የኃጢአት እሳት መለኮታዊውን እሳት አይቋቋመውም

17.1 - በትልቁ (መለኮታዊው) እሳት የተያያዘውን አማኝ ትንሹ እሳት ሊጎዳው አይችልም

ስለ መለኮታዊውና ዓለማዊው እሳቶች በምናስብበት ወቅት ፍፁም ልንረሳው የማንችለው ነጥብ ቢኖር፥ ዘለዓለማዊው የመንፈስ ቅዱስ እሳት የድል ኃይል መሆኑን ነው፡፡ በየትኛውም ዓይነት አቅጣጫ ብናስብ፥ መለኮታዊው ከፍጥረታዊው፣ ዘለዓለማዊው ከጊዜያዊው፣ እንደሚበረታ፥ እንዲያውም ሊነጻጸሩ የማይችሉ ነገሮች መሆናቸውን ከማወቅ የሚከለክለን ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ በመለኮታዊውና በፍጥረታዊው ነገሮች መካከል ያለው ልዩነት፣ በሁለቱ እሳቶች መካከልም የሚታይ ጉልህ እውነታ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችንም ይህን ያረጋግጥልናል፡፡

በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ ሦስት ላይ እንደምናነበው የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ቁመቱ 60 ክንድ ወርዱም 6 ክንድ የሆነ የወርቅ ምስል (ጣዖት) አሠርቶ በአንድ አደባባይ ላይ ያቆመዋል፡፡ አዋጅ ነጋሪውም ለዚያ ምስል ተደፍቶ የማይሰግድ ሰው በሙሉ፥ እጅግ ታላቅ በሆነ እቶን ውስጥ በሚቀጣጠል እሳት ውስጥ ተጥሎ እንደሚገደል ያውጃል፡፡ ይህን አስፈሪ የንጉሥ አዋጅ በመፍራትም አሕዛብ ሁሉ በግንባራቸው መሬት ላይ በመውደቅ ለወርቁ ምስል ይሰግዳሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ትርምስ ውስጥ ሳይሰግዱ ቀጥ ብለው የቆሙ ሦስት ወጣቶች ይገኛሉ፡፡ እነርሱም የእውነተኛው አምላክ የእግዚአብሔር አገልጋዮች የነበሩት፣ ሲድራቅ፣ ሚሳቅ እና አብደናጎ የተሰኙት እስራኤላውያን ምርኮኞች ነበሩ፡፡ ከለዳውያኑም ወደ ንጉሡ ቀርበው ይከሷቸዋል፤ ነገሩ በተመረመረ ጊዜም በእርግጥ ለምስሉ እንዳልሰገዱ ይታወቃል፡፡ ንጉሡም "ተደፍታችሁ ላሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው፤ ባትሰግዱ ግን በዚያ ጊዜ በሚነድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው?" ብሎ ያስፈራራቸዋል (ዳን. 3፡15)፡፡ የነርሱ መልስ ግን ቁርጥ ያለ ነበር፡፡ "‹የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል... ነገር ግን እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ› አሉት" (ቁ. 17-18)፡፡ ስለዚህ እሳቱ የባሰ ሰባት እጥፍ እንዲነድ ተደረገ፤ እነርሱም ወደ እሳቱ ተጣሉ፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል? መለኮታዊ እሳትና ፍጥረታዊ እሳት መች ይዳረሱና! በነርሱ ልብ ውስጥ የሚነደው መለኮታዊ እሳት እጅግ ብርቱ ከመሆኑ የተነሣ በዙሪያቸው ይንቀለቀል የነበረውን የእሳት ወላፈን እንደ ኢምንት ስላደረገው፥ እንኳን ሊያነዳቸው የፀጉራቸውን ጫፍ እንኳ ሊነካ አልቻለም፡፡ በነርሱ ልብ ውስጥ ይነድ የነበረውን እሳት ቴርሞሜትር ሊለካው አይችልም ነበር፡፡ በዙሪያቸው ይነድ የነበረውን እሳት ግን ሊለካው ይችላል፡፡ በሁለቱ መካከል ዘለዓለማዊ ልዩነት ነበር፡፡ ስለዚህም ምንም ሳይጎዱ በሚነድደው የእሳት እቶን ውስጥ ይመላለሱ ነበር፤ አንድ መልአክም አብሯቸው ይመላለስ ነበር፡፡ በትልቁ እሳት አስቀድመው ተያይዘው ስለነበር ትንሹ እሳት (ምንም እንኳ ሰባት እጥፍ ቢነድ ፍጥረታዊ ሰለሆነ ትንሽ ነው በመለኮታዊው እሳት ፊት ሲታይ) አልጎዳቸውም፡፡ በአንፃሩ እነርሱን ወደ እቶኑ የጣሏቸውን ወታደሮች ግን በሩቁ የእሳቱ ወላፈን በላቸው፡፡ ምን ዓይነት እሳት ቢሆን ነው በውስጡ ያሉትን ሳይነካ በርቀት ያሉትን የሚፈጅ? ለነገሩ እንኳ፥ በውስጡ የነበሩት እነ ሲድራቅ በእርግጥ በርሱ ውስጥ (በቁጥጥሩ ሥር) አልነበሩም፡፡ ምክንያቱም በመለኮታዊው እሳት ሥር ስለነበሩ ነው፡፡ እነኛ ወታደሮች ግን በቦታ ራቅ ብለው ቢገኙም በውስጡ (በቁጥጥር ሥር) ነበሩ፡፡ ምክንያቱም መለኮታዊው እሳት በውስጣቸው ስላልነደደ፥ በውስጣቸው ይቀጣጠል የነበረው የሥጋ እሳት ብቻ ነበር፡፡ በአጭሩ በትልቁ እሳት የነደደውን ትንሹ ሊጎዳው አይችልም፤ ያልነደደውን ግን እጅግ ትንሿ እሳትም ታጋየዋለች፡፡

ይህን የሲድራቅን ታሪክ ወደኛ ዕለታዊ መንፈሳዊ ጉዞ አስገብተን ብናየው፥ በመንፈስ ቅዱስ እሳት ተቀጣጥለን መከራና ፈተና በበዛበት ሁኔታ ውስጥ እንኳ ብንገኝ የፈተናው እሳት ያጠራናል እንጂ አይጎዳንም፡፡ በአንፃሩ ግን በሥጋ እሳቶች (ለምሳሌ በፍትወት እየተቃጠልን) ፈተና በሌለበት ቦታ እንኳ ብንገኝ፥ ወዳቂዎችና ፈተናውን ራሳችን ፈልገን ቀስቃሾች ሆነን እንገኛለን፡፡ በትልቁ እሳት የተቀጣጠለውን ትንሹ ሊያጠፋው አይችልም፡፡ ምክንያቱም በዓለም (በፈተና በችግር) ውስጥ ቢገኝም፥ እርሱ ግን ከዓለም [ከፈተናው ከእሳቱ (ትንሹ እሳት ማለት ነው)] ወገን አይደለምና!

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።