እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ጾምን ጾምኩ ማለት...

ጾምን-ጾምኩ ማለት...

የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሆነችሁንና የእግዚአብሔር መንፈስ በውሰጣችሁ መኖሩን ታውቁ  የለምን? እንግዲህ ሰው የእግዚአብሔርን ቤተመቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ቅዱስ ነው፡፡ ይህም ቤተመቅደስ እናንተ ናችሁ፡፡1ኛ ቆሮ፡16-17፡፡

ሰው የእግዚአብሔር ንብረት ስለሆነ ወደ እግዚአብሔርም ይመለሳል የእግዚአብሔር መሆኑ በጊዜ የተጀመረ ሳይሆን ከጊዜ በፊት የተጀመረና ለዘላለሙ የሚኖር ነው፤ ስለሆነም የባለቤትነትና የንብረትነት ጥያቄ ወይንም ጉዳይ ነው፡፡ ቁመቱም፤ ጥልቀቱም፤ ወርዱም ሆነ ስፋት ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር ብቻ ነው ማወቅ የሚችለው፡፡

እንግዲያውስ ሰው ይህንን አውቆና አምኖ በነጻነቱ ተቀብሎ ሲኖረው ለምልአት/ለቅደስና/ ይበቃል፤ ቅድስና ማለትም የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ዕቅድ ሙሉ በሙሉ አሜን ብሎ በመቀበል በኖረው ሰው ላይ የሚፈጸም ተግባር ነው፡፡

ጾም ወደዚሁ ግብ ለመመራት የሚያግዝ መሣሪያ ነው እንጂ ራሱ ግብ አይደለም፤ ግባችን ፈጠሪያችን ብቻ ነው፡፡

ጾመ-መጾም ማለት ተወ-መተው ማለት ነው፡፡ ምንን? ብለን ስንጠይቅ ደግሞ መልሱ ወደ ፈጠሪው መራመድንና ማደግን የሚከለክክል እንቅፋት ሊሆንበት የሚችለውን ነገር፤ መንገድ፤ ሁኔታን ጓደኛን…ሁሉ በመተውና በመጸጸት-ንስሓ እየገባም፤ እየተለወጠ መኖር ማለት ነው ማለት፡፡

ስለዚህ ስንጾም ከሚጎዱን ነገሮች እንርቃለን፤ የሚጎዱንንም ነገሮች ከኛ ወዲያ እናርቃቸዋለን፤ የሚጠቅሙንን እንቀርባቸዋለን እናቀረባቸውማለን፡፡ የሚጎዱንና የማይጠቅሙንን ሁሉ መራቅና ማራቅ እንደሚያስፈልገን ሁሉ፤ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡንን ቦታዎችን፤ ነገሮችን፤ ሁኔታዎችንና ሰዎችን መቅረብና መለማመድ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የቀረብነውን ያህል ከመሰናክል እንርቃለን እናርቅማለን፡፡ ሰው ወደፊት እርምጃውን ባደረገ ቁጥር ከኋላ እየራቀ ይሄዳል፤ ወደፊት ወዳለው ቦታም እየቀረበ ይሄዳል ማለትም ራሱን ከመጥፎ ነገር ባስወገደው መጠን በበጎ ነገር ደግሞ ይሞላል ትክክለኛ /መልካም/ የሆነው ብቻ ይሞላናል፤ መልካም ደግሞ ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡

ጾም የሚጾመው ለመሰጠት ነው፤ ፈጣሪ ማንነቱን ለኛ ሙሉ በሙሉ እንደሰጠን ሁሉ፤ እኛም በባሕርያችን  ወይም ተፈጥሯችን በሚፈቅድልን መጠን ተመሳሳይ ተግባር ለመፈጸም ነው፡፡ ወደ ዓለም ስንመጣም ከእሱ ነን፤ የእሱም ነን፤ እግዚአብሔር ለሁሌም የርሱ መሆናችን እንዲቀናነስበት አይፈልግም፤ ስለሆነም የሱ የሆነውን እንዳለ በታማኝነት በመጠበቅ ሕያዋን ሆነን የሕያው አምላክ ልጆች ሆነን ለመቅረትና ጌታ ራሱ ያንን ጠላት የሆነውን አውሬ በመቃወም ሕይወቱን ለአንድ ትልቅና ለማያዳግም ዓላማ መሥዋዕት ያቀረበበት ግብ እኛን ማለትም የሰውን ልጅ የማያልፈውን ሕይወት ለማውረስ ነው፡፡ ስለዚህ ጸዋሚው በውስጡ ያለውን ማለትም በራሱ፤ በፈጣሪውና በጓደኛውም ለይ የሚያሳምጸውን ባሕርይ ለይቶ ማውቅና በሚመቸው መሣሪያ ማጥቃት ይጠበቅበታል፡፡

ይህንን ለማድረግ እንግዲህ ሰው ከራሱ ጋር የሚገናኝበትን ጊዜ መፍጠር/ማግኘት/ አለበት፡፡ አለበለዚያ ራሳችንን መውደድ እንጂ ማፍቀር አንችልም፤ ራስ ወዳድነት ደግሞ ራስን መገንባት ሳይሆን ራስህን ማፍረስ ማለት ነው፤ የዚያኑ ያህል ደግሞ ሌላውንና አምላካችንን እንጎዳለን፡፡

ጧት ከእንቅልፍ ስንነሳ ሁኔታችን ማታ ከመተኛታችን በፊት እንደ ነበረ ከሆነ አንድ ችግር አለ ማለት ነው፤ ስለሆም ወደ መኝታ/አልጋ/ የተሄደው ለይስሙላ እንጂ በተግባር ሲታይ ለእንቅልፍ አይደለም፡፡ እንቅልፍ ማለት እረፍት ማለት ነው፡፡ የእንቅልፉ ሰዓት አለፈ እንጂ አልተኛንም ማለት ነው። እንዲሁም የጾም ወቅትም ውሳኔ ካልትጨመረበትና ንስሐ / የባሕርይ/ መለወጥ ካልታከለበት/ ጾም ለራሱ እንጂ ለኛ ትርጉም አልባ ሆኖ ይቀራል፡፡ ስለዚህ ጾም ወደ ንስሓ መምራት አለበት፤ ንስሓ ማለት ደግሞ መለወጥ ማለት ነው፤ የጾም ዓላማም ይህ ነው፤ ራስህን ለፈጣሪ ማስገዛት፤ እኛነታችንን ለመግራትና ስለአለፈውም በደል ካሳ መክፈል ማለት ነው ፡፡

ሰው በመሠረቱ የሁለት ዓለማት ዜጋ ነው፤ ሰማያዊና ምድራዊ፤ የዘላለምና የጊዜያዊ ቅምር ነው። አምላክ እሱን ለመፍጠር ካሰበበት ቅጽበት ጀምሮ በዘላለማዊ ክልል /ክፍል/ መርሓግብር ውስጥ ነው ያለው፡፡ ወደፊት ቀጥሎ የመኖር ዕድል እንጂ ወደኋላ የመመለስ ዕድል የለውም፤ ይህ ታላቅ ዕድል ደግሞ በሰው ነፃነታዊ ምርጫ ወደ ክፉ ፍጻሜ ሊደርስ ይችላል እንጂ ፈጣሪውማ የሰው ፍጻሜ ወሰን/ገደብ-አልባ ሕይወት እንዲኖረው ነው፡፡ ይህም የተመደበው በእግዚአብሐር ዘላለማዊ ጥበብ ብቻ ነው፡፡

ስለዚህ  ይህ ዓይነቱ ፍጡር/ሰው/ በይበልጥ ደግሞ ክርስቲያን የጾምን ትርጉም የሚያውቅ፤ ሕይወትንና የመፈጠርን ትርጉም የሚያውቅ፤ ለዓላማ መፈጠሩን፤ ለዓለማ መጠራቱን፤ የሚጠብቀው መጪው ታላቅ ጊዜ መኖሩን፤ አንድ ቀን የመጨረሻ ሂሳብ ትርፍና ኪሳራ በማቅረብ በመጨረሻው ኦዲተር/ፈጣሪ/ ፊርማ የሚዘጋበት ሁኔታ ከፊቱ ያለ መሆኑን የሚያውቅ ፍጡር/ሰው/ በዘፈቀደ ማለትም በፊትም አሁንም፤ ለወደፊትም በቀጣዩ የሕይወት ጊዜ በጨፈና እንዳይኖር/እንዳንኖር/ ነው ቅድስት ቤተክርስቲያን በመድኃኔዓለም ተመሥርታ በየወቅቱ የጸጋን አውታሮች በክርስቶስና በራሷ አዘጋጅነት ዘረግታ ጥሪ የምታቀርበው።

ጥሪውንም የማድመጥና መልስ የመስጠት ጊዜ አሁን ነው፤ በተፈቀደለትና በተሰጠው ጊዜ የማይጠቀም ግን የቤቱን መሠረት በአሸዋ ላይ የሚያንጽ ሞኝ…ማቴ.7፡ 26-27፤ የሚሰማና የሚኖር ግን የቤቱን መሠረት በዓለት ላይ የሚገነባ ብልህ ሰው ይመስላል…የማቴ.7፡24-25፡፡

መልካም የጸጋ ጊዜ/የዐቢጾም/ወቅት ያድርግልን፡፡

አባ ገብረወልድ ወርቁ ሲታዊ - ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን አዲስ አበባ።


አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት