እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

6. የሚንበለበሉ የዲያብሎስ ፍላጻዎች

6. የሚንበለበሉ የዲያብሎስ ፍላጻዎች

 

ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ውስጥ፣ ስለ እምነት ገድል በሚናገርበት ወቅት፣ የዲያብሎስ ፍላጻዎች እንደ እሳት የሚንበለበሉ እንደሆኑ አመልክቷል፡፡ "ከዚህም ሁሉ በላይ እንደ እሳት የሚንበለበሉትን የዲያብሎስን ፍላጻዎች ሁሉ ማጥፋት የምትችሉበትን እምነት እንደ ጋሻ አነሡ፡፡" (ኤፌ. 6፡16) የሚነድዱ ፍላጻዎች ከቀዝቃዛ ፍላጻዎች የበለጠ እንደሚወጉና ጉዳት እንደሚያስከትሉ የታወቀ ነው፡፡ ጠላታችን ሰይጣን በኛ ላይ የሚያስፈነጥረው ፍላጻም ተራ ፍላጻ ሳይሆን የሚነድ፣ ለማቁሰልና ለመግደልም ኃይል ያለው አደገኛ ፍላጻ ነው፡፡ ይህን ፍላጻ በሰው ሠራሽ ጥበብ መመከትም ይሁን ማጥፋት አይቻልም፡፡ ሊመክተው የሚችለው የእምነት ጋሻ ብቻ ሲሆን ሊያጠፋውና ሊደመስሰው የሚችለውም የመንፈስ ቅዱስ ሰይፍ ነው፤ ይህ ሰይፍም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ጳውሎስ እንዳለው፣ የእምነትን ጋሻ በማንሣትና የመዳንን ራስ ቁር በራሳችን ላይ በመድፋት ከክፉው ነበልባላዊ ፍላጻዎች መጠበቅ እንችላለን፡፡ ራሳችንን ከአደጋ የምንጠብቅበት የመከላከያ ስልታችን ይህ ሲሆን፣ በተከላካይነት ብቻ ልንወሰን ግን አይገባንም፤ ማጥቃትም አለብን፡፡

ውጊያችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፣ ስልታችንም መንፈሳዊ እንጂ ሥጋዊ ሊሆን አይገባውም፡፡ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ጠላትን የምናጠቃበት መሣሪያችንም የመንፈስ ቅዱስ ሰይፍ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል በመያዝ ነው፡፡ በሌሎቹ ሥጋውያን እሳቶች ላይ ድልን የሚያጎናጽፈን መንፈስ ቅዱስ (የመንፈስ ቅዱስ እሳት) እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ ከዲያብሎስ ጋር በምናደርገው ውጊያም ላይ ዲያብሎሳዊ (ሰይጣናዊ) እሳቶችን ለመደምሰስ የሚያስችለን አሁንም መንፈስ ቅዱስ (የመንፈስ ቅዱስ እሳት) ነው፡፡

 

ቅዱስ ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ ትግላችን ስልት ሲናገር እንዳለው፣ መሣሪያዎቻችን መለኮታዊ ኃይል ያላቸው እንደሆኑ አመልክቷል፡፡

 

"በሥጋ አስተሳሰብ እንደምንመላለስ አድርገው በሚገምቱት በአንዳንድ ሰዎች ፊት ግን በድፍረት ለመናገር እችላለሁ፡፡ ምንም እንክ በዓለም ብንኖር፣ የምንዋጋው እንደ ዓለም ሰዎች አይደለም፡፡ የጦር መሣሪያዎቻችንም ምሽግ ለማፍረስ የሚያስችል መለኮታዊ ኃይል ያላቸው ናቸው እንጂ እንደ ዓለም የጦር መሣሪያዎች አይደሉም፡፡" (2ቆሮ. 10፡2-4)

 

የዲያብሎስ መሣሪያዎች ግዙፋዊ ሳይሆኑ የረቀቁ መንፈሳዊ ፈተናዎች ስለሆኑ፣ እርሱን የምንገጥመውም በመንፈሳዊ የጦር መሣሪያዎቻችን ነው፡፡ እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ በኖረው በመንፈስ ቅዱስ እና የአዳኛችን የጌታ ኢየሱስ ክቡር ደም የተረጨባቸው ሰዎች በመሆናችን ምክንያት የታጠቅነው መሣሪያ መለኮታዊ ኃየል አለው፡፡ ኃይሉ የእግዚአብሔር እንጂ የእኛ አይደለም፡፡ ውጊያውም ቢሆን የአምላካችን እንጂ የእኛ አይደለም፡፡ ስለዚህም በተሰጡት መንፈሳውያን መሣሪያዎች ተጠቅመን የዲያብሎስን ምሽግ ማፈራረስና መደምሰስ እንችላለን፡፡

 

በዓለም ውስጥ እንኳ ብንኖርም የዓለም ግን አይደለንምና፣ ውጊያችንም እንደ ዓለም ሰዎች ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ የሚካሄደው መንፈሳዊ ውጊያ ነው፡፡ የጠላታችንን ኃይልም ይሁን ብርታት አሳንሰንም ይሁን ከሚገባው በላይ አጋነን ልንመለከተው አይገባንም፡፡ ትክክለኛ ማንነቱን አውቀን ተገቢውን መልስ መስጠት ይኖርብናል፡፡ ይህም የመንፈሳዊ ውጊያችን አንዱ ተግባር ነው፡፡ ብዙዎች ሰይጣንን ከሚገባው በላይ አሳድገው ያዩትና በፍርሃት የተነሣ የእርሱ እስረኞች ሆነው ይቀራሉ፤ ብዙዎችም ሰይጣንን እንደሌለ አድርገው ይገምቱና ሳያውቁት በወጥመዱ ውስጥ ይገባሉ፤ መውጣት ተስኗቸውም የጣረ ሞት መፍጨርጨርን ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ በሁለቱም ጫፎች (አቅጣጫዎች) ከሚገባው በላይ ማሰብ አደገኛ ነው፡፡ የዲያብሎስን ሕላዌ መካድም ይሁን ከሚገባው በላይ አሳድጎ መመልከት ሁለቱም የዲያብሎስ ማጭበርበሪያ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ለግልጽ እንደሚያስተምረን፣ እግዚአብሔርን በመካድና ለእርሱ ባለመታዘዝ ምክንያት የወደቁ መላእክት አሉ፡፡

 

ምንም እንኳ ከእግዚአብሔር ተለይተው ያመፁም ቢሆኑ፣ ሥጋውያን (ግዙፍ) ሳይሆኑ መናፍስት ናቸው፡፡ መንፈስ ረቂቅ ነው፤ ከሥጋዊ ፍጡር የበጠ እውቀትና ችሎታም አለው፡፡ እነኚህ ርኩሳን መናፍስትም ቢሆኑ ይህን ኃየል እንደያዙ ነው የተጣሉት፤ ሥልጣናቸውን እንጂ ኃይላቸውን አልተቀሙም፡፡ ስለዚህ በእውቀትም ይሁን በኃይል በኩል ከሰው በላይ የሆነ ችሎታ አላቸው፡፡ ይህን ከፍተኛ ችሎታቸውንም ሰውን ከእግዚአብሔር ነጥለው የገሃነም ዜጋ ለማድረግ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ሰው በራሱ እውቀትና ኃይል ብቻ ተደግፎ ሊቋቅማቸው ከቶውንም አይቻለውም፡፡ ስለዚህም ከእርሱ በላይ የሆነ ብርቱና ኃይለኛ ረዳት ያስፈልገዋል፡፡ የምሥራቹ ቃልም፣ ከተፈጠሩ ኃይላት ሁሉ በላይ የሆነ የአምላክ ኃይል የፍጡር ሳይሆን የፈጣሪ (ኃይል) ከተጠመቅንበት ጊዜ አንሥቶ በኛ ውስጥ መኖሩ ነው፡፡ በተጨማሪም፣ ለአምላካቸው በታማኝነት የቆሙ ቅዱሳን መላእክትም እኛን ለመርዳት የተሰለፉ መሆናቸው አጽናኝ እውነታ ነው፡፡ "ታዲያ ቅዱሳን መላእክት የሚድኑትን ለማገልገል የሚላኩ የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሆኑ መንፈሶች አይደሉምን?" (ዕብ. 1፡14)

 

ምንም እንኳ ደካሞችና በኃይልና በችሎታም ከዲያብሎስ በታች ብንሆንም በኛ ውስጥ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ የተነሣ ከዲያብሎስ በላይ የሆነ ኃይልና ችሎታ ተሰጥቶናል፡፡ ጌታ ኢየሱስ በሞቱና ትንሣኤው የሞትን፣ የኃጢአትንና የዲያብሎስን ኃይል ሁሉ ድል ስላደረጋቸው ተከታዮቹ የዚህ ድል ተካፋዮች ሆነዋል፡፡ በጥምቀታችን ከክርስቶስ ጋር ተቀብረናል፤ ስለዚህም የትንሣኤውም ተሳታፊዎች ሆነናል፡፡ "ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ ለመሆን የተጠመቅን ሁሉ፣ የሞቱም ተካፋዮች ለመሆን መጠመቃችንን አታውቁምን?  በጥምቀት ከእርሱ ጋር በተቀበርን ጊዜ የአርሱ ሞት ተካፋዮች ሆነናል፤ ስለዚህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሞት እንደተነሣ፣ እኛም በአዲስ ሕይወት እንኖራለን፡፡ በሞቱ እርሱን በመምሰል ከተባበርን፣ በትንሣኤውም እርሱን እንደምንመስል የተረጋገጠ ነው፡፡" (ሮሜ. 6፡3-5) የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ተባባሪ መሆን ማለት የድሉ ተባባሪ መሆን ማለትም ነው፡፡ እኛም በመጠመቃችን የተነሣ የዚህ ድል ተሳታፊዎች ሆነናል፡፡

ከተጠመቅንበት ጊዜ አንስቶ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያዎች እንጂ የሰይጣን ማደሪያዎች አይደለንም ስንጠመቅ አጋንንትን፣ ዲያብሎስን፣ ሰይጣንን፣ የጨለማ ኃይላትን ሁሉ ክደን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተናል፡፡ ትልልቆች ሆነን ከሆነ የተጠመቅነው እኛው ራሳችን፣ ሕጻናት ሆነን ሳለ ከሆነም በወላጆቻችንና በጥምቀት አባትና እናቶቻችን አማካይነት ሰይጣንን ስንክድ እንዲህ ብለን ነበር፡- "ሰይጣን ሆይ እክድሃለሁ፤ ርኩስ ሥራህን እክዳለሁ፡፡ አጋንንትህንና ክፉ ሠራዊትህን እክዳለሁ፤ ኃይልህን ሁሉ፣ ሥልጣንህንና ርኩሳን መላእክትህን ሁሉ እክዳለሁ፡፡ ሥርዓትህን ሁሉ፣ መንጋህን ሁሉ፣ የጨለማና የአሳሳች ወጥመዶችህንም ሁሉ እክዳለሁ፡፡ ጥልህንና ዓመፃህን ሁሉ፣ ወራዳ ሥራህንና የጥርጣሬ ቅሬታህን ሁሉ እክዳለሁ፡፡" ከዚህ በኋላም አጥማቂው ካህን በፊታችን ላይ ሦስት ጊዜ (በቅድስት ሥላሴ ምልክት) እፍ በማለት ሰይጣን ከኛ እንዲወጣና እንዲርቅ በመገሰጽና "ርኩስ መንፈስ ሆይ ውጣ" በማለት ትእዛዝን በዚህም ሰይጣንና ጭፍራው ሁሉ ከኛ ነፍስ ተጠራርጎ ወጥቷል፡፡ ሰይጣንን እንድንክድ ስንጠይቅ ሦስት ጊዜ "ሰይጣን ሆይ እክድሃለሁ" ብለን መልሰናል፡፡ ርኩስ መንፈስ ከሰው ከወጣ በኋላ የዚያ ሰው ነፍስ ባዶ ሆና መቅረት የለባትም፤ አለዚያ ርኩሱ መንፈስ ከሱ የከፋ ሰባት እጥፍ አጋንንትን ጠርቶ ወደ ቀድሞ ቤቱ መመለሱ አይቀርም፤ ለዚያ ሰውም ከበፊቱ የኋለኛው ይብስበታል፤ (ማቴ. 12፡43-45 ተመልከት)፡፡

 

ይህ እንዳይሆን፣ ሰይጣንን እንደካድንና ሰይጣንም ከኛ ከወጣ በኋላ ወዲያውኑ በመንፈስ ቅዱስ እንድንሞላ ካህኑ ይጸልዩልናል፡፡ መጀመሪያ "በጸሎተ ሃይማናት ዘሐዋርያት" ላይ የተጠቃለሉትን የእምነት አንቀጾች መቀበል አለመቀበላችንን ተጠይቀን መቀበላችንን ጸሎቱን ከልብ በማድረስ እንመልሳለን፡፡ ጌታ ኢየሱስ የሕይወታችን ጌታ እንደሆነም እናረጋግጣለን፡፡ ካህኑ ይህን ካዩ በኋላ ልክ ሰይጣንን ሦስት ጊዜ እንደካድነው ሁሉ የቅድስት ሥላሴን ምስጢር አምነን እንደምንቀበል ወይም እንደማንቀበል ለማረጋገጥ ይጠይቁናል፡፡ እኛም ሦስት ጊዜ "አምናለሁ" ብለን መልስ እንሰጣለን፡፡ ከዚህ በኋላም ነው በውኃ የሣንጠመቀው፡፡ የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስን ስም እየጠሩ ካህኑ በውኃ ካጠመቁን በኋላ በፊታችን ላይ ሦስት ጊዜ እፍ በማለት "መንፈስ ቅዱስን ተቀበል" ብለው ይጸልዩልናል፡፡

 

በጥምቀት ሰይጣንን መካድና ከግዛቱ ነፃ መውጣት ብቻ ሳይሆን፣ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያዎችም ሆነናል፡፡ ከዚያ ቀን አንሥቶ ሰይጣን እኛን ይፈራል እንጂ እኛ ከእርሱ የሚያስፈራን ነገር ሊኖር አይችለም አይገባምም፡፡ እኛ እንኳ በውስጣችን የሚኖረውን የአምላካችን መንፈስ ብንዘነጋው፣ ሰይጣን ግን በኛ ውስጥ ያለውን አምላክ ሁልጊዜ ይመለከተዋል፤ ወደኛ መቅረብም ይቸግረዋል፡፡ ምክንያቱም እኛን ሳይሆን በኛ ውስጥ የሚኖረውን ጌታ እጅግ ስለሚፈራው ነው፡፡ ሰይጣን ወደ እኛ ሊጠጋ፣ ከሆነለትም ሊገባ የሚችለው አውቀንና ፈልገን በፍቃዳችን እጃችንን የሰጠነው እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ይህን እስካላደረግንለት ድረስ ግን በሚንበለበሉት ፍላጻዎቹ ከውጭ ሆኖ ሊወጋንና ሊያቆስለን ከመሞከር አይቆጠብም፡፡

 

ጠላታችንን በመፍራት ሳይሆን ተንኮሉን በሚገባ በማወቅ ተጠንቅቆ መጠበቁ የኛ ፈንታ ነው፡፡ በአዳኛችን ቅዱስ ደም ተረጭተናል፤ ስለዚህም የመዳን በር ተከፍቶልናል ደኅንነትንም እንደ ራስ ቁር በራሳችን ላይ አጥልቀናል፡፡ ከዚህ ቅዱስ ደም የተነሣ ዘለዓለማዊ ጥበቃ አለን፡፡ የማይተኛውና የማያንቀላፋው አምላካችን በየትኛውም ጊዜና ቦታ ይጠብቀናል፡፡ ከጠላታችን የሚያስፈራን ነገር እንዳይኖርም የሚያደርገን ይህ አምላካዊ ጥበቃ ነው፡፡ በየዕለቱ በቅዱስ ደሙ ነፍሳችንና ሥጋችን እንዲሸፈኑ በመጸለይ ከጠላት ጥቃት ሁሉ ነጻ መሆን እንችላለን፡፡

 

ስለ ክርስቲያናዊ ማንነታችን በጥልቀት ካጠናን ከጠላታችን ከሰይጣን በላይ የሆነ ሥልጣን እንደተሰጠን እንረዳለን፡፡ ጌታ ኢየሱስ የሾማቸው ሰባ መልእክተኞች አጋንንትን በስሙ ማስወጣት በመቻላቸው ተደስተው ይህንን ለጌታ በነገሩት ጊዜ፣ እርሱ በበኩሉ "ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ፡፡ እነሆ፣ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፣ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፣ የሚጐዳችሁም ምንም የለም" የሚል መልስ ነበር የሰጣቸው፡፡ (ሉቃ. 10፡ 17-20 ተመልከት)፡፡ ከነኚህ ሰባ ተከታዮቹ በፊት አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ሲልክም በርኩሳን መናፍስትና በደዌ ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቷቸው እንደነበርም በማቴ. 10፡1-4፤ ማር.3፡14-19፤ እና ሉቃ. 9፡1-2 ላይ እናነባለን፡፡ ይህ ታላቅ ሥልጣን ለቤተ ክርስቲያን ተሰጥቷታል፤ ቤተ ክርስቲያን ማለትም እኛ ነን፡፡ ጠላታችን ሰይጣን መንፈስ ስለሆነ ከኛ በላይ የሆነ ኃይል ሊኖረው ይችላል፤ ሥልጣኑ ግን የኛ ነው፡፡

ኃይል ያለ ሥልጣን ዋጋ የለውም፡፡ ኃይል ከሥልጣን ጋር ግን ብርቱ መሣሪያ ነው፡፡ በሉቃስ ወንጌል ላይ እንደምናነበው ለሐዋርያት የተሰጣቸው ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ኃይልም ጭምር ነው፡፡ "አሥራ ሁለቱምን ሐዋርያት በአንድነት ወደ እርሱ ጠርቶ በአጋንንት ሁሉ ላይ ደዌንም ይፈውሱ ዘንድ ኃይልና ሥልጣን ሰጣቸው" (ሉቃ. 9፡1) ይህ ኃይልና ሥልጣን ሥጋዊ ሳይሆን መንፈሳዊ ስለሆነ እጅግ ብርቱ ነው፡፡ እኛም በጥምቀታችን ምክንያት የክርስቶስ አካላትና የሐዋርያት ወራሾች ሆነናልና የዚህ ኃይልና ሥልጣን ተቋዳሾች ነን፡፡ በትክክል ልንጠቀምበትም ይገባናል፡፡ ምንም እንኳ የጠላታችን ሰይጣን ፍላጻዎች እንደ እሳት የሚያቃጥሉና የሚንበለበሉም ቢሆኑ፣ እኛም ከዚያ በላይ የሆነ ሥልጣንና የመንፈስ ቅዱስ ኃይል አለንና ልንፈራ አይገባንም፡፡ አዎ የጠላታችንን ማንነት አሳንሰንም ይሁን አግዝፈን አንመልከተው፡፡ ትክክለኛ ማንነቱን እንወቅ፡፡ በዚህ ብቻ ግን አንወሰን፡፡ በተሰጠን ኃይልና ሥልጣንም በአግባቡ እንጠቀም፤ ድሉም የኛ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በዓለም ካለውና ከሰይጣን ክንድ ይልቅ በእኛ ውስጥ ያለው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል እጅግ ከፍተኛ ነውና፡፡

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት