ፈጣሪ ፍጡሩን አገለገለ

በጸሎተ ሐሙስ እለት ደቀመዛሙርቱ ለምግብ ሲታደሙ ይህ ለእርሱ የመጨረሻው እንደሆነ ኢየሱስ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ እርሱ የሚናገራቸው ነገሮች በሙሉ ልዩ ቦታ ነበራቸው። እያንዳንዱ ቅጽበት በትርጉም የተሞላ ነበር፡፡ ኢየሱስ ውርሱን ተወ፡፡ እርሱ አንድ የቤት ሠራተኛ /አገልጋይ/ የሚሠራውን ሠራ፡፡ ይኸውም በወዳጆቹ ፊት ተንበርክኮ እግሮቻቸውን አጠበ፡፡ ይህንን ክስተት የሚነግረን ቅዱስ ዮሐንስ ሁለት ነገሮች ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡

የመጀመሪያው ትኩረቱ ለአስቆርታዊው ይሁዳ ኢየሱስን የመክዳት ሀሳብ ሠይጣን አስቀድሞ በውስጡ እንዳሳደረበት ነው፡፡ ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግሮች ያጠበው እነርሱ በጣም ጥሩዎችና አፍቃሪዎች ስለሆኑ ሳይሆን እርሱ እስከ መጨረሻው ከማፍቀር ውጭ ሌላ በማያውቀው  ፍቅሩ ስላፈቀራቸው ነው፡፡ በእነርሱ ፊት ራሱን እጅግ ዝቅ አደረገ፡፡ ሌላው ቀርቶ አኩይ ሐሳብ ያደረበት ይሁዳ ሳይቀር ኢየሱስን /ጌታውን/ በእግሩ ሥር አየው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ወንጌላዊው ዮሐንስ ኢየሱስ ትኩረት ማድረግ የፈለገው እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር እንደሰጠው፣ እርሱም ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ እንደመጣ፣ ወደ እርሱም እየተመለሰ እንደሆነና በዚህ ሰዓት እርሱ ራሱ አምላክ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ያውቅ እንደነበር ነው፡፡ የሕጽበተ እግሩ ምሳሌ ወዳጅነትን ማሳየት ወይም የመምህራቸውን ትሕትና ማሳያ ሳይሆን እግዚአብሔር በፍጡሮቹ ፊት ተንበርክኮ ማገልገሉን ነው፡፡ እግዚአብሔር የሆነው ሰው ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆች አገልጋይ /ባሪያ/ በመሆን የመጨረሻውን ዝቅተኛ ቦታ ያዘ፡፡

የእኛን ሌሎችን የመጫንና የራሳችን መብትና ክብር የመፈለግ ዝንባሌያችን በዚህ ምስጢር ፊት ስናየው እጅግ አስቂኝና ሞኝነት ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር መሆን ከፈለግን አንድ መንገድ ብቻ አለን፡- ዝቅ ብለን ማገልገል!!

አባ ተሻለ ንማኒ - ሲታዊ

ምንጭ:- This is the day the Lord has made 365 daily meditations: By Wilfrid Stinissen