የመንፈስ ቅዱስ ሀብቶች

የመንፈስ ቅዱስ ሀብቶች

መንፈስ ቅዱስ በእኛ ላይ ሲወርድ የሚከተሉትን ሰባቱን ሰማያዊ ሀብቶቹን ያድለናል፡፡

1ኛ ጥበብ፣ በዚህ ምድር ይህን መንፈሳዊ ሀብት የሚመስል እንደማይገኝ ብርሃኑ ከፀሐይና ከጨረቃ ይልቅ እንደሚደምቅ ጥበበ ሰሎሞን ያስገነዝበናል (ጥበብ ሰሎሞን 7፡29)። ይህ ጥበብ ኃጢአት የሚያስከትለውን ጉዳት ያስረዳናል፤ ለዚህም ጉዳት መድኃኒቱን ይጠቁመናል፡፡ ምድራዊ ነገር ከንቱ እንደሆነና የዚህ ሐሳባችን እዚያው መቅረት እንደሚያስፈልገው ይነግረናል፡፡ ሥጋዊ ፍላጐታችንና ዓለምን እንዳትከተል አእምሮአችንን ያበራልናል፡፡

2ኛ ልቦና፣ ጥበብ ፍጡር ምን መሆኑን ሲገልጽልን ልቦና ደግሞ ፈጣሪ ማን መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ የፈጣሪ ትልቅነት፣ ችሎታ፣ ፍጽምና … ብዙ ነገሮችን ይገልጽልናል፡፡ በአምላክ የሚገኝ መንፈሳዊ ሰላም፣ ደስታ፣ ብፅዕና ያሳየናል፡፡ ልቦና እግዚአብሔርን አሳውቆ እርሱን እንድንወድ፣ ወደ እርሱ አቅርቦ ከእርሱ ጋር እንድንኖር ያደርገናል፡፡ “ጌታ ሆይ እዚህ ካንተ ጋር መሆን ጥሩ ነው” ማለትን ያስከትላል- ማቴ. 17፡4፡፡ እግዚአብሔር ማን እንደሆነ ስናውቅ፣ ፍቅሩን ስንቀምስ ዓለም ያስጠላናል፡፡ የአምላክ ፍቅር ጣፋጭነት ይስበናል፡፡ ፍጡሮችን ትተን ፈጣሪን ራሱን እንፈልጋለን፡፡

3ኛ እግዚአብሔር መፍራት፣ መጽሐፈ ምሳሌ የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት እንደሆነ ያስተምረናል - ምሳሌ 1፡7፡፡  “እግዚአብሔርን የሚፈራ ብፁዕ ነው” ይላል ዳዊት፡፡ ይህ ፍርሃት “እግዚአብሔርን በድየዋለሁና እንዳይቀጣኝ” የሚል ተራና ያለፍቅር የሆነ ፍርሃት ሳይሆን መንፈሳዊ ፍርሃት ነው፡፡ “እግዚአብሔር ፈጣሪያችንን፣ አባታችንን፣ ወዳጃችንን እንዳናሳዝነው” የሚል ቅዱስ ጭንቀትና ጥንቃቄ ነው፡፡ ይህ ፍርሃት ኃጢአት ከመሥራት ይገታናል፤ ጸጋ ያመጣልናል፡፡ እግዚአብሔርም የሚፈሩትን ይባርካቸዋል፡፡

4ኛ ምክር፣ ይህ አንድ ሰማያዊ ብርሃን ነው፡፡ በዚህ የምክር ሀብት መንፈስ ቅዱስ በውሳኔ በምርጫ ጊዜ አእምሮአችንን ያበራልናል፡፡ ለደኅንነታችን የሚሆነውን መንገድ እንድንመርጥ ይረዳናል፡፡ ደግሞ በፈተና ጊዜ ይመክረናል፡፡ ከክፉ ጥሩ፣ ከሥጋዊ ጥቅም የነፍስን ጥቅም፣ ከዓለም እግዚአብሔርን እንድንመርጥ ይገፋፋናል፡፡

5ኛ ብርታት፣ በዚህ መንፈሳዊ ኃይል መንፈስ ቅዱስ በችግራችን ጊዜ ይረዳናል፡፡ ይህ ብርታት  ሕይወታችንን አስተካክለንና አርመን ለመጓዝ ይጠቅመናል፡፡ የሚገባ ትጋትና ጽናትንይሰጠናል፡፡ ሁሉንም ረጋ ብለን ሳንቸኩል እንድናደርግ ይረዳናል፡፡ በጭንቀት ጊዜ መታወክን ትተን እርጋታንና ትዕግስትን እንድንላበስ ያደርገናል፡፡

6ኛ እውቀት፤ መንፈስ ቅዱስ የፍጥረትን መሠረታዊ ተፈጥሮ እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡ ሁሉ ነገር አላፊ እንደሆነ አሳውቆ ፍጡሮችን እንዳንከተልና የዓለምን ስጦታ በስስት እንዳንፈልግ፤ ሀብትን ስናገኝ ደግሞ  መጥነንና አስተውለን እንድንጠቀምበት ያስታውሰናል፡፡

7ኛ ቸርነት፣ እግዚአብሔርን ስናውቅ እንደ ፈጣሪያችን፣ አምላካችን፣ ወዳጃችን እንድናከብረውና እንድንወደው ማስተዋል እንጀምራለን፡፡ ልክ ወላጆቻችን ሕይወት ስለሰጡን ባደረጉልን መልካም ነገር ሁሉ እንደምናመሰግናቸውና እንደምናከብራቸው እንዲሁ ደግሞ ይህንን ሰማያዊ ወዳጃችንን ሁሉን የሚሰጠንና የሚያስብልንን ማመስገንና ማክበር አለብን፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለእግዚአብሔር ስግደትና ውዳሴ እንድናቀርብለት ፍላጐታችንን ትተን ፍላጐቱን እንድንፈጽም ይገፋፋናል፡፡ ሕይወታችንን በአገልግሎት እንድናሳልፈው ያሳስበናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በነዚህ በሰባቱ ሀብቶች ከእኛ ጋር አለ ወይ ከሌለ እንደገና ውስጣችንን ማለትም ሕይወታችንን በሀብቶቹ እንዲሞላልንና እንደሚገብን እንድንመላለስ መንፈሳችንን እንዲያድሰው እንማጠነው፡፡

ምንጭ፡ መንፈሳዊ ማሳሰቢያ

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።