ክርስቶስ ንጉሥ

ክርስቶስ ንጉሥ
Christ the KING

ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን በታላቅ መንፈሳዊነት ከምታከብራቸው በአላት አንዱ የክርስቶስ ንጉሥ በአል ነው፡፡ የክርስቶስ ንጉሥ በአል እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1925 ዓ.ም በር.ሊ.ጳ.ፒየስ 11ኛ Quas Primas በተሰኘው ሐዋርያዊ መልእክታቸው የተጀመረ በአል ነው፡፡
ር.ሊ.ጳ.ፒየስ 11ኛ በጊዜው ለነበረው ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ መዋቅር መልስ ለመስጠት ይህንን በዓል አውጀዋል፡፡ ጊዜው በታላላቅ አምባገነን ፖለቲካዊ ኃይል የተሞላ ከመሆኑ ባሻገር በጊዜው የነበሩት ማህበራዊ መዋቅሮች ለክርስቶስ ቦታ ያልነበራቸው ነበሩ፡፡ በርካታ ክርስቲያኖች በፖለቲካው ፈርጣማ ኃይሎች ፍልስፍና በመማከራቸው ክርስቶስ በሕይወታቸው ውስጥ ቦታ አልነበራቸውም ንጉሣዊ የፍጥረት ጌትነቱንም አይቀበሉም ነበር፡፡ ር.ሊ.ጳ. ፒየስ 11ኛ ለጊዜው ምልክቶች ትኩረት በመስጠት ይህንን በአል ሲያውጁ የተወሰኑ ነጥቦችን ግልጽ ለማድረግ አስበው ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡-
1. ቤተክርስቲያን ከየትኛውም ፖለቲካዊ ርዮተ ዓለም በላይ ነፃነት ያላት በመሆኗ ከመንግስት ተጽዕኖ ነፃ መሆኗን ለማሳየት (Quas Primas፣32)
2. መሪዎች እና ሕዝቦቻቸው የክርስቶስን ዘላለማዊ ንጉሥነት እንዲገነዘቡ በር ለመክፈት (Quas Primas፣31)
3. ክርስቶስ በአማኞች ልብ አዕምሮ አካል እና ሰውነት ውስጥ መንገሥ እንደሚገባው በማሳየት ክርስትያኖች በዓለም ፊት ስለክርስቶስ ንጉሥነት ለመመስከር የሚችሉበትን መልካም አጋጣሚ ለመፍጠር ናቸው፡፡
ዛሬም ቢሆን ዓለማችን ከራሷ ምድራዊ መሪዎች ባሻገር ወደ ክርስቶስ አትመለከትም፡፡ ክርስቲያን መሪዎችም ቢሆኑ መሪነታቸው ከሥልጣን ጋር የተያያዘ የስራ ዘርፍ እንጂ ከክርስቶስ ንግሥና ጋር የሚገናኝ አገልጋይነት መሆኑ አይታያቸውም፡፡ ግላዊ ስልጣን የግል ችሎታ የግል ሐሳብ ብቻ ሲንሸራሸር እናስተውላለን፡፡ ይህ በሁሉም ቦታ የሚታይ ችግር ነው፡፡ የክርስቶስ ንጉሥ በዓል በዚህ ውስጥ ብቅ ያለው እውነተኛው ንጉሥ እርሱ ብቻ መሆኑን ለመመስከር ነው፡፡ ሌሎች ምድራዊ መሪዎች ሁሉ የአንዱ እውነተኛ ንጉሥ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅጥረኞች ናቸው፡፡ እውነተኛ አገልግሎታቸውን እና ሥልጣናቸውን የሚያገኙት ከእርሱ ጋር ሠላማዊ ግንኙነት ሲመሰርቱ ብቻ ነው፡፡ በጊዜው የነበረው ንጉሥ ጲላጦስ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ “አንተ ንጉሥ ነህን?” በማለት ጥያቄውን ያቀርባል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መልስ ይሰጠዋል፡፡ “እኔ ንጉሥ እንደሆንሁ አንተ ትላለህ ፤ እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ፤ ስለዚህም ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል” (ዮሐ 18፡37)፡፡
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ንጉሥነት ስናከብር ራሱን ለዓለም ቤዛ አድርጎ ያቀረበውን ንጉሥ በዓል እያስከበርን ነው፡፡ እርሱ እንዲህ ይላል “እንዲሁ የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” (ማር 10፡47) ፡፡ ይህ ንጉሥ አገልጋይ ሆኖ መጣ ፣ ይህ ንጉስ የህዝቡን እግር የሚያጥብ ሆኖ መጣ ፣ ይህ ንጉስ እናንተ ሸክም የከበደባችሁ ወደ እኔ ኑ ብሎ መጣ ፣ሰው ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ የሚያሳርፍ ሆኖ መጣ፡፡ የክርስቶስ ንጉሥነት በትህትና እና በአገልግሎት የተገለጠ ንጉሥነት ነው፡፡ በዚህ አይነት ክርስቶስ አዲስ የመሪነት መንፈስ ይዞ ወደ ዓለም መጥቷልና የአለምን ምድራዊ መሪዎች ገጽታ እና የመሪነት እሳቤ ለውጧል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትሁት ንጉሥ ነው፡ ይህ ደግሞ ከመጀመሪያው ጀምሮ በተግባር የታየ እውነታ ነው፡፡ ልደቱ በከብቶች ግርግም ውስጥ እንደነበረ እናስታውሳለን፡፡ እርሱ ምድራዊውን የንጉሥ ዝና እና ስልጣን ሁሉ ሽሮ በምትኩ አዲስ የንጉሥ መልክ ተክሏል፤ ይህ ንጉሥ ገዢ ሳይሆን አገልጋይ ንጉሥ ነው፡፡ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ፍቅሩ በፍቅር እንድንገዛለት ያደርገናል፡፡ በፍርሀት ሳይሆን በእውነት መንፈስ እንገዛለት ዘንድ ትህትናው ይጠራናል፡፡
ኢየሱስ ንጉሥ ነው! ነገር ግን መንግስቱ ከዚህ ዓለም አይደለም፡፡ የዚህ ዓለም ሰዎች በሀይልና በስልጣን ሌሎችን ይገዛሉ፤ ሌሎችን ከእነርሱ በታች አድርገው ይበዘብዛሉ፣ በኢየሱስ መንግስት ግን ይህ አይነቱ ሥልጣን ቦታ የለውም፡፡ በዓለም ላይ ኃይል እና ሥልጣን ያላቸው ሁሉ ሥልጣናቸውን በተለያየ መንገድ ይጠቀማሉ ፤ አንዳንድ ጊዜ ይህንን ስልጣን የለአግባብ ተጠቅመው ሌሎችን ይበድላሉ ኢየሱስ ግን በመስቀል ላይ ኃይል የሌለው ትሁት ንጉሥ ሆነ ራሱን እንኳን ማዳን ያልቻለ ንጉሥ ሆነ “ሌሎችን አዳነ እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ ከሆነ ራሱን ያድን እያሉ አፌዙበት” (ሉቃ 23፡35)፡፡ ነገር ግን የክርስቶስ መንግስት የትህትና እና የአገልግሎት መንግስት ነው፡፡
ኢየሱስ ንጉሥ ነው፣ ነገር ግን መንግስቱ ከዚህ ዓለም አይደለም፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ባለሥልጣናት ሥልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀማቸው ምክንያት ር.ሊ.ጳ. ፒየስ 11ኛ “የክርስቶስ ንጉስ በዓል” እንዲከበር ዐወጁ፡፡ እንግዲህ የዚህ በዓል መነሻ ባለሥልጣናት ኃይላቸውን ያለአግባብ መጠቀማቸው ነው፤ የኃይል አጠቃቀማቸው ከኢየሱስ የኃይል አጠቃቀም ተቃራኒ ነበር፡፤ ኢየሱስ ስልጣኑን ያለአግባብ አልተጠቀመም ፤ እርሱ ለባለሥልጣናት የሥልጣን አጠቃቀም አብነት ነው፡፡ በኢየሱስ መንግስት ለስልጣን መስገብገብ ፣ አልጠግብ ባይነት ወይም ግፍ የለም፡፡
በተለያዩ አጋጣሚዎች እንዳየነው የኢየሱስ ሥልጣን ከዚህ ዓለም ባለሥልጣናት ኃይል ጋር ተቃራኒ ነው፡፡ ኢየሱስ ከቀረጥ ሰብሳቢዎች፣ ከኃጢያተኞች እና ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር ሲነጋገር፣ ሲበላ፣ ሲወያይ ይታያል፡፡ በዚህም ምክንያት የጊዜው ባለሥልጣናት “በላተኛ እና የወይን ጠጅ ጠጪ፣ የቀራጮችና የኃጢያተኞች ወዳጅ ” (ሉቃ 7፡34) ብለው ፈረዱበት፡፡ ባለሥልጣናት ክብር ያላቸውን ሰዎች እና ኃብታሞችን ሲቀበሉ ኢየሱስ ግን ታናናሾችን ፣ በማህበረሰቡ ዘንድ የተናቁትን እና ድሆችን ይቀበል ነበር፡፡ ዓላማውም ባለሥልጣናት ወደ እነርሱ ከሚመጡ ሰዎች እጅ መንሻ ስጦታ ይፈልጋሉ፤ ኢየሱስ ግን ለሰዎች ሰጦታ ይሰጥ ነበር፡፡ ጤና ላጡ ጤናቸውን ይመልሳል፣ ለታሰሩ መፈታትን፣ ለዐይነ ሥውራን ብርሀንን ያድል ነበር፡፡
ኢየሱስ ንጉሥ ነው፤ ንጉሥ ስለሆነ አክሊል ደፍቷል፡፡ ነገር ግን የእርሱ አክሊል እንደዚህ ዐለም ባለሥልጣናት አይደለም፡፡ የእርሱ ዘውድ የእሾህ ዐክሊል ነው፡፡ ኢየሱስ ንጉሥ ነውና ባንዲራ አለው፡፡ የእርሱ ባንዲራ የተቀደሰው መስቀል ነው፡፡ ስለዚሀ የእርሱ የሆኑት ሁሉ ይህን ባንዲራ ይዘው እንዲከተሉት ይጋብዛል “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” (ሉቃ 14፡27)፡፡ ስለዚህ የኢየሱስ መንግስት ከዚህ ዐለም ገዢዎች ተቃራኒ ነው፡፡ ኢየሱስ እውነት እና የህይወት ንጉስ፣ ኢየሱስ የቅድስና እና የጸጋ ንጉሥ፣ ኢየሱስ የሰላም፣ የፍትህ እና የፍቅር ንጉሥ ነው፡፡
ነገር ግን ይህ መልእክት ከቤተክርስትያን የሚነገር መልእክት ብቻ ሳይሆን ለቤተክርስቲያንም የሚነገር መልእክት ነው፡፡ ከሁሉ በፊት የክርስቶስ ንጉሣዊ ባህርይ በቤተክርስቲያን ውስጥ ህያው ሆኖ መታየት አለበት፡፡ ቤተ ክርስቲያን እኛ ራሳችን እያንዳንዳችን ነን እንጂ ቤተክርስቲያን ሲባል ጳጳሳትን፣ ካህናትን፣ መነኮሳትን ብቻ አይምሰላችሁ፡፡ በቅድስት ሥላሴ ስም የተጠመቀ ክርስቲያን ሁሉ የክርስቶስ ንጉሣዊ ባሕርይ ተካፋይ ነው፡፡ በጥምቀት አማካኝነት በክርስቶስ ንጉሣዊ ባሕርይ ውስጥ ተካፋይ የሆነ ሰው ሁሉ እውነተኛውን የንጉሥነት ተግባር በሕይወቱ መግለጥ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ዓይነት ቤተክርስቲያን የእውነተኛውን ንጉሥ ባሕርይ የለበሱ የንጉሥ ሕዝቦች ጉባዔ ትሆናለች፡፡ በዚህች ቤተክርስቲያን ውስጥ ሕዝቦች በትህትና እና በአገልጋይነት መንፈስ መኖር አለባቸው፤ ምክንያቱም የቤተክርስቲያን ራስ እና የመላው ዓለም እውነተኛ ንጉሥ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ከእኔ ተማሩ እኔ የዋህ እና ትሁት ነኝ” (ማቴ 11፡29) ይላል፡፡ በእውነትም እርሱ ትሑት እና አገልጋይ ንጉሥ ነው፡፡ እንግዲህ ጳጳሳት፣ ካህናት እና ሕዝበ እግዚአብሔር በጥምቀት አማካኝነት የለበሱትን የንጉሥነትሥልጣን እና ባሕርይ በየተሰማሩባቸው የአገልግሎት ዘርፎች በሚሰጡት አገልግሎት በተግባራዊ የሕይወት ምስክርነት መግለጥ ይገባቸዋል፡፡ በዚህ ዓይነት በዓለም ያሉት ሰዎች ሁሉ ስለእኛ ትሑት አገልግሎት መጠየቅ ይጀምራሉ፡፡ እኛም ለተቀረው ዓለም እውነተኛው ንጉሥ ክርስቶስ ያስተማረንን ትሕትና እና አገልግሎት እንመሰክራለን፡፡
ምዕመናን በክርስቶስ ንጉሣዊ ባህርይ ውሰጥ ያላቸው ተሳትፎ
ክርስቲያኖች በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሳዊ ባሕርይ ውስጥ ሱታፌ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ንጉሳዊ ተሳትፎአቸው ኃጢአትን ድል ለማድረግ እና የእግዚአብሔርን መንግስት ለመመስረት በሚያደርጉት ትግል በተግባር ተገልጦ ይታያል፡፡ በዚህ ትግል ውስጥ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር አሰልፈው በመስጠት በሕዝቦች መካከል በወንድሞቻቸው እና በእህቶቻቸው ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስን ያገለግላሉ፡፡ ጌታችን “ከእነዚህ ታናናሾች ለአንዱ ያደረጋችሁት ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው፡፡” (ማቴ 25፡40) ይላል፡፡
የክርሰቲያኖች ንጉሳዊ ማንነት ከምድራዊ ነገሮች ጋር ሳይሆን ከሰማይ ኃይሎች ጋር በውጊያ ይፈተናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንኑ በግልጽ ያስተምረናል፡፡“መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፣ ከአለቆች እና ከሥልጣናት ጋር፣ ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዢዎች ጋር፣ በሰማያዊም ስፍራ ካሉት ከክፋት መንፈሳዊያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ” (ኤፌ 6፡12) ስለዚህ ንጉስ መሆናችን የሚገለጠው በምንድነው? ንጉስ መሆናችን የሚገለጠው ከእውነተኛ ንጉስ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሳዊ ባህርይ በተነሳ ነው፡፡ የእርሱ ንጉሳዊ ባሕርይ መሪ መሆን ብቻ ሳይሆን የደቀመዛሙርቱን እግር የሚያጥብ አገልጋይ መሆንም ጭምር ነው፡፡ ውጊያውን ድል የምናደርግበት መሣሪያ ትሕትና ነው፡፡ በትሕትና ልዕልና ይገኛል! የክርስቲያኖች ጥሪ በትሕትና ንጉሡን መምሰል እና ራሳችንን ስለወንድሞቻችን እና ስለ እህቶቻችን አሳልፈን መስጠት ነው፡፡
ከዚህም በላይ ክርስቲያኖች ሁሉን ነገር በኢየሱስ ክርስቶስ በመጠቅለል ለአብ የተቀደሰ መሥዋዕት አድርገው ማቅረብ አለባቸው፤ ይህ ደግሞ በዙሪያቸው ካለው ነገር ይጀምራል፡፡ በተለይ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ላይ የበላይ ባለዐደራ አስተዳዳሪ በመሆኑ (ዘፍ 1፡28) በተፈጥሮ ልዩ ጥበቃ ማድረግ ይገባዋል፡፡ ተፈጥሮን መበደል የፈጣሪን ድንቅ ስጦታ ማባከን ስለሆነ ከተፈጥሮ ጋር ባለን ግንኙነት ጠንቃቆች መሆን መቻል አለብን፡፡ በተፈጥሮ ላይ ንጉሥ የሆንነው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያስተምረን ተፈጥሮን ለመንከባከብ፣ ለማልማት እና ለመጠበቅ ነው፡፡ (ዘፍ2፡ 15)
የክርስቶስ ንጉሥ በዓል በየትኛውም የስራ ዘርፍ ሥልጣን እና ኃላፊነት ተሰጥቷቸው እየሰሩ የሚገኙ ሁሉ ሥልጣናቸውን በምን መልኩ እንደሚጠቀሙ ይፈትሹ ዘንድ የቀረበ ጥሪ ነው፡፡ ክርስቶስ “ከእኔ ተማሩ” (ማቴ 11፡29) ይላል፡፡ የእኛ የሥልጣን አጠቃቀም ከክርስቶስ የሥልጣን አጠቃቀም ጋር ሲተያይ ምን ይመስላል? ይህ እኔን ጨምሮ ለእያንዳንዱ ሰው የቀረበ ጥያቄ ነው፡፡ ሥልጣናችን ሌሎችን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ የምናገለግልበት መሣሪያ ወይስ ከእኛ በላይ ናቸው ብለን የምናስባቸውን ሁሉ ወደታች ለማውረድ እና ከእግራችን በታች የምናደርግበት መንጠቆ ነው? ሥልጣናችንን የምንጠቀምበት መንገድ “መንግስትህ ትምጣ በማለት ዕለት ዕለት ለምንደግመው ጸሎት የተዘጋጀ መሆን አለበት”፡፡ ምክንያቱም የክርስቶስ መንግሥት የትሕትና እና የአገልግሎት፣ የሰላም እና የፍትህ መንግሥት ነው፡፡ በተለይ በዚህ በሥልጣን በሚያምን ማኅበራዊ ዐውድ ውስጥ በቅድስት ሥላሴ የምናምን ክርስቲያኖች ሁሉ የክርስቶስ ንጉሣዊ ምስክሮች በመሆን በሥልጣን ማገልገል እና ትሁት መሆን እንደሚቻል ማሳየት አለብን፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ ነው! የእርሱን ንጉሥ መሆን የሚጠራጠር ማንም ክርስትያን የለም፡፡ ክርስቲያኖች የተለያዩ የእምነት ቀኖናዎች ቢኖሩን እና በተወሰኑ መንገዶች የተለያየን ብንሆንም እንኳን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለን እምነት አንድ ያደርገናል፡፡ እኛ ከልዩነቶቻችን በላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለን አንድነት ስለሚበልጥ ዘወትር በአንድ ገበታ ዙሪያ የሚያሰባስቡንን መልካም አጋጣሚዎች መፈለግ አለብን፡፡ እነሆ ዛሬ አንድ አዲስ በአል አግኝተናል፤ ይህውም የክርስቶስ ንጉሥ በአል ነው! የክርስቶስ ንጉሥን በዓል ለማክበር ክርስቲያን መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ክርስቲያን ምዕመናን ግብዣ ማቅረብ እወዳለሁ፡፡ በቀጣዩ ዓመት የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች በዓል ሆኖ እንዲከበር ተስፋ አለኝ፡፡ በዚህ በአል ላይ የተገኛችሁ ምዕመናን የክርስቶስ ንጉሥ በዓልን በተመለከተ ለሌሎች ክርስትያኖች እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሁሉ እንድታካፍሉ አደራ እላችኋለሁ! እኔም በኢትዮጵያ ለሚገኙ ክርስቲያን ወንድሞቼ ጳጳሳት፣ የምዕመናን መሪዎች፣ ለአብያተክርስቲያናት ኃላፊዎች ተመሳሳይ ግብዣ እንደማቀርብላቸው ቃል እገባለሁ፡፡
በመጨረሻም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በምትሰጣቸው አገልግሎቶች ሁሉ የክርስቶስን ንጉሥ ባሕርይ በመላበስ ሕብረተሰቡን በትሕትና በማገልገል እውነተኛ ምስክር እንድትሆን
የሁላችንም ተግባራዊ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ የነገ ሀገር ተረካቢ በሆነው ትውልድ ውስጥ የክርስቶስ ንጉሥን ባሕርይ በማስረጽ ለነገ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል፡፡

መልካም የክርስቶስ ንጉሥ በዓል!

ከሳምሶን ደቦጭ - ቅ. ዮሴፍ ቁምስና ዘሲታውያን አ.አ