“ልጄ ሆይ ትኩር ብለህ ሰማይን ተመልከት!”

ከሞት በኋላ ፍርድ አለ፤ ቀጥሎም ደግሞ ሰው ሁሉ እንደየሥራው ወደ መንግሥተ ሰማያት ወይም ወደ ገሃነመ እሳት ይወርዳል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ኃጢአተኞች ወደ ዘለዓለማዊ ሥቃይ፤ ጻድቃን ደግሞ ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገባሉ” ብሏል (ማቴ.25:47)። እንዲሁም “እናንተ የአባቴ ቡሩካን ኑ! ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” ይላል (ማቴ.25:30)።

 

መንግሥተ ሰማያት ምንድነው? ብለን ብንጠይቅ በሕይውታችን በዚህ ምድር ላይ ሆነን የመንግሥተ ሰማያትን ጣዕም፣ ደስታና ክብር ሙሉ ለሙሉ ልንረዳውና ልናውቀው አንችልም። መግለጹም አዳጋች ይሆንብናል፤ ቅዱስ ጳውሎስ አንድ ቀን ወደ ሰማይ ተነጥቆ እስከ ሦስተኛ ሰማይ ከደረሰ በኋላ በዚያ አካባቢ በሰው ቃል ሊገለጥ፣ ሰው ሊናገረው የማይችለውን ነገር እንደሰማና እንዳየ መሰከረ (2ቆሮ.12:2-4)። እንዲህም አለ “የሰው ዓይን ያላየውን፣ የሰው ጆሮ ያልሰማውን፣ የሰው ልብም ያላሰበውን ነገር እግዚአብሔር ለሚወዱት አዘጋጅቷል።” (1ቆሮ.2:9)። በትንሹ ያየውን ጥቂት የመንግሥተ ሰማያት ጮራ ግን እንዴትና ምን እንደነበረ ለመግለጥ ስለተሳነው በቃላት ሊገልጠው አልቻለም።

 

ቅዱስ ቦናቬንቱራ ስለ መንግሥተ ሰማያት ደስታ ሲጽፍ “በዚያ የሚገኝ መልካም ነገር በፍጹም ትልቅና ብዙም ነው፤ የሰው ሃሳብ ሊደርስበት አይችልም” ብሏል። ቅዱስ አውጎስጢኖስም ስለ መንግሥተ ሰማያት ምንነት ቅዱስ ሄሮኒሞስን ለመጠየቅ አስቦ ሳይጠይቀው ሄሮኒሞስ ሞተ። ከሞተ በኋላ ለቅዱስ አውጎስጢኖስ በሕልም ታየውና “አውጎስጢኖስ ሆይ! ምድርን በእጅህ መዳፍ ውስጥ ልትጨብጣት ትችላለህን?” ብሎ ሲጠይቀው አውጎስጢኖስም “አልችልም፤ ውቅያኖሶችን፣ ቀላዮችንና ወንዞችን ሁሉ በአንድ ጣሳ መያዝ ይቻላልን? ሲል መለሰለት። ቅ. ሄሮኒሞስም “እንግዲያውስ የመንግሥተ ሰማያት ደስታም እንዴት እንደሆነ በሙሉ ሊገባህ የማይቻል ነው” በማለት መለሰለት።

 

ምንም እንኳ መንግሥተ ሰማያት እንዴት እንደሆነ ልንረዳው ባይቻለንም መንግሥተ ሰማያት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መኖና እግዚአብሔርን ማየት ስለሆነ ደስታና ክብሩ ምን ያህል እንደሆነ መገመቱ አያዳግትም። ቅዱስ ዮሐንስ “ወዳጆቼ ሆይ! አሁን የእግዚአብሔር ነን፤ ወደፊት ምን እንደምንሆን ገና አልታወቀም። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ውነተኛ መልኩን ስለምናይ እርሱን እንደምንመስል እናውቃለን።” ይላል (1ዮሐ.3:2)።

 

ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ “አሁን ብመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን። በዚያን ጊዜ ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ፤ በዚያን ጊዜ ግን እኔ እንደታወቅሁ አውቃለሁ” ይላል (1ቆሮ.13:12)። ቅዱስ ቶማስም “በሰማያዊ አገር እግዚአብሔርን እንዳለ እናየዋለን፤ ከምናውቀው ጋር እንደምንገናኝ እንዲሁ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንገናኛለን” እያለ ያስረዳናል። ቅዱስ ዮሐንስም በራእይ 21:3 ላይ “እነሆ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው፤ ከእርሱም ጋር ያድራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔርም እሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ይሆናል፤ አምላካቸውም ይሆናል” ይላል።

 

እንግዲህ መንግሥተ ሰማያት ራሱ እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር ደግሞ ሊነገር የማይችል ፍጽምና፣ ትልቅነት፣ ሀብትና እውቀት ነው። ስለዚህም በመንግሥተ ሰማያት መኖር ማለት ከእርሱ ጋር መኖር፣ እርሱን መገናኘትና ዘወትር ፍጻሜ የለሽ ደስታን መኖር ማለት ነው። በመንግሥተ ሰማያት ኀዘን፣ ስቃይና መከራ ይቅርና በምድር ላይ መልካም የሆኑ ነገሮች ብለን ልናስባቸው የምንችላቸው ነገሮች ሁሉ እዚያ አይገኙም፤ ምክንያቱም ምድራዊ መልካም ነገሮች  በመንግሥተ ሰማያት መልካም የመባል ብቃት የላቸውም።

 

ቅዱስ ዮሐንስ በተገለጠለት ራእይ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርንም አየ፤ ፊተኛው ሰማያ ፊተኛዪቱ ምድር አልፈዋልና፣ ባሕርም ወደፊት የለም... እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ጩኸት ወይም ስቃይ ከእንግዲህ አይሆንም” ይላል (ራእይ 21:1-4)። ቅዱስ ጴጥሮስ በደብረ ታቦር ተራራ የመንግሥተ ሰማያትን ጮራ ስላየ “ጌታ ሆይ! እዚህ ብንሆን መልካም ነበር” እስከማለት ደረሰ (ማር.9;7)። መንግሥተ ሰማያት ያለመጠን ጣፋጭ ናት፤ ደስታዋ ልብን ያማልላል፣ ልብን ይነጥቃል።

 

በርናርዴት በሉርድ እመቤታችንን ለመጀመሪያ ጊዜ ካየች በኋላ፤ በሚያንጸባርቅ ብርሃንዋና ውበቷ ተገርማ በምድር የሚገኝ መልካም ነገር ሁሉ ውበት የሌለውና ጨለማ መስሎ እንደታያት ተናገራለች። የመንግሥተ ሰማያት ደስታ ልባችንን በሐሴት የሚሞላና የሚያንቀሳቅስ ልዩ ሐሳብ ነው።

 

ቅዱስ ዮሴፍ ካፋሴ የሚባል አንድ ቅዱስ “መንግሥተ ሰማያት ሆይ! አንቺን የሚያስብ ሁሉ ድካም አይሰማውም፤ ሁልጊዜ ደስተኛ ነው” ይል ነበር። መንግሥተ ሰማያትን ማለም የዚህ ዓለም ስቃይ በትእግሥት እንድንቀበል ያበረታታናል። ቅዱስ ጳውሎስ “ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ” ይላል (ሮሜ 8:18)።

 

ቅዱስ ፍራንቺስኮስ ዘአሲዚ ደግሞ “የመንግሥተ ሰማያት ቤትን ሳስብ የዚህ ዓለም መከራ ደስታ ሆኖ ይሰማኛል” ይል ነበር። መንግሥተ ሰማያትን ስናልም ከክፉ ድርጊት ርቀን ወደ በጎ እንድናዘነብል፣ የኃጢአትን ሥራ ንቀን የጽድቅን ሥራ እንድንከተል ያበረታታናል።

 

ቅዱስ ቶማስ ዘቢላኖቫ የተባለ ሌላ ቅዱስም በበኩሉ “ለጸሎት ቀዝቃዛ መንፈስ የሚኖረን፣ መልካምን ነገር ከማድረግ ቁጥብ የምንሆነው ወይም በፈተና ጊዜ ስንፍናና  እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች የሚደርሱብን መንግሥተ ሰማያትን ስለማናስብ ነው” በማለት ያስተምረናል።

 

በመጽሐፈ መቃባውያን ውስጥ የሰባቱ መቃባውያን ልጆች እናት በመጨረሻ ልጇ ስቃይ ወቅት ከሰማዕትነት ወደ ኋላ እንዳያፈገፍግ ፈርታ “ልጄ ሆይ! ሰማይን ትኩር ብለህ ተመልከት” እያለች በአጽንዖት መከረችው (2ኛ መቃ.7:8)። እኛም በዚህ የስደት ምድር ሳለን አሸቅበን ወደ ላይ እናልም፤ እውነተኛ አገራችንና ርስታችን እሷ ናት። እግዚአብሔርም የፈጠረን ለርስዋ ነው።

 

"መንፈሳዊ ማሳሰቢያ” የተወሰደ።

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።