ፋሲካ-ትንሣኤ- ሽግግር…

ፋሲካ-ትንሣኤ- ሽግግር

ኢየሱስ ከሞት ተነሣ፤ ማቴ.28፡1-15፡፡

ሕይወትና የሕይወት ባለቤት እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ራሱ እኔ ትንሣኤና ሕይወትም  ነኝ ብሏል፡፡ዮሐ.11፡25፡፡

ትንሣኤ-መነሳት-ተነሣ፤ ማለትም ከተቀመጡበት፤ ከተኙበት፤ ካንቀላፉበት… ሲባልም መንፈሳዊ  ሕይወትን በመዘንጋት፤ ኃላፊነትን፤ ግዴታን፤ ጥሪን… ተነሥተን መንቀሳቀስ መቻልና ሕይወት እንዳለን ማሳየት ማለት ነው፡፡ በመሠረቱ ለአንድ ክርስቲያን/ሰው/ በእግዚአብሔር ጸጋ በሚገኝበት ሰዓት መቸውም መች ቢሆን ትንሣኤ ነው፤ ምክንያቱም ዘመናትና ዘመን፤ ዓመታትና ዓመት፤ ወራትና ወር፤ ሳምንትና ሳምንታት፤ ቀንና ቀናት፤ ሰዓትና ሰዓታት፤ ደቂቃትና ደቂቅ፤ ሰከንዳትና ሰከንድ፤ የተገነቡት ወሳኙ ሰከንድ በመሆን ነው፤ ሰከንድና ደቂቃዎች ከሥር ከሌሉ… ዓመታትና ዘመናት አይታሰቡም፤ እንዲሁም በየቀኑ… ትንሣኤን የማይለማመድ ሰው የትንሣኤን ምንነት እንዴት ሊረዳው ይችላል… መኖር ማለት በትክክሉ እሱ ነውና፤ ቅዱስ ዳዊት ራሱ እንዲህ ይላል ሕያዉ ሰው የእግዚአብሔር ክብር ነው፡፡ ሕይወት በባሕርይዋ ተንቀሳቃሽ ናትና መኖርን ለማየት ለማወቅ ዓይነኅሊናን መክፈት ማለት  ነው፤ ጊዜው ቀን እንጂ ሌሊት አለመሆኑን ማስተዋል ማለት ነው፡፡ልባችን በመሬት ላይ ብቻ አተኩሮ እንዳይቀር መንቃት… ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው -ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ-… ትነሣኤህን ላመነው ብርሃንህን በኛ ላይ ላክ.. በማለት የሚዘመረው፡፡

ሕይወት ዘላለማዊት  ስለሆነች አትሞትም፡፡ እግዚአብሔር ሕይወት ነው፡፡ የሰው ልጅም ሕይወት የተለኮሰችው ከዘላለማዊ ሕይወት ነው፤ ዘፍ.2፡7፡፡ ስለሆነም ሕይወትን ሕይወት እንዳልሆነች ሊያረጋት የሚችል ምንም ዓይነት ኃይል መቼውም መች፤ የትም ቢሆን ሊኖር አይችልም፡፡ የሕይወት ሌላ ስም ብርሃን ነው፤ ብርሃኑም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማውም ብርሃንን ከቶ ሊያሸንፈው አይችልም፡፡ ይህችም ብርሃን የሰው ሕይወት ነበረች፡፡ዮሐ.1፡5፡፡  ጨለማ ብርሃንን ገደለ፤ ውሸትም እውነትን፤ጊዜያዊ ዘላለማዊዉን፤ ፍጡር ፈጣሪውን…

እግዚአብሔር ግን እግዚአብሔር ነውና ሞቱ ሕይወትን ትሰጣለችና ሕይወትን ለመስጠት የማይሞተው ሞተ፤ ሞተ ከመ ያሕይውዎሙ ለሙታን…ለሞቱት ሕይወትን ለመስጠት-በኃጢአት ለሞቱት የቅድስናን፤ የንጽሕናን ሕይወት፤ አዲስ ፍጥረት ለማድረግ አምላክ ሞተ፡፡

የፈጣሪ መሞት እውነትን የሚፈልጋት ሁሉ እንዳይሞትና እሱን እንዳያጣው ነው፡፡ የሰውን ልጅ የፈጠረው ለዚሁ ነውና፤ ሰው ሆይ ለዘላለም ትኖር ዘንድ እግዘአብሔር ይጠረሃል፤ ትንሣኤው ላንተ ነው/ለኛ/ነው፤ አምላክ ሞትን አያውቅም፤ ያወቃትና የተለማመዳት ለኛ ሲል ብቻ ነው እንጂ፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ ራሳችንን እንድናይ ጥያቄ ያቀርብልናል፡፡

በእውነት በሕይወት አለሁ ወይስ ተንቀሳቃሽ መሣሪያ… ከውጭ ለሚያየው ሕያው በራሱና በፈጣሪ ፊት ግን የሞተ…ሕይወት አልባ ሕይወት ነኝ… ብለን ራሳችንን እንይ። ስለዚህ ፋሲካ ሽግግር ነውና ከየት ወዴት ተሻገርኩኝ…ዐቢይ ጾም ምንን ፀንሶ ምንንስ ወልዶ ይሆን…ስደክም ውዬ ተኛሁኝ ነግቶ ከእንቅልፌ ስነሳስ ምን ለውጥ አለኝ… እንበል። ሰዎች በሰኔ/በዝናም ወቅት/ዘርተው በመስከረም ወይንም በአጨዳ ጊዜ ለመሰብሰብ…ምንስ…እንዴትስ ተንከባከብኩኝ…ምንስ ልሰበስብ በማለት ከመሬት ማለስልስ ብሎም እስካጨዳ እንደማይቦዝኑ ሁሉ የኛም ሕይወት በጊዜዋ ከነፍሬዋ እንድትነሣ አናኗራችንንና ትንሣኤያችንን እንመርምር።  እንግዳውስ የክርስቶስ ትንሣኤ እንደመስተዋት ከፊታችን ይሆንና ራሳችንን እያሳየን በል እስኪ..እውነት ተናገር የትንሣኤ ልጅ ነህን? መልስህ አዎን ከሆነ ብጹዕ ነህ፤ አይደለም ከሆነ ደግሞ ያንተን ትንሣኤ ለማክበር እንደገና አሁንም ጊዜው ያንተው ነው፡፡ ምክንያቱም ትንሣኤ የግል ጉዳይ እንጂ የወቅት/የወቅቶች/ጉዳይ አይደለም። ጊዜውን/ወቅትን/ ካየሁ አለፏል እንደልማዱም ሊያልፍ ነው፤ ጊዜ ተንቀሳቃሽ ባቡር…መኪና…መሣሪያ ነው ሰውም/እኛም በዚሁ ባቡር፤ መኪና…ላይ ተሳፍረናል ተሽከርካሪው ከተወሰነለት ቦታ ሳይደርስ መቆምን አያውቅም ሹፌሩም በማያሳስት ሁኔታ ወደ ግቡ እያበረረው ነው፤ አንተ ተሳፋሪ ሰው ወዴት ነህ…ሌሎች ሲሳፈሩ ብቻ አይተን ነው ወይስ…አስበንና አውቀን፤ ወደንም…ነው የተሳፈረነው… እንግዲያውስ የጊዜውን ተሽከርካሪ የኛ ትንሣኤ  ግብን ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡

በሕይወት የሚያምኑና ሕይወትንም የሚኖሩ ሊሞቱና እንደሌሉ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ልጅ በተፈጥሮ ወላጅን ይመስላል ባህሪያውም ነውና፤ ዘላለማዊ እግዚአብሔር ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔር እንደመሆኑ መጠን ፈጣሪያችን፤ ሰው እንደመሆኑም መጠን ወንድማችን እኛም ልጆቹ፤ ወንድሞቹ እህቶቹ፤ በሕይወትም በሞትም፤ በትንሣኤም እሱን እንድንመስል ዘላለማዊ ፈቃዱ ሆኖአል፡፡ እግዚአብሔር በባህርዩ/በማንነቱ/ በሁለ ነገሩ ልዩ የሆነና ልዩነቱንም ለሰውም ልጅ በፍጡር ደረጃ ያካፈለንና የሕያዋን አምላክም ነው እንጂ የሙታን አምላክ አይደልም፤ ማር፡12፡27፡፡ እንግዲያውስ ፋሲካችን ከአሮጌ ሕይወት ወደ አዲስ የምንሸጋገርበት የደስታ እወጃ/ብሥራት/ ነው፤ በብሥራት ደስታ እንጂ ሐዘን የለም፡፡ ስለሆነም በራሱ በጌታ ደስ ይበለን፡፡

የተባረከና የተቀደሰ ዘመነ ትንሣኤ ያድርግልን፡፡ አሜን፡፡

አባ ገብረወልድ ወርቁ - ሲታዊ

ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን አዲስ አበባ።