እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የአባ ስብከትና እኛ

መግባቢያ

sbket-2አንድ ቦታ አባ ይሰብካሉ፤ እኔም በግማሽ ጆሮዬ እና በግማሽ ልቤ የአባን ስብከት እየኮመኮምኩ በግማሽ ልቤ አንዲት ወጣት ላይ ተመስጬ ነበር፡፡ ወጣቷ ቆንጆ የምትባል አይደለችም (እርሷስ ምን ብላኝ ይሆን?)፣ የለበሰችው ግጥም ያለ ሐበሻ ቀሚስ በመሆኑ መቼም በሌላ ነገር ከቶ እንዳልጠራጠር ያግዘኛል፡፡ ታዲያ ምን ሆኜ ነው ልቤን ሁለት እኩል ቦታ ከፍሎ ግማሹን ለአባ ስብከት ግማሹን ለእርሷ ካቶሊካዊነት ሰጥቼ ቁጭ ያልኩት?

ወጣቷ ክፉኛ ተበሳጭታለች፤ ከእርሷ የሰውነት ይዘት በላይ ጉንጯ እስኪቀደድ ድረስ ቁና ቁና ትተነፍሳለች፤ አስሬ ትቁነጠነጣለች፣ አያልቅም እንዴ? ብላ አጠገቧ የተቀመጠችውን ወጣት ጠየቀቻት፤ ወጣቷ ጥያቄውን ከመመለስ ይልቅ እርሷን በላይ በላይ ትተነፍስ ጀመር፡፡ የ‹‹ኡፍፍ›› መዓት በዓይነቱ ቀጠለ... ኡፍፍ.... ኡፍፍ... በኢየሱስ ስም ኡፍፍ... ሁለቱ ወጣቶች ከበስተኋላዬ ስለነበሩ ነፋስ ጆሮዬን ሲያነቃንቀው ይህ ነገር በመደዳ ከሆነ እኔም ‹‹ኡፍፍ!›› ልበል እንዴ? የሚል ተባራሪ ሐሳብ ነካ አርጎኝ አለፈ፡፡ {jathumbnail off}

ምስኪን አባ በፈገግታ ይሰብካሉ! ይህንን በኢየሱስ ስም የታጀበ መንፈሳዊ ‹‹ኡፍፍታ›› ቢሰሙ ‹‹እናንተ ሸክም የከበዳችሁ... ይሉ ይሆን?›› አያልቅ የለምና ምስኪን አባ ከሁለቱ ወጣቶች ያልተመዘነ የ‹‹ኡፍፍታ›› ክምር በኋላ የዕለቱን ስብከት ጨርሰው ወደ ወንበራቸው ሲያዘግሙ ከጀርባዬ የነበረው ‹‹ኡፍፍታ›› ወደ ‹‹ጐሸሽታ›› ተቀየረ፡፡ ከዚያስ? የአስተያየት መዓት... ነጻ አስተያየት.. ያረረ አስተያየት... ልማታዊ አስተያየት፣ ጥራዝ ነጠቅ አስተያየት፣ ፉከራ አዘል አስተያየት... ቁጭት የወለደው አስተያየት ወዘተ... ሁለቱ ወጣቶች ይህንን ሁሉ አስተያየት የሚሰጡተ ከቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውጪ ወደ ቤት በእግር እያዘገሙ፣ ከጨዋ ኮረዳ የድምፅ ልኬት ትንሽ ከፍ ባለ ኃይል ቃል ስለነበር እኔ ከበስተኋላቸው ስከተል ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ አድማ እንዳይመስል ሰግቼ መንገድ ቀየርኩ፡፡ መልካም ጉዞ፡፡

የአስተያየታቸውን፣ የብስጭታቸውን እና የኡፍፍታቸውን መነስኤ እስካሁን ስላልነገርኩህ አንተ ራስህ አንድ ‹‹ኡፍፍ››ታ እንደምተጨምር ተስፋ አለኝ፡፡ ታዲያ አባ ስለምን ቢሰብኩ ነው? ምን ነካቸው? ወይ አባ! ምን ብለው ይሆን?

በመሠረቱ አባ በዛሬው ስብከታቸው እጃቸውን ጭነው በመጸለይ የማንንም ራስ ምታት አላስለቀቁም፣ ከምዕመናን መካከል የተቀደደ መቶ ብር የያዘ አንድ ሰው ወደ መንበረ ታቦቱ ጠርተው በዚህ በተቀደደ መቶ ብር ፈንታ ጌታ ብዙ እንደሚያበለጽገው አልተነበዩም፣ ወይም ራሳቸው መጠነኛ መንፈሳዊ ውዝዋዜ የሞላው ስብከት አልሰበኩም፤ ሮጥ፣ ዘለል፣ ሄድ፣ መለስ (ጠብቆ ይነበብልኝ አደራ) እያሉ መጠነኛ ስብከተ ወንጌላዊ ትወና አላሳዩም! አባ ምን ነካቸው? ራሳቸው ሮጥ፣ ዘለል፣ ቁጭ፣ ብድግ፣ ሄድ፣ መለስ ማለት ባይችሉ እንኳን ‹‹እስቲ ጠጋ ጠጋ ብላችሁ ተቀመጡ›› በማለት ምቹ ሁኔታ ፈጥረው ሕዝቡን ቢያንቀሳቅሱ ምን ነበረበት?

ታዲያ እንግዲህ አባ ምን አድርገው ነው? እንጃ! ብቻ ግን በዛሬው ስብከታቸው ስለ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አስተምሕሮ፣ የጸሎት ሐሳብ እና ር.ሊ.ጳ. ለሁላችንም ስላበረከቱት ‹‹የወንጌል ደስታ›› ስለተሰኘው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው (መቼም ደርሶህ አንብበኸዋል!) ወዘተ ሰበኩ፡፡ እና ምን ይሁን! ምን ይሁን? ሁለቱ ሴቶች እኮ ብስጭት ያሉት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ብሸቅ፣ እርር፣ ድብን (ጠላት ብሽቅ፣ እርር፣ ድብን ይበልና) ያሉት ስለ እርሳቸው ብዙ በመስማታቸው ነው፡፡ ሁለቱ ሴቶች ሲነጋገሩ እንደሰማሁት እና በቅንነት እንደተረዳሁት ‹‹የንግሥ በዓል እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ምን አገናኛቸው? እርሳቸው እንዲህ አሉ፣ በዚህ ገቡ፣ በዚህ ወጡ፣ እዚህ ደረሱ ከማለት ‹ቃል› መስበክ አይሻልም? ቃሉ ለእኛ ምን ይላል የሚለውን ቢነግሩን ጥሩ ነበር! ብቻ እኛ ቤተክርስቲያን ‹የቃል› እጥረት አለ፤ ‹ቃል› አይሰበክም!››

ምስኪን አባ ይሄ ሁሉ አስተያየት እርሳቸው ጋር ሳይደርስ እኔ ላይ ወቀደ፡፡ ታዲያ ጎበዝ! ይሄ ነገር ውሎ አድሮ ያንገበግበኝ ጀመር! አንድ ሌሊት በጥናት ጠረጴዛዬ ላይ እያነበብሁ ሳለ በጠረጴዛዬ ላይ የተጋደመው መስታወት ሥር ያሉትን ካቶሊካዊ ምስሎች ስመለከት የር.ሊ.ጳ.ዮሐንስ 23ኛ፣ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ የቤኔዲክቶስ 16ኛ፣ የብጹዕ ካርዲናል ሄነሪ ኒውማን፣ የአቡነ ብርሃነ ኢየሱስ፣ የአቡነ ጸጋዬ ቀነኒ፣ (የአቡነ ልሣነ-ክርስቶስ ሮፎ የለም፣ ምናልባት ቶሎ ቶሎ በአካል ስለማገኛቸው ይሆናል) እና የር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ ፎቶዎች አሉኝ ለካ! ለምን አስቀመጥኳቸው? ምናልባት በየአጋጣሚው ሲታደል ለምዶብኝ ይሆን? እንግዲህ ቀደም ብዬ የገለጽኩት የሁለቱ ሴቶች ብስጭት በጠረጴዛዬ ላይ ከተደረደሩት ፎቶዎች ጋር ተደማምሮ ስለ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ማንነት ከፍቅር ቃላት ሳይሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት ጋር አጣቅሼ ለመጻፍ ጌታ አነሣሣኝ፡፡

እንግዲህ ከሲታውያን አባቶቼ መነኮሳን የቃረምኩትን እና ከታላቁ አቡነ ቡሩካዊ ልግስናቸው ያካፈሉኝን ሐብት ‹‹አቤቱ ልቤ አይታበይብኝ፣ ዐይኖቼም ከፍ ከፍ አይበሉብኝ›› እያልኩኝ እያንዳንዱን ያረካው ዘንድ ሳይሆን የእያንዳንዱን መንፈሳዊ ረሐብ ያቀጣጥል ዘንድ ስለ ር.ሊ.ጳ. ካቶሊካዊ ማንነት እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ግልጠት እጽፋለሁ፡፡

ቤተ-ክርስቲያን

ቤተ-ክርስቲያን በጉዞ ያለው የእግዚአብሔር ሕዝብ ማኅበር ናት፡፡ እርሷም በአንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተች አንዲት (ማቴ.16፡18)፣ በእርሱ ዘላለማዊ ቅድስና የተሸለመች ቅድስት (ኤፌ.5፡26)፣ አዳኟ ለሁሉም ሞቶ በደሙ ገዝቷታልና የሁሉ የሆነች ካቶሊካዊት (ኤፌ.2፡19)፣ ወደ ዓለም ሁሉ ሄደው ወንጌልን የመስበክ አደራ ከክርስቶስ በተቀበሉት አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት በዓለም ዙሪያ የተገለጠች ሐዋርያዊት (ኤፌ.2፡20)፣ እና እስከ ዓለም ዳርቻ ደርሳ ወንጌልን ለመስበክ የተጠራች ሚሲዮናዊት (ማቴ.28፡19)፣ ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡

እግዚአብሔር ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ እስከ ዘለዓለም ድረስ ‹‹ሰው ብቻውን መኖሩ መልካም አይደለም›› (ዘፍ.2፡18)፣ ስለዚህ ‹‹ተስማሚ እና ረዳት ጓደኛ ያስፈልገዋል›› (ዘፍ.2፡18) በማለት የሰውን ማኅበራዊ ገጽታ እና ካቶሊካዊ ተፈጥሮ ይገልጣል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ቅዱስ አድርጎ በተናጥል፣ አንዱ ከሌላው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እና ትሥሥር ሳይኖረው ይድን ዘንድ አላደረገም፡፡ ይልቁንም የሰው ልጆችን አንድ ሕዝብ በማድረግ ይደሰታል፡፡ ስለዚህ የእስራበኤልን ነገድ የራሱ ሕዝብ አድርጎ መረጠው፣ ከእርሱም ጋር ቃልኪዳኑን አፀና፡፡ (LG 9) ብሉይ ኪዳን እስራኤልን ‹‹የእግዚአብሔር ሕዝብ›› እያለ ይጠራዋል፡፡ እግዚአብሔር እስራኤልን በቀይ ባሕር መካከል አሻግሮ እራሱ ባዘጋጀው ምድር በማስፈር የራሱ ንብረት አድርጎታል፡፡ የእስራኤል የእግዚአብሔር የተመረጠ ሕዝብ የመሆን ጥሪ ክርስቶስ ‹‹በደሙ›› ለሚመሠርተው አዲስ ኪዳን ምሳሌ ነው፡፡ በዚህ አዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የመሆን እና የመዳን ጥሪ ለአንድ ሕዝብ፣ ለአንድ ነገድ ወይም ለአንድ ምድር የተቀመጠ ውርስ ሳይሆን ለሰው ዘር ሁሉ ያለ ልዩነት የቀረበ የመዳን ጥሪ ሆኗል፡፡ የብሉይ ኪዳን ድንግዝግዝ ግልጠቶች በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር ቃል ሥጋ ለብሶ የመገለጥ እውነታ ውስጥ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል፤ ይህ ሥጋ የለበሰው ቃል ሁሉንም በደሙ ማሕተም አትሟል፤ ‹‹ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው››፡፡ በዚህ ዓይነት የአዲስ ኪዳን ራስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁዳዊ እና በአረማዊ መካከል ምንም ልዩነት ሳያደርግ በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ አንድ ሕዝብ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም አዲሱ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆኗል፡፡

ይህ አዲሱ የእግዚአብሔር ሕዝብ ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ በመስቀል ሞት የገዛ ንብረቱ አድርጎ ይህንን ሕዝብ በመንፈሱ በመቀደስ በሚታይ ማህበራዊ ትሥሥር ለዘላለሙ አንድ አድርጎታል፡፡ እስከ ዓለም ፍጻሜ እርሱ ከዚህ ሕዝብ ጋር እንደሚጸና ቃል ገብቷል፡፡ (ማቴ.28፡20) በዚህ አዲስ ቃልኪዳን አማካኝነት ቤተ-ክርስቲያን ለዓለም ሁሉ የተከፈተች የመዳን በር ሆናለች፡፡ የአዲስ ኪዳን ሕዝበ እግዚአብሔር የተመሠረተው በክርስቶስ የማዳን ሥራ ነው፡፡ እርሱ ራሱ በምድር ላይ በተመላለሰበት ዘመን እና ወደ ክብሩ በገባበት ወቅት ለዓለም ሁሉ ያበረከታት የመዳን ምሥጢር ቤተ-ክርስቲያን ናት፡፡ በእርሷ ውስጥ እና በእርሷ በኩል የእርሱ ምሥጢራዊ ሕልውና ዘለቄታዊ ይሆናል፡፡ በመሆኑም የቤተ-ክርስቲያን ጉባኤ፣ አዲሱ ሕዝበ እግዚአብሔር ኢየሱስ የመዳን ሁሉ ምንጭ መሆኑን እና የሰላም፣ የአንድነት ምልክት መሆኑን በእምነት ዐይን ይመለከታል፡፡ እንግዲህ አዲሱ ሕዝበ እግዚአብሔር ሆና በኢየሱስ ክርስቶስ በመመረጧ ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር ለመላው የሰው ዘር ያለውን አባታዊ ፍቅር እና ምሕረት ማሳያ ምልክት ሆናለች፡፡ ይህም የሰው ዘር በሙሉ በቤተ-ክርስቲያን በኩል በክርስቶስ ክህነት፣ ነብይነት እና ንግሥና ውስጥ ሱታፌ ይኖረዋል፡፡

ይቀጥላል - ከመ/ር ሳምሶን ደቦጭ - ቅ. ዮሴፍ ቁምስና ዘሲታውያን አ.አ.

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት