የሰው ልጅ ፍጥረት

God-Adam

የሰው ልጅ ፍጥረት


እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጠረው፡፡ ዘፍ.1፡26-27፡፡

እግዚአብሔር ፡-

እግዚአብሔር ሁሉንም ነገሮች ያለው  በምልአት ነው፤ ሰው ግን ፍጡር እንደመሆኑ መጠን በመለኮታዊ ባሕርያት ውስጥ መሳተፍና መቀበልም የሚችለው በፍጥረት አቅም መጠን ብቻ ነው፤ ስለሆነም ማንኛውም ነገር ማለትም በሰው ቋንቋ ስለ እግዚአብሔር የሚባለው ሁሉ ትንሽ ለማመሳሰል ያህል ነው እንጂ በተመሳሳይና በበቂ ደረጃ ማስቀመጥ አይቻልም፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር ዓይን አለው ስንል ቶሎ ብሎ ወደ አእምሮአችን የሚመጣው የራሳችን /የሰው/ዐይን ነው፤…ያ ደግሞ ብዙ ጉድለት አለበት፤ ስለዚህ ስለእግዚአብሔር ስናስብ፣ ስንናገርና ስንገልጽ ማስተዋል ይጠበቅብናል ማለት ነው፡፡


ስለዚህ ሰው ዘላለማዊ ነው ስንል መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ የለውም ማለታችን ነው እንጂ ልክ እንደ ፈጣሪው ነው ማለት አይቻልም፤ በእርግጥ ነገሮች ሁሉ ከሰው ልጆች አእምሮ በላይ ናቸው። ማለትም የሰውን ከ…እስከ…ማብራራት አይቻለንም፤ ለምሳሌ ያህል ሰውን ራሱን ስንወስድ አምላክ እሱን መቼ እንዳሰበውና እንዲኖርም እንደወሰነው፤ መለኮታዊ ስጦታውና ታላቅነቱ ምን ያህል እንደሆነ… ማንም አያወቅም፤ ሆኖም ግን ሰው ዘላለማዊ መሆኑን ማንም ሊጠራጠር አይችልም፡፡ የሰው ልጅ የዘላለማዊነት ባሕርይ ነጻ የፈጣሪ ስጦታ (ጸጋ) እንጂ ከራሱ የተፈጥሮ ባህርይ የሚመነጭ/የመነጨ/ አይደለም፡፡


ይህንን ራሱ ክርስቶስ በግልጹ አስቀምጦታል፤…. እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ…የሐ.6፡5።

በሌላ በኩልም ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይናገራል፤ እግዚአብሔር ዓለምን እጅግ ስለወደደ አንድያ ልጁን ሰጠ፤….ዮሐ.3፡16፡፡


ሐዋርያ ጳውሎስም ይህንኑ በሚያሰገርም ሁኔታ ይገልጻል እንዲህ ሲል፤ በሰማይ መንፈሳዊ በረከትን በመስጠት በክርስቶስ  የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር አባት የሆነው አምላክ ይመስገን፡፡ ቅዱሳንና ነቀፋ የሌለብን ሆነን በፊቱ እንድንገኝ፤ ዓለም ሳይፈጠር በክርስቶስ መረጠን፡፡ ኤፌ.1፡3-4፡፡


የክርስቶስ ሰው መሆን በራሱ ሰው ዘላለማዊ ዋጋ ያለው ለመሆኑ የመጀመያርውና የማያዳግም ማስረጃ ነው፤ ማለትም ክርስቶስ ሰው የሆነውና በሰው ልጆችም ታሪክ ውስጥ ለመጋባት የፈለገውና የተትረፈረፈ ሕይወት እንዲያገኙ… ነው ያለው ያም ሕይወት እሱ ራሱ እንደሆነና ያንንም ሕይወት የሚኖር ዘላለማዊ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ዮሐ.10፡6፡፡


ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣው እንዲሁ ለጊዜያዊ ነገር ብቻ ቢሆንማ ኖሮ ምንም አያስገርምም ነበር፤ ምክንያቱም ሞቶ ከሞት ያስነሣቸውም ሰዎች ተመልሰው ሞተዋል ማቱሰላም ምንማ ያህል ረጅም ዕድሜ ቢሰጠውም ሞት አልቀረችለትም፤ እንዱሁም ዓለም እስከምታልቅ ድረስ እያንዳንዱን ሰው ከሞት ካስነሣ በኋላ ሁሉም ተመሳሳይ ዕድል ተሰጥቶአቸው ከዚያ በኋላ ሁሉም አለቀ… ሆኖ በቀረ ነበር ማለት ነው፡፡


እንደዚህ እንዳልሆነ ነው ቅድስት ቤተክርስቲያንም እንዲህ በማለት የምታስተምረን:-

ማን ፈጠረን? - እግዚአብሔር፡፡

ለምን ፈጠረን? - እንድናውቀው፤ እንድንወደው፤ ትእዛዙንም ፈጽመን/ጠብቀን/ መንግሰተ ሰማይ እንድንገባ፡፡

የሰው ፍጻሜዎች ስንት ናቸው? - አራት ናቸው እነሱም፡-

ሞት፤ ፍርድ፤ ገሃነመ እሳት፤ መንግሥተ ሰማያት፡፡

እንግዲያውስ ያ መንግሥተ ሰማያት የሚባለው ነው ዘላለማዊ ነው የምንለው፡፡ ዘላለማዊ ማለትም

ራሱ የእግዚአብሔር ሌላ ስሙ ማለት ነው፡፡

ስለዚህ የሰው ልጅ የመጨረሻው ደሞዙ ምንድነው ከተባለ እግዚአብሔር ራሱ ነው ማለት ነው፡፡

ያንን ደመወዝ አለማግኘት እንግዲህ ምንና ምን ያህል ኪሳራ መሆኑን የሚያውቅና የሚሠራ እንዴት ያለ ጥበበኛ ነው ማለት ይቻል ይሆን! ስለመፈጠሩ ማወቅን ችላ ብሎ፣ ፈጣሪውን እያወቀ እንዳላወቀ መሆንስ … ምን ዓይነት ዕድል ሊሆን ይችላል? ያላወቀ እውነትም አላወቀም ነው፤ ያወቅነውስ?

ሰው ክቡር መሆኑን አላወቀም እንስሳንም መሰለ ይላል ቃለ እግዚአብሔር፡፡


አባ ገብረወልድ ወርቁ - ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን። አዲስ አበባ