ሴኮንድ ናት፡፡ "አሁን" ተብላ እየተጠራች ሳለች አሁኑኑ በዚህች ሴኮንድ ላይ ቆን ከክርስቶስ ጋር ያለንን ንብረት ልንመዝን ይገባናል፡፡ በትናንትናው ጽድቃችን ወይም "ነገ እቀደሳለሁ" በሚል ያልተጨበጠ ተስፋችን ላይ ልንደገፍ አንችልም፡፡ ሁለቱም የኛ አይደሉምና፡፡ "አሁን" ግን ለእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ (መዝ. 119፡ 126፤ መዝ. 12፡5) ሲሆን፣ ለእኛ ደግሞ "የተወደደ ሰዓት እና የመዳን ጊዜ (ቀን) ነው" (2 ቆሮ 6፡2 ተመልከት)፡፡

 

መቼም የተፈጠርነው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ ነው፡፡ እዚያ ለመድረስም ትክክለኛውን መንገድና አቅጣጫ መያዙ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ የድሬዳዋን መንገድ ይዞ ጎንደር ለመድረስ የሚሻ ተጓዥ፣ አንድም ጂኦግራፊያዊ እውቀት የሌለው፣ አልያም አእምሮውን የሳተ ሰው መሆን አለበት፡፡ እንደዚሁም በሥጋዊ፣ ዓለማዊና ሰይጣናዊ እሳቶች እየጋየ የአምላካዊ ክብር ብርሃንን ሊጎናጸፍ የሚሻ ሰውም ወዴት በመጓዝ ላይ እንዳለ የማያውቅ መንገደኛ ነው፡፡ የምንይዛቸው መንገዶችም ሆኑ በኛ ውስጥ የሚነዱት እሳቶች ያለ ምንም ስሕተት ወደ ፍጻሜአቸው ያደርሱናል፡፡ ምርጫውን የምናደርገው እኛው ራሳችን ስንሆን፣ ለምርጫው "ነገ፣ ከነገ ወዲያ" የለውም፡፡ እያንዳንዷ ሴኮንድም በያዝነው መንገድ ለመቀጠልም ይሁን መንገዳችንን ለመቀየር የምታስችለን የውሳኔ ጊዜ ናት፡፡ በዚህች "አሁን" ወይም "አፍታ" ውስጥ የመዳንንም ሆነ የመጥፋትን መንገድ መምረጥ እንችላለን፡፡ ያ በጌታ ኢየሱስ ቀኝ ተሰቅሎ የነበረው ወንበዴ የስርቆት እሳት ለረጅም ጊዜ ሲነድበት የኖረ ቀማኛ ነበር፡፡

 

በዚያች የምድራዊ ሕይወቱ መደምደሚያ አስፈሪ ሰዓት ላይ እንደደረሰ ግን መንገዱን ቀየረ፡፡ ከመድኅኑ ጋርም ታረቀ፡፡ ዘመኑን ሁሉ ሲሰርቅ ኖሮ በመጨረሻ ላይም እጅግ ከፍተኛ የሆነ ስርቆትን ፈፀመ፡፡ በፊት የሰው ንብረት ይሠርቅ ነበር፤ በዚያች ወሳኝ ወቅት ግን በአንዲት ንስሐ የእግዚአብሔርን መንግሥት ሰረቀ (ሉቃ. 23፡ 40-43) አሰራረቅ ይሏል እንዲህ ነው! የሌላኛው ወንበዴ አፈጻጸም ግና ያማረ አልነበረም፤ ምክንያቱም ያምንም ንስሐ በዚያው በመቀጠሉ ነው፡፡ በሞት አፋፍ ላይ ለነበረው ወንበዴ የመጨረሻዋ ደቂቃ ለደኅንነቱ ከጠቀመችው፣ ለኛስ እያንዳንዷ ሰዓትና ደቂቃ ለምን አትጠቅመንም? ነገር ግን "ዛሬ ድምፁን ስትሰሙ፣ ልባችሁን እልኸኛ አታድርጉ" (ዕብ. 4፡7) የሚለውን ማስጠንቀቂያ መዘንጋት የለብንም፡፡

 

የፍጥረታዊ እሳት የመጨረሻ መድረሻው ገሃነመ እሳት እንደሆነው ሁሉ፣ የመለኮታዊው እሳት መድረሻም መንግሥተ ሰማይ ነው፡፡ በምድር ላይ ሳለን ከአንዱ እሳት ወደ ሌላኛው መሸጋገር እንችላለን፤ በወዲያኛው ዓለም ግን ሽግግር ብሎ ነገር የለም፡፡ ከገሃነም ወደ መንግሠተ ሰማይ ወይም በተቃራኒው አቅጣጫ የሚደረግ ልውውጥ የለም፡፡ እዚህ ላይ የንስሐ ቦታን ከገሃነም ጋር አደባልቀን እንዳናየው መጠንቀቅ ያሻናል፡፡ የንስሐ ቦታ የመጥሪያና የመንዳት ስፍራ እንጂ ዘለዓለማዊ ቦታ አይደለምና፡፡ በንስሐ ቦታ የሚገኙ ነፍሳት በእርግጥም አንድ ቀን ወደ መንግሥተ ሰማይ ይገባሉ፤ ቢሆንም የንስሐ ቦታ ውስጥ እስካሉ ድረስ እጅግ ከባድና አስጨናቂ ጊዜን እንደሚያሳልፉ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡

 

የገሃነመ እሳትን አስፈሪነት በማየት ከዚያ ለማምለጥ ሳይሆን፣ የአምላክ ፍቅር ግድ እያለን ቅዱስ ሕይወትን ልንኖር ይገባናል፡፡ የመጀመሪያው ምክንያትም ቢሆን በቅድስና እንድንኖር ከረዳን የሚከፋ አይደለም፤ ፍፁም ፍቅር ካለን ግን ፍርሃታችንን ያስወግድልናል፡፡ የተፈጠርነው ለመንግሥተ ሰማይ ክብር ሆኖ ሳለ፣ አረማመዳችን ግና ወደ ገሃነም የሚወስድ ከሆነ መንገዳችንን መቀየሩ ግዴታችን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በኛ ላይ የሚነደው የገሃነም ፍንጣሪ እሳት ከሆነ፣ አሁኑኑ በመለኮታዊው እሳት መያያዝ መጀመር ይኖርብናል፡፡ አለዚያ ፍጻሜአችን አያምርም፡፡ ግን በምን ዓይነት መንገድ ነው ከፍጥረታዊውና ደምሳሹ እሳት ነፃ ወጥተን በመለኮታዊውና ቀዳሹ እሳት የምንያያዘው? መልሱ ቀጥለን እንደምናየው ትንሹን እሳት በትልቁ እሳት በማጥፋት ብቻ ነው፡፡

 

9. እሳትን በእሳት