ጥሪ፣ የእግዚአብሔር የፍቅር ስጦታ

ጥሪ፣ የእግዚአብሔር የፍቅር ስጦታ - የቅዱስ አባታችን ቤኔዲክቶስ የጥሪ ቀን መልእክት

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፡-

dominican-sisters-of-mary-mother-of-the-eucharistከፋሲካ በኋላ በሚውለው አራተኛ እሑድ የሚከበረው ዓለም አቀፍ ለጥሪ የጸሎት ቀን "ጥሪ፡ የእግዚአብሔር የፍቅር ስጠታ" በሚለው ዋነኛ መልእክት ላይ እናስተንትን፡፡

የአስደናቂ ስጦታ ሁሉ ምንጭ፣ ፍቅር የሆነው እግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነው፡፡ "በፍቅር የሚኖር በእግዚብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል፡፡" 1ኛ ዮሐ 4፡16 መጽሐፍ ቅዱስም ከፍጥረት ሁሉ በፊት ስለሚገኘው ስለዚሁ በእግዚአብሔር እና በሰው መካከል ያለውን ፍጹማዊ ትስስር ይነግረናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን ከተማ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች በላከው መልእክቱ ላይ ለእግዚአብሔር አንድ የምስጋና መዝሙር ይዘምራል ለዚህም ምክንያቱ በዘመናት ሁሉ መካከል ወሰን አልባ በሆነው ፍቅሩ የሰው ልጆችን ለማዳን የነበረው የእግዚአብሔር ዓላማ ፍቅር እንደሆነ ማወቁ ነበር፡፡ በልጁ በክርስቶስ አማካይነት፤ ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚለው "ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።" ኤፌ 1፡4 ገና ከመፈጠራችን በፊት እንኳን በእግዚአብሔር ፍቅር ተወደናል፡፡ በእውነተኛ እና ምክንያት አልባ በሆነ ፍቅሩ ፈጥሮን "ከተፈጠሩት ነገሮች አይደለም" 2መቃባውያን 7፡28 እንዲሁም ያደረገን ከእርሱ ጋር ፍጹም አንድነት እንዲኖረን ነው፡፡

በእግዚአብሔር መለኮታዊ ጥበቃ ፊት በግርምት የቆመው መዝሙረኛ እንዲህ ይላል "የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ፣ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሰራሃቸውን፤ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድነው?" መዝ 8፡2 ስለዚህ የመፈጠራችን ትልቁ እውነታ በዚህ አስደናቂ ምስጢር ውስጥ የታመቀ ነው፣ ፍጥረት በሙሉ እንዲሁም እያንዳንዱ የሰው ልጅ ድንበር የለሽ፣ ታማኝ እና ዘላቂ የሆነው የእግዚአብሔር የፍቅር ሥራ እና የጥበቡ ፍሬ ነው፡፡ /ኤር 31፡3/ ይህንን እውነታ ማወቁ በእውነትም ሕይወታችንን በሚገባ መለወጥ ነው፡፡

ከቅዱስ አውጐስጢኖስ ኑዛዜዎች መካከል ብዙዎች የሚያውቁት ምዕራፍ አውጐስጢኖስ በታላቅ ኃይለ ቃል ውብ እና ፍጹም ፍቅር የሆነውን ሁልጊዜ ለእርሱ ቅርብ የሆነውን አምላክ እንዲሁም እርሱ ራሱ ይለወጥ ዘንድ ልቡንና አዕምሮውን ስለሰጠው እግዚአብሔር ሲናገር "እጅግ ጥንታዊ እጅግ አዲስ ውበት ሆይ የማታ ማታ አፈቀርኩህ፤ አንተ በውስጤ ነበርህ እኔ ግን በውጪ ነበርሁ፤ የፈለግሁህም በዚያ ነበር፤ በእኔ አስቀያሚነት አንተ ከእኔ ጋር ነበርህ እኔ ግን ከአንተ ጋር አልነበርኩም፡፡ ፍጥረት ካንተ አራቀኝ ዳሩ ግን ፍጥረት ባንተ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር ሕልውና የለውም፡፡ ተጣራህ፣ ጮህክ፣ ድንቁርናዬን ሰብረህ ገባህ፡፡ አንተ ብልጭ አልክልኝ፣ በደንብ አበራህልኝ እና እውርነቴን ገፈፍክ፡፡ መዓዛህን በእኔ ላይ ተነፈስክ፣ እኔም እየተነፈስኩ ወዳንተ ቀረብሁ አሁን ይበልጡን እጠማለሁ፡፡ ቀመስኩህ አሁንም ይበልጡን አንተን እራባለሁ፣ እጠማለሁም አንተ ዳሰስከኝ እኔም በአንተ ሰላም ተቃጠልኩ /ኑዛዜዎች 27፡38። እነዚህን ምስሎች በመጠቀም የሄፖው ቅዱስ ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገውን በቃላት የማይገለጽ ውብ ምስጢሩን ለማስረዳት ይሞክራል፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ፍቅር የሰውን ሁሉ ሕይወት ይለውጣል፡፡

ይህ ገደብ የሌለው ፍቅር ነው፤ ዘወትር በመንገዳችን ይቀድመናል፣ በሕይወታችን የሚጠብቀን እና በሕይወት መንገዳችን ላይ የሚጠራን ነው፡፡ ይህ ፍቅር በእግዚአብሔር ፍጹም ነፃ ስጦታ ውስጥ የተመሠረተ ነው፡፡ ከእኔ በፊት የነበሩት ብፁዕ ዮሐንሰ ጳውሎስ ዳግማዊ በተለይም ስለክህነት አገልግሎት ሲናገሩ፡- "እያንዳንዱ የክህነት አገልግሎት ቤተክርስቲያንን ወደማፍቀር እና ወደ ማገልገል ሲወስደን ራስ፣ እረኛ እና የቤተክርስቲያን እጮኛ የሆነውን ክርስቶስን ለሰጠን ነፃ እና ከልካይ የሌለው ፍቅር ምላሽ ነው፡፡ /Pastores dabo Vobis 25/ እያንዳንዱ ጥሪ በተለየ መልኩ የሚወለደው ከእግዚአብሔር በጐ ፈቃድ ነው፤ እርሱ የእግዚአብሔር የፍቅር ስጦታ ነው! "በመጀመሪያ ደረጃ" የሚራመደው እርሱ ነው፤ እኛ ውስጥ አንዳች መልካም ነገር አግኝቶ ሳይሆን የእርሱ ፍቅር በእኛ ውስጥ በመገኘቱ "በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለፈሰሰ ነው" ሮሜ 5፡5፡፡

በዘመናት ሁሉ የመለኮታዊ ጥሪ ምንጭ የሚገኘው ራሱን ሙሉ በሙሉ በኢየሱስ ክርስቶስ በገለጠው ፍፃሜ አልባ የእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ ነው፡፡ በመጀመሪያው የሐዋርያዊ መልእክቴ /Deus caritas est/ እግዚአብሔር ፍቅር ነው "በእርግጥ እግዚአብሔር አያሌ በሆኑ መንገዶች ተገልጧል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ በተዘረዘረው የፍቅር ታሪክ ወደ እኛ መጣ፣ ልባችንንም ሊገዛ ፈለገ፣ እስከ መጨረሻው እራት ድረስ፣ በመስቀል ላይ ልቡን እስከተወጋበትም ድረስ፣ ከትንሳኤውም በኋላ ራሱን እስከገለጠበት ግንኙነት ድረስ በሐዋርያቱም አማካይነት ባከናወናቸው ታላላቅ ተግባራት በእድገት ላይ ያለችውን ቤተክርስቲያን በመንገዷ ሁሉ ይመራታል፡፡ የእርሱን ሕላዌ በሚያንጸባርቁ ወንዶች እና ሴቶች፣ በቅዱስ ቃሉ፣ በምስጢራት እና በተለይም በምስጢረ ቁርባን እንደ አዲስ ከኛ ጋር ይገናኛል" ቁጥር 17

የእግዚአብሔር ፍቅር ለዘለቄታው ነው፣ እርሱ ለራሱ ታማኝ ነው፤ "እስከ ሺህ ትውልድ ያዘዘውን ቃሉን" መዝ 1ዐ5፡8 ያከብራል፡፡ ዳሩ ግን የዚህ መለኮታዊ ፍቅር የሚያጓጓ ውበት ከፊታችን የሚቀድመው በጉዟችንም የሚያጅበን ቃል በየጊዜው እንደ አዲስ መነገር አለበት፤ በተለይም ደግሞ ለአዲሱ ትውልድ እንዲህ ሊደረግ ይገባል፡፡ ይህ መለኮታዊ ፍቅር የተሸሸገ ግፊት ነው፤ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳን የማይከዳን መነሳሳት ነው፡፡

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፡- ለዚህ ፍቅር ሕይወታችንን ክፍት ማድረግ አለብን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በየቀኑ ወደ አብ ፍጹም ፍቅር /ማቴ 5፡48/ ይጠራናል የክርስትና ሕይወት የላቀ መንፈሳዊነት ሊሳካ የሚችለው እግዚአብሔር እኛን እንዳፈቀረን እኛም ሌሎቹን ማፍቀር ስንችል ነው፡፡ ይህ ፍቅር ሙሉ በሙሉ በታማኝነት እና ራስን አሳልፎ በመስጠት ፍሬ ይለገጣል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ዘመስቀል ለአንዲት የሴት መነኩሲት አለቃ በጻፈው መልእክቱ ላይ ሁሉንም ካህን አድርጐ ከቀባው ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ ምንም አታስቢ፤ ፍቅር በሌለበት ቦታ ሁሉ የፍቅር ምክንያት ሁኚ፤ በዚህ ቦታ ፍቅርን ትቀጂአለሽ፤/ ደብዳቤዎች 26/

እያንዳንዱ ጥሪ የሚወደለደው እና የሚያድገው ለም አፈር በሆነው በእኛ ለእግዚአብሔር ፍቅር ባለን ግልጽነት እና ራስን የመስጠት ፍሬ ነው፡፡ በጸሎታችን ከዚህ ምንጭ በመቅዳት፣ ቀጣይነት ባለው የቃለ እግዚአብሔር ጥናት፣ ዘወትር ምስጢራትን በመሳተፍ በተለይም ቅዱስ ቁርባንን በማዘውተር ባልንጀሮቻችንን በማፍቀር የተሞላ ሕይወት መኖር እንችላለን፡፡ የጌታን ትክክለኛ ገጽታ ማግኘት የምንችለው በዙርያችን በሚኖሩ ባልንጀሮቻችን ውስጥ ነው /ማቴ 2531-46/ እነዚህ ሁለት ፍቅሮች፡- የእግዚአብሔር ፍቅር እና የባልንጀራ ፍቅር የተሳሰሩበትን ይህንን ሕብረት ለማስረዳት ር.ሊ.ጳ ቅዱስ ግሪጐሪ ታላቁ የዘር መዝራትን በምሳሌነት ይጠቀማሉ በልባችን ባለው ለም መሬት ላይ እግዚአብሔር የእርሱን ፍቅር ያለማበታል፤ ከዚህ በመነሳት ልክ እንደ ቅርንጫፍ ሁሉ የእርስ በእርሳችን ፍቅር ያብባል /Moralium Libri, siveexposition Librum B.Job,Lib.VII, ch.24, 28; PL75,780D/ እነዚህ ሁለት ፍቅሮች ተመሳሳይ ሲሆኑ ከአንድ ምንጭ ይፈልቃሉ፤ ተመልሰው ወደ ምንጩ ይገባሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ራሳቸውን አሳልፈው ለክህነት አገልግሎት በመስጠት የተቀደሰ ሕይወት ለመኖር ለሚፈልጉ ሁሉ በከፍተኛ ፍላጐት በንጹሕ ልብ ሊጠብቋቸው የሚገቡ እና በሕይወታቸውም ላይ መታየት ያለባቸው ነጸብራቆች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ፍጹም ባይሆንም ካህናት እና መነኮሳት እንዲሁም በመሃላ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር የሰጡ ሰዎች የእግዚአብሔር ፍቅር ያሳዩ ዘንድ ተጠርተዋል፡፡ ይህም ፍቅር ክርስቶስ ለሚጋብዛቸው የክህነት ሕይወት ወይም የወንጌል ማኀበርተኛ የመሆን ጥሪ መልስ የሚሰጡበት ዋነኛ ምክንያታቸው ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ያለማመንታት ለመለኮታዊ እረኛ መልስ ሰጠ "ጌታ ሆይ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ" ዮሐ 21፡15 ይህ መልስ በሙላት ለክርስቶስ የተሰጠ፣ በሚገባ ጥሪዋን የኖረች እና በእውነት ደስተኛ የሆነች ነፍስ ምስጢር ነው፡፡ ሌላው ለባልንጀራችን የምናሳየው ፍቅር ተግባራዊ ገጽታና በተለይ በስቃይ ውስጥ በችግር ላይ ለሚገኙ የምናደርግላቸው ተግባራዊ ምላሾች ካህኑን ወይም የተቀደሰ ሕይወት ለመኖር ራሱን የሰጠውን ሰው በማኀበረሰቡ ውስጥ የተስፋ የምሥራች ዘር አብሳሪዎች እንዲሆኑ ከሚያደርጓቸው ምልክቶች አንዱ ነው፡፡ ካህኑ እና የተቀረው ሕዝበ ክርስቲያን ግንኙነት በጣም ወሳኝ እና አስፈላጊው ገጽታ ግንኙነታቸው መሠረቱ ያደረገው በእግዚአብሔር ፍቅር ላይ መሆኑ ነው፡፡ የእርስ መንደር ቆሞስ እንደሁ ሲል ተአምጧል ካህናት ስለራሳዠው ሳይሆን ክህነታቸው ለእናንተ ነው፡፡ /Le cure d'Ars.Sapensèe-Son Coevr, foi vivante, 1966p.100/

የተወደዳችሁ ጳጳሳት ወንድሞቼ፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ መነኮሳት፣ ካታኪስቶች፣ የሐዋርያዊ ሥራ ባልደረቦች እና ወጣቶችን በማስተማር እና በማሰልጠን ዘርፍ ያላችሁ በሙሉ ለቁምስናዎች ማኀበራት ትኩረት በመስጠት ለክህነት ወይም ለምንኩስና እንዲሁም በመሃላ ለተቀደሰ ሕይወት እንደተጠሩ የሚሰማቸውን ወጣቶች በማበረታታት እና ለሚጠራቸው የእግዚአብሔር ፍቅር በለጋስነት እሺ ብለው እንዲመልሱ ማስቻል ለቤተክርስቲያን ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን የማንኛውም ጥሪ መንገድ መነሻ እና መድረሻ ቅዱስ ቁርባን መሆን አለበት፡፡ በቅዱስ ቁርባን በጌታ ኢየሱስ የተገለጠውን ፍቅር እንመለከታለን፤ በቅዱስ ቁርባን ዘወትር አዲስ የሆነ እና በእግዚአብሔር ሕይወት የበለፈገ ሕይወት መኖር እንችላለን፡፡ ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር መንግስት የተሰጠውን ሕይወተ ውበት ማድነቅና መረዳት የምንችለው በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በጸሎት እና በቅዱስ ቁርባን አማካይነት ነው፡፡ በየሀገሩ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ እና ከእነርሱም ጋር ሕብረት ያላቸው የተለያዩ ቡዩኖች ጥሪ በጥንቃቄ እንክብካቤ የሚያገኙባቸው እና እውነትነቱ የሚፈተንበት ቦታዎች እንዲሆኑ፤ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች ጥሪን በተመለከተ የበሰለ ድጋፍ እና መመሪያ የሚያገኙባቸው ሥፍራዎች ይሆን ዘንድ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ራሱን ስለቤተክርስቲያኑ የሰጠውን የክርስቶስ ፍቅር የሚያንጸባርቁ /ኤፌ 5፡32/ የክርስቲያን ቤተሰቦች የሕይወት እና የፍቅር ማኀበራት /Gaudium et spes 48/ በመሆናቸው ወጣት ወንዶችና ሴቶች የዚህን ራስን አሳልፎ የመስጠት አስደግቂ ልምድ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የክርስቲያኖች ቤተሰብ ስለ እግዚአብሔር መንግስት ይቀደስ ዘንድ ለሚሰዋ ሕይወት የመጀመሪያዎቹ የለሙ ማሳዎች ናቸው፡፡ /Familaris Consortio 53/ እነዚሁ የአንድነት ቤተሰቦች እና ትምህርት ቤቶች ይበዙ ዘንድ በምድር ላይ የቅዱስ ስላሴን ሕይወት በገለጠው የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ አብነት ዘወትር ካህናት እና የወንጌል አገልጋዮች ከምእመናን ጋር በፍቅር ይተባበሩ፡፡

በዚህ በጸሎት በታጀለ ተስፋ ሆኜ ሐዋርያዊ ቡራኬዬን እሰጣችኋለሁ፤ ወንድሞቼ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ገዳማዊያን፣ ወንድ እና ሴት መነኮሳንና መነኮሳት እንዲሁም መላው ሕዝበ እግዚአብሔር በተለይም በገር ልቦና የእግዚአብሔርን ድምጽ ለመስማት ለታገሉ ወንዶች እና ሴቶች ወጣቶች በመሉ መልስ ለመስጠት ዝግጁ ለሆኑትም አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ይባርካችሁ ይጠብቃችሁ፡፡

ከቫቲካን ጥቅምት 7 ቀን 2004 ዓ.ም.

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛው