ትልቅ ጥያቄ ከታላቁ ጠያቂ

ትልቅ ጥያቄ ከታላቁ ጠያቂ

መቼም ጥያቄ ሲባል መሠረታዊ እውነቱ መልስን የሚፈልግ ነገር ነው፡፡ መልስ ደግሞ በተራው መላሽን ይሻል፡፡ ይብዛም ይነስም መልስ የመላሽን ማንነት ይገልፃል፤ ሰዎች በተፈጥሮአችን ማንነታችንን በቀላሉ መግለጽ ስለሚያታግለን ብዙ ጊዜ ምላሾችን በፍጥነት መስጠቱ ይከብደናል፡፡ ባብዛኛውም ከጥያቄዎች የመሸሽ ጥረታችን የሕይወታችን አንዱ አካል ሆኖ ይስተዋላል፡፡ በትምህርት ክፍል ውስጥ የሚደረገው ከአስተማሪ ለሚመጡ ጥያቄዎች ግንባር ቀደም ላለመሆን ወደኋላ ለመቀመጥ የሚደገረው የሽሽት ጥረት ወይም በጥያቄ ሰዓት የመምህሩን ዓይን ላለማየትና ላለመጋፈጥ የሚደረጉ ማጎንበሶች ሁሉ የምናስታውሳቸው እውነታዎች ናቸው፡፡ ሕይወትን ወይም የሰው ልጅ እድሜን እንደ አንድ የትምህርት ሂደት ካየነው ግን በጉዟችን ከሚነሱ ጥያቄዎች ጋር ሁልጊዜ ድብብቆሽን መጫወት አይቻልም፡፡ አንዳንዴ ስንሸሸው የሚሸሽ ጥያቄ አለ፤ ልንርቀው ስንሞክር ደግሞ ይበልጥ ቅርብ ሆኖ የሚወተውተን ጥያቄ አለ፡፡

በዚህ ጽሑፍ ዓላማችን የጥያቄዎችን አይነት እያነሳን ለመጣል ሳይሆን የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናትን ልንሸሸው የማንችለው የሱን ጥያቄ መጋፈጥ እንዲኖርብን ነው፡፡ ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን "የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?" አለው፡፡ ጴጥሮስም "አዎን ጌታ ሆይ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ" አለው፡፡ /ዮሐ. 21፡15/

ይህን ጥያቄ ኢየሱስ ሦስት ጊዜ ደጋግሞ ስምዖን ጴጥሮስን ጠየቀው እሱም ሦስት አዎንታችን መለሰ፡፡ በመልሶቹም ውስጥ "ጌታ ሆይ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ" የሚል ተደጋጋሚ ዓረፍተ ነገር እናገኛለን፡፡ የፍቅር መድረሻ ግብ ትስስር ነውና ኢየሱስን ለሚከተል ሰው ከኢየሱስ ጋር ያለውን ፍቅር ደግሞ መጠየቅና መመለስ የግድ መሆኑን ያስረዳናል፡፡

አገልጋይ ጌታውን ማገልገል ካለበት ጌታውን ማወቅ አለበት፡፡ ይህ ለምድራውያን ጌቶችና አገልጋዮች በቂ ነው - ጌታውን ማፍቀር የግድ አይደለም - ውስጥ ውስጡን እያጉረመረመ እየተማረረ እንጀራ ነውና እስከ ኀልፈቱ ያገለግላል፡፡ ክርስቲያኖች ግን ጌታችን የምንለውን ክርስቶስን ለማገልገል ስንወስን እርሱ ማወቅና ማፍቀር የሚለያዩ ነጥቦች አይደሉም፡፡ እውቅ ኢየሱሳዊ አባ አንቶኒ ዴ ሜሎ "ስለ ኢየሱስ ያለን እውቀት ጥልቅ በሆነ መጠን ፍቅራችን ታላቅ ይሆናል፤ በይበልጥ ባፈቀርነው ቁጥር ስለ እሱ የጠለቀ እውቀት ይላሉ፡፡ የስመጥሩው ነገር መለኮታዊ ሊቅ ካርል ባርት ባልንጀሮች የእኚን የሊቅ ሃሳቦች ይበልጥ ለማወቅ በሚል ጉጉት ምሽቱን አብረው ከእርሳቸው ጋር ያሳልፋ ነበር፡፡ ከነሱም አንዱ ባርትን " እስከ ዛሬ ድረስ በአእምሮዎት ውስጥ ከተመላለሱት ሃሳቦች ሁሉ ይበልጥ ጥልቅ የሚሉት ሃሳብ የትኛው ነው?" ሲል ይጠይቃቸዋል፡፡ ከጥቂት የማሰላሰል ጊዜ በኋላ ባርት ቀለል ባለ ሁኔታ እንዲህ በማለት መለሱለት "እስካሁን ድረስ ከሚታወቁኝ ሃሳቦች ሁሉ ይበልጥ ጥልቅ የሆነ ሃሳብ የምለው አንድ ቀላል እውነት ነው እሱም፡- ኢየሱስ እኔን ይወደኛል ... ይህን አውቃለሁ ምክንያቱም ቅዱስ መጽሐፍ ይህን ስለሚነግረኝ ነው"፡፡

በርግጥ እዚህ ላይ ተቃዋሚ ካለ እጅ ያንሣ የሚያስብል ነጥብ አይደለም አዎ ክርስቶስ ሁላችንንም ያፈቅራል፡፡ ለዚህ ፍቅር ግን የሚመለሰው የያንዳንችን ምላሽ ላይ ሁላችንም በሙሉ ድምጽ ላንስማማበት እንችላለን፡፡ ስለዚህም ነው ክርስቶስ ጴጥሮስን "እኔን ትወደኛለህን?" የሚለው፡፡ ካስተዋልነው "ከእነዚህ ይልቅ ትምህርቴን፣ አኗኗሬን፣ በኔ መጠራትን፣ እኔን ማገልገልን፣መመሪያዎቼን ... ትወዳለህን? አላለውም "እኔን ትወደኛለህን?" ነው ጥያቄው፡፡ የክርስቲያንነታችንና የአገልግሎታችን ብቸኛ ምክንያት ሊሆን የሚገባው ለክርስቶስ ያለን ፍቅር መሆን አለበት፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ሌሎች ነገሮች ሁሉ ተከታይ መሆናቸውን ለማስረዳት "የክርስቶስ ፍቅር ለሥራ ይገፋፋናል" ይላል፡፡

ስለዚህ ፍሬያማነታችን የሚወሰነው ልባችን ከኢየሱስ ጋር ባለው ቁርኝት ነው፡፡ የ13ኛ ክፍለ ዘመን ታላቅ ጸሐፊ ዳንቱ አሊጌሪ "እስከ ዛሬ ድረስ ፈጣሪም ሆነ ፍጡራን ያለፍቅር ኖረው አያውቁም" ይለናል፡፡ እናም ያለፍቅር መኖር እንደማንችል የሁላችንም ተፈጥሮ በጋራ ቢመሰክርልንም የፍቅራችንን ግብ ወይም ምን እንደምናፈቅር ግን እያንዳንዳችን ነው መመለስ የምንችለው፡፡ ቅ. አውጐስጢኖስ እንማሚለው ፍቅር የራሱ የስበት /የመጐተት/ ሕግ አለው፡፡ ቀልባችን፣ ኃይላችን፣አካላችነ በአጭሩ ማንነታችን የሚባክነው ላፈቀረው ነገር ነውና የፍቅራችን አቅጣጫ የማንነታችንን አቅጣጫ ይጠቁማል፡፡ ክቡር ነገርን ያፈቀረ የከበረ ሩጫ ሲኖረው ርካሽ ነገር ያፈቀረ ወደ ርካሽ ነገሮች ይሮጣል፡፡ ጌታም ሰው ሃብቱ ባለበት በዚያ ልቡ አለ ይላል እንዲሁም በድን ባለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ ይላል፡፡

ስለዚህ የየራሳችንን አድራሻ ለማወቅ ልባችን የት እንደሚገኝ እንመልከት፡፡ ልቤ እገሌ/እገሊት ጋር ከሆነ ማንነቴ እዚያ ነው፤ ልቤ የሆኑ ነገሮች ጋር ከሆነ እኔነቴን ከነሙሉ ኃይሉና ችሎታው በነገሮች ገድቤዋለሁ እንዲሁም ልቤ ክርስቶስ ጋር ከሆነ ማንነቴን በዚያ አገኘዋለሁ፡፡ ቁምነገሩ ለሰዎች ልባችንን አንስጥ አይደለም ግን ቅድሚያ ልባችን ለክርስቶስ ከሆነ ለሌሎች የሚኖረን ፍቅር ሁሉ በዚያ ይካተታል ከዚያም ይመነጫል፡፡

ሰበብ

ሰበብ ከሰው ልጅ ጋር ያለውን ቁርኝት ለማየት የአዳምና የሔዋንን የውድቀት ትረካ ማጤኑ በቂ ነው፡፡ በወንጌል ውስጥም ክርስቶስ የሚሰጠን ምሳሌ አለ፡፡ ሉቃ 14፡ 15-24 ከዚያም በራሳችን ሕይወት ብዙ ብዙ ምሳሌዎች ይኖሩን ይሆናል፡፡ ሰበብ ሁልጊዜ ትንሽ እውነትን ጐላ አድርጐ ለማሳየት የሚደረግ ጥረት ነው፤ ግን እውነት በተፈጥሮው አንድም ሙሉ ነው አሊያም ባዶ ነው፤ አለ ወይም የለም፤ ትንሽ እውነት ብሎ ነገር የለም፡፡ ክርስቶስን ላለማፍቀር የምንሰጠው ምንም በቂ ምክንያት የለንም፤ አለኝ ካልን ደግሞ ሰበብ ነው፡፡

"ሰበብ" ይላሉ ታላቁ ር.ሊ.ጳ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ "ከውሸት እጅግ የከፋና መጥፎ ነገር ነው፤ ምክንያቱም ሰበብ የተድበሰበሰና በምክንያቶች የተጀቧቦነ ውሸት ነውና፡፡" ከዚህ ነጥብ አንጻር ስናየው በሕይወታችን እና በአገልግሎታችን ክርስቶስን ማፍቀር ቀጠሮ የምንይዝለት ጉዳይ እንዳልሆነ እናያለን፡፡

ሥነ ልቦናዊ የሰበብ እይታም እንደሚነግረን ከሆነ ሰበብ የሰው ሁለንተናዊ ምላሽ ሳይሆን አእምሮአዊ ምላሽ ብቻ ነው ያም ጐደሎ ነገር ማለት ነው፡፡ ሁሌም ለአንድ ሰው ሰበብን ስንሰጥ ሽራፊ ማንነታችንን ነው የምንገልጥለት፡፡ ይህም ሙሉ ትስስርን ወይም ቅርርብን አይፈጥርም፡፡ ሁል ጊዜ በሰውም ሆነ በክርስቶስ ፊት በሰበብ መኖር አይቻልም። ወንጌል "በሙሉ ኃይልህ፣ በሙሉ ሃሳብህ፣ በሙሉ ልብህና በሙሉ ነፍስህ አምላክህን እና ጐረቤትህን አፍቅር" ይለናል፡፡ ማር፡ 12፡3ዐ

ፍቅር ሲታደስ ሁሉ ይታደሳል

"አንድ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ይኸውም የቀድሞውን ፍቅርህን ትተሃል" ይላል ራእ. 2፡4 ክርስቶስ እኛን ከነቀፈ የሚነቅፍበት ብቸኛ ምክንያት፤ ካሞገሰም የሚያሞግስበት ብቸኛ ምክንያት ፍቅር! ቅ. በርናርዶስ ዘክሌርቮ፡- "ያለምንም ጥርጥር እግዚአብሔር የሚያፈቅረን እንድናፈቅረው ብቻ ብሎ ነው፤ የሚያፈቅሩት በማፍቀራቸው ደስተኛ እንደሚሆኑ ያውቃል" ይላል፡፡ ደስታ ከመፈቀር ብቻ የሚመጣ ሳይሆን ከማፍቀርም ነው፡፡ በሕይወታችን ደስታ መኖር ካለበት ደግሞ "ትወደኛለህን?" ለሚለው የክርስቶስ የፍቅር ጥያቄ ምልስ መስጠት ይኖርብናል፡፡

በሕይወታችን፣ በክርስትናችን፣ በአገልግሎታችን ዝለት የሚሰማን ከሆነ አሁንም ክርስቶስን እንስማው፡፡ "በዚች ዓለም ውስጥ ባዶ ሆነው የሚመላለሱ ሰዎች የማያፈቅሩ ሰዎች ብቻ ናቸው" ይላል አንድ ጸሐፊ፡፡ ስናስበውም አፍቃሪ ሰው ያፈቀረውን ለማስደሰት ምን የማያደርገውና የማይሆነው አለ? እንዴትስ ግድየለሽና ባዶ ሆኖ በሕይወቱ ሊመላለስ ይችላል?

በ2ዐኛው ክፍለ ዘመን በሰሜን አሜሪካ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሰዎች ላይ ክርስቲያናዊ እሴቶች እንዲሰርጹ እግዚአብሔር ከተጠቀመባቸው ካህናት ዋነኛ ተጠቃሽ የሆኑት ሰባኪና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ፉልተን ሺን አንድ ጥያቄ አንስተው ይመልሳሉ እሱም፡- "ለምንድነው በሕይወታችን ትጋትና ቅንአት የማይኖረው? ባጭሩ መልሱ ከጌታ ጋር ፍቅር ስላልያዘን ነው፤ ከርሱ ጋር ከተፋቀርን ከእርሱ ጋር መሆንን እንሻለን" ይላሉ፡፡ የኃይሌ ምስጢር ብለው ያመኑበትን ሲናገሩ ደግሞ "ለስብከት በምቆምበት ጊዜ ሰዎች ያዳምጡኛል፣ በንቃት ይከታተሉኛል፣ ይህም በፍጹም የኔ ኃይል እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ በ55 ዓመት የክህነት ሕይወቴ በቅዱስ ቁርባን ማለትም በጌታ ፊት አንድ ሰዓት ያላሳለፍኩባት አንዲትም ቀን የለችም፡፡ ኃይሌ የሚመነጨውም ሆነ መልካም የሆነ ሃሳቦች ተጸንሰው ስብከቶቼ የሚወለዱት ከዚያ ነው፡፡ ታላላቅ ሃሳቦች የሚፈልቁት ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት በምንሆንበት ሰዓት ነው" ይላሉ፡፡ እኚህ ሊቀ ጳጳስ ስለ ርእሰ ሊቀ ጳጳስ ዮሐንስ ዳግማዊ ሲመሰክሩ "ዮሐንስ ጳውሎስ ደግማዊ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን በቅዱስ ቁርባን ፊት በሚሆኑበት ጊዜ ትንሽ የማስታወሻ ደብተር አይለያቸውም እኔም ይህንኑ አደርጋለሁ ምክንያቱም ሁሌም ቢሆን አፍቃሪ ከተፈቃሪው ጋር በሚሆንበት ጊዜ የአቅሙን ያህል የተሻለ ነገር ስለሚያደርግ ነው" ይላሉ፡፡

ይህ የብዙዎች ቅዱሳን የተቀደሰ ልማድ ነው፡፡ በቅዱስ ቁርባን ፊት የተወሰነ ሰዓት መቀመጥና ማሰላሰል ኃይላችንን ከሚያባክኑ በዙሪያችን በከበቡን ብዙ ነገሮች ወጣ ብለን ምን ያህል እንደተፈቀርንና እንዳፈቀርን ለማየት ጊዜ ይኖረናል፤ ቅዱሳኖች ሲወስኑም ሆነ ሲናገሩ ከርሱ ጋር መማከርን ያውቁበታል ውጤቱን ያውቁታልና፡፡ አፍቃሪ ፍቅረኛውን ይተማመንበታል ቅ.ጳውሎስ በፍቅር ማኅሌቱ ውስጥ "ፍቅር ሁሉን ያምናል" እንደሚለው ማለት ነው 1ቆሮ. 13፡7፡፡ ይህ መተማመን ካለ መታከትና መሰልቸት አብረው መሆን አይችሉም፤ ስለዚህም ክርስቶስን በማፍቀር በርሱ ከተማመንን የኃይላችንን ምስጢር ከዚያ እናገኛለን፡፡ "ብላቴኖች የደክማሉ ይታክቱማል፤ እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን የድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፣ አይታክቱም ይሄዳሉ አይደክሙም" ኢሳ. 4ዐ፡31፡፡

ሄንሪ ናውዌን የተባለ ጸሐፊ ካህን የኢየሱስ ፍቅር መገለጫና ራሱ ፍቅር ማለትም እግዚአብሔር ከሆነው ከቅዱስ ቁርባን ጋር ባደረጉት "መጋፈጥ" ክህነታዊ ሕይወታቸውን እንዴት እንደለመለመ እንዲህ ይመሰክራሉ፡፡ "ከጥቂት ዓመታታ በፊት የካልካታዋን እማሆይ ተሬዛ የመገናኘት አጋጣሚ ነበረኝ፡፡ በወቅቱ ብዙ ነገሮች ይታገሉኝ ስለነበር አጋጣሚውን ተጠቅሜ ከርሳቸው ምክርን ለመጠየቅ ወሰንኩ፡፡ አብረን እንደተቀመጥን ወዲያው ችግሮቼንና ሸክሞቼን አሳማኝ ነው ባልኩት ሁኔታ እበያቀናበርኩ ውስብስብነቱን ለመግለፅ ሞከርኩ፡፡ ከ1ዐ ቀቂቃ በጥሩ የማስረዳት ጥረት በኋላ ጸጥ አልኩኝ፡፡ እማሆይ ተሬዛም በጥሞና ከተመለከቱኝ በኋላ 'በል እንግዲህ በየቀኑ ለአንድ ሰዓት ጌታን በቅዱስ ቁርባን ስታመልከው፤ ስትሰግድለት ፍቅርህን ስትገልጽለት እንዲሁም ደግሞ መጥፎ ወይም ስህተት መሆኑን እያወቅክ የምታደርገውን ነገር መተው ስትጀምር ሁሉ ነገር ይስተካከላል' አሉኝ፡፡ ይህንን ባሉኝ ሰዓት በሕይወቴ ላይ ሮሮን በሮሮ ደራርቤ ትልቅ ሆኖ የነበረው የተነፋ ፊኛ ሲተነፈስ ታወቀኝ፤ በዚህም መልኩ እውነተኛ የፈውስ ቦታ ወደ ሆነው መሩኝ፡፡ አመስግኛቸውም ተሰናበትኳቸው፤ ግን የተናገሩኝ ጥቂት ቃላቶች በልቤ ተቀርጸው ቀርተዋል እውነቱን እንደተናገሩኝና እኔም በቀሪው ሕይወቴ እኖረው ዘንድ እንዳለብኝ አወቅኩ" ይላሉ፡፡

ኢየሱስ ለሚያቀርብልን ፍቅራዊ ጥያቄ ፍቅራዊ ምላሽን ካልሰጠን ሕይወት አዎን በላያችን ላይ ያለች ትልቅ ሸክም ብቻ ሳትሆን ማንነታችን ራሱ በሄደበት ቦታ ሁሉ ሸክም እንደሚሆን ውስጣችን ይነግረናል፡፡ የክርስቶስን ጥያቄ ያለመጋፍጥ እንደ አዳም የመሸሽ፣ እንደ ቃየል የመቅበዝበክዝ ብሎም እንደ ይሁዳ ራስን እስከመካድ የሚያደርስ መዘዝ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህም ይህ እውነታ ገብቶን ከጳውሎስ ጋር "ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆን፣ ግዛትም ቢሆን ... በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቻለሁ" ሮሜ 8፡ 38-39 የምንልበትንና ለሌሎችም "ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቀቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፤ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ" ኤፌ. 3፡18-19 በማለት ሕይወታችን እንዲያውጅ ጸጋውን ያብዛልን፡፡