እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

7. ተገቢ ያልሆነ እሳት፣ ለቅስፈት

7. ተገቢ ያልሆነ እሳት፣ ለቅስፈት

 

ሕይወታችን የኛ ሳይሆን የአምላካችን ነው፡፡ መኖራችን መጀመሪያ ለእርሱ ክብር እንዲሆን ይፈልጋል፡፡ የመፈጠራችን ትርጉም እንደ እንስሳት አንድ ጊዜ በዚህ ምድር ላይ መወለድ ማደግና መሞት ሳይሆን ከአምላካችን ጋር ዘለዓለማዊ ኅብረት እንዲኖረን ነው፡፡ ኅብረታችን አሁን እዚህ ምድር ላይ እያለን ይጀምርና በወዲያኛው ዘልዓለማዊ ሕይወት ውስጥ ያለማቋረጥና ያለፍጻሜ በቀጣይነት ይዘልቃል፡፡ ከአምላካችን ጋር ያለንንና የሚኖረንን ኅብረት በአንድ ቃል ብንገልጸው ያ ቃል "አምልኮ" የሚለው ቃል ሆኖ ይገኛል፡፡ አምልኮ ለተወሰኑ ሰዓታትና ደቂቃዎች ብቻ የሚከናወን የሕይወት አንድ ክፍል ሳይሆን አጠቃላይ የሕይወት እርምጃ ነው፡፡

አምልኮአችን በጸሎት ሰዓቶቻችን ላይ ብቻ የሚታይ ቁንጽል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ መውጣት መግባታችንም ሁሉ አምልኮ ነው፡፡ ከመወለድ እስከመሞት፣ ከጧት እስከ ማታ የሚከናወነው ዕለታዊ የሕይወት እርምጃችን በሙሉ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ አምልኮ ነው፡፡ ምክንያቱም የተፈጠርነው እግዚአብሔርን ለማምለክ ስለሆነ! አምልኮአችን በተወሰኑ ሰዓታት ላይ ብቻ የሚፈጸም ጉዳይ አድርገን ስለምናስብ፣ ከጸሎት ጊዜያችን ውጪ ያሉትን ሰዓታት በሙሉ እንደ ትርፍ ሰዓታት ወይም እንደገዛ ራሳችን ነፃ ጊዜ አድርገን እንገምትና ዘመኑን ያለመዋጀት በከንቱ እናሳልፈዋለን፡፡ ሐቁ ግና "እንግዲህ እናንተ የእግዚአብሔር ናችሁ እንጂ የራሳችሁ አይደላችሁም፡፡ ምክንያቱም እርሱ በዋጋ ገዝቶአችኋል፤ ስለዚህ በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ" በሚሉት የቅዱስ ጳውሎስ ቃላት ተደምድሞልናል (1ቆሮ. 6፡19-20 ተመልከት)፡፡ ስለዚህ የገዛ ሰውነታችንም ይሁን፣ ያለን ንብረት ወይም በዚህች ምድር ላይ በሕይወት እንድንኖር የተሰጠን ጊዜም ጭምር የእኛ ሳይሆን የሰጪው የእግዚአብሔር ነው፡፡ እኛ የነዚህ ስጦታዎች ባለአደራዎችና አስተዳዳሪዎች ስንሆን ባለቤቱ ግን እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ የተሰጡንን ስጦታዎች በሙሉ እንደ ባለቤቱ ፍቃድና ፍላጎት ማስተዳደር ነው የኛ አምልኮ፡፡ እንደ ፍቃዱ ስንጸልይ፣ ስንኖር፣ ስንመላለስ፣ ስናገለግል፣ ዕረፍት ስናደርግ አምልኮአችን ሙሉ ይሆናል፡፡ ይህንንም ሁሉ ጌታ እንደሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ይቀበልልናል፡፡

 

የዕለታዊ ኑሮአችንን አካሄድ በመመልከት "ጌታ ሆይ ይህ ለአንተ የማቀርብልህ የተቀደሰ መሥዋዕቴ ነው" ብንል ያለምንም ፍርሃትና ጥርጣሬ ለእግዚአብሔር ልናቀርብለት እንችል ይሆን? ሕይወታቸውን በሙሉ ከጧት እስከ ማታ እንደ ጌታ ፍቃድ የሚመሩ ቅዱሳን ይህን ሊሉ ይችላሉ፡፡ አብዛኞቻችን ግን ኃጢአቶቻችንንና ከዓለም ጋር ያለንን ወዳጅነት በመመልከት በድፍረት ይህን ጸሎት ማድረግ ይከብደናል፡፡ ማን ነው ለእግዚአብሔርር ኃጢአቱንና ጉድፉን "ይኸው መሥዋዕቴ" ብሎ የሚያቀርብ? ይሁን እንጂ ሺህ ጊዜም እንኳ ጻድቃንና ቅዱሳንም ብንሆን ያለምንም እንከን በጌታ ፊት የተመላለስን ፍጹም ንጹሐን ልንሆን አንችልም፡፡ ምሕረቱ እንጂ ጽድቃችን አላቆመንም አያቆመንምም፡፡ በመዝሙር መጽሐፍ እንደምናነበው "ኃጢአታችንን ብትከታተል፣ ማን ከፍርድ ሊያመልጥ ይችላል? ነገር ግን አንተን በማክበር እንድንታዘዝህ ይቅር ትለናለህ፡፡" (መዝ. 130፡ 3-4) ስለዚህም የአምልኮአችን ሙሉ ያለመሆን ወደ ንስሐና ወደልብ ለውጥ ይጠራናል፡፡ ያለፈውን በንስሐና በጸጸት በአምላክ እግር ስር ጥለን ዛሬን በተስፋና በእምነት እንደ አዲስ "ሀ" ብለን በጽድቅ ለመኖር እንድንጀምር ይገፋፋናል፡፡ አለዚያ ግን አለአግባብ የሚቀርብ የእሳት መሥዋዕት ቅስፈትን ይጠራልና ፍጻሜአችን የማያምር እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

 

የሕይወታችንን መሥዋዕት በተገቢ ሁኔታ ለአምላክ ማቅረብ እንዳለብን በማሰብ፣ ልናደርገው ስለሚገባን ጥንቃቄ ስናሰላስል፣ በአሮን ልጆች በናዳብና በአቢሁ (አብዩድ) ላይ የደረሰው መቅሰፍት ብዙ ትምህርት ይሰጠናል፡፡

 

"ዳብና አቢሁ የተባሉት ሁለቱ የአሮን ልጆች እያንዳንዳቸው ጥናቸውን ወስደው የእሳት ፍም ጭረው ጨመሩበት፤ በእርሱም ላይ ዕጣን አድርገው ወደ እግዚአብሔር አቀረቡ፤ ያም እሳት የተቀደሰ አልነበረም፤ ምክንያቱም ያንን ዓይነት እሳት ያቀርቡ ዘንድ እግዚአብሔር አላዘዛቸውም፤ ከዚህም የተነሣ በድንገት ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ እሳት ስለበላቸው በእግዚአብሔር ፊት ሞቱ፤ ሙሴም አሮንን ‹እግዚአብሔር› በፊቴ ቀርቦ የሚያገለግለኝ ሁሉ ቅድስናዬን ያክብር፤ እኔም በሕዝቤ ፊት የተከበርሁ እሆናለሁ" እያለ በተናገረበት ጊዜ ይህንኑ ማስጠንቀቁ ነበር እኮ› አለው፡፡ አሮንም መልስ ሳይሰጥ ዝም አለ፡፡" (ዘሌ. 10፡1-3)

 

ሕይወታችን ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት ከሆነ፣ የግድ ቅዱስ መሆን ይገባዋል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ለመቀደስ የሚፈልጉና የሚቻላቸውን የሚያደርጉ ሰዎች እንድንሆን ጌታ ይፈልጋል፡፡ የአሮን ልጆች የእሳት መሥዋዕት አቅርበዋል፤ ግን እግዚአብሔር ካዘዛቸው እሳት ውጪ የተለየ እሳት ስለነበር ተቀሰፉ፡፡ የነርሱ እሳት ምሕረትንና በረከትን ሳይሆን መቅሰፍትን ነበር የጠራው፡፡ ምክንያቱም ከእግዚአብሔርር ፍቃድ ውጪ ስለነበረ ነው፡፡ የኛን መሥዋዕት ብንመለከት ከነርሱ የባሰ ከጌታ ፍቃድ ውጪ ስለነበረ ነው፡፡ የኛን መሥዋዕት ብንመለከት ከነርሱ የባሰ ከጌታ ፍቃድ ውጪ የሆነና የተለየ እሳት በፊቱ እንደምናቀርብ እናያለን፡፡ መለኮታዊውን የበረከት እሳት ወደ ሕይወታችን ከመጥራት ይልቅ የቅጣትና የመቅሰፍት እሳትን ስንጋብዝ እንታያለን፡፡ አምላክ ግን አልተወንም፤ በኛ ላይም የቁጣ ክንዱን ሳይሆን የምሕረት እጆቹን ሲዘረጋልን እያየነው ነን፡፡ የመሥዋዕት እሳታችንን ብናየው ከአቤል መሥዋዕት ይልቅ የቃየልን ይመስላል፡፡ አቤል የበለጠውንና ጥሩውን ለጌታ ሲያቀርብ ቃየል ግን ጥራጊውንና ጉድፉን ለአምላኩ አቀረበ፤ የአቤል ተቀባይነትን አገኘ የቃየል ግና ያለ ተቀባይ ቀረ፡፡ እኛም ብዙ ጊዜ የሕይወታችንን ምርጥ ምርጡን ለእግዚአብሔር ከመሠዋት ይልቅ ትርፍራፊውን ስናቀርብለት እንገኛለን፡፡ በዚህም ጌታን እንደ አምላክ ሳይሆን እንደ ቁሻሻ መጣያ አድርን እናቀርበዋለን፡፡ ይህ ጌታን በእጅጉ ያሳዝነዋል፡፡ የመሥዋዕታችን እሳት ንፁሕና ቅዱስ ሕያውም እንዲሆን ጌታ ይፈልጋል፡፡ ይኸውም ሰውነታችን ሙሉ ለሙሉ ለእርሱ ክብር እንዲውል ይሻል፡፡

 

"እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፣ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራሄ እለምናችኋለሁ፣ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ፡፡" (ሮሜ. 12፡1-2)

 

እነኚህ የቅዱስ ጳውሎስ ቃላት መሥዋዕታችን ምን መምሰል እንዳለበት ጥርት አድርገው ያሳዩናል፡፡ መሥዋዕታችን፡- እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ፣ ሕያው እንጂ ሙት ያልሆነ፣ ቅዱስ እንጂ ያልረከሰ፣ በጌታ ፍቃድ የሚመራ፣ መልካም የሆነ፣ ፍፁም የሆነ የሕይወት (የሰውነት ወይም የኹለንተና) እና የአገልግሎት መሥዋዕት እንዲሆን ጳውሎስ አደራ ይላል፡፡ የመሥዋዕት እሳታችን መቅሰፍትን ሳይሆን በረከትን የሚጠራው እንዲህ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ለአባቱ በመታዘዝ ያቀረበው መሥዋዕት የሕይወት መሥዋዕትነት ነበር (ዕብ. 10፡5-10 ተመልከት)፡፡ የኛም መሥዋዕት ይህን እንዲመስል ይፈልጋል፡፡ የኛን የመሥዋዕት እሳት የጠራና የተቀደሰ ሊያደርገው የሚችለውም የአርያሙ ቅዱስ እሳት ነው፡፡ የአምላክ ቅዱስ እሳት በውስጣችን ሲነድ፣ የምናቀርበውን መሥዋዕት በቅድስናና በሕያውነት እንድናሳርገው ያደርገናል፡፡ እሳት ከላይ አሜን!

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት