ትልቅ ጥያቄ ከታላቁ ጠያቂ

Written by Super User on . Posted in የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች

ትልቅ ጥያቄ ከታላቁ ጠያቂ

መቼም ጥያቄ ሲባል መሠረታዊ እውነቱ መልስን የሚፈልግ ነገር ነው፡፡ መልስ ደግሞ በተራው መላሽን ይሻል፡፡ ይብዛም ይነስም መልስ የመላሽን ማንነት ይገልፃል፤ ሰዎች በተፈጥሮአችን ማንነታችንን በቀላሉ መግለጽ ስለሚያታግለን ብዙ ጊዜ ምላሾችን በፍጥነት መስጠቱ ይከብደናል፡፡ ባብዛኛውም ከጥያቄዎች የመሸሽ ጥረታችን የሕይወታችን አንዱ አካል ሆኖ ይስተዋላል፡፡ በትምህርት ክፍል ውስጥ የሚደረገው ከአስተማሪ ለሚመጡ ጥያቄዎች ግንባር ቀደም ላለመሆን ወደኋላ ለመቀመጥ የሚደገረው  የሽሽት ጥረት ወይም በጥያቄ ሰዓት የመምህሩን ዓይን ላለማየትና ላለመጋፈጥ የሚደረጉ ማጎንበሶች ሁሉ የምናስታውሳቸው እውነታዎች ናቸው፡፡ ሕይወትን ወይም የሰው ልጅ እድሜን እንደ አንድ የትምህርት ሂደት ካየነው ግን በጉዟችን ከሚነሱ ጥያቄዎች ጋር  ሁልጊዜ ድብብቆሽን መጫወት አይቻልም፡፡ አንዳንዴ ስንሸሸው የሚሸሽ ጥያቄ አለ፤ ልንርቀው ስንሞክር ደግሞ ይበልጥ ቅርብ ሆኖ የሚወተውተን ጥያቄ አለ፡፡

በዚህ ጽሑፍ ዓላማችን የጥያቄዎችን አይነት እያነሳን ለመጣል ሳይሆን የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናትን ልንሸሸው የማንችለው የሱን ጥያቄ መጋፈጥ እንዲኖርብን ነው፡፡ ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን “የዮና  ልጅ ስምዖን ሆይ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?” አለው፡፡ ጴጥሮስም “አዎን ጌታ ሆይ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው፡፡ /ዮሐ. 21፡15/

ይህን ጥያቄ ኢየሱስ ሦስት ጊዜ ደጋግሞ ስምዖን ጴጥሮስን ጠየቀው እሱም ሦስት አዎንታችን መለሰ፡፡ በመልሶቹም ውስጥ “ጌታ ሆይ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” የሚል ተደጋጋሚ ዓረፍተ ነገር እናገኛለን፡፡ የፍቅር መድረሻ ግብ ትስስር ነውና ኢየሱስን ለሚከተል ሰው ከኢየሱስ ጋር  ያለውን ፍቅር ደግሞ መጠየቅና መመለስ የግድ መሆኑን ያስረዳናል፡፡

አገልጋይ ጌታውን ማገልገል ካለበት ጌታውን ማወቅ አለበት፡፡ ይህ ለምድራውያን ጌቶችና አገልጋዮች በቂ ነው - ጌታውን ማፍቀር የግድ አይደለም - ውስጥ ውስጡን እያጉረመረመ እየተማረረ እንጀራ ነውና እስከ ኀልፈቱ ያገለግላል፡፡ ክርስቲያኖች ግን ጌታችን የምንለውን ክርስቶስን ለማገልገል ስንወስን እርሱ ማወቅና ማፍቀር የሚለያዩ ነጥቦች አይደሉም፡፡ እውቅ ኢየሱሳዊ አባ አንቶኒ ዴ ሜሎ “ስለ ኢየሱስ ያለን እውቀት ጥልቅ በሆነ መጠን ፍቅራችን ታላቅ ይሆናል፤ በይበልጥ ባፈቀርነው ቁጥር ስለ እሱ የጠለቀ እውቀት ይላሉ፡፡ የስመጥሩው ነገር መለኮታዊ ሊቅ ካርል ባርት ባልንጀሮች የእኚን የሊቅ ሃሳቦች ይበልጥ ለማወቅ በሚል ጉጉት ምሽቱን አብረው ከእርሳቸው ጋር ያሳልፋ ነበር፡፡ ከነሱም አንዱ ባርትን “ እስከ ዛሬ ድረስ በአእምሮዎት ውስጥ ከተመላለሱት ሃሳቦች ሁሉ ይበልጥ ጥልቅ የሚሉት ሃሳብ የትኛው ነው?” ሲል ይጠይቃቸዋል፡፡ ከጥቂት የማሰላሰል ጊዜ በኋላ ባርት ቀለል ባለ ሁኔታ እንዲህ በማለት መለሱለት “እስካሁን ድረስ ከሚታወቁኝ ሃሳቦች ሁሉ ይበልጥ ጥልቅ የሆነ ሃሳብ የምለው አንድ ቀላል እውነት ነው እሱም፡- ኢየሱስ እኔን ይወደኛል … ይህን አውቃለሁ ምክንያቱም ቅዱስ መጽሐፍ ይህን ስለሚነግረኝ ነው”፡፡

በርግጥ እዚህ ላይ ተቃዋሚ ካለ እጅ ያንሣ የሚያስብል ነጥብ አይደለም አዎ ክርስቶስ ሁላችንንም ያፈቅራል፡፡ ለዚህ ፍቅር ግን የሚመለሰው የያንዳንችን ምላሽ ላይ ሁላችንም በሙሉ  ድምጽ ላንስማማበት እንችላለን፡፡ ስለዚህም ነው ክርስቶስ ጴጥሮስን “እኔን ትወደኛለህን?” የሚለው፡፡ ካስተዋልነው “ከእነዚህ ይልቅ ትምህርቴን፣ አኗኗሬን፣ በኔ መጠራትን፣ እኔን ማገልገልን፣መመሪያዎቼን … ትወዳለህን? አላለውም “እኔን ትወደኛለህን?” ነው ጥያቄው፡፡ የክርስቲያንነታችንና የአገልግሎታችን ብቸኛ ምክንያት ሊሆን የሚገባው ለክርስቶስ ያለን ፍቅር መሆን አለበት፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ሌሎች ነገሮች ሁሉ ተከታይ መሆናቸውን ለማስረዳት “የክርስቶስ ፍቅር ለሥራ ይገፋፋናል” ይላል፡፡

ስለዚህ ፍሬያማነታችን የሚወሰነው ልባችን ከኢየሱስ ጋር ባለው ቁርኝት ነው፡፡ የ13ኛ ክፍለ ዘመን ታላቅ ጸሐፊ ዳንቱ አሊጌሪ “እስከ ዛሬ ድረስ ፈጣሪም ሆነ ፍጡራን ያለፍቅር ኖረው አያውቁም” ይለናል፡፡ እናም ያለፍቅር መኖር እንደማንችል የሁላችንም ተፈጥሮ በጋራ ቢመሰክርልንም የፍቅራችንን ግብ ወይም ምን እንደምናፈቅር መመለስ የምንችለው ግን እያንዳንዳችን ነን፡፡ ቅ. አውጐስጢኖስ እንማሚለው ፍቅር የራሱ የስበት /የመጐተት/ ሕግ አለው፡፡ ቀልባችን፣ ኃይላችን፣ አካላችን በአጭሩ ማንነታችን የሚባክነው ላፈቀረው ነገር ነውና የፍቅራችን አቅጣጫ የማንነታችንን አቅጣጫ ይጠቁማል፡፡ ክቡር ነገርን ያፈቀረ የከበረ ሩጫ ሲኖረው ርካሽ ነገርን ያፈቀረ ወደ ርካሽ ነገሮች ይሮጣል፡፡ ጌታም ሰው ሃብቱ ባለበት በዚያ ልቡ አለ ይላል እንዲሁም በድን ባለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ ይላል፡፡

ስለዚህ የየራሳችንን አድራሻ ለማወቅ ልባችን የት እንደሚገኝ እንመልከት፡፡ ልቤ እገሌ/እገሊት ጋር ከሆነ ማንነቴ እዚያ ነው፤ ልቤ የሆኑ ነገሮች ጋር ከሆነ እኔነቴን ከነሙሉ ኃይሉና ችሎታው በነገሮች ገድቤዋለሁ እንዲሁም ልቤ ክርስቶስ ጋር ከሆነ ማንነቴን በዚያ አገኘዋለሁ፡፡ ቁምነገሩ ለሰዎች ልባችንን አንስጥ አይደለም ግን ቅድሚያ ልባችን ለክርስቶስ ከሆነ ለሌሎች የሚኖረን ፍቅር ሁሉ በዚያ ይካተታል ከዚያም ይመነጫል፡፡ ታፈቅረኛለህን? የሚለው ጥያቄ አሁንም የአንተን/ያንቺን መልስ በመጠበቅ በውስጥህ/ሽ ያቃጭላል።