የኃጢአት ምክንያት

የኃጢአት ምክንያት

በእግዚአብሔር ፊት ንስሐ ስንገባ “በኃጢአቴ ስለ በደልኩህ እጅግ አዝኜአለሁና ማረኝ ዳግመኛ ወደ ኃጢአት አልመለስም በጸጋህ ከኃጢአት ምክንያት ሁሉ እርቃለሁ” እንላለን፡፡ በሠራነው ኃጢአት ተጸጽተን ዳግም ወደ እርሱ እንዳንመለስ ወደ ኃጢአት ከሚወስደን ምክንያት ሁሉ ለመሸሽ ቁርጥ ፈቃድ እናድርግ፡፡ ይህ ግዴታ አስፈላጊ ነው፣ ምክንያቱም ኃጢአትን የምንጠላ ከሆነ ወደ እርሱ የሚመራንን ምክንያት ደግሞ ልንጠላው ይገባናል፡፡ ልብሳችን አንዳይቆሽሽብን ብንፈልግ ሊያቆሽሽብን ከሚችል ነገር ሁሉ መራቅ ያስፈልገናል፡፡

ከበሽታ ለመዳን መድኃኒት መፈለግ ብቻ አይበቃም፡፡ የበሽታ ጠንቅ ከሚሆን ነገርና ከመድኃኒቱ ጋር የማይስማማ ነገር ሁሉ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ እንዲሁም ደግሞ በኃጢአት እንዳንወድቅ ከፈለግን ከኃጢአት ምክንያቶች ሁሉ ልንርቅ ይገባናል፡፡ የኃጢአት ምክንያቶችን የማንሸሻቸው ከሆንን ከክፉ ሥራ መራቅን የማንጠላ በኃጢአት መውደቅን የምንፈቅድ መሆናችንን ይገልጻል ማለት ነው፡፡ ከኃጢአት አጠገብ፣ ከክፉ ጓደኞች አጠገብ ቀርበን በኃጢአት ሳትወድቅ መቅረብ ዘበት ነው፡፡ በባሕሪያችን በጣም ደካሞች ስለሆንን እንሳሳታለን፣ በኃጢአትም እንወድቃለን፡፡ ቅዱስ በርናርዶስ በኃጢአት ስለመውደቅ ሲያስረዳ “በኃጢአት መካከል ተቀምጠህ ኃጢአት አልሠራም ከማለት የሞተውን ማንሳት ይቀላል” ይላል፡፡ መንፈስ ቅዱስም በሲራክ አፍ “ድንገትን የሚወድ በእርሱ ይጠፋል” ሲራክ 3፡27 እያለ ያስጠነቅቀናል፡፡ ይህ እውን ነገር ነው፤ በገዛ ራሳችን ደህና አድርገን እናውቀዋለን፡፡

ኃጢአታችን አብዛኛውን በቸልታ ከምንመለከታቸው የኃጢአት ምክንያቶች የሚመጡ ናቸው፡፡ ከመውደቃችን በፊት እንፈራውና እንጠረጥረው የነበረ ነገር ይጠልፈናል እንወድቃለንም፡፡ መፍራትና ጥንቃቄ መውሰድ ሲገባን “ይህ ምን አለው? ምንም የለበትም፣ ደህና ነው፣ አያሰጋም፣ እጠነቀቃለሁ ወዘተ … እያልን በኃጢአት ምክንያት ውስጥ እንገባለን፣ እንሰጋበት፣ እንፈራው የነበረው ነገር ሳናስተውል አሳስቶን ወደ ኃጢአት እንወድቃለን፡፡

ለምንድን ነው ዛሬ ተናዝዘን፣ ንስሐ ገብተን፣ ቁርጥ ፈቃድ አድርገን በማግሥቱ ወደ ኃጢአት ኑሮ የምንመለሰው ውሳኔአችንና ቁርጥ ሐሳባችን በግብር የማናውለው ለምንድነው የዚህ መልስ ከኃጢአት ምክንያት ያለመሸሻችን ነው፡፡ ከኃጢአት ምክንያት እስከልራቅን ድረስ ዘወትር ወደ ኃጢአት ስንመላለስ እንኖራለን፤ ቁርጥ ሐሳባችን ፈጽሞ ተግባራዊ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ኃጢአት የሰይጣን ተግባር ስለሆነ ይህ እኛን ለማጥፋት የማያፍር ጠላታችን ሊጥለን የሚያቀርብልን መጥመድ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ኃጢአት ምክንያት ምን ማድረግ እንደሚገባን ሲያስተምረን “ዓይንህ የኃጢአት ምክንያት ቢሆንብህ አውጥተና ጣለው፤ ቀኝ እጅህ የኃጢአት ምክንያት ቢሆንብህ ቆርጠህ ጣለው” ይላል፡፡ ማቴ 25፡29-3ዐ ይህን ሲል የኃጢአት ምክንያት የሚሆንብህ አካልህ ከሆነ በቁጥጥርህ ሥር ለማድረግ መቻል አለብህ ማለቱ ነው፡፡ አካልህን እዘዘው ማለቱ ነው፡፡

ቅዱስ ሄሮኒሞስ ዓለምን ንቆ በቤተልሔም ባሕታዊ ሆኖ ሲኖር አንድ ቀን ቀድሞ በሮም ያውቀው የነበረ ጓደኛው ቪጂላንዚዮ የሚባል ዓለማዊ ወጣት ሲጎበኘው፣ ሄሮኒሞስ በተጋድሎ በጣም ደቆ በዋሻ ውስጥ ተደብቆ ስላየው ሄሮኒሞስን “ስለምን እንደ እንስሳ በዋሻ ውስጥ ትደበቃለህ ማንን ፈርተህ ነው?” ሲል ጠየቀው፡፡ ቅዱስ ሄሮኒሞስ ትኩር ብሎ ተመለከተውና “ማንን እንደፈራጉ ለማወቅ ከፈለግህ በአንተ ውስጥ ካለው ብዙ ድንገተኛ አደጋዎችን  ከሚያደርሰው መንፈስን ከሚያውክ እርባናቢስ ንግግርና ጭቅጭቅ፣ ቆሻሻ፣ ንፍገትንና የድንገታዊት ሴት ዓይኖች ፈርቼ ነው” በማለት መለሰለት፡፡ ቪጂላንዚዮ እንደገና “ይህማ ስንፍና ውሸት ነው በክፋት መካከል ሳይሸነፉ መኖር ይበልጣል” ብሉ ቀለደበት፡፡ ቅዱስ ሄሮኒሞስም እንደገና “ቪጂላንዚዮ ይብቃህ የኔው ስንፍና መሆኑን አምናለሁ እኔ ሰነፍ ስለሆንኩ በዚያ መካከል ተቀምጬ ከምሸነፍ መሸሹ ይሻለኛል ብዬ ነው” በማለት ከኃጢአት ምክንያት መሸሽ ማሽነፍ መሆኑን አስረዳው፡፡ እኛም እንደዚህ ቅዱስ ሰው ከኃጢአት ምክንያት ሁሉ አስቀድመን መሸሽ ጠቃሚ መሆኑን ተረድተን ከኃጢአት ምክንያት ሁሉ እንራቅ፡፡

ምንጭ፡- መንፈሳዊ ማሳሰቢያ - ጥቅምት 1


አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።