እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የኢየሱስ ጥምቀት ምሳሌነት

የኢየሱስ ጥምቀት ምሳሌነት

ቅዱስ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ አይሁዳውያንን ሲያጠምቅ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተራ ሰው መስሎ መጣ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ገርሞት “እኔ ነኝ በአንተ ልጠመቅ የሚገባኝ እንጂ አንተ እንዴት ወደ እኔ ትመጣለህ?” ማቴ. 3፡14-15 በማለት ማጥመቁን እምቢ አለ፡፡ ኢየሱስ ግን “አሁንስ ተው አትከልክለኝ የምጠይቅህን ጥምቀት ስጠኝ፡፡ ምክንያቱም ሕግን ሁሉ መፈጸም  ተገቢ ነው፡፡” ሲለው የጥምቀት ውኃ በራሱ አፈሰሰበት፡፡ ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወደያው በራሱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ፡፡ ሰማይም ተከፈተ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ማቴ. 3፡17 የሚል ድምጽ ከሰማይ መጣ፡፡

baptism_1_frontኢየሱስ የተጠመቀው ግዳጅ ስለነበረበት አይደለም፡፡ ሕግን ሁሉ መፈጸም እንዳለበት በተለይ ደግሞ ምስጢረ ጥምቀት ለደኀንነታችን የግድ አስፈላጊ መሆኑን ሊያስተምር ፈልጐ ነው፡፡ ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ እንደገና ካልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይችልም” ዮሐንስ 3፡5 ሲል ተናገረው እንዲሁም “ወደ ዓለም ሙሉ ሄዳችሁ ወንጌልን ለሕዝብ ሁሉ ስበኩ በአብ፣ በወለድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው፡፡ ያመነና የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ግን ይፈረድበታል” ማር. 16፡16

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ከዮርዳኖስ ወንዝ ሳይወጣ እዚያው ቆሞ እያለ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ ወረደ፡፡ “በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው” እያለ እግዚአብሔር አብ ተናገረ፡፡ ይህ ጥምቀት በሚቀበል በእያንዳንዱ ሰው ይደገማል፡፡ እኛ ጥምቀትን ስንቀበል መንፈስ ቅዱስ በማይታይ ሁኔታ በእኛ ላይ ይወርዳል፡፡ እግዚአብሔር ያን ጊዜ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” እያለ ተሰስቶ ይቀበለናል የላቀና የጠለቀ ደስታውን ይገልጣል፣ የእግዚአብሔር ልጆችና የመንግሥተ ሰማያት መራሾች ያደርገናል፣ በጥምቀት ጸጋ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከባርነት ወደ ነጻነትና ጽድቅ እንሻገራለን፣ የቅድስት ሥላሴ ማደሪያና ምድራዊ መኖሪያ እንሆናለን፡፡ ጥምቀት ስንት መንፈሳዊ ሀብትና ጸጋ እንደሁም ከፍ ያለ የእግዚአብሔር ልጆች ክብር ይሰጠናል፡፡

ግን ምድራዊ ሀብት ጠንቀቅ ብለን ካልጠበቅነው ሊጠፋና ሳንጠቀምበት ሊቀር እንደሚችል እንዲሁም የጥምቀት መንፈሳዊ ሀብት ተግተንና ነቅተን ካልሰራንበት ጥቅም ሳይሰጠን ባክኖ ሊቀር ይችላል፡፡ ጥምቀት ስለተቀበልን ድነናል ብቁዎችም ሆነናል መንግሥተ ሰማያትን ወርሰናል ማለት አይደለም፡፡ ደኀንነታችን ፍጹም እንዲሆን መንግሥተ ሰማያት እንድንገባ በበኩላችን በደካማ አቅማችን በሚፈቅደው ያላሰለሰ ጥረትና ትግል ማድረግ አለብን፣ የደኀንነታችን መሠረት ልንቀጥለውና መልካም ፍሬ እስከሚሰጥ ድረስ ልናሳድገው እንዲሁም ግራና ቀኝ ሳንል በደኀንነት ጐዳና እንድንጓዝ ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህ አንድ ጊዜ ጥምቀት ተቀብለናል፣ ተጠምቀናል ይበቃናል፣ አሁንስ ለዘለዓለም ድነናል ብለን ከመንፈሳዊ ጥረት ውጊያ ተግባር ማረፍና ማቋረጥ አይገባንም፡፡ በጥምቀት ጸጋ ተመርተን እንድንሄድና ኑሮአችን ከሕይወታችን አረማማድ ከመንፈስ ጥምቀት እንዲስማማ ማድረግ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ “እምነት ያለሥራ የሞተ ነው” ያዕቆብ 2፡26 እያለ ያስጠነቅቀናል፡፡

ቤተክርስቲያን ስንጠመቅ “በዘለዓለም ሕይወት ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመውረስ ከፈለግህ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ጠብቅ፣ እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ ውደድ፣ ባለንጀራህንም እንደራስህ አድርገህ ውደድ፤ ሰይጣንና ሥራውን ሁሉ ካድ በኢየሱስ እመን” እያለች ታስጠነቅቀናለች፡፡ እኛም ደግሞ እክዳለሁ ... አምናለሁ ...” እያልን እንመልስላታለን፡፡ እንግዲህ ቃላችንን እንጠብቅ መሐላችንንና እምነታችንን ፍሬ አፍርተን በተግባር እናሳይ፡፡ ያን የጥምቀት ጸጋ በበለጠ ጥረት ኰትኩተን እናዳብር፡፡

መልካም የጥምቀት በዓል ይሁንልን፡፡ አሜን፡፡

ምንጭ፡ መንፈሳዊ ማሳሰቢያ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት