የገና በዓል አጀማመር

ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያኖችን መንፈሳዊ ሕይወት ከዕለት ዕለት በጋለ ሁኔታ ለማሻሻል እንዲረዳ በዓመቱ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ በዓላትን ታከብራለች ከእነዚህም በዓላት በጣም በደመቀ ሁኔታና በታላቅ ደስታ የሚከበረው የልደት በዓል ነው፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት የክርስቶስ ልደት የእምነታችን መክፈቻ በር በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ሁኔታው ከማህበራዊ ህይወታችን ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት በየትኛውም የዓለም ክፍል አዲስ ህፃን ተወልዶ ወደ ህብረተሰቡ በሚቀላቀልበት ጊዜ የሚኖረው ደስታና ፈንጠዝያ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ የህፃኑም ልደት በየዓመቱ በሚከበርበት ጊዜ በመጀመሪያ የቤተሰቡ ከዚያም የወዳጅ ዘመድና የጓደኛ ደስታ ፍፁም ልዩ ነው እንዲሁም የክርስቶስ ልደት በክርስቲያን ቤተሰቦች ዘንድ በትልቅ ጉጉትና ደስታ የሚጠበቅ ልዩ ቀን ነው ማለት ይቻላል፡፡

 presepe2በሰማይና በምድር ለሚገኙ ነገዶች የእልልታና የምስጋና ምንጭ የሆነው ነቢያት የተመኙት መላእክት ያወደሱት እረኞች ያወሩለት ሰብዓልሰገል የሰገዱለት ኃጢያተኞች የዳኑበት ግዞተኞች የተፈተኑበት ሀዋርያት የከበሩት ክርስቲያኖች የወረሱት ለሰዎችና ለመላእክት ታላቅ ደስታ የሆነው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓል አከባበር አጀማመር እንዲህ ነበር፡፡

 ከጥንት ጀምሮ ሮማውያን እውነተኛ ፀሐይ የተወለደበት ቀን እያሉ ታህሳስ 16 ቀንን ያከሩ ነበር ምክንያቱም በሮማውያን ግዛት የረጅሙ የክረምት ወቅት አብቅቶ በመጀመሪያ ጊዜ የፀሐዩን ብርሃን የሚያዩት በዚህች ቀን ነው፡፡ ሮማውያን በተለምዶ ከዚያ ከሚያኮራምት የክረምት ወቅት በማለፍ ብርሃንና ሙቀትን ስለሚያገኙ ለተክሎቻቸው ልማት ለከብቶቻቸውም የፍንደቃ ወቅት ስለሆነ ለዚህ ብርሃን በየዓመቱ የምስጋና መስዋእትን በመያዝ ሁላቸውም ወደ ተራራ ጫፍ ላይ በመውጣት መስዋዕትን ያቀርቡ ነበር፡፡

 ክርስቲያኖች እስከ አራተኛ ክፍለ ዘመን ድረስ በስደት ላይ ባልተረጋጋ ህይወት ውስጥ ስለነበሩ እምነታቸውም በዓለም ላይ በሰፊው ያልታወቀበት ዘመን ስለነበር ስለ ጌታችን ልደት ብዙም ትኩረት አይሰጡም ነበር፡፡ ስለዚህ እንደማንኛውም ሮማዊ በአባቶቻቸው የወረሱትን አምልኮ /የፀሐይ አምልኮ/ መስዋዕትን ይሰው ነበር፡፡ ወደ 320ዎቹ ገደማ ለመጀመሪያ ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች በእርጋታ መኖር የጀመሩ ክርስቲያኖች የጌታችን ልደት በታህሳስ 29 ማክበር ጀመሩ፡፡ በ354ዓ.ም ግን ሮማዊው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊብሮስ ክርስቲያኖች “ሳትሩን” እየተባለ በሚጠራው የፀሐይ አምላክ ፈንታ መንፈሳዊ የፍትህ ፀሐይ ክርስቶስ የተወለደበት የደስታና የነፃነት አብሳሪ ልደት በታህሳስ 16 ቀን እንዲከበር ለዓለም ሁሉ አዋጅ አስተላለፋ፡፡ በወቅቱ ብዙ የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት የ­­ ሊብሮስ አዋጅ አልተዋጠላቸውም ነበር፡፡ በኋላ ግን ር.ሊ.ጳ ግርጐሪዮ ቀዳማዊ በ601ዓ.ም ለሚስዮናውያን በሙሉ እንዲህ የሚል መምሪያ አወጡ “ የጣኦት ጐጆ አይፍረስ በውስጣቸው ያለ ቁሳቁስ ሁሉ ይፈራርስ በተባረከ ውሃ /ፀበል/ ቤተ መቅደሶቻቸውን እርጩት መንበረ ታቦት ይቀደስ ሕዝቡም የቤተመቅደሶቻቸውን መፈራረስ አይተው በስሕተት እንዳያዝኑ እውነተኛ አምላክን ተረድተው ኮርማዎቻቸውን ከጣኦት ይልቅ ለእውነተኛ አምላክ እንዲሰውና እንደሰግዱ አድርጉ ለዚህም አምልኮ የተለየ አከባበር ይሰጠው በዓላቸውንም መንፈሳዊ በማድረግ እግዚአብሔርን እያመለኩ በዚህ አጋጣሚ ወደ መንፈሳዊ ደስታ በመለወጥ ይበልጥ ይጓዙ፡፡ ከዚህ በኋላ አብዛኛዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ታህሳስ 16ትን እንደ ጌታ ልደት ቀን ተቀበሉ፡፡ የአርመንያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዘግይታም ቢሆን በ16ኛ ክፍለ ዘመን እንደ ኩላዊት ቤተክርስትያን የሊብሮስን አዋጅ ተቀበለች የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ግን እስከ ዛሬ በታህሳስ 29 የጌታን ልደት ያከብራሉ፡፡

 ለገና በዓል ቀን እያንዳንዱ ክርስቲያን ሁለት ሽህ ዓመታት በሀሳብ ወደ ኋላ ተመልሶ በቤተልሔም በከብቶች ግርግም ውስጥ ክርስቶስ የተወለደበትን ምሽት ያስታውሳል በጣም ጣፋጭ ምሽት አብዛኛውም ክርስቲያን ወንድ ሴት ህፃን ሽማግሌ መስዋእተ ቅዳሴን ለመስማት በምሽት ወደ ቤተክርስቲያን ያዘግማል፡፡ ምክንያቱም አምላክ ሰው የሆነበት የተባረከች እለት ናትና ለአምላኩ ምስጋና ያቀርባል ለክርስቲየኖች ትልቅ በዓል በመሆኑ አብያተ ክርስቲያናት በልዩ ሁኔታ ያሸበርቃሉ አበባዎች፣ ምንጣፋ፣ሻማው ጌጣጌጡ ሁሉም ልዩ ነው እንዲሁም በማንኛውም ቋንቋ የሚዘመሩት የልደት መዝሙሮች በጣም ውቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህንን በዓል በውጫዊ መልኩ በድምቀት እንደምናከብረው ሁሉ በውስጣችንም ህፃኑ ኢየሱስ መቀበል ይገባናል ምክንያቱም ክርስቶስ የተወለደው ሰው መሆን ምን እንደሚመስል አይደለም አምላክ ነውና ሁሉን ያውቃል ይልቁንም ከገባንበት የኃጢአት ማቅ ውስጥ ሊያወጣን በትምህርቱና በህይወቱ አብነት ሊሆነን በመጨረሻም በሞቱ የክብሩ ተካፋዮች ሊያደርገን በማሰብ ነው፡፡

ጌታችን በተወለደበት በዚያች ሌሊት መንጋቸውን ለሚጠብቁ እረኞች የእግዚአብሔር መላእክት “በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሰላም ይሁን” ሉቃ 2፡14 ብለው እንደዘመሩ ክርስቶስ የመጣው በሰዎች ሰላምን ለማምጣት ነው፡፡ ስለዚህም በጌታ ልደት ቀን አሁንም ደግሞ በልባችን ሊወለድ የሚፈልገውን ክርስቶስ ሰላሙን ይሰጠን ዘንድ በንጹህ ልብ እንቀበለው፡፡

 እንዲሁም በጌታችን ልደት በዓል ልናስተውለው የሚገባ የእመቤታችንን ታላቅነት ነው፡፡ አምላክ ከሁሉም በላይ ወዶና መርጦ ማደሪያው እንድትሆን የመረጣት እመቤታችንን ነው፡፡ እመቤታችን መልአኩ ገብርኤል “ያለ ወንድ ትወልጃለሽ” ብሎ የነገራት ትርጉሙ ባይገባትም በእግዚአብሔር ላይ በነበራት ታላቅ ፍቅርና ትህትና በእምነት ሁሉን ተቀብላለች እመቤታችን ማርያም በጊዜዋ እንዲሁ ያለ ባል መውደሉ በድንጋይ ተወግሮ ለመገደል የሚያበቃ ኃጢያት መሆኑን ብታውቅም በእግዚአብሔር በመታመን ከሰዎች የሚመጣባርን ይሉኝታ ወደ ጐን በመተው ይህንን ታላቅ ሚስጢር ተቀብላ በአለም ብርሃንን ሰጥታናለች፡፡ ይህም ወደ ትልቅ ክብር እንድትደርስ አድርጓታል፡፡ እኛም በክርስቶስ ፍቅር ብለን “አንተ እንዳልክ ይሁንልኝ” ብለን የእግዚአብሔርን ፍቃድ ለመፈጸም ያለ ይሉኝታ ለምናደርገው ጥረት በቃላት ሊገለጽ የማይችል ክብር ይጠብቀናል፡፡

 የልደት በዓል በምናከብርበት ጊዜ በየቤተክርስቲያናችን አንድ ለየት ያለ ልማድ አለ ይኸውም በልደት በዓል ከሁለት ሺ ዓመት በፊት በቤተልሔም ክርስቶስ በበረት የተወለደበትን በማስታወስ በተለያየ ሁኔታ የበረት ቅርጽ ይደረጋል፡፡ ይህ በየአብያተ ክርስቲያኑ የሚገኘው በፊት በእያንዳንዱ ክርስቲያን በልቡ ውስጥ ልዩ መንፈሳዊነትንና ደስታን ይፈጥራል፡፡ ይህ ልማድ የተጀመረው በ13ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በትልቁ ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ሲሆን በወቅቱም ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ጌታችን የተወለደበትን ሁኔታ ለማስታወስ ይህን በረት ሰርቶ በቅዳሴው መሀል በሕፃኑ እየሱስ መልክ የተቀመጠውን አሻንጉሊት ባነሳ ጊዜ ህፃኑ ህይወት ዘርቶ እንዳቀፈው በቅዱስ ፍራንቸስኮ ታሪክ ተጽፎ እናገኛለን ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ይህ የበረት አምሳል በየቤተክርስቲያኑ እየተሠራ በጌታችን ክርስቶስ ልደት ወቅት በቤተክርስቲያናችን ልዩ ድምቀትን ይሰጣል፡፡ ክርስቲያኖችም በዚህች ሌሊት ወደ በረቱ በመጠጋትና ተንበርክከው በመጸለይ ከ2ዐዐዐ ዓመት በፊት የተወለደውን ክርስቶስ ዛሬም በየቤተክርስቲያናችንና በየልባችን እንደሚወለድ ያስታውሳሉ፡፡

 

ምንጭ

መልካም ዜና ቁጥር 21