እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

8.1 ገሃነመ - እሳት

8.1 ገሃነመ - እሳት

 አጥፊ ስለሆነው ዓለማዊ እሳት ተናግረን የእርሱ ፍጻሜ የሆነውን ዘለዓለማዊ የእሳት ባሕር ሳንጠቅስ ልናልፍ አይቻለንም፡፡ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ የሚጫሩ እሳቶች (መልካምም ይሁኑ ክፉ) ለአንድ - አፍታ ብልጭ ብለው የሚጠፉ የእሳት ፍንጣሪዎች አይደሉም፡፡ አንድ ጊዜ ከተጫሩ ያለ ፍጻሜ ሲነዱ ይኖራሉ፤ ከዚህኛው ዐለም ወደ ቀጣዩም ይሸጋገራሉ፤ ያሸጋግራሉም፡፡ በሞት ድልድይ ላይ ከተሻገርን በኋላ የሚጫርብን የማናውቀው አዲስ እሳት አያጋጥመንም፤ አሁን የምናውቀው፣ እንደ ነዳጅ ሆኖም የሚያንቀሳቅሰን እሳት ነው ያኔ በስፋትና በጥልቀት አድጎና ቦግ ብሎ የሚታየው፡፡ አሁን በምድር ላይ ሳለን የአምላክ ፍቅር ነዶብን ከሆነ፣ ከሞት በኋላም ይኸው እሳት ነው የበለጠ የሚንቦለቦልብን፤ በተቃራኒውም የትኛውም ዓይነት ይሁን ደምሳሹ እሳት አሁን እየነደደብን ከሆነና ያለ ሕይወት ለውጥና ንስሐ በዚያው ከቀጠልን፣ ከሽግግራችን በኋላም ይኸው እሳት ነው እጅግ ገዝፎና የባሰ ደምሳሽ ሆኖ የሚነድብን፤ የሚያነደንም፡፡ ዘለዓለማዊ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ ወይም በሌላ አነጋገር፣ ገሃነምም ይሁን መንግሥተ ሰማይ፣ ከሞት (ሽግግር) በኋላ የሚታደሉ የሎተሪ ዕጣዎች ሳይሆኑ በምድር የተጀመረው ሕይወት ተቃጥላ የሆኑ ምዕራፍ ሁለቶች ናቸው፡፡ የመንግሥተ ሰማይን ጣዕም አሁን ያልቀመሰ የዜግነት መታወቂያውንም አሁኑኑ ያልያዘ ከቶ አይገባባትም፤ ለገሃነመ እሳትም እንዲሁ ነው፡፡ አሁን የማናውቀውን አገር አንናፍቀውም፤ የማንናፍቀውንም አገር አንረግጠውም፡፡ ስለዚህም ነው በሰው ሕይወት ውስጥ የተጫሩ እሳቶች ያለፍጻማ ሲነዱና ሲያነዱ ለዘለዓለም ይኖራሉ ያልኩት፡፡

 

አንድ ጊዜ የተጫረን እሳት በማዳፈን ወይም በመሸፋፈን ማንነትን መቀየርም ይሁን የዘለዓለማዊ ኑሮን እድል ፈንታ መለወጥ አይቻልም፡፡ ይህን ለማድረግ ሥር ነቀል የሆነ እርምጃን መውሰድ ይጠይቃል፡፡ በምድራዊ እሳቶች እየጋዩ የመንግሥተ-ሰማያትን ብርሃናዊ ክብር መመኘት አይቻልም፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ የሚኖር ሰው ካለም፣ በውስጣዊ ጦርነት ነበልባል በመንደድ ላይ የሚገኝ ሰው ወይም በማይታረቁ ሁለት ዓለሞች ውስጥ አንዱን እግሩን ወዲህ ሌላኛውን ደግሞ ወዲያ አኑሮ ለመራመድ የሚሞክር የሕልም ተጓዥ ብቻ መሆን አለበት፡፡ የሕልም ጉዞውም የትም አያደርሰውም፤ ከእንቅልፍ ሲነቃ እዚያው በተኛበት ቦታ ላይ እንዳለ፣ ምንም ፎቀቅም እንዳላለ ይመለከታል፡፡

 

ሕላዌአችን ቅዠት ወይም ሕልም ወይም ደግሞ የአእምሮ ጨዋታ አይደለም፤ ተጨባጭ ሐቅ ነው፡፡ ጅማሬ እንዳለው ሁሉ ፍጻሜና መድረሻም አለው፡፡ ጅማሬአችን በጊዜ የሚወሰን ነው፤ ማለትም በምድር ላይ ያልነበርንበት ጊዜ ነበር አዎ ሕላዌ ያልነበረን ጊዜ ነበረ፡፡ በእርግጥ በእግዚአብሔር ሐሳብ ውስጥ "ዓለም ሳይፈጠር፣ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ ተመርጠናል" (ኤፌ. 1፡4 ተመልከት)፡፡ ኋላ ግን በአምላክ ፍቃድ መሠረት ነፍስና ሥጋ ያላቸው ፍጡራን ሆነን ወደዚህች ዓለም መጣን፤ ሕላዊንም ሕልውናንም አገኘን፡፡ የበለጠ ትክክል በሆነ መንገድ ከገለጽነው፡- ሕልውና የሰጠንም አምላካችን ነው፡፡ ፍጻሜአችን ግን በጊዜ የሚለካ ወይም የሚወሰን ሳይሆን የታቀደልን ደረጃ ላይ መድረስ ነው፡፡ ስለዚህ አንዴ ከተፈጠርን በኋላ፣ ማለትም ሕልውና ከተሰጠን በኋላ ሕልውናችንን የምንነጠቅበት ወየም እንደልተፈጠሩ የምንሆንበት ጊዜ ከቶውንም አይመጣም፡፡ የተፈጠርነው ዘለዓለማዊ ሕይወትን ለመውረስ ነው፡፡ ድሃውን ከሃብታሙ፣ ደካማውን ከብርቱው፣ ፊሪውን ከጀግናው፣ ተራውን ከባለሥልጣኑ፣ ባሪያውን ከንጉሡ የማይለየውና፣ ያለ አድልዎ ሁሉንም በየተራ የሚያሰናብተው በብዙዎች ዘንድ የገነነውና የሚፈራው ኃይለኛው ሞትም እንኳ ቢሆን የማንንም ሕልውና ሊነጥቅና እንዳልተፈጠረ ለማድረግ አይችልም፡፡

 

የሰውን ልጆች ሁሉ የሚያሸንፍ ብርቱ ተጻራሪ እንኳ ሆኖ ቢታይም፣ በር እንጂ መድረሻ አይደለም፡፡ ሁሉም በእርሱ በኩል ያልፋሉ፤ ሕልውናቸው ግን መልኩን ይቀይራል እንጂ አይጠፋም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን "ለሰው አንድ ጊዜ መሞት የተገባ ነው፤ ከሞት በኋላም ፍርድ አለበት፡፡" (ዕብ. 9፡27) "ለሰው አንድ ጊዜ መሞት የተገባ ነው" ብቻ ሳይሆን "ከሞት በኋላም ፍርድ አለበት" የሚል ተጨማሪ ማብራሪያን ነው ይህ ያነበብነው ክፍል የሚሰጠን፡፡ ይህ የተባለው ፍርድ ከሞት በኋላም ቢመጣ፣ ሕልውናችንን የሚገፍና የሚያጠፋ ሳይሆን፣ ከሞት በፊት በነበረን የሕይወት ጉዞ ላይ ተመርኩዞ ቀጣዩንና ዘለዓለማዊውን ዕጣ ክፍላችንን ይፋ የሚያደርግ መድረክ ነው፡፡ በዚህ የፍርድ መድረክ ላይ የመንግሥተ ሰማይ ወይም የገሃነም ነዋሪዎች መሆናችን ለሁሉም በይፋ ይታወጃል፡፡ መንግሥተ ሰማይ በቅድስና የመኖራችን መድረሻ ሲሆን ገሃነም ግን ከአምላክ ተነጥለን ከኖርን በመጨረሻ የሚቆየን ዘለዓለማዋ መነጠል ነው፡፡

 

ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገሃነም እሳት ምን ይላል?

 

በትንቢተ ኢሳይያስ ውስጥ ስለ ዓመፀኞች እንዲህ ተብሏል፡- "ወጥተውም በእኔ ያመፁብኝን ሰዎች ሬሳቸውን ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትምና፤ እሳታቸውም አይጠፋምና፤ ለሥጋ ለባሽም ሁሉ አስጸያፊ ነገር ይሆናሉ፡፡" (ኢሳ. 66፡24) በመጽሐፈ ዮዲት ውስጥም እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች በመጨረሻው ቀን እንዴት አድርጎ እንደሚበቀላቸው ተገልጿል፡፡

 

"በዛሬ ላይ በጠላትነት ለሚነሡ አገሮች ወዮላቸው፤ ሁሉን ቻይ የሆነው ጌታ በፍርድ ቀን ይቀጣቸዋል፡፡ እርሱ በሥጋቸው ላይ እሳትንና ትልን ይሰድባቸዋል፤ እነርሱም ለዘለዓለም በስቃይ ያነባሉ፡፡" (ዮዲት 16፡17)

 

በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተለይም በወንጌሎች ውስጥ፣ የኃጢአተኞች መጨረሻ የዘለዓለም ቅጣት እንደሆነ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ይህን የቅጣት ስፍራ ገሃነም ብሎ ይጠራዋል፡፡ ገሃነም የሚለው መጠሪያ ለዚህ የስቃይ ቦታ መግለጫነት የተሰጠው፣ ኢየሩሳሌም አቅራቢያ ይገኝ ከነበረ፣ አስቀድሞ "የሄኖም ልጆች ሸለቆ" በመባል ይጠራ ከነበረ ዘወትር ሲነድና ሲጨስ ይታይ ከነበረ የጉድፍ መጣያ ሥፍራ ነው፡፡ (2 ነገ፤ 23፡10፤ ኤር. 7፡31-32 ተመልከት)፡፡ በዚህ ሸለቆ ላይ ጥንታውያን እስራኤላውያን ጣዖትን በማምለክ ልጆቻቸውን የእሳት መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ ነበር (2 ነገ. 16፡3 ተመልከት)፡፡ ኋላ ስሙ ጌሄና (ገሃነም) ተብሎ በሚጠራበት ጊዜም ቢሆን ዘወትር የቁሻሻ (ጉድፍ) መጣያ ስፍራ ስለነበር፣ እሳትና ጭስ ተለይቶት አያውቅም ነበር፡፡ ስለዚህም የርኩሰት፣ የክፋትና፣ የመጥፎ ነገሮች ሁሉ ምሳሌ ሆኖ በእስራኤላውያን ዘንድ ይታይ ነበር፡፡ ከዚህም በመነሣት የዘለዓለማዊ ቅጣት ስፍራን ለመግለጽ፣ ጌታ ኢየሱስ /ገሃነም(ጌሄና) የሚለውን አጠራር ሲጠቀም እናያለን፡፡ (ማቴ. 5፡22፣ 29፣ 30፤ 10፡28፤ 23፡15፣ 33፤ ማር. 9፡43-48 ተመልከት)፡፡ አዲስ ኪዳን በግልጽ እንደሚያሳየው፣ ገሃነመ እሳት፣ ዘለዓለማዊ እሳት ነው (ማቴ. 5፡22፤ 18፡9፤ ማቴ.25፡41 ተመልከት)፤ ትሉ የማይሞትበትና እሳቱም የማይጠፋበት ስፍራ ነው (ማር.9፡43-48)፤ የማይጠፋ እሳት ነው (ማቴ. 3፡12፤ ማር. 9፡42)፤ እቶነ - እሳት ነው (ማቴ. 13፡42፣ 50)፤ የዘለዓለም ስቃይና ቅጣት ነው (ማቴ. 25፡46)፡፡

 

በዚያ ጭለማ ይሆናል (ማቴ. 8፡12፤ 22፡13፤ 25፡30) ይህም እጅግ አስገራሚ የገሃነም ገጽታ ነው፡፡ እጅግ ታላቅና ኃይለኛ የሆነ ደምሳሽ እሳት በዚያ እያለ ብርሃን ግን የለም፤ በብርሃን ፈንታ ጭለማ ይሆናል፡፡ በባህሪያዊ መንገድ ስንመለከት እሳት ካለ ብርሃንም ይኖራል፤ በገሃነመ እሳት ውስጥ የሚነደው እሳት ግን ያሳውራል እንጂ ዓይንን አይከፍትም፣ ያደነቁራል እንጂ አእምሮን አያሰፋም፡፡ የብርሃናት አምላክ በሌለበት ስፍራ ቀድሞውኑስ ብርሃን ከየት ሊመጣ ይችላል?

8.2 ገሃነመ - እሳት  በሚል ርእስ ይቀጥላል

 

 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት