የኢየሱስ ሕማማት

ኢየሩሳሌም በጠላቷ ተሸንፋ ስትወድቅ ኤርሚያስ በጣም አዝኖ በመንገድ ላይ ቁጭ ብሎ “እናንተ በመንገድ የምታልፉ ሁሉ… ሐዘኔን የሚመስል ሐዘን እንዳለ አስተውሉ” ሰቆ. ኤር. 1፡12 እያለ አምርሮ ያለቅስ ነበር፡፡

ቤተክርስቲያን በዚህ አጋጣሚ ይህንን የኤርምያስ ቃል እየጠቀሰች የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሐዘን፣ ስቃይና ሞት እንድናስብ ትጠራናለች፡፡ ቃሏን ሰምተን ወደ ኢየሱስ ሕማማት እንሂድ፡፡ ቅዱሳን  እንደሚሉት ከሁሉ የበለጠ የሐሳብ ጸሎትና ለመንፈሳችንም ጠቃሚው ልምምደ የኢየሱስን ሕማማት ማስተንተን ነው፡፡ “ከሁሉ የበለጠ ለደኅንነታችን የሚጠቅመንና ብዙ የሚረዳን ነገር የአምላክ ልጅ ስለ እኛ የተሰቃየውን ማሰብ ነው” ይላል ቅዱስ አጉስጢኖስ፡፡ “የሕሊናችንን ቁስል ለማከምና ነፍሳችንን ለማንጻት ከኢየሱስ ቁስሎችና ስቃይ ሞትን ከማሰብ የሚበልጥ የለም” በማለት ቅዱስ በርናርዶስም ይናገራል፡፡ ቅዱስ ቦናቨንቱራ ደግሞ “የኢየሱስን ሕይወት የተቀደሰ ሕማማቱን የሚያስብ የፈለገውን ያገኛል” ይላል፡፡ ኢየሱስ ራሱ ደግሞ ለቅድስት ዠልትሩድ “መስቀሌን በመንፈሳዊነት የሚመለከቱን እኔ በምሕረት ዓይኔ እመለከታቸዋለሁ” አላት፡፡ በእነዚህ መንፈሳዊ ምክሮች ተነሣሥተን ለእኛ ብሎ ተሰቃይቶ የሞተውን አምላክ ለማስታወስና ለመውደድ ትጉሆች እንሁን፡፡

በመንገድ የምታልፍ ሁሉ ሐዘኔን የሚመስል ሌላ ሐዘን እንዳለ አስቲ አስተውል፡፡ አዎ ኢየሩሳሌም ብዙ ግፍ ቀምሳ ተሰቃየች፡፡ ግን ይህ ሁሉ ኢየሱስ ከቀመሰው በእርሱ ላይ ከደረሰው ግፍና ስቃይ ሊወዳደር ሊስተካከል ፈጽሞ አይችልም፡፡ ቅዱሳንና ቴዎሎጂያውያን እንደሚያስተምሩን ኢየሱስ በሕማማቱ ጊዜ የተቀበለው ውርደት፣ ስቃይ፣ ሐዘን ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ፣ ሰው በልዩ ጸጋ እንጂ በኃይሉ ሊሸከመው  የማይችል ነው፡፡ ይህ ስቃይ ለኢየሱስ ሰው እንደ መሆን መጠን ተሰማው፡፡ “አምላኬ ሆይ! አምላኬ ሆይ! ለምን ተውኸኝ?” ማቴ. 27፡47 እስከሚል ድረስ ተሰቃየ፡፡ “ባየነው ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም፡፡ የተጣለ ከሰውም የተናቀ፣ መከራ የደረሰበት የተዋረደ ሰው ነው… መከራችንን ተሸክሞ ስለ እኛ ተሰቃይቶ አይተናል፡፡ በኃጢአታችን ቆስሎ፣ ተሰቃይቶ ሰላማችን በእርሱ ሆነ፣ ይህን ሁሉ መከራ እግዚአብሔር ስለ ኃጢአታችን ብሎ ሰጠው፡፡ ከእግሩ እስከ ራሱ ድረስ የቆሰለ አካሉ ለምን” ይላል ኢሳ. 53፡3

የኢየሱስ ሕይወቱ ሙሉ ስቃይና መስቀል ነበር፡፡ ሲወለድ በስቃይ መሃል ተወለደ በስቃይ መሃል አደገ፣ ሲሞትም ሊነገር በማይችል ስቃይ ሞተ፡፡ “እኛ ሞት የማይገባው ሞትን ስቃይ የማይገባው ስቃይን በፈቃዱና በአባቱ ፈቃድ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ እንደሰጠው እንናገራለን፡፡ የአምላክን ልጅ ይዘው አሠሩት፣ ወስደው ፍርድ ፊት አቆሙት፣ እንደ በደለኛ ከሰሱት፣ ሊያላግጡበት ብለው ሰገዱለት፣ በጥፊም መቱት፣ በሁለት ወንጀለኞችም መካከል ሰቀሉት” ይላል ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡፡ ይህ ሁሉ ውርደት በፈጣሪ ላይ ወረደ፡፡ ይህ ሁሉ ስቃይ የሁሉ የነገሥታት ንጉሥ በሆነው በአምላክ ልጅ ላይ ወረደ፡፡ ፈጣሪ በፍጡሮች ተዋረደ፡፡ ይሁዳ አሳልፎ ሰጠው፣ አይሁዳውያን አሰቃዩት፣ ጲላጦስ ሞት ፈረደበት፣ ወታደሮቹ ገረፋት፣ በመስቀል ላይ ሰቀሉት፣ መንገደኛ ሁሉ ሰደበው፣ አላገጠበት፣ በክፉታችን ሰበብ ተሰቃየ፣ እኛን ከአባቱ ጋር ሊያስታርቅ ይህን ሁሉ መከራ ተቀበለ፡፡

ምንጭ:- መንፈሳዊ ማሳሰቢያ