እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር

ኢየሱስ ወደ ሰማያዊ አባቱ የሚመለስበት ጊዜ ሲደርስ ያፈቅራቸው ለነበሩ ሐዋርያቱ የፍቅርሩን መጨረሻ ምልክት አሳያቸው፡፡ ዮሐ. 13፡1 ይሁዳ ከጻፊዎችና ከሊቃነ ካህናት ጋር ተስማምቶ በእጃቸው አሳልፎ እንደሚሰጠው ሲያውቅ ሐዋርያት የሚደርስባቸውን መከራ አሰታወቃቸው፡፡ ከእነርሱም ጋር የመጨረሻ ትልቅ ምሰጢር ያለው እራት በላ፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ፋሲካን ከእነርሱ ጋር አከበረ፡፡

እርሱ ይፈልገው እንደነበረ ከሐዋርያቱ ጓደኞች በአንዱ ቤት ተሰበሰቡ “ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር” ሉቃ. 22፡2ዐ አላቸው፡፡ ሲበሉም ሳለ እንጀራውን አንስቶ የምስጋና ጸሎት ወደ አባቱ ካቀረበ በኋላ እንጀራውን ባርኮ ቆረሰው፡፡ ከዚያም ለሐዋርያቱ “እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው” ሉቃ. 22፡19 እያለ ሰጣቸው፡፡ ቀጥሎም ጽዋውን አንስቶ ጸሎት ካደረገ በኋላ “እንካችሁ ጠጡ ለኃጢአት ስርየት ለብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው” አላቸው፡፡ ሉቃ. 22፡2ዐ በዚህም ኢየሱስ ከሐዋርያቱና ከሁሉም ተከታዮቹ ጋር እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ በምድር የሚኖርበትን ምስጢረ ቁርባን ሠራ፡፡ ከበሉም በኋላ የልቡን ሐዘን ገለጸላቸው፡፡ “ከእናንተ አንዱ ይክደኛል” አላቸው ማር.14፡18 ሁሉም በጣም ደነገጡ እርስ በርሳቸውም ተያዩ “እኔ እሆን?” እያሉ ተጠያየቁ፡፡ ማር. 14፡19 እንደገና ኢየሱስ ጠላቶቹ ይዘውት ሁሉም በፍርሃት ጥለውት እንደሚሸሹ አስታወቃቸው፡፡

በልተውም ከጨረሱ በኋላ ኢየሱስ ወገቡን ሸብ አድርጐ ውኃ በሳህን አድርጐ እግራቸውን ማጠብ ጀመረ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ጋ ሲደርስ ግን ገርሞት መታጠብን እምቢ አለ፡፡ ኢየሱስ ግን “ ካለታጠብክ ከእኔ ጋር ህብረት የለህም” ዮሐ. 13፡ 6-9 ሲለው ፈርቶ ታጠበ፡፡ እግራቸውን ካጠበ በኋላ “ያደረግሁላችሁን አስተዋላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ እንዲሁም ነኝና መልካም ትላላችሁ፡፡

“እንግዲህ እኔ መምህርና ጌታ ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል” ዮሐ. 13፡ 12-14 እያለ ተናገራቸው፡፡ ቀጥሎም ደግሞ “አዲስ ትዕዛዝ እሰጣችኋለሁ እርስ በርሳችሁ ተፋቀሩ… ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚያ ያውቃሉ” ዮሐ. 13፡34 አላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ይዟቸው ወደ ጌተሰማኒ ሄደ፡፡ እዚያ ሲደርስ ሌሎችን ትቶ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስና ያዕቆብን ለይቶ ወሰዳቸው ጥቂት እንደተጓዙም እነርሱን ትቷቸው ሄደ፡፡ ተንበርክኰም ጸሎት ማድረግ ጀመረ፡፡

የሕማማቱ ከባድነት ታየው ወደ ሶስቱ ተመልሶ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች” አላቸው፡፡ ቀጥሎም ደግሞ “አባቴ ሆይ ይህችን ፅዋ ሳልጠጣት ታልፍ ዘንድ የማይቻል እንደ ሆነ እንደ ፈቃድህ ይሁን” ማቴ. 26፡ 38-39 እያለ ጸለየ፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ይሁዳ ከጠላቶቹ ጋር መጣ፡፡ ወደ እርሱም ቀርቦ “መምህር ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን” እያለ ሳመው፡፡ እነርሱም በፍጥነት ያዙት እጆቹንም አስረው መሰዱት፡፡

ኢየሱስ የፍቅሩ መጨረሻና ዋና ምልክት አድርጐ የተወልን በዚህ በስደት ሕይወት መንፈሳዊ ስንቃችን እንዲሆን ፈልጐ ቅዱስ ቁርባንን ሠራልን በደስታ እናመስግነው፡፡ ለዚህ የምስጢራት ራስ ለሆነው ቁርባን በልባችን ተደፍተን እንስገድለት፡፡ የልባችን ምኞትም እሱ ይሁን ዘወትር ከእርሱ ጋር መሆንን እንፈልግ፡፡

ኢየሱስ ለሐዋርያቱ እግራቸውን በማጠብ የተወልንን አብነት፣ ፍቅር፣ ትሕትና እንመልከት፡፡ እርሱ በመጨረሻ የተማፀነን የእርስ በርስ ፍቅር በማስታወስ በተግባር እናውለው፡፡ ተከታዮቹ መሆናችን የሚታወቀው በሌላ ሳይሆን ባልንጀራችንን በማፍቀር ነው፡፡

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት