የፋሲካ ምስጢር

ቤተክርስቲያን በቅዱስ ቁርባን ምስጢር አማካይነት ብቻ ሳይሆን በሥርዓተ አምልኮዋ ሁሉ  የክርስቶስን ፋሲካ እጅግ እውነተኛ በሆነ መንገድ ታስተላልፋለች፡፡ እኛ ደግሞ በቤተክርስቲያን አማካይነት የክርስቶስን ቸርነት በመከተል እራሳችንን መግለጥ መቀጠል አለብን፡፡

በተቀደሰው ሳምንት (ሰሙነ ሕማማት) ውስጥ ቤተክርስቲያን የክርስቶስን መከራና ሥቃይ ታስባለች ኅብረትንም ትጐናጸፋለች፤ ስለ ሰው ልጅ ኃጠአት ኢየሱስ ከከፈለው ከፍተኛ መስዋዕትነት ጋር የመለወጥና የእርቅ ቃላትን ታስተምራለች፡፡ ጌታ አስፈሪውን ሞት ድል በመንሳት ለሰዎች ደኅንነት ያለውን ቁርጠኝነት በታላቅ ክብር አሳይቷል፡፡ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ለፈጸም ከፊታችን የሚመጣውን መከራ ሁሉ በመጋፈጥ ቤተክርስቲያን አንድነትን ትፈጥራለች፡፡

በፋሲካ በሚደረሰው የቅዱስ ቁርባን ጸሎት መግቢያ ላይ “በሞቱ ሞታችንን አሸንፏል፤ በትንሣኤውም ሕይወታችንን አድሷል” የሚል ቃል ተጽፏል፡፡ ይህም የፋሲካ መልዕክት ዋነኛ ቁልፍ ነው፡፡ በኢየሱስ ሞቶ መነሣት የእኛ መሞት የተፈጥሮአዊ ይዘቱ የተጠበቀ ቢሆንም ወደ ጨለማ ምዕራፍ ወይም ወደ ምንምነት መሸጋገሪያ መሆኑ ቀርቷል፡፡ ሞት ድል የተነሳ እውነታ ሲሆን የወደፊት ሐሳባችንንና ተስፋችንን ለማጨለም ኃይል የሌለው፣ በቁጥጥር ሥር የዋለ ክስተት ሆኗል፡፡

በአንጻሩም ሐሳባችንና የወደፊት ዕቅዶቻችን ሰፋ ያለ አድማስና የመፈጸም ዕድል ሊኖራቸው የሚችለው ለእግዚአብሔር ብቻ ከሚገባውና እኛም ከሞት የተነሳው ክርስቶስ ከቀረበልን ዘለዓለማዊ ሕይወት ጋር የተጣጣመ አንድነት ሲኖረን ብቻ ነው፡፡ ከሞት ነጻ መውጣታችን፣ ሁሉንም ነገር የሚወስን ነጻነት ሲሆን ቋሚ፣ ለታሪክና ለሰው ልጅም ተስፋ ሰጪ ለሆኑ ገንቢ ዕቅዶችም መንገድ ከፋች ነው፡፡

ይህ ለእኛም እንደዚህ መሆኑን ራሳችን እንጠይቃለን፡፡ ጥቂት እምነት ላለው አማኝ ያለው እውነተኛ አመለካከት በክርስቶስ የማዳን ጸጋ የሚገኘው ዘለዓለማዊ ሕይወትን ያካተተ ነው፡፡ ለዘለዓለማዊ ሕይወት ግልጽ መሆን ማለት የአንድን ሰው አኗኗርና የአስተሳሰብን መንገድ መለወጠ ነው፤ ይህ ለውጥ በትንሣኤ ብርሃን የፋሲካን አካሄድ የተከተለ ይሆናል፡፡

ይህ ብርሃን በእኛ ሕይወት ውስጥ በጭላንጭል ሳይሆን በሮችንና መስኮቶችን በመክፈት እኛ ውስጥ ገብቶ እንዲፈነጥቅ ከፈቀድንለት እንዴት በሆንን ነበር?

ይህ ቢሆን በምንሠራበት አካባቢና በቤተሰባችን ውስጥ የሚኖረው ግንኙነት  የጋራ ችግሮቻችን፣ በተለይ ለምንወድዳቸው ለሌሎች ሰዎች ሥቃይ ያለን አመለካከት እንዴት የተለየ በሆነ ነበር፤ በትንሣኤ ብርሃን ሁሉም ነገር ትርጉም አለው፤ ሁሉም ነገር መለኮታዊ ቃና ይኖረዋል፡፡ ሁሉም በተስፋ መዳኑን ለማመን ዝግጁ ይሆናል፡፡

ምንጭ፡ ጉዞ ከጌታ ጋር