እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

“ቀድሱ ጾመ… ጾምን አክብሩ፤ ጹሙ” ኢዮኤል 1፡14

ዓርባ ጾም

እግዚአብሔር በተወሰነ ጊዜና አደራረግ ከአንዳንድ ምግቦች እንድንከለከል ማለትም እንድንጾም ይፈልጋል፡፡ “ቀድሱ ጸመ… ጾምን አክብሩ፤ ጹሙ” ኢዮኤ 1፡14 ይለናል፡፡ ጾም እግዚአብሔርን የማያስደስት ለነፍሳችን  ደግሞ አስፈላጊ መንፈሳዊ ተግባር ነው፡፡ ለሥጋችን መግቻ ልጓም ተጋድሎም ነው፡፡ በጾም ሥጋችንን እንቀጣዋለን እናደክመዋለን፡፡ የኃጢአታችንን ምሕረት ደግሞ እንለምናለን፡፡

ኢየሱስ ጾም አስፈላጊ እንደሆነ እኛን ለማስረዳት ሲል አርባ ቀን ጾመ፡፡ ቤተክርስቲያን ደግሞ ፈለጉን በመከተል ልጆቿ ሁሉም እንዲጾሙ አዘዘቻቸው፡፡ ፍሬውንም አይታ በዓመት ብዙ ጊዜ እንዲጾሙ ፈለገች፡፡ ከብዙዎቹ የሕዝበ ክርስቲያን ጾሞች አንዱ ሕዝቡ በአክብሮት የሚያየውና በተስፋ የሚጠብቀው የአርባ ጾም ነው፡፡ ይህ የጾም ጊዜ የኢየሱስን ጾም ያስታውሰናል፡፡ በተለይም ደግሞ የደኀንነታችን መጨረሻ የሆነው የትንሣኤ በዓል ማስተናገጃ በመሆኑ ቤተክርስቲያን በጥሩ ሁኔታ ጾመን እንድናሳልፈው ትመክረናለች፡፡

በአርባ ጾም መግቢያ ላይ ቤተክርስቲያን “እነሆ የተመረጠው ሰዓት አሁን ነው፤ የደኅንነትም ቀን አሁን ነው፡፡ አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ በምንም ነገር ለማንም መሰናከያ አንሆንም፡፡ ይልቅስ መከራን ችግርን ጭንቀትንም እየታገስን የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆናችንን በሁሉ በኩል እንገልጣለን” 2ቆሮ 6፡2 የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስን ቃል እየጠቀሰች አርባ ጾም ምን እንደሆነ እንዴት አድርገን ማሳለፍ እንደሚገባን ታስተምረናለች፡፡

ዓርባ ጾም ቅዱስ ወቅት የጸጋና የደኅንነታችንም ጊዜ ነው፡፡ እንደዚህ ከሆነ በቅድስና ልናሳልፈው፣ ጸጋውንም ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ ይህንንም እንድናደርግ ከላይ የጠቀስነውን የቅዱስ ጳውሎስን ቃል እንከተል፡፡

እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ሐሳብ አርባ ጾምን በሚገባ እንድናከብረው በመጀመሪያ ኃጢአትን መተው ቀጥለን ደግሞ መልካም ሥራ ማዘውተር አለብን፡፡

ሀ.  ኃጢአትን መተው፣ “በምንም ነገር ለማንም መሰናከያ አንሆንም” ይለናል እግዚአብሔርንና ባልንጀራችንን የሚያሳዝን ሃይማኖታችንን የሚያስነቅፍ ሥራ ማድረግ የለብንም፡፡ በአነጋገራችን ወይም በሥራችን አምላክንና ሰውን እንዳንበድል መፍራት አለብን፡፡ ስለዚህ ከመጥፎ ንግግር (ውሸት፣ ስድብ፣ ሐሜት፣ እርግማን) ከመጥሮ ሥራ (ቂም መያዝ፣ ዓመጽ፣ ጥል፣ ሌብነት፣ አመንዝራነት፣ ባልንጀራን በሆነ መንገድ መጉዳት…) መጠንቀቅ አለብን፡፡ ይህም የመልካም ሥራ መሠረት ነው፡፡

ለ.  መልካም ማድረግ፣ “መከራን ችግርን ጭንቀትንም እየታገስን የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆናችንን በሁሉ በኩል እንገልጣለን” እየለ ያሳስበናል፡፡ ኃጢአትን ስንተሙ መልካም ሥራን ደግሞ ማድረግ አለብን፡፡ ቆሻሻ ልብስ አውልቀን ንጹሑን እንደምንለብስ እንደዚሁም ደግሞ የኃጢአት ልብስን አውልቀን የጽድቅን ልብስ መልበስ አለብን፡፡ በእውነት የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሚያደርገን እርሱን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ስንፈጽም ነው፡፡ ይህም ደግሞ ፍቅር፣ ጸሎት፣ ተጋድሎ፣ ጾም፣ ትሕትና፣ ትዕግስት፣ ምሕረት ነው፡፡ ከአምላክ ቀጥለን በአምሳሉ የፈጠረውን ባልንጀራችንን ልናከብረውና ልናስደስተው ይገባናል፡፡ በመሆኑም ከማንኛውም ሰው ጋር የመቃረን፣ የጥላቻ፣ የአምባጓሮ ምልክት እንዳይኖረን ብቻ ሳይሆን ፍቅርም እንዲኖረን ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ዓይነት መንፈስ ነው አርባ ጾም በጥሩ ሁኔታ ሲያልፍ አምላክን ሊያስደስት እኛንም ሊጠቅመን የሚችለው፡፡

ብዙ ጊዜ የሂደት ዋናው ነገር ይረሳና ሌላ ተጨማሪ ነገር እናደርጋለን፡፡ የሚበዛው ጾም ቢሆንም ዋናው ነገር መጥፎ ነገርን መተው መልካም ነገርን ማድረግ ቸል በማለት ለውጫዊው ነገር እንጨነቃለን፡፡ አንዳንዶቹ ክርስቲያኖች ይሰክራሉ፣ ይጨፍራሉ፣ ይሰርቃሉ፣ ያመነዝራሉ፣ ያምጻሉ፣ ባልንጀራቸውን ይጠላሉ፡፡ ለትልቅ ኃጢአት አይጨነቁም ለጾም ግን የጨነቃሉ፡፡ እንዳያፈርሱ ብለው እስከ ሞት ይደርሳሉ፡፡ ነፍሳቸው ግን በትልቅ ኃጢአት እንዳትበላሸ የሚያደርጉት ነገር የለም፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን እግዚአብሔር “እኔ የምፈልገው ጾም የዚህ አይነት ጾም ነውን? ይህንን ደግሞ ጾም ትሉታላችሁን? የዚህ ዓይነተ ጾም ጸሎታችሁ እንዳይሰማ ያደርገዋል” ኢሳ. 58፡3 እያለ ይናገራቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ “ጽድቅ እንዴት ከኃጢአት ጋር ልትሆን ትችላለች እንዴትስ ብርሃን ከጨለማ ጋር ሊተባበር ይችላል?” 2ኛ ቆሮ. 6፡1ዐ እያለ ይናገራል፡፡ “ስንጾም ሕይወታችን ከቅድስና መንፈስ ጋር የማይስማማ ከሆነ አረማውያን ይንቁናል መጥሮ ልማዳቸውም የእምነታችን ተቃራኒ ሆኖ ይገኛል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ምግብን መተው ባይሆን ኃጢአትን በመተው ላይ ነው” ይላል ቅዱስ ጎርጎርዮስ ትልቁ፡፡

ውጫዊ ጾማችን ከውስጣዊ ጾማችን ጋር ካልተባበረ ፍሬ የለውም ጐደሎ ነው፡፡ በጀመሪያ ከምግብ ከመከልከላችን በፊት ከኃጢአት መከላከል እንደለብን አንዘንጋ፡፡ ኃጢአት በተፈጥሮው ክፉ በመሆኑ ክልክል ነው፡፡ ጾም ያለው ምግብ ግን በተፈጥሮ መጥፎ ባይሆንም ኃጢአት የሚሆነው ስለ ተከለከተ ነው፡፡ የሚከለከልበት ጊዜ በግሞ የተወሰነ ነው፡፡ ሁል ጊዜ አይደለም፡፡ እምነት ያለ ሥራ የሞተች ናት፡፡ መልካም ሥራ ደግሞ ያለ እግዚአብሔር ጸጋ ፍሬ የለውም፡፡ እንደዚሁም ጾም ያለ ንጽሕና ፍሬ የለውም፡፡ ጥሩ ምግብን በቆሻሻ ዕቃ እንደማቅረብ ነው፡፡

ዓርባ ጾማችን ጥቅም ያለው እንዲሆን ከፈለግን የቅዱስ ጳውሎስን ምክር እንከተል፡፡ ጾማችን ውጫዊ እንዲሆን አናድርገው፡፡ በሥጋችንና በንፈሳችን እንጹም፡፡ ከኃጢአትና ከጥፋት እየተከላከልን መልካም ተግባር እያደረግን ለፋሲካ እንሰናዳ፡፡

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት